>

ወልቃይት ጠገዴና የራያ  ዘራቸውን ከሚያጠፋቸው ይልቅም ከአማራ ወገናቸው ጋር  ነው መኖር ያለባቸው. ..!!!  (ዶ/ር  ምስጋናው አንዱዓለም) 

ወልቃይት ጠገዴና የራያ  ዘራቸውን ከሚያጠፋቸው ይልቅም ከአማራ ወገናቸው ጋር  ነው መኖር ያለባቸው. ..!!!
 ዶ/ር  ምስጋናው አንዱዓለም 

 ከዚህ የሕግ ማስከበር ወጊያ ማግስት በትግራይና በአማራ ክልል መካከል የግጭት አውድማ ሆነው የቆዩት የወልቃይት ጠገዴና የራያ እጣ ፈንታ ምን ይሆን የሚለው የብዙዎች ጥያቄ ነው።
የወልቃይት ጠገዴና ጠለምት እንዲሁም የራያ ጉዳይ እጣ ፋንታ የታወቀ ነው፡፡ እነኝህ ቦታዎች በሕወሓት ወራሪነት ወደ ትግራይ ክልል በጉልበት፣ በማናለብኝነት፣ በሕገ-ወጥነት የተካለሉ ናቸው፡፡ የመሬቶቹ በጉልበት ወደ ትግራይ መካለል ብቻ አይደለም፡፡ በእነኝህ መሬቶች የሚኖሩ አማሮች ከባርነት የከፋ፣ ከአፓርታይድ የጭቆና ሥርዓት የመረረ ግፍን ያስተናገዱበት ነው፡፡ በተለይ ወልቃይት ጠገዴ ጀምላ የሰው ዘር ፍጅት የተፈፀመበት ቦታ  ነው፡፡ መሬቱን በመፈለግ ሕዝቡን የማጥፋት ሙከራ የተደረገበት አስከፊ የታሪካችን አካል  ነው፡፡
እና እነዚህ ቦታዎች እጣ ፋንታቸው ምን መሆን እንዳለበት የሚያከራክር አይደለም፡፡ ጥያቄው ውሎ ያደረ፣ መፍትሔውም ከታወቀ የከራረመ ነው፡፡ የመጀመሪያው መፍትሔ በጉልበት ከተካለሉበት የትግራይ ክልል ወደ እናት ምድራቸው አማራ (በቀድሞው ጎንደር ክፍለ አገር እና ወሎ ክፍለ አገር) መመለስ ነበር፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ራያ ሕዝብ ለዓመታት ይህንን ሰሚ ያጣ አቤቱታ ሲያሰማ ነበር የከረመው፤ ምላሹ እስራት፣ መፈናቀል እና የዘር ማጥፋት ይሁን እንጅ፡፡ ስለሆነም የእነዚህ ቦታዎች እጣ ፋንታ በእናት ምድራቸው እንዲኖሩ ዘራቸውን ከማያጠፋቸው ይልቅም እህቴ እና ወንድሜ ከሚላቸው አማራ ወገናቸው ጋር መኖር ነው፡፡
ብልጽግና ፓርቲ እና የአማራ ክልል መንግሥት እነኝህን ቦታዎች እና ማኅበረሰቦች በተመለከተ የማያወላዳ አቋም ሊይዙ ይገባል፡፡ መፍትሔው ወደነባር ቦታቸው መመለስ እና የሕዝቡን ጥያቄ አድሬስ ማድረግ እንደሆነ ወጥ የሆነ እና የማይታጠፍ አቋም ሊይዙ ይገባል፡፡ መሬቶቹ በሕግ ያልሄዱ በመሆናቸው ሕግ ጠቅሶ ሊከራከሩበት የሚገባ ጉዳይ አይደለም፡፡ በሄዱበት መንገድ ነው መመለስ ያለባቸው፡፡ እንደመታደል ሆኖ አሁን በሄዱበት መንገድ ተመልሰው በባለቤቱ እጅ ይገኛሉ፡፡ ይህንን ድል በፖለቲካዊ ድል ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በእነዚህ ቦታዎች ላይ የተፈፀመው ግፍ በልዩ አጥኝ ቡድን ተጠንቶ በሰነድ እንዲቀመጥ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከመነሻው የሕወሓት የጫካ ትግል ጀምሮ የተፈፀሙ እያንዳንዶች ግፎች ተቆጥረው ካሳ እንዲከፈልባቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ያለ ጥርጥር የዘር ማጥፋት ተፈጽሟል፡፡ የዘር ማጽዳት (ማፈናቀል) ተፈጽሟል፡፡ ከሞት በተረፈው፤ በነዋሪው ሕዝብ ላይ የሞራል ስብራት ደርሷል፡፡ ስለሆነም በደል ያደረሱ አካላት በሕግ መጠየቅ አለባቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ተገቢ የሆነ ማናቸውም ካሳ ሊከፈላቸው ይገባል፡፡ አስተዳደራዊ መዋቅሩን ማስተካከል ብቻ ሳይሆን የበደል ካሳ ያስፈልጋል፡፡ ጉዳዩ በዓለም ዐቀፈ የዘር ማጥፋት ወንጀልነት እንዲታወቅ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ለዘር ማጥፋቱ መታሰቢያ ሐውልቶች እና መሰል ምልክቶች ሊገነቡ ይገባል፡፡ በመላው አማራ ከተቻለም በመላው ኢትዮጵያ ይህንን የዘር ማጥፋት ወንጀል የሚቃወም ሕዝባዊ ሰልፍ ማስተባበር ያስፈልጋል፡፡
ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ከወልቃይት የተፈናቀለ አማራ ወገን አለ፡፡ ይህ በዘመቻ መልክ ባፋጣኝ ወደቀየው መመለስ አለበት፡፡ ይህም ዝም ብሎ እንዲሁ የሚደረግ ሳይሆን የመልሶ ማቋቋም ሥራ የሚያስፈልገው ነው፡፡ መላውን ኢትዮጵያዊያን በማስተባበር የመልሶ ማቋቋሚያ ድጋፍ ፈንድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ጎን ለጎንም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሊደረግ ይገባል፡፡ ከእናት ምድርና ሕዝባቸው ተቋርጠው በሞት ጥላ ውስጥ የኖሩት የወልቃይት ጠገዴ ጠለምት እና ራያ ወገኖች ከመላው አማራ ሕዝብ ጋር በአንድ መድረክ ተገናኝተው ደስታቸውን የሚገልጹበት ዕድል መመቻቸት አለበት፡፡ ይህ በሁለት ዙር ሊከናወን ይችላል፡፡ ከእነዚህ ቦታዎች ወደ መሃል አማራ የሚደረግ የእርስ በርስ ግንኙነት ዘመቻ እና ከመሃል አማራ ወደ እነዚህ ቦታዎች የሚደረግ የእርስ በርስ ግንኙነት ዘመቻ ተብሎ፡፡ ዝርዝር አፈጻጸሙን ፓርቲውና መንግሥት ለራሱ በሚያመቸው መንገድ ሊያደርገው ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አካባቢዎቹ ለም እና አምራች በመሆናቸው የክልሉ መንግሥት ሰላምን በአስተማማኝ በማረጋገጥ የኢንቨስትመንት እና ሰፋፊ ልማቶች ኮሪዶሮች ሊያደርጋቸው  ይገባል፡፡
አንዳንድ ወገኖች የሕዝቡን ሥነ ልቦና እና ያለፈበትን ሰቆቃ በበቂ ሁኔታ ባለመገንዘባቸው የእነኝህን ቦታዎች ጉዳይ ተራ የርስት ማስመለስ እና የመሬት ይገባኛል ጉዳይ አድርገው ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይህ እጅግ በጣም መሠረታዊ ስህተት ያለበትን አነጋገር እና አስተሳሰብ ብልጽግና ፓርቲ እና የአማራ ክልል መንግሥት ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ወደነዚህ ቦታዎች በመውሰድ ተገቢውን ግንዛቤ እንዲጨብጡ ቢያደርጉ መልካም ነው፡፡
የፌዴራል መንግሥቱም ሚናውን ሊወጣ ይገባል፡፡ ከክልሉ መንግሥት ጋር በመተባበር የሕዝቡን ጥያቄ አስቸኳይ ፖለቲካዊ መፍትሔ እንዲያገኝ ማድረግ ይገባዋል፡፡ አከላለሉን ማስተካከል፣ ካሳ እንዲከፈል መታገል፣ ግፈኞችን ለፍትሕ ማቅረብ፣ ጉዳዩም ተገቢውን አለማቀፍ ትኩረት እንዲያገኝ ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ በተለይም የፌዴራል መንግሥት ከአማራ ክልል መንግሥት እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር በመምከር በአማራና ትግራይ ሕዝብ መካከል ስለሚኖረው ቀጣይ ግንኙነት መምከር ያስፈልጋቸዋል፡፡ ዋና ትኩረቱም ሁለቱ ሕዝብ በቀጣይነት በሰላም እና በአብሮነት የሚኖርበትን ሁኔታ መሻት መሆን ይገባዋል፡፡ እነኝህን ቦታዎች የግጭት ሳይሆን የአብሮነት ምክንያቶች እንዲሆኑ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ እነኝህን ቦታዎች እና ነዋሪውን ኅብረተሰብ ወደነበረበት የትግራይ ክልላዊ አስተዳደር ለመመለስ የሚደረግ አጉል ሙከራ በአማራና ትግራይ ሕዝብ መካከል ግጭት ሊቀሰቅስ የሚችል አደገኛ ጉዳይ መሆኑ ሊሰመርበት እና በጥንቃቄ ሊያዝ ይገባዋል፡፡ በተለይ ለትግራይ ሕዝብ በቀጣይ ወንድም ከሆነው የአማራ ሕዝብ ጋር በሰላም እንዲኖር ካስፈለገ የሕወሓትን የበደል ጣሪያ የሚያስታውሰውን ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ እና የዘር ማጥፋት ወንጀል ማውገዝ ይጠበቅበታል፡፡ የፌዴራል መንግሥቱ በዋናነት በዚህ ጉዳይ ላይ ቸልታ ሊያሳይ አይገባም፡፡
Filed in: Amharic