>
5:13 pm - Thursday April 19, 6773

አምባገነናዊ ዝቅጠት ፡ የኢሕአዴግ ጥቁር ምላስ እና ብልፅግና...!!! (አንሙት አብርሐም)

አምባገነናዊ ዝቅጠት ፡ የኢሕአዴግ ጥቁር ምላስ እና ብልፅግና…!!!
 አንሙት አብርሐም

በረከት ስምዖን ፡  ⁽⁽የኢሕአዴግን ጥቁር ምላስ ባለቤትነት⁾⁾ በቅርብ ባወጣው መፅሐፉ መስክሯል። ድርጅቱ አምባገነናዊ የዝቅጠት አደጋን ተንትኖት ፡ ሰግቶት ፡ፈርቶት በዚያው ዝቅጠት ሞቷል።
በረከት በመፅሐፉ ከ1983-1993 የነበረውን ኢሕአዴግ የአምባገነናዊ ዝቅጠት መገለጫዎችን ሲያብራራ የፈራውን እየኖረ ፡ የግንባሩም መቃብር በዚያው ስጋት ገቢራዊነት መሆኑን መረዳት ይቻላል።
የ90ዎቹን የዝቅጠት ምልክቶች ሲገልፃቸው፤
1) ⁽⁽ በትግል የተወገደውን አሮጌ  ሥርዓት ዋና የሕልውና ፈተና ምንጭ የሚያስመስል አቀራረብ ይዘወተር ነበር። ይህ ነጋ ጠባ በአሮጌው ስርዓት ኃይሎች ላይ በማትኮር በአንጻሩ ደግሞ ስለአዳዲሶቹ ችግሮች ባለማንሳት የሚገለጽ የግንዛቤ ጉድለት ነበር። ⁾⁾
2) ⁽⁽ በድርጅቱ የአመራር አባላት ዘንድ የሚታዩ የሥነ-ምግባር ብልሽቶችን በማስመልከት ድርጅቱ ይሰጥ የነበረው ትንታኔ..  ብልሽቱ በግለሰብ ደረጃ ፈተናውን ለማለፍ በመቸገር ምክንያት የተከሰተ እንደሆነ የሚያስመስል ነበር።
የግለሰቦች ሥነ-ምግባራዊ ጉድለት እየተበራከተና አንዳንድ ኃላፊዎች ስልጣናቸውን ካለአግባብ ለመጠቀም የሚያደርጉት ሙከራ እየተደጋገመ ሲሔድ ጉዳዩ ከግለሰባዊ ሥነ-ምግባራዊ ማዕቀፍ ወጥቶ የሥርዓት ችግር እንዳለ ያመለክታል።
ይሁን እንጂ የዲሲፕሊን ግድፈቶችንና ሥነ-ምግባራዊ ችግሮችን  ላይ ላዩን ከመነካካት ባለፈ ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ለመገምገምና ለመፍታት ሳይችል ቀረ።
:
አንዳንዶቹም ራሳቸውን በተስፈኛ ገዢ መደብ መነጽር ማየት የጀመሩ ነበሩ። ⁾⁾
3) ⁽⁽ ሌላው ችግሮችን ውጫዊ የማድረግ ዝንባሌ ነው!
የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ምንጭ የኤርትራ መንግሥት ወደመሆን ተሸጋግሮ ነበር። “ሻዕቢያ እስካለ ድረስ ሰላም አናገኝም” በሚል አመክንዮ በተያዘው አቋም የአገሪቱ ችግሮች ከራሷ ውስጣዊ ሁኔታ ለዚያውም ከአዲሱ  ሥርዓት ባሕሪያት የሚፈልቁ መሆናቸው ቀረ። ⁾⁾
ይሔም አመለካከት ሔዶ ሔዶ ድርጅቱን ወደቦናፓርቲስታዊ ዝቅጠት እንዳደረሰው በረከት መገለጫውን ያስቀምጣል።
 [  የፈረንሳይን አቢዮት ፍፃሜ ተከትሎ  ናፖሊዮ ቦናፓርት ለፈረንሳይ አርሶአደሮች  ያደረገውን የስሙኒ (0.25 ሳንቲም) የግብር ቅናሽ ተከትሎ በአርሶአደሩ ዘንድ ከመጣው ውለታ ቆጣሪነትና እርካታ ጋር ተያይዞ ፡ ከ35 አመት በኋላ የመጣው ሊዊ ቦናፓርት የተባለ መሪ  የቀዳሚዊ ቦናፓርትን ዝና ተውሶ “እኔ እኮ የስሙኒዋ ጌታ የታላቁ ናፖሊዮን የአጎት ልጅ ነኝ ” በማለት ተመርጠ። እናም ባገኘው ድምፅ  ልማታዊ አምባገነናዊ መንግስት እንደተከለው ፡ የኢሕአዴግ አመራርም “እኔ እኮ የመሬት ፣ የብሔር እኩልነት እና የዲሞክራሲ ጥያቄህን የመለስኩልህ ድርጅትህ ነኝ ” ወደማለት መቃረቡን አስቀምጧል።
ከዚህ የሚቀራረብ ነገር ገብሩ አስራት ያነሳል።
ሕዝቡ አመራሩን ጠበቅ አድርጎ ምሬቱን ማሰማት ሲጀምር “እኛ እኮ ለሕይወታችን ሳንሳሳ በረሃ ገብተን ወጣትነታችንን ለሕዝብ ትግል ያሳለፍን ነን” ይል ነበር።
ይሕ ሁሉ እንደበረከት ስርዓቱ በግልፅ ወደ አምባገነናዊ ዝቅጠት የሚያስገባ ስለነበር “እኛ ሀብታም ሳንሆን ሌሎች ዜጎችን ያለልዩነት ሀብታም በማድረግ ዝቅጠትን መፋለም” የሚል እቅድ መውጣቱንና ኋላም አንጃ ፈጠረ የተባለ አመራር ተባሮ መቀጠሉን ያነሳል።
ኢሕአዴግ ምላሱ ጥቁር ነው። የተነተነውንና የፈራውን እየሆነ ኖሮ ተቀበረ። የቦናፓርት መጨረሻ በመሠረተ ልማት የፈረጠመች ግን ጥያቄው ባልተመለሰ አርሶአደር የጦርነት አዙሪት የምትታመስ ፈረንሳይ መፍጠር ነበር።
ኢሕአዴግ የሰጋውን እየተጋተ ቀጠለ።
ቦናፓርቲስታዊ ዝንባሌ ያሳዩትን አስወገድኩ ብሎ በለየላቸው ቦናፓርቲስቶች ተተካ።
“ተስፈኛ ገዢ መደብ” አመራር  ወደለየለት የካፒታሊስት ገዢ መደብነት ተቀየረ፣  “ያለልዩነት ዜጎችን ሀብታም ማድረግ” የሚለው ክልልና ብሔር መርጦ ቢሮክራሲያዊ መድሎን መገለጫው ያደረገ ብሶት በመላ አገሪቱ ፈጠረ።
ዲሞክራሲን እየማለበት ሳይኖረው አምባገነንነት ከግራ ዘመም ቀለሙ ጋር ተሰፋ።
እንዲህ ከራሱ ትንታኔ ጋር እየተቃረነ ኖሮ በደል ባንገሸገሸው ኃይል ተፈንግሎ ጉድጓድ ሲገባ እንደፈረንሳዩ ቦናፓርት በመሠረተልማት የተሻለች ተከታታይ እድገት ያስመዘገበች ግን አምባገነን፡ የሀብት ኢ-ፍትሐዊነት ያስመረረው ፡  በልዩነት ዝግመት የተከፋፈለ አገርና ሕዝብ፡ አገራዊ ስሜትና አብሮነትን አጣብቂኝ የከተተ አገር ትቶ ሊሞት በቃ።
ብልፅግናስ የዝቅጠት ስጋት አለበት?
1- በአዲሱ ስርዓት የአገሪቱና የለውጡ ህልውና ስጋት ፡ የመለያየት ዝግመትን ፀንሶ እየተጓዘ ያለ መዋቅራዊ ስሪት ወይስ የዚህ ስሪት ባለቤቶች የትናንት ተግባርን መኮነን
➤ችግሮችን ስርዓታዊ ስሪት ያደርጋል ወይስ የትናንት አፈፃፀም ማስተካከል እያለ ይቀጥላል?
➤ አዲስ የአገር ግንባታና አብሮነት ስርዓት ወይስ የትናንት ፀረ-አማራ ትርክትና ስጋትን ማስቀጠል?
➤ እኩል የዜጋ አገልግሎት መስጠት ተስኗቸው የኖሩትን አገራዊ ተቋማት በመሠረታዊነት መለወጥ ወይስ ቀለምና ብራንድ ቀባብቶ በተስፈኛ ተረኞች ቢሮክራሲያዊ መድሎን (bureaucratic favour) ባሕሪያቸው እንዲያደርጉ ማበጃጀት?
➤ ሁሉንም ዜጎች ያለልዩነት ለማገልገል የሚያስችል የ”እኩል እድል” ስርዓት ሜዳ መፍጠር ወይንስ የጉዳት ካሳ አለብን የሚል “እኩል ውጤት”ን ለማረጋገጥ መታገል?
ትናንት የተወገዘውን ምዝበራ ቅርፅና መልክ ቀይሮ መቀጠል?
2- የአመራርና አባላትን የዲሲፕሊንና የሥነ-ምግባር ውድቀቶች በግለሰቦች ማዕቀፍ ያየዋል ወይስ ስፋቱን መዝኖ ከስርዓት መገለጫነት አኳያ በልኩ ያርመዋል
3- የኢትዮጵያ ችግሮች ሁሉ ምንጭ ስርዓታዊና መዋቅራዊ ያደርጋል ወይስ ውጫዊ ያደርጋል ?
“ይሔ ሕገመንግስታዊ መዋቅራዊ ስሪት ካልተስተካከለ ሰላም አናገኝም” ይላል ወይስ ኢሕአዴግ “ሻዕቢያ እስካለ..”  ይል እንደነበረው “ህወሓትና ተከታዮቹ እስካሉ”  እያለ ይቀጥላል?
➤ ያላሰለሰው የዜጎች ሞት  በለውጥ ስርዓቱ  አመራር ጤና መታወክ የመጣ ስርዓታዊ አደጋ አድርጎ ያየዋል ወይስ በወደቀው  አመራር ወይም የጥቂት አመራሮች ችግር የወለደው እያደረገው ይቀጥላል?
4- ለዘመናት ሊፈታ ያልቻለውን የአገሪቱንና የሕዝቡን መሠረታዊ ችግሮች ለመፍታት ይረባረባል ወይስ ፡  ” እኔ እኮ ወያኔን እና ኢሕአዴግን ያስወገድኩ ነኝ” እያለ ይቀጥላል።
መሠረታዊ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ያመጣል ወይስ “እኔ እኮ በአንድ አመት አለምአቀፍ መዝናኛ ፓርክ ሠርቼ ያሳየሁ ነኝ” እያለ ይቀጥላል?
5- ኢትዮጵያን የሁሉም አገርና የጋራ ቤት ያደርጋል ወይስ ⁽⁽ ከእንግዲህ እኛ ያልፈቀድንለት አገሪቱን አይመራም⁾⁾ እያለ ይቀጥላል?
6- ብሔረ-ኢትዮጵያን ለመገንባት የጋራ እሴት ግንባታ ላይ ይሠራል ወይስ እንደትናንቱ  ብሔረ-ኢትዮጵያ የለችም መኖርም የለባትም ብሎ ብሔረ-ኦሮሞ ፣ ብሔረ-አማራ-፣ ብሔረ-ትግሬ፣ ወዘተ ለመገንባት “ሕብረ-ብሔራዊነት” በሚባለው መርህ ሁሉም ራስ-በቅ አገር የመሆን ትግሉን ይቀጥላል?
የብልፅግና ምርጫ ከታሪክ መማር ነው!
ፎቶ: ከmakbel
Filed in: Amharic