>

ዕብደትና ድንቁርና የሠለጠነበት ፖለቲካ?! (ከይኄይስ እውነቱ)

ዕብደትና ድንቁርና የሠለጠነበት ፖለቲካ?!

ከይኄይስ እውነቱ


የትኛው የኢሕአዴግ (‹ብልጽግና›) ድርጅት ወይም የጐሣ ድርጅት ነው ሕይወቴ የሚለውን የወያኔን ‹ሕገ መንግሥት›፣ የወያኔን የጐሣ ፌዴራሊዝም፣ የወያኔን የ‹ክልል› መዋቅር፣ የወያኔን የዘር ፖለቲካና አስተሳሰቡን፤ ባጠቃላይ የወያኔን አፓርታይዳዊ የጥላቻና ዝርፊያ ሥርዓት ከሥር መሠረቱ እንዲለወጥ የሚፈልግ?

ዛሬ በገዛ አገሩ በሕይወት ሳለ የግሌ የሚለው ኩርማን መሬት፣ በሞቱ ደግሞ የመቃብር ክንድ ከሥንዝር ቦታ ያጣ ብቸኛ ዜጋ በዓለም ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡

ሕይወቴን፣ አካሌን፣ ነፃነቴን፣ ሀብት ንብረቴን የሚቀማኝ እና በአገሬ ባይተወር መጻተኛ ያደረገኝ ሁሉ ጠላቴ እንጂ ወዳጄ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ባዕድ ሆነ የ‹አንድ አገር ሰው› ምን ልዩነት ያመጣል?

30/40 የማይሞሉ የወያኔ አመራሮችን ለመያዝ እጅግ አውዳሚ ጦርነት የተካሄደው ሕወሓትን ‹በትግራይ ብልጽግና› (በተቀሩት ሕወሓት) ለመተካትና የሕወሓት አስተሳሰብ ገዥ ሆኖ እንዲቀጥል ከሆነ የተከፈለው መሥዋዕትነት በብላሽ ነው ማለት ነው? የስልቻ-ቀልቀሎ ፖለቲካ ልበለው?

ስሙን ከለወጠውና የወንጀለኞች ሥርዓትን ካቆመው ኢሕአዴግ ከሚባል የወያኔ አጓጉል ፍጥረት፣ በወንጀል የነተበ ማንነታቸውን ‹ብልጽግና› በሚል ‹አዲስ እራፊ› ከጣፉት አባላት፣ ከዚህም ነውረኛ ድርጅት ፍርፋሪ ከሚጠብቁ አብዛኛው ‹ተቃዋሚ› ተብዬዎች ለኢትዮጵያ ድኅነትን የምንጠብቅ ወገኖች ነፋስን እየጐሰምን÷ ጉም እየዘገንን እንደሆነ ተረድተናል?

ሕዝባችን የሚገባውን አገዛዝ ነው ያገኘው ወይም በየጊዜው ከሚያሳየው ጠባይ ተነስተን የሠለጠነና የተሻለ ሥርዓት ለማስተናገድ በሚችልበት አቋም ላይ አይገኝም የሚል አሳማኝ መከራከሪያ ካልቀረበ በስተቀር (ይህ ደግሞ ባርነትን ወዶ ፈቅዶ መቀበል ስለሚሆንብኝ ትክክል አይመስለኝም) ኢትዮጵያን የምታህል የሺህ ዓመታት የሀገረ መንግሥትነት ታሪክ ያላት አገር፣ ጊዜአቸውን የሚመጥን ታላላቅ ነገሥታት የተነሱባትና ያስተዳደሯት አገር፣ ከሕዝባቸው ጋር በመሆን ሕይወታቸውን ከፍለው ነፃነቷን ከግዛት አንድነቷ÷ ሉዐላዊነቷን ከነ ሙሉ ክብሯና ኩራቷ ያቈዩልን አገር፣ ኢሕአዴግ የሚባለውና አሁንም የቀጠለ የጐሣ አፓርታይዳዊ ሥርዓት በብዙ መልኩ ቢሸረሽረውም ፈሪሃ እግዚአብሔር ያለው ሕዝብ ያላት÷ በእምነት ዕሤቶች የበለጸገችና ድልብ ማኅበራዊ ጥሪት ያላት አገር፣ ጊዜውን የዋጀና እያደጉና እየተበራከቱ ያሉ (አንዳንዶቹም ካደጉት አገራት ተወዳዳሪ የነበሩ) ተቋማት  (ቴሌኮሙኒኬሽን፣ አየር መንገድ፣ ንግድ ባንክ፣ የአገር መከላከያ፣ የፖሊስ፣) የነበሯት አገር፣ ተስፋ ሰጭ ኢኮኖሚ የነበራት አገር፣ ሀገር በቀሉን ዕውቀትና ባህላዊ ትምህርት መሠረት አድርጎ የተገነባ ባይሆንም ደረጃውን ጠብቆ እያደገና እየሠፋ በመሄድ ላይ የነበረ ዘመናዊ የትምህርት ሥርዓት የዘረጋች አገር፣ በልዩ ልዩ የዕውቀት÷ የጥበብና የሙያ መስኮች ባገር ውስጥም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ አንቱ የተሰኙ ባለሙያዎችን አፍርታ የነበረች አገር ወዘተ. ዛሬ (ከ50 ዓመት ወዲህ) የት ነው ያለችው?

ዛሬ የኦነጋውያኑ ድንክዬዎች  የእነ  ታዬ ደንድአ፣ አዲሱ አረጋ፣ ሽመልስ አብዲሳና የአለቃቸው፤ የነውር ቁንጮው የብአዴኖቹ የእነ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአገኘሁ ተሻገር፣ የተመስገን ጥሩነህ እና የአለቃቸው ደመቀ መኮንን፤ የቤኒሻንጉል-ጉምዙ ነፍሰ ገዳይ የእነ አሻህድሊ፤ የሲዳሞዎቹ የእነ ደስታ ሌዳሞ፣ አብርሃም ማርሻሎ፤ የትግራዩ የእነ ሙሉ ነጋ፣ የነቢዩ ስሁል፤ የሶማሌው ማፍያ የእነ አህመድ ሺዴ፤ የሐረሮቹ የእነ ኦረዲን በድሪ፤ የደቡቡ የእነ ርስቱ ይርዳው፤ የአፋሩ የእነ አወል አርባ፤ የጋምቤላው የእነ ጋትሉዋክ ቱት ኮት፣ ላክዴር ላክባክ፤ እና ላለፉት 27 ዓመታት በየክፍላተ ሀገሩ ከተጠቀሱት ቀድመው የነበሩ ጐሠኛ ‹አመራሮች› መጫወቻ ነበረች/ሆናለች፡፡ ሀገር ሲፈታ/ሲያረጅ የጃርት መብቀያ ይሆናል የሚባለው ለካስ መሠረት አለው፡፡ ዲፕሎማሲውና ዓለም አቀፍ ግንኙነቱማ አይነሳ፡፡ የደናቁርትና የወንጀለኞች ስብስብ የነ ሽፈራው ሽጉጤ፣ ብርሃኑ ጸጋዬ፣ ጊና ባጫ፣ መለስ ዓለም፣ ሱሌማን ደደፎ፣ ወዘተ. (በዘመነ ወያኔ የሕወሓት፣ አሁን ደግሞ የኦሕዴድ ቅርንጫፍ ጽ/ቤቶች መሆናቸው ሳይዘነጋ) የመሳሰሉ ወራዶች ተሰማርተውበት አገራችን በድንክዬዎች ተዋርዳለች፡፡ 

ግለሰቦችን ለአብነት አነሳናቸው እንጂ ብልሽቱ ወያኔና ኦነግ ከተከሉት የማስመሰያ ‹ሕገ መንግሥቱ› ጀምሮ ሥርዓታዊና መዋቅራዊ መሆኑ እስኪታክተን አንስተናል፡፡ ስለ መፍትሄውም ብዙ ተብሏል፡፡ ይሁን እንጂ በተደራጀ ሕዝባዊ እምቢታ ካልሆነ ከአገዛዞች በልመና የሚገኝ አይደለም፡፡ ማነው ከወንጀል ከለላ/መደበቂያ፣ ለዝርፊያና ለሕገ ወጥ ብልጽግና ደግሞ ዋስትና ይሆነኛል ከሚለው ሥርዓት በገዛ ፈቃዱ የሚላቀቀው?  

ብዙዎቻችን ለምን ወረተኛ እንደምንሆን አይገባኝም፡፡ የጐሣ አፓርታይድ ሥርዓቱን ደግፈው ወይም ተደግፈው ውዥንብር የሚፈጥሩትን እያልኩ አይደለም፡፡ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከልብ እንጨነቃለን የምትሉ ጽኑ መርህና አቋም ካላችሁ ነፋስ ይዞ ከሚመጣው ወቅታዊ አጀንዳ ጋር ለምን ትገለባበጣላችሁ? 

እኔ የኦሕዴድ አመራሮችን ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት እያሰብሁ የነውረኞች ቁንጮ የሆነው ብአዴንን ሙታንነትና የአማራ ሕዝብ ደመኛ ጠላትነት ከማንሳት አልታቀብም፡፡ ደጋግሜ እንደገለጽኹት (2020-02-21 https://www.ethioreference.com/archives/21180) ከዚህ ጭንጋፍ ስብስብ በጎ ነገር የምትጠብቁ የሞተ ዘመድ የሌላችሁ ሳትሆኑ አትቀሩም፡፡ እንደኔ የግል እምነት ኢሕአዴግ በሚባለው ‹የቈነሰ ኩሬ› ውስጥ የተጠመቁ ድርጅቶችና ግለሰብ አባላት በተለይም አመራሮቹ እንኳን ኢትዮጵያን ለመታደግ ለራሳቸውም የመለወጥ ዕድል ያላቸው አይመስልም፡፡ ቅጥፈትና ክህደት የባሕርያቸው ይመስለኛል፡፡ በዚህ በበሰበሰ አገዛዝ ውስጥ የአንድ ጎልማሳ ዘመን አሳልፈው አስተሳሰባቸው የበለጠ ሲከፋና ሲከረፋ ነው የታዘብነው፡፡ አገርን ዕለት ከዕለት ወደ መቀመቅ ሲዶሉ፣ ሕዝብን ካንዱ መከራ እጅግ ወደ ከፋ መከራ ሲዳርጉ ነው ያስተዋልነው፡፡ የትኛው የኢሕአዴግ (‹ብልጽግና›) ድርጅት ወይም የጐሣ ድርጅት ነው ሕይወቴ የሚለውን የወያኔን ‹ሕገ መንግሥት›፣ የወያኔን የጐሣ ፌዴራሊዝም፣ የወያኔን የ‹ክልል› መዋቅር፣ የወያኔን የዘር ፖለቲካና አስተሳሰቡን፤ ባጠቃላይ የወያኔን አፓርታይዳዊ የጥላቻና ዝርፊያ ሥርዓት ከሥር መሠረቱ እንዲለወጥ የሚፈልግ? የተለየ ምርምር የሚጠይቅ ሆኖ እኔ ያልደረስኹበት ካለ ንገሩኝ፡፡ 

እንዴት ጥቂቶች የአስተሳሰብ ድውያን ጊዜ የሰጣቸውን ጉልበትና ኃይል ተመክተው ዕድሜ ልካችንን ሲጫወቱብን ይኖራሉ? እስከ መቼ በገዛ አገራችን ባሪያ ሆነን እንኖራለን?

ዛሬ በገዛ አገሩ በሕይወት ሳለ የግሌ የሚለው ኩርማን መሬት፣ በሞቱ ደግሞ የመቃብር ክንድ ከሥንዝር ቦታ ያጣ ብቸኛ ዜጋ በዓለም ላይ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚገኝ አይመስለኝም፡፡

 አያት ቅድመ አያቶቻችን በባዕዳን ቅኝ ግዛት ሥር ያልወደቀች ነፃ አገር ያስረከቡን ኢትዮጵያውያን በውኑ የነፃነት ትርጕሙ ገብቶናል? ከዓድዋውና ከ5ቱ ዓመታት የጠላት ወረራ የነፃነት ተጋድሎ ምንድነው የተማርነው? በየዓመቱ የምናዘክረው ለምንድን ነው? 

ሕይወቴን፣ አካሌን፣ ነፃነቴን፣ ሀብት ንብረቴን የሚቀማኝ እና በአገሬ ባይተወር መጻተኛ ያደረገኝ ሁሉ ጠላቴ እንጂ ወዳጄ ሊሆን አይችልም፡፡ በዚህ ረገድ ባዕድ ሆነ የ‹አንድ አገር ሰው› ምን ልዩነት ያመጣል? ባዕዳን ጠላት የተባሉ ያልፈጸሙትን ዘግናኝ ግድያ እኮ ነው በሕፃናት፣ በእናቶችና በአረጋውያን ላይ እየተፈጸመ ያለው፡፡ ለዚህ እኮ ነው መንግሥት የለም የምንለው፡፡ 

30/40 የማይሞሉ የወያኔ አመራሮችን ለመያዝ እጅግ አውዳሚ ጦርነት የተካሄደው ሕወሓትን ‹በትግራይ ብልጽግና› (በተቀሩት ሕወሓት) ለመተካትና የሕወሓት አስተሳሰብ ገዥ ሆኖ እንዲቀጥል ከሆነ የተከፈለው መሥዋዕትነት በብላሽ ነው ማለት ነው? የስልቻ-ቀልቀሎ ፖለቲካ ልበለው? 

አሁን በተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች በተለይም በጎጃም መተከል፣ በወለጋ፣ በኮንሶና ወያኔ ኦሮምያ ብሎ በፈጠረው ግዛት ውስጥ በአማራና አገው ተወላጆች እንዲሁም በሌሎች ዜጎቻችን ላይ በየዕለቱ የሚፈጸመው እልቂት ከሕወሓት ጋር ከተደረገው ጦርነት እጅግ ባነሰ መሥዋዕትነት መቈጣጠር ሳይቻል ቀርቶ ነው ወይስ ባለመፈለግ? የዐቢይ አገዛዝ የቅርብ የፖለቲካ አማካሪ ያደረጋቸው፣ ኦሮሚያ በተባለው ልዩ ኃይል ውስጥ በመደበኛነት ያሰለፋቸው፣ የተለያየ የሲቪል ሹመት ሰጥቶ ያሰማራቸው፣ ከኦሕዴድ ጋር የዓላማ ተካፋይ የሆነው ኦነግ የሚባለው አሸባሪ ድርጅት አባላት አይደሉም? በመሆኑም በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው ምክንያት ለሚያልቁት ዜጎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተጠያቂና ኃላፊ ነው፡፡ በሎሌዎቹ ታዬ ደንድአ እና በአዲሱ ቂጤሳ አማካይነት የሚጫወተው የከረፋ ፖለቲካ የጐሠኛው ዐቢይ ካልሆነ የማን ነው? በወሬ ሳይሆን በተግባር የምናየውን ዐቢይ ከወያኔ/ኢሕአዴግ አስተሳሰብ እና የሁለት ሳንቲም አንድ ገጽታ ከሆኑት ኦሕዴድና ኦነግ ለይቶ የሚያይ በእኔ እምነት ለኢትዮጵያ የጥላቻና ሴራ ፖለቲካ እንግዳ መሆን አለበት፡፡

ስሙን ከለወጠውና የወንጀለኞች ሥርዓትን ካቆመው ኢሕአዴግ ከሚባል የወያኔ አጓጉል ፍጥረት፣ በወንጀል የነተበ ማንነታቸውን ‹ብልጽግና› በሚል ‹አዲስ እራፊ› ከጣፉት አባላት፣ ከዚህም ነውረኛ ድርጅት ፍርፋሪ ከሚጠብቁ አብዛኛው ‹ተቃዋሚ› ተብዬዎች ለኢትዮጵያ ድኅነትን የምንጠብቅ ወገኖች ነፋስን እየጐሰምን÷ ጉም እየዘገንን እንደሆነ ተረድተናል? አይደለም መንግሥተ ሕዝብ የሰፈነበት የእኩልነት ሥርዓት ህልውናዋን ጠብቆ ማቆየት የሚቻል አይመስለኝም፡፡ አሸባሪዎችን አቅፎና ደግፎ የያዘ አገዛዝ በምርጫ ተአምር ይፈጥራል ብሎ መጠበቅ ነሆለልነት ነው፡፡ ከኢትዮጵያ ጠንቆች ፈውስን መጠበቅ ጽኑ የአእምሮ መቃወስ እንጂ ጤና ሊሆን አይችልም፡፡  

ርእሰ መጻሕፍቱ እግዚአብሔርን እሺ በጄ በሉት፤ ሰይጣንን እምቢ ወግድ በሉት ይለናል፡፡ በውሸት ትርክት ባንድ አገር ሕዝብ መካከል ጥላቻን ማስፈን፣ ሕዝብን በጐሣ ከፋፍሎ ማለያየት፣ በአርዓያ ሥላሴ የተፈጠረን ሰው በሚከተለው እምነትና ወዶ፣ ፈቅዶና መርጦ ባላገኘው የጐሣ ማንነት ምክንያት አሰቃቂ እልቂት መፈጸም፣ ባገሩ በመረጠው የትኛውም ቦታ መኖር ከልክሎ ተቅበዝባዥ ማድረግ ምን የሚሉት ዕብደት ነው? ምድር በሙሉ የእግዚአብሔር አይደለም እንዴ? እንኳን ባገሩ ማነው ፈቃድ/ማነው ከልካይ? ይህን የመሳሰለው ሁሉ የጨለማ የሰይጣን ሥራ በመሆኑ እምቢኝ አሻፈረኝ ልንል ይገባል፡፡ በሥጋ ሁለቴ ለማንኖርባት ምድር ሰው ሆነን እንኑር፣ ሰው ሆነን እንለፍ፡፡ የውኃ ትንታና እንቅፋት ሊገድለው የሚችል፣ ባጭር ቁመት በጠባብ ደረት የተወሰነ የኛ ቢጤ ደካማ ሰው እንዴት ይጫወትብናል?

ለነፃነት፣ ለፍትሕ እና ለእኩልነት መታገል ሰብአዊ ብቻ ሳይሆን ሃይማኖታዊም ግዴታ ነው!!!

እነ እስክንድርን ባስቸኳይ ልቀቁ!!! በኦነግ የታገቱ ልጃገረድ ተማሪዎችን ያሉበትን ሁናቴ ለወላጆቻቸውና ለኢትዮጵያ ሕዝብ አሳውቁ!!!

የኢትዮጵያ አምላክ ክፉዎችንና የተንኰል ሥራቸውን እምቢ የምንልበትን በጎና ጥቡዕ መንፈስ ያሳድርብን፡፡

Filed in: Amharic