>
5:13 pm - Thursday April 20, 8750

አሥር ሞት፤ አቦይ ስብሃት እና በነፍስ የተያዙ የህውሃት አመራሮች....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

አሥር ሞት፤ አቦይ ስብሃት እና በነፍስ የተያዙ የህውሃት አመራሮች….!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ልክ እንደ አቦይ ስብሃት የቀሩትም የህውሃት አመራሮች በህይወት ተገኝተው በሕግ ጥላ ስር እንዲሆኑ እመኛለሁ። በህይወት እንዲገኙ መመኘቴ መቼም ሳይገባችሁ አይቀርም። እነሴኮ ቱሬ አንድ ሞት ነው የሞቱት። እኔ ለህውሃት አመራሮች አንድ ሞት ስለሚያንሳቸው አሥር ሞት ነው የምመኘው። አሥር ሞት ደግሞ አንቱ በተባልክበት ቴሌቪዥን ጣቢያ ‘ጁንታው ስብሃት ተያዘ’ ከሚለው ይጀምራል። ብዙዎችን በግፍ ወዳሰቃየህበት ቃሊቲ መውረድ ሌላው ሞት ነው። በወንጀል ሊያውም በአለም አቀፍ ወንጀል ጭምር በሚያስከስስ ወንጀል መከሰስ ደግሞ የሞት ሞት ነው። በየቀኑ ያንን ቢጫ የእስረኞች ቱታ አጥልቀው ይንቁት በነበረው ችሎት ፊት መቅረብ ዘጠነናው ሞት። በየቀኑ ሱፍና ከረባት አጥልቀህ በምትንጎማለልበት ከተማና አሥሬ ስምህ በበጎ በሚጠራበት ቴሌቪዥን ላይ ዳኞች ፊት ቀርበኽ የፍርድ ቤት ውሎህ እና የወንጀል ታሪክህ ሲዘከዘክ እና መጨረጫም ሲፈረድብህ አሥር ሞት ማለት ነው።
ላለፉት ሰላሳ አመታት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን የገደሉና ያስገደሉ፣ በየእስር ቤቱ  አጉረው ፍጹም ጸያፍ በሆነ መንገድ ያሰቃዩና የደበደቡ፣ ብዙሺዎችን ከአገር ያሰደዱ፣ ሚሊዮኖች ከቤት ንብረታቸው እንዲፈናቀሉ ያደረጉ፣ ኢትዮጵያን በጎጥ ከፋፍለው ህዝቡን ወደ እርስ በርስ ግጭት የዶሉ፣ የብዙ ሺህ ወጣቶችን ህልም እና ተስፋ ያጨለሙ፣ የአገር ሃብት የዘረፉ እና ያዘረፉ፣ እጅግ የከፋ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን የፈጸሙና ያስፈጸሙ እነዚህ የህውሃት አመራሮች ለፍርድ ቀርበው በጥፋታቸው ልክ ሲቀጡ ማየት የዘወትር ምኞቴ ነበር።
እነዚህ ሰዎች ሁሉም በጦርነቱ ተደምሰው ቢሆን ኖሩ በብዙ መልኩ ጥሩ እንድምታ አይኖረውም ነበር። ሌላውን ልተወውና የሁሉም መሞት አንዱ መጥፎ እንድምታ እነዚህን ሰዎች ታሪካቸውን በደንብ ካለማወቅ፣ የፈጸሙትን የወንጀል ልክ በቅጡ ካለመረዳት በተወላጅነትም ይሁን በሌላ መልኩ ሲደግፏቸው የኖሩ እና አሁንም የሚደግፏቸው ሰዎች ከምን አይነት ሰዎች ጀርባ ወይም ጎን እንዲቆሙ እንዳያውቁ እና ሰዎቹንም እንደ ጀግና በወንጀል የተዘፈቁ አጢያኖች መሆናቸውንም ይረዳሉ።
ነጻና ፍትሐዊ በሆነው የፍርድ ሂደት ህውሃት እና አመራሮቿ ከውልደታቸው እስከ ክሽፈታቸው የፈጸሙት ወንጀል በግልጽ ችሎት ፊት ይነገራል ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ። የሰሯቸው ወንጀሎች ከነማስረጃዎቹ በአግባቡ ተሰንደው ለታሪክም ጭምር ይቆያሉ። ፍትህም ቀና ትላለች። ተበዳዮችም ቢያንስ በሞራል ይካሳሉ። የዛሬዎቹም ሹሞች ከህውሃት ውድቀት ትምህርት ይወስዳሉ ብዮ ተስፋ አደርጋለሁ።
ለዛሬዎቹ ሹሞች ከዚህ የሚማሩበት ልቦና ይስጣቸው
Filed in: Amharic