>
5:13 pm - Tuesday April 18, 1122

የአሜሪካ አማጽያን - በታላቁ የአሜሪካ ቤተ ጉባዔ.  !!! (በዳዊት ከበደ ወየሳ)

የአሜሪካ አማጽያን – በታላቁ የአሜሪካ ቤተ ጉባዔ.  !!!

(በዳዊት ከበደ ወየሳ)

 

 …ማክሰኞ ጃኑዋሪ 5 ቀን፤ 2021 ዓ.ም በጆርጂያ የሚደረገው የሴኔት ምርጫ ተጠናቀቀ። የእነዚህ ሁለት የዲሞክራት ፓርቲ እጩዎች ምርጫውን ካሸነፉ፤ ሴኔቱን በመቀላቀል፤ የሃይል ሚዛኑን እንደሚያዛቡት ግልጽ ነው። እናም በሚቀጥለው ቀን ማለትም እሮብ ‘ለት ዲሞክራቶች ደስታቸውን ሲገልጹ፤ ዶናልድ ትራምፕ እና ተከታዮቻቸው ግን በኋይት ሃውስ የብሽቀት ንግግር በማድረግ ላይ ተጠምደው ነበር። ከዚህ በፊት በኢትዮጵያዊያን አዲስ አመት መስከረም 1 ቀን፤ ማለትም ሴፕቴምበር 11 ቀን የአሸባሪዎች ጥቃት ተፈጽሞ አለምን እንዳስደነገጠው ሁሉ፤ አሁን ደግሞ ኢትዮጵያዊያኑ የገና በአልን ለማክበር በዝግጅት ላይ ሳሉ፤ በዋዜማው ያልታሰበ እና አስደንጋጭ ታሪክ ተፈጸመ። የሆነውም ነገር ይህ ነው።
ጃኑዋሪ 6 ቀን፣ 2021 ዓ.ም በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ ጥቁር ነጥብ ጥሎ የሚያልፍ፤ አሳዛኝ እና አሳፋሪ ቀን ሆኖ አለፈ። ይህ እለት የአሜሪካ ኮንግረስ እና ሴኔት በታላቁ ቤተ-ጉባዔ ማለትም በካፒቶል ህንጻ ተገኝተው፤  የጆ ባይደንን ፕሬዘዳንትነት የሚያጸድቁበት እለት ነበር። ይህን የፕሬዘዳንትነት ሲመት ስነ ስርዓት ለማስፈጸም ደግሞ፤ የዶናልድ ትራምፕ ምክትል ፕሬዘዳንት ማይክ ፔንስ በስፍራው ተገኝተው፤ ሲመቱን ለማወጅ የድምጽ አሰጣጥ ስነ ስርአቱን ለማስፈጸም በዝግጅት ላይ ነበሩ። በሌላ በኩል ግን… ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥቂት ቀናት የቀራቸው ዶልናልድ ትራምፕ በኋይት ሃውስ ለተገኙ ደጋፊዎቻቸው ንግግር ባማድረግ ላይ ናቸው።
ዶናልድ ትራምፕ እንዲህ አሉ። “ወደ ካፒቶል ህንጻ እንሄዳለን። ከዚያም ጀግና ኮንግረስ እና ሴኔት አባሎቻችንን እናበረታታለን። ለአንዳንዶቹ ግን ይህን ማበረታቻ አናደርግም። ከእንግዲህ አገራችንን በደካማነት አናነሳትም፤ ጥንካሬያችሁን ማሳየት አለባቹህ፤ ጠንካራ መሆን አለባቹህ። ካስፈለገ እኔም ከናንተ ጋር እሰለፋለሁ” የሚል መልዕክት ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን፤ ምክትል ፕሬዘዳንታቸውን ማይክ ፔንስ በካፒቶል ህንጻ ተገኝተው የሚያደርጉትን ህጋዊ አሰራር አጥብቀው ኮነኑ። ከዶናልድ ትራምፕ በተጨማሪ… የህግ አማካሪያቸው ጁሊያኒም ሆኑ የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ንግግር በማድረግ፤ በኋይት ሃውስ ለተገኙት ደጋፊዎቻቸው የልብ ልብ ሰጧቸው።
በዚህ የረብሻ ንግግር የተነሳሱት የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊዎች ከኋይት ሃውስ ከወጡ በኋላ፤ በቀጥታ ወደ ካፒቶል ህንጻ ነበር ያመሩት። ረብሸኞቹ ወይም ደግሞ አመጸኞቹ ወደ ካፒቶል ህንጻ በንዴት ጦፈው፤ ለጥፋት እና ለውድመት ሲያመሩ በካፒቶል ህንጻ ውስጥ ደግሞ የህዝብ ተመራጮች ታሪካዊ ስብሰባ በማድረግ ላይ ነበሩ። ምክትል ፕሬዘዳንቱ ማይክ ፔንስ ስብሰባውን እየመሩ ናቸው። በዚህ እለት… በመላው የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች የሚገኙ ኤሌክቶራል ኮሌጅ፤ የተሰጡት ድምጾች ትክክለኛ እና ተቀባይነት ያላቸው መሆናቸውን በማረጋገጥ፤ ለአዲሱ ፕሬዘዳንት የሲመት ምስክር ወረቀት የሚሰጥበት እለት ነበር። የዶናልድ ትራምፕ አማጽያን ግን ይህን ስነ ስርአት በሚገርም ሁኔታ፤ ሂደቱን ለአጭር ጊዜም ቢሆን አሰናከሉት።
እነዚህ አማጽያን… ወደ ካፒቶል ህንጻ በማምራት፤ በሰላሙ ጊዜ ተሻግሮ ለመሄድ የማይቻለውን ጎዳና እያለፉ ሲሄዱ፤ በአካባቢው ፖሊስ ያለ አይመስልም ነበር። ካፒቶል ህንጻ ሲደርሱ፤ ግቢውን የሚጠብቁትን ፖሊሶች ጥሰው፤ ፖሊስ ያስቀመጠውን መስመር አልፈው፤ አጥር ግንቡን ተንጠላጥለው… ግቢውን አልፈው ህንጻውን ወረሩት። ለማመን በሚያዳግት ሁኔታ የህንጻውን መስኮት እና በሮች ሰባብረው፤ የካፒቶል ህንጻ ፖሊሶችን እየገፈታተሩ… የአሜሪካ ሴኔት እና ኮንግረስ አባላት ስብሰባ እያደረጉ ወዳለበት አዳራሽ አመሩ። በታላቁ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የሚገኙት የህዝብ ተመራጮች እየሆነ ባለው ነገር ተረበሹ፤ ስብሰባውን ይመሩ የነበሩት ምክትል ፕሬዘዳንት ማይክ ፔንስ እና ናንሲ ፔሎሲ በጠባቂዎቻቸው ታጅበው እንዲወጡ ሲደረግ፤ ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት የጋስ ጭንብላቸውን በማጥለቅ የስብሰባ አዳራሹን ለቀው እንዲወጡ ተደረገ። እድለኛ የሆኑ የህዝብ ተመራጮች ወደየቢሯቸው በመሄድ ተደበቁ፤ ሌሎች ደግሞ በአንድ ክፍል ውስጥ ታጭቀው፤ ከአማጽያኑ እይታ አመለጡ።
የዶናልድ ትራምፕን ባንዲራ በመያዝ ቤተ ጉባዔውን በኃይል የያዙት አማጽያን፤ “ደካማ” የተባለለትን የካፒቶል ፖሊስ አሸንፈው፤ ህንጻውን ተቆጣጠሩት። ከሁለት መቶ አመታት በፊት ማለትም በ1814 ዓ.ም በዚሁ ስፍራ ላይ ሆኖ የነበረው ወረራ በካፒቶል ህንጻ ላይ በድጋሚ ተፈጸመ። በ1814 ዓ.ም በእንግሊዝ ደጋፊዎች የሚመራ የአማጽያን ቡድን የካፒቶል ህንጻን በተመሳሳይ ሁኔታ በመውረር፤ (በወቅቱ የኮንግረስ ቤተ መጽሃፍት በዚሁ ህንጻ ውስጥ ይገኝ ነበር) በኮንግረስ ላይብረሪ የሚገኙ የጽሁፍ ዶክመንቶችንና መጻህፍቶችን አነደዱ። እሳቱ እየተባባሰ ሲመጣ፤ በዘመኑ ዘመናዊ የእሳት አደጋ ተከላካይ መኪኖች ባይኖሩም፤ ኃይለኛ ዝናብ በመዝነቡ ሊደርስ የነበረው ከፍተኛ ቃጠሎ፤ በዚህ አይነት ከሸፈ። ነገሮች ካለፉ በኋላ… የኮንግረስ ላይብረሪ በተሻለ ሁኔታ ተሰርቶ አብዛኛዎቹ መጽሃፍቶች ተሟልተው፤ አዳዲስ ተጨምረውበት፤ በአሁኑ ወቅት የአለማችን ቁጥር አንድ ቤተ መጽሃፍ ለመሆን በቅቷል። የሆነ ሆኖ… በዘመናችን በተፈጸመው የአመጻ ግርግር የኮንግረስ አባላት ቢሮ ተመዝብሯል፤ የአፈ ጉባኤዋ ናንሲ ፔሎሲ ቢሮ ጭምር ተደፍሯል።
በአፈ ጉባዔዋ ቢሮ ውስጥ የተገኘ አንድ ግለሰብ፤ እግሩን ጠረጴዛ ላይ አነባብሮ ፎቶ ተነስቷል። አማጽያኑ የተገንጣዮችን ወይም የኮንፌዴሬሽን ባንዲራ ይዘው፤ ወደ ተከበረው ኮንግረስ ዋና መሰብሰቢያ ቤተ-ጉባኤ በመዝለቅ፤ የነበረውን እንዳልነበረ አድርገዋል። በሴኔት መሰብሰቢያ ገብተው፤ በሴኔቱ ፕሬዘዳንት መንበር ላይ በመሆን ፎልለዋል። በካፒቶል አውደ ግቢ ውስጥ የሚገኙ ሃውልቶችን አዋርደዋል። በእነዚህ የጥንት የአሜሪካ ፕሬዘዳንቶች ሃውልት ላይ የዶናልድ ትራምፕን ባንዲራ በማድረግ ፎቶ ሲነሱ ውለዋል። በአጠቃላይ በሚሊዮኖች ዘንድ ታላቅ ክብር የሚሰጠውን የካፒቶል ቤተ-ጉባዔ እንዳልነበረ በማድረግ፤ አልፎ ተርፎም ከጠባቂዎቹ ጋር በመደባደብ ጭምር የአገሪቱን ክብር አፈር ከድሜ አስግጠውታል።
እናም ከኋይት ሃውስ የተነሳው የአማጽያን ቡድን፤ “በሰለጠነው ዘመን ሊደረግ ይችላል” ተብሎ የማይገመት አመጻ እና ረብሻ ሲፈጽም የሚያሳዩ ፎቶ እና ቪዲዮዎች፤ ከአሜሪካ አልፈ በመላው አለም በመታየታቸው፤ የአሜሪካን ክብር እና ዝና ዝቅ አድርገዋል። በዚህ አመጻ አራት ያህል ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በዚህ ድርጊት አንዳንድ የዶናልድ ትራምፕ ተከታዮች እና ባለስልጣናት፤ በሃፍረት አንገታቸውን የደፉትን ያህል፤ አሁንም በአሸናፊነት የሚፎክሩ የዶናልድ ትራምፕ ደጋፊ አሜሪካዊያን አልታጡም። በተለያዩ የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች ተመሳሳይ የአመጻና የረብሻ ተግባር ለመፈጸም ቢሞከርም፤ ሁሉም ጥረት “ቀቢጸ ተስፋ” ሆነው አልፈዋል። በዚያም ተባለ በዚህ ግን… ስልጣናቸውን ለመልቀቅ ጥቂት ቀናት የቀራቸው ዶናልድ ትራምፕ፤ በውድ ሳይሆን በግድ፤ ተወደው ሳይሆን ተዋርደው ስልጣናቸውን ሊለቁ ነው። ደጋፊዎቻቸውም ከዚህ አመጻ ምንም ሳያተርፉ፤ አራት ሞቶባቸው፣ ብዙዎች ታስረው ሁሉም በያሉበት ድምጻቸው እንደጠፋ ቀርቷል። እናም ይህንን መጥፎ ቀን በዚህ ዘመን ያሉ ሰዎች ይገረሙበታል፤ መጪው ትውልድ ደግሞ “ለካስ ይሄም ነበር” እያለ ይማርበታል። ለማንኛውም ግን ይህ  እለት በአሜሪካውያን ዘንድ እንደሴፕቴምበር 11 ቀን፤ በሃዘን ብቻ ሳይሆን በሃፍረትም ጭምር ይታወሳል።
Filed in: Amharic