>
5:13 pm - Monday April 19, 5920

ነፍሴ ስለ ሀገሬ ታወከች . . .  (አሰፋ ሀይሉ)

ነፍሴ ስለ ሀገሬ ታወከች . . . 

አሰፋ ሀይሉ

አንዳንዴ ግን ግርም ብሎኝ አላባራ የሚለኝ ነገር አለ በእውነት! ብዙ ጠይቄ አንድ ስንጥር የምታህል መልስ የማላገኝለት ሺህ ጥያቄ እየተመላለሰ ውስጤን ያቆስለኛል! ብዙ፣ የማያባራ ሰንሰለት ይሆንብኛል አንዳንዴ! የሀገሬ ነገር! የእኛ ነገር! ከየት ተነስተን የት እንደምንደርስ!
ቆይ ግን ለሺህ ዓመታት ክርስትና (እና እስልምና) በተሰበከባት የቀደምት ሐይማኖቶችና ሐይማኖተኞች ሀገር – እንዴት እንዲህ በጠራራ ፀሐይ የዜጎች ደም በግፍ የሚዘራባት ሀገር ልትሆን በቃች? ‹‹ተደመሰሱ!›› ‹‹ተገደሉ!›› ‹‹ታረዱ!›› ‹‹እርምጃ ተወሰደባቸው!››…!! እንዴ? ምን ጉድ ነው? እነዚህን ቃላት እኮ ከመልመዳችን የተነሳ የማስፈራትና የማሳዘን ኃይላቸው ጠፍቶ እንደ ዕለት ቀለብ እያወራረድናቸው ነው!
ለነገሩ በሀገራችን አንዱ ባለጊዜ ወድቆ በሌላው ሲተካ – ከበፊቱ የበለጠ ግፍን መዝራት እንጂ፣ ሁሉን የሚፈውስ ጽድቅን መትከል በፍጹም የማይታሰብ ከሆነ ብዙ ቆየ፡፡ ተፈሪ መኮንን አብሮ አደጋቸውን የአደራ ባለመንበር – ልጅ እያሱን ከሥልጣን ማውረዳቸው ሳያንስ እስከ ዕለተ ሞቱ ያደረሱበት ስቃይና ግፍ ጤነኛ አዕምሮ ከሚያስበው በላይ እንደነበር ታሪክ መዝግቦ አኑሮልን ሰምተነዋል፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም መጥቶ እነዚያን ከፉም ለሙም በአንድ ወቅት ሀገሪቱን በክብር ያስተዳደሩ መሳፍንትና መኳንንት መሪዎች እንደ ሰው ልጅ ሳይሆን እንደ ጅብ መንጋ – በጅምላ ገድሎ በጅምላ ቀበራቸው፡፡
ወያኔ ደሞ መጣና ግፉን አሻሽሎት – ‹‹ደርግ›› ብሎ የሚጠራቸውን ለዚህች ሀገር በቻሉትና በሚያውቁት መንገድ የተዋደቁ መኮንኖች ለዓመታት በእስር እያማቀቀ፣ በአሻንጉሊት ችሎት እየቀለደ በቁማቸው ጨረሳቸው፡፡ አሁን ወያኔዎቹ ሸሽተው ጥጋቸውን ያዙ ሲባል – ያ የደም አበላ የለመደ ወንበር በሠላም ሊያልፍልን ነው ስንል – አሁንም ከቀድሞው ብሶ ተደገመ፡፡ በአንድ ወቅት ሀገርን የመሩና ሀገርን ወክለው በዓለም አደባባይ የቆሙ እነዚያ የወያኔ መሪዎች ደሞ በተራቸው – እንዲህ እንደ ውሻ በየመንገዱና በየጫካው እየተሳደዱ የሚረሸኑባት፣ ጠዋት ተረሽነው ማታ ‹‹ተደመሰሱ›› ‹‹ተገደሉ›› እየተባለ የሚነገርበት የሰበር ዜና ዘመን ላይ እንገኛለን፡፡
ፍትህ የማይታወቅባት፣ ህግ የማይከበርባት፣ ከሳሹም፣ ዳኛውም፣ ገራፊውም አንድ የሆነባት፣ እሾህን በእሾህ፣ ግፍን በግፍ የምታወራርድ፣ ወገን ጎራ ለይቶ እርስ በእርሱ በጥይት አረር የሚረግፍባት፣ በዚህም ሞት በዚያም መርዶ የሞላባት፣ በዚያም ለቅሶ በዚያም ሀዘን ያጠላባት፣ እንዲህ ዓይነት የግፍ፣ የሞት፣ የሀዘን፣ የስደት፣ የዋይታ፣ የትርምስና የግራመጋባት ሀገር ይዘን ምን እንሁን? ሠላማዊ ነፍሶች መድረሻቸው ወደየት ነው? በሠላም ወጥቶ መግባት የሚቻለው እንዴት ነው? አሳዛኙ የሰው ልጅ ሞት – ‹‹የምሥራች ምስር ብሉ›› እየተባለ የሚነገርባት – እና የሰው ልጅ ሞት የሰውን ልጅ ጮቤ የሚያስረግጥባት ሀገር እነዴት ልትሆንብን ቻለች – ውዲት ውዲቷ (እናት ኢትዮጵያ)?
እናት ኢትዮጵያችን በፅኑ ታማለች! የሚያደማት እንጂ የሚፈውሳት እጅ አጥታለች! የጽድቅ ፈራጃችን የጽድቁን መንገድ ሰውሮብናል! ሕሊና በየጎራው ተሸጉጣ መተንፈሻ ሥፍራ አጥታለች! ይሉኝታና ይቅርባይነት ከናካቴው በንነው ጠፍተዋል! ‹ዓይን ያወጣ ዓይኑ ይውጣ!› በሚል ያለፈበት የሃሞራቢ የበቀል ፍትህ እየተመራን – አንዳችን የሌላኛችንን ዓይን እየደነቆልን – ሁላችንም ልንታወር ጥቂት እንደቀረን የሚነግረን ሀገር የሚያፍረው፣ ሰው የሚሰማው፣ አስታራቂ የተከበረ ሰው አጥተናል! ለእውነትና ለፍቅር፣ ለይቅርታና ለአብሮነት ራሳችንን አሳውረናል!
ለሁሉም የሚሆን አማካይ መፍትሄ ተጋርዶብናል! የይቅርታ በሮች ተዘግተዋል! የመደመር መንገዶች በተቀየዱበት ፍጥነት ከምድራችን ላይ መክነዋል! መቀነስ፣ መቀናነስ፣ መገዳደል፣ መጠፋፋት ብቻ ውጦናል! መፍትሄ የሚያመላክት አዋቂ የለንም! ሁሉም ጎራ ለይቶ በል-በለው የሚባባልባት የመጋደያ ባድማ ሆናለች ሀገራችን! ስንት ሊቃውንትን ያበቀለች ሀገር በጭንቅ ቀኗ የምሁር ምድረበዳ ወርሷታል! ወደየትም በማያደርስ የጥላቻና የእልህ አዙሪት ተጠምደን የሞት ሞታችንን ወደየመጥፊያችን እየተፍገመገምን እያዘገምን ነው! እየተጠፋፋን፣ እየተላለቅን፣ እየተጋደልን፣ እየተወጋጋን፣ እየተደማማን፣ እየተሞሸላለቅን… ወደ የት ይሆን መድረሻችን? የት ላይ ይሆን የደም መፋሰሳችን ማቆሚያው? ጠላታችን የማያልቀው ስለ ምንድነው? ወገንነትን እና ጠላትነትን የሚፈጥረውን የጎራ መንፈስ በምን ቃላት እንርገመው?
ተዉ ጠብ አይበጅም፣ ግፍ ይብቃ፣ ቂም-በቀል ወደ ሰገባው ይከተት፣ መጠፋፋት ከመካከላችን ይጥፋ፣ መበላላት በፍቅር ተበልቶ ይሙት – የገባንበት በደም አበላ የተነከረ የመጠፋፋት ዳስ ለትውልድ አይበጅም – ሀገር አያሰነብትም – ለህሊና እሾህ ነው… ለሠላም ፀር ነው… ይቅር ለእግዜር እንባባል… ምድሪቱን በደስታ እናስቦርቃት… የሀዘንን ሸማ ከላያችን አውልቀን መጣያችን ጊዜው አሁን ነው…  የሚል፣ ተስፋን የሚያስታጥቅ፣ የተጣላን የሚያስታርቅ፣ የተጎዳዳን የሚያካክስ፣ የተካረረን የሚያረግብ…. እንዴት አንድ እንኳ እውነተኛ ሽማግሌ ጠፋ በሀገሩ? ለሺህ ዓመታት ቀን ከሌት የፈጣሪ ስም እየተጠራ ሲቀደስባት፣ ሲዘየርባት፣ ሲሸበሸብባት በኖረች ሀገር – እንዴት አስታራቂ ዳኛ ጠፋ በመካከላችን የሚቆም? ምን ነክቶናል? ምን ዓይነት ጋኔን ነው የተጠጋን? እና እንዲህ የእውር-ድንብራችንን በያቅጣጫው እርስ በርስ የሚያጠፋፋን? ምን ጉድ ነው?
እውን ለሺህ ዓመታት ስሙን ስንጠራው የኖርነው ፈጣሪ – አሁንስ ይሰማናል ወይ? ‹‹አቤቱ ማረን!›› ብለን ብንጮህ..  ይሰማን ይሆን ወይ እግዜሩ? ቂም ይዞ ፀሎታችን ከፈጣሪ ጆሮ ዘንድ ይደርሳል ወይ? የታቦቶቻችን ተዓምር፣ የአባቶቻችን ማህላ፣ የመነኮሳታችን ሱባዔ፣ የባህታዊዎቻችን ግዝት፣ የሼሆቻችን ዚያራ፣ የእናቶቻችን እንባ…. እውን እነዚህ ሁሉ አጥብቀን የምንሻውን ሠላምን፣ ፍቅርን፣ መዋደድን፣ ወገንነትን፣ ሰብዓዊነትን… ጽድቅን… ያመጡልን ዘንድ እንዴት አቅም አጡ? ወይስ እነዚህን የጽድቅ በረከቶች የሚሸከም ልብ አልታደልንም? ምን ሆነናል?
ያለንን ሁሉ እንዳንጠቀምበት፣ እንዳናየው፣ እንዲሰወርብን፣ እንዳይበረክትልን፣ እንዲህ እንድንባክን ያደረገን… ያ የጎደለን ዋና ነገር ምንድነው? በጉዟችን፣ በጥድፊያችን፣ በሽሚያችን መሐል የጣልነው፣ እና ያጣነው.. ያ ሰብዓዊ ሌማት ምንድነበር? ከማንስ ዘንድ እናግኘው? ወደ ሠማዩ እናንጋጥጥ? ወደ ወገናችን እንመልከት? ወደ ራሳችን እንመልከት? የሠላም፣ የእፎይታ፣ የአብሮነት፣ የፍትህ፣ የእውነት፣ የሕሊና፣ የሚዛን፣ የፈሪሃ-እግዜር… እና የተትረፈረፈ ነፃነት… የእነዚህ ሁሉ ኢትዮጵያዊ በረከቶች… ወይም የእነዚህ ሁሉ ጭላንጭል ተስፋ መገኛቸው… ከወደ የት ይሆን?
ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ ትዘረጋለች!
Ethiopia shall soon stretch out her hands unto God!
የፈጣሪ በረከት ከሁላችን ጋር ይሁን! የፈጣሪ ምህረት አይለየን! 
የፍቅር ትንሣዔ ለኢትዮጵያ! 
Filed in: Amharic