>

ሕግ እና ፍትህ አልባዋ ኤርትራ፤ ሕግ ለማስከበር በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ተሳትፋ ከሆነ ውርድ ከራስ ነው...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሕግ እና ፍትህ አልባዋ ኤርትራ፤ ሕግ ለማስከበር በተካሄደው ጦርነት ውስጥ ተሳትፋ ከሆነ ውርድ ከራስ ነው…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ሕግ ለማስከበር በሚል ትግራይ ላይ ከህውሃት ጋር በተደረገው ጦርነት የኤርትራ ጦር ድንበር አልፎ በቀጥታ መሳተፉን የአሜሪካን መንግስትን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ሲናገሩ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ ጊዜያዊ የመቀሌ ከንቲባ ሆነው በአብይ አስተዳደር የተሾሙ ሰው የኤርትራን ጣልቃ ገብነት ማረጋገጣቸውን የሚያሳይ ቪዲዮ ወጥቷል። ይሄ ነገር እውነት ከሆነ እንደ አገር አሳፋሪ እና ሊወገዝ የሚገባው ተግባር ነው። ኢሳያስ አፎርቄ የሚያስተዳድራትን ኤርትራን አፍኖ ለሰላሳ አመታት ያለ ሕገ መንግስት፣ ያለ ምርጫ፣ ያለ ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ያለ ነጻ ሚዲያ ጠርንፎ የያዘ እና በአለማችን ስመ ጥር ከሆኑ አንባገነን መሪዎች አንዱ ነው። ይህ ሰው በአገሩ ያላስከበረውን ሕግ ኢትዮጵያ ውስጥ ‘ሕግ ለማስከበር’ በሚል በተካሄድው ጦርነት ውስጥ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንዲኖረው ተፈቅዶለት ከሆነ ይህ መጥፎ የታሪክ ጠባሳ ብቻ ሳይሆን የአብይን አስተዳደርም የሚያስጠይቅ ነው። መንግስት አሁንም በዚህ ጉዳይ ላይ እውነቱን ይፋ ሊያደርግ ይገባል።
እንደሚባለው ከሆነ ወደ ትግራይ የገቡት የኤርትራ ሠራዊት አባላት በንብረት እና በሰው ሕይወት ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሰዋል፣ ዘርፈዋል፣ ተቋማትንም አውድመዋል የሚባል ክስ በአለም አቀፍ ሚዲያዎች ጭምር እየተሰራጨ ነው። የአብይ አስተዳደር እነዚህን ዘገባዎች ሊያጠራ የሚችለው ጉዳዩ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራ ሲፈቅድ ብቻ ነው። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ልክ በማይካድራ ላይ እንዳደረገው በቀሩት የትግራይ ክልል ዞኖች ውስጥ ተፈጸሙ የተባሉትን የመብት ጥሰቶች፤ እንዲሁም የኤርትራን ጣልቃ ገብነት ቶሎ አጣርቶ ይፋ እንዲያደርግ ለፍትህ የቆሙ አካልት እና ሰዎች ሁሉ ሊያሳስቡ ይገባል።
Filed in: Amharic