>

ምጽዓት [ፕ/ር መስፍን ወልደ ማሪያም]

መስከረም 2007

በግዞትም ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደኤርምያስ መጣ፡– ሂድ ለኢትዮጵያዊውም ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው፤ — የእሥራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ ፣ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤- እነሆ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል፤ በዚያ ቀን አድንሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም፤ ፈጽሜ አድንሃለሁ፤ ነፍስህም እንደምርኮ ትሆንልሃለች እንጂ በሰይፍ አትወድቅም፤ በበእኔ ታምነሃልና ይላል እግዚአብሔር፡፡ ትንቢተ ኤርምያስ 39/15-18

ኑዛዜ ኤርምያስን አነበብሁ፤ጉድ ነው! አንድ የማውቀውን ነገር አረጋግጥሁ፤ ብዙ የማላውቃቸው ነገሮችን አወቅሁ፤ የማውቀው ነገር ሂሳብ የተማረ ሰው ምን ጊዜም ጭፍን ሎሌ መሆን የማይችል መሆኑን ነው፤ሂሳብ የተማረውን ሰው ለጭፍን ሎሌነት የሚቀጥረው ሰው ግን አንጎሉ የፈረጠ ነው፡፡

የማላውቃቸው ነገሮች ዝርፊያ በየፈርጁ! በቃሊቲ ወህኒ ቤት የትምህርት ቤት የነበረ ሕንጻ ወደእስር ቤት መለወጡን አይቼ ነበር፤ አሁን ደግሞ የሕዝብ ትምህርት ቤት ለግለሰብ መሸጡን አወቅሁ፤ ጡንቻ ነው እንጂ ትምህርት ምን ዋጋ አለው! ይህ ሁሉ ዝርፊያ፣ ይህ ሁሉ ወንጀል ሲፈጸም ሌላው ሁሉ ጮሆ አቤት ለማለት እንኳን የማይደፍር ሆኖ ነው ወይስ የሕግ አስከባሪ በአገሩ ጠፍቶ ነው? ድፍረቱን አጥፍተውት ከሆነ በከበደ ሚካኤል ብእር ፋሺስቱ የተናገረው ልክ ነበር ማለት ነው፤–

መሬት የሁሉ ነች ባለቤት የላትም!

ኃይለኛ እየሄደ ያስገብራል የትም፤

መሬት ባለቤት ከሌላት ሰዎች አገር የላቸውም ማለት ነው፤ አገር የሌላቸው ሰዎች ዶላር ይዞ ለመጣ ቤታቸውንና መሬታቸውን እንዲያስረክቡ ይገደዳሉ፤ ሕገ መንግሥቱ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ስለሚል ባለዶላር ወይም ባለሀብት ሕዝብ የሚለውን ይተካል።

ኑዛዜ ኤርምያስን ያነበበ የወያኔ ባለሥልጣኖችን ራቁታቸውን ያያቸዋል፤ ካልዋሸ ራሱንም ራቁቱን ቆሞ ያየዋል፤ ከዚህ በፊት ብዙ ጊዜ ደጋግሜ እንዳልሁት ጨቋኝና ተጨቋኝ ተደጋጋፊዎች ናቸው፤ አንዱ ያላንዱ አይኖርም፤ በኑዛዜ ኤርምያስ ላይ ጎልቶ ለሚታየው የጨቋኞቹ ቆራጥነትና ጭካኔ ጉልበቱን ከየት አገኙት ቢባል መልሱ ቀላል ነው፤ ከተጨቋኞቹ ተንጋልሎ ጭቆናን ከመቀበል ችሎታ ነው፤ድፍረታቸውን አደንቃለሁ፤ድፍረታቸው ወደወንበሩ ስቧቸው ወጡበትና (ተቀመጡበት እንዳልል አልተመቻቸውም፤) ዘመኑ የፍርሃት፣  እንቅልፍ አጥቶ የመባነን፣ የመደናበር ሆኖባቸዋል፤ የፍርሃት በሽታ ዓይንን ይሰውራል፤ ጆሮን ይደፍናል፤ አቅምን እንዳያውቁ ያደርጋል፤ በዚህ ሁሉ ምክንያት ከማይችሉት ጋር ያላትማል።

ምጽዓት የሚል ግጥም አለኝ፤ ትዝ አለኝ!

ባሳብ ባሕር ዘፍቆ የሰው ልጅ ሲጨነቅ፣

ሃይማኖት ሲራባ ፍልስፍና ሲረቅ፣

ነፍስ እምነትን አጥታ፣ መንምና በችጋር፣

እውነቱ ሲያሳፍር፣ ሲያስጠላ፣ ሲያስመርር፣

ኃይል ክፋት ሲሆን የደካሞች ጭነት፣

ፍቅር ጥምቡን ጥሎ ሲገዛ እንደኩበት፣

ፍርሃት ትእግስት ሆኖ ድንቁርና ኩራት፣

ውርደትም ትሕትና ጮሌነትም እውቀት፣

ትምህርትም ጌጥ ሆነ ያውም የተውሶ፣

ስንፍናም ጨዋነት ሰውነት ረክሶ፣

ማተብ ክርስትና ነጭ ጥምጥም ክህነት፣

ሀብት ብልጽግና መቾት ትልቅነት/

ምኞት ተስፋ ሆኖ መቃብርም ኑሮ፣

እንጉርጉሮው ዘፈን፣ ዘፈኑ እንጉርጉሮ፣

ባዳ ሆነ ዘመድ ባለቤቱ እንግዳ፣

ሆድም አምላክ ሆነ አውሬውም ለማዳ፣

ገንዘብ ዳኛ ሲሆን ወንጀል ከሳሽ ሆኖ፣

ግብዝነት ደላው ጽድቅ ተኮንኖ!

ወጣትነት ጫጨ እርጅና እየለማ፣

የኋሊት መገስገስ የጊዜው ዓላማ!

ከራስ በላይ ነፋስ ትልቁ ሃይማኖት፣

ዘረፋን ሲያውጀው ቂም ሲያስረግዝ ጥቃት፣

ዓይን አያይም አሉ፤ ጆሮም አያዳምጥ!

ተለጉሞ አንደበት ሁሉም ይዞታል ምጥ!

በቁንጣን በስካር ጥቂቶች ሲንሩ፣

ብዙዎቹ ደግሞ በረሃብ መንምነው በቁንጫ ሲያርሩ.

የደሀ እንባ ሲጎርፍ መሬቱ ሲሸበር፣

ፍትሕ በሌለው ፍርድ ሚዛኑ ሲሰበር፣

ዝብርቅርቁ ወጣ!

ህይወት ትርጉም አጣ!

ኧረ የት ነው ጉዞው? ዓላማው ምንድን ነው?

ቀድመው የሄዱትን ምነው አናያቸው!

የት ገቡ? የት ጠፉ? ፋና እንኳን አይታይ፤

ብልጭ የሚል የለ፤ ከመሬት ከሰማይ!

መንገዱ ጠበበ ትርምስምሱ በዛ፤

እሪታው ኡኡታው ቀለጠ እንደዋዛ፤

መሬቱም ዓየሩም በክፋት ጠነዛ፤

ጥላቻና ቂሙ በሰፊው ተነዛ፤

እምቢልታው ሲጣራ፣ ነጋሪት ሲያገሳ፣

የአለው ሁሉ ሞቶ የሞተው ሲነሣ፣

ምጽዓት መድረሱ ነው፤ ሊስተካከል ነው ፍርድ፤

በግና ፍየሉ ሊለዩ በገሀድ!

የሚጠየቅ ሰው ቢኖር አንድ ቀላል ጥያቄ መጠየቅ እፈልግ ነበር፡- የዝርፊያው ፉክክር የት ለመድረስ ነው? በአንድ ቤተ ክርስቲያን ወይም መስጊድ ጓሮ ሁለት ሜትር በአንድ ሜትር ክፍል የሬሳ ቤት ለማሠራት? አይ ሰው!

Filed in: Amharic