>

"ትልቋ ኢትዮጵያ " (ጸጋው ማሞ)

“ትልቋ ኢትዮጵያ “

ጸጋው ማሞ

 

 “ኢትዮጵያኖች ጨርሶ የፈጠራ ስራ የሚያንሳቸው ናቸው “
በአሜሪካዊው መንዜ በዶናልድ ናታን ሌቪን
    በ1940ዎቹ  ከትውልድ አገሩ አሜሪካ ከችካጎ ዩኒቨርስቲ  ተነስቶ እስከ አውሮፓ ድረስ በኘሌን ከአውሮፓ እስከ ምጽዋ 10 ቀን ሙሉ በባሕር ተጉዞ ኢትዮጵያ ከገባ በኋላ እንደሱ ገለጻ ጨዋወች፣ ኩሩዎችናደጎች ወደ ሚኖሩበት  ያልተበረዘ አማርኛ ወደ ሚነገርበት ጭው ወዳለው ገጠር መንዝ በመግባት ከገበሬዎች ጋር  አብሮ  መደብ ላይ እየተኛ እርሻና ጎልጓሎ ሳይቀር እየተሳተፈ  የማሕበረሰቡን ስነ ልቦና ፣ ታሪክ እና ማሕበራዊ ስሪት በማጥናት አጠቃላይ የአማራን ህዝብ በጥልቀት በመመርመር” Wax and Gold ” የሚል መጽሐፍ አሳተመ ።በኢትዮጵያኖች ፍቅር ነደደ ።
    ————-
   በመቀጠልም አጠቃላይ የኢትዮጵያን ሕዝብ የሚመለከት  greater Ethiopia  (ትልቋ ኢትዮጵያ ) የሚል መጽሐፍ በማሳተም በሶሾሎጂ ጥናት  በኢትዮጵያ ፈር ቀዳጅ  ለመሆን በቃ ።
 ——–
ትልቋ ኢትዮጵያ የሚባለው መጽሐፉ በመጀመሪያው ገጾቹ  ኢትዮጵያ በዓለም ላይ  ያላትን ገናና  ሥእለ ህሊና ምትሃት ወይንም ልቦለድ በሚመስሉ እውናዊ ተረኮች በማስረጃ ይተነትናል ። .ይቀጥልና… ሕዝቧ ሱሪና ጫማ መልበስ ሳያውቅ ሰልጥኖ የተገኘ እርሱ ብቻ ነው… ” ኢትዮጵያን ደህና አድርጎ የሚያውቃት አንድ ሰው ስለ አገሪቷ በሃቅ መናገር የማይቻልባት ናት  ”  በማለት በወቅቱ በነበረው ጥናት ጽፎልናል ።  እርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስልጡን ነውን?  ስልጣኔ ምንድን ነው?  አሁን ላይ ያከራክራል ።
   ———
የግሪክ አማልክቶች  ለሽርሽር ከገነት ይልቅ
የሚመርጧት…የግሪካውያን አምላኮች ከኢትዮጵያን ሰዎች ጋር  ምግብ  ለመብላት የሚጓጉ መሆናቸውን  እየገለጠ… ኢትዮጵያ የሰው ልጅ ስብእና መገለጫ የአፍሪካውያን የነጻነት የተስፋ ችቦ ፣የስርዓተ መንግስት ሃውልት ፣የጥቁሮች የመንፈስ አባት አገር ፣ የንቃት ምልክት ፣የሰውነት ሚዛን እንደሆነች ከተለያዩ ምንጮች እየጠቀሰ ይናገራል ።
     ———-
    ሌቪን በዚህ መጽሐፉ ኢትዮጵያ የብዙ ሕዝቦች ድምር ውህድ ውጤት እንደሆነች ይተርካል ። የአማራን ሕዝብ የግለኝነት አስተሳሰብ የግሩብ አስተሳሰብ አንደሌለውና የአገራዊ ወኔውን ከብዙ ታሪኮች ጋር ይተነትናል ። የኦሮሞ  ሕዝብንም እንቅስቃሴና የአዋኻጅ ጠባይንም በመተንተን ይተርካል። ሌሎችንም  በርካታ የኢትዮጵያ ብሔረሰቦችንም በማጥናት የተዋሃደ ሕዝብ እንደሆነ በጥናቱ አስረድቷል ። ሌቪን ኢትዮጵያ በልቤ ታትማ ቀርታለች በማለት ለኢትዮጵያኖች ነጻነት ከንጉሡ ጀምሮ በሦሥቱም መንግስታት እንደ አንድ ጭቁን አርሶ አደር  ታግሏል ። ከአገርም ተባሯል ።
    ——
 ይህ  ትውልደ አሜሪካዊ የችካጎ ዩኒቨርስቲ ፕሮፌሰር ስለ ኢትዮጵያ ሦስት መጻሕፍትን ጽፎ አልፏል ።   እነሱም  Wax and Gold ፣ Greater Ethiopia  and  Interpreting Ethiopia የሚሉ ከእነዚህ ውስጥ ሁለቱ  Wax and Gold እና Greater Ethiopia ተተርጉመዋል ።
   ዶናልድ ሌቪን በማንኛውም ነገር ላይ ሲፈርም
    ሌቪን ገብረ ኢትዮጵያ(ሌቪን የኢትዮጵያ አገልጋይ)  ብሎ ነው ።    የሌቪንን የጥናት ውጤት ማየት በኢትዮጵያ ላይ አይን ይገልጣል ።
 ———
  ኢትዮጵያኖች ግን እውን አድስ ነገር መፍጠር አይችሉም?  መፍጠር ከቻሉስ በ20ኛውና በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፈጥረው ለዓለም ያበረከቱት  አዲስ ግኝት  ምንድነው?
Filed in: Amharic