>

በጦርነቱ የተገኘውን ድል ለአገራዊ ጠቀሜታ እንዴት እናውለው? (ከይኄይስ እውነቱ)

በጦርነቱ የተገኘውን ድል ለአገራዊ ጠቀሜታ እንዴት እናውለው?

ከይኄይስ እውነቱ


የዐቢይ አገዛዝ ጁንታ ካለው የሕወሓት ጥቂት ክፍል ጋር  የጀመረው ወታደራዊ ዘመቻ  መቐለን በመቆጣጠር እንዳበቃ ነግሮናል፡፡ ምንም እንኳን የወንበዴው ቡድን እዚህም እዚያም በሽምቅ ትንኮሳውን እንደሚቀጥል ቢገመትም፡፡ ወቅቱ ስለ ዐቢይ የተለመደ የፖለቲካ ዲስኩር የምናወራበት አይደለም፡፡ የአገዛዝ መሪዎች ከሕዝብ ተቀባይነትን ለማግኘት፣ ስለራሳቸው ዝና እና የፈጸሙትን አገራዊ ጥፋት ለመሸፈን ወይም ለመከላከል ባማሩ ቃላት የማይቀባጥሩት ውሸት የለምና፡፡ 

መሠረታዊው ጥያቄ በብዙ መሥዋዕትነትና በአገራዊ ሀብት ውድመት የተገኘውን ወታደራዊ ድል ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ወደ ተሻለ አዲስ ምዕራፍ ሊያሻግር በሚችልበት ጥበብና ማስተዋል በተመላበት ሁናቴ እንዴት እንጠቀምበት? የሚለው ይመስለኛል፡፡ አብዛኛው ሕዝባችን ከዚህ ጦርነት ስለሚፈልገው ውጤት በስፋት ሲነገርና ሲጻፍ ሰንብቷል፡፡ አገዛዙ ደግሞ ዓላማውንም ሆነ ውጤቱን ከሕዝብ ተቃራኒ በሆነ መንገድ ሲናገርና ሲጽፍ አስተውለናል፡፡ አገዛዙ ሲፈጅና/ሲያስፈጀው የነበረውን ሕዝብ በጭንቁ ሰዓት ከተጠቀመበት በኋላ መጨረሻው በክህደት እንደሚደመደም አስተውሎቱ የነበራቸውና ያላቸው ይህንን ግምታቸውን አስቀድመው ተናግረዋል፡፡

ዐቢይም ሆነ ሌሎች የአገዛዙ ባለሥልጣናት የወታደራዊ ዘመቻው ዓላማ ሕግን ለማስከበር መሆኑን ደጋግመው ነግረውናል፡፡ ይህም ማለት ላለፉት 27 ዓመታት የሚጠላውን አገርና ሕዝብ በጐሣና ቋንቋ ከፋፍሎ ሲገዛ የነበረውን፣ ኢትዮጵያን በግድያና በዝርፊያ ምድራዊ ሲዖል በማድረግ ህልውናዋን የተፈታተነውን፣ የዐቢይ አገዛዝ ከመጣ ወዲህ ደግሞ የትግራይን ክ/ሃገርና ሕዝብ መያዣ በማድረግ በመላ አገሪቱ ሽብር ሲያከፋፍል ከነበረው ወንጀለኛ ድርጅት ሕወሓት ውስጥ በቊጥር ተለይተው የሚታወቁ ግለሰቦችን ይዞ ሕግ ፊት ለማቅረብ እና ወያኔ ለአገዛዜ ይጠቅመኛል ብሎ ከግብር ወንድሙ ኦነግ ጋር የጐሣ መድልዎ ሥርዓት ያነገሠበትን ‹ሕገ መንግሥት› ለማስከበር መሆኑን በማሻያማ ቋንቋ ነግረውናል፡፡ ይህንን አጥተነው አይደለም ከአገዛዙ በተለየ የጦርነቱ ዓላማ እና ውጤት እንዲህ መሆን ይኖርበታል እያልን ስንሞግት የሰነበተነው፡፡ ብልህ መሪ አጋጣሚውን (የሕዝብን ድጋፍና መነቃቃት) ተጠቅሞ እንደ ውቅያኖስ የሰፋና የጠለቀ ችግሮች ውስጥ የምትገኘዋን አገራችንን ለማዳን ይጠቀምበት የምንለው፡፡ 

በቅድሚያ ‹ሕግን ለማስከበር› ማለትም ሕወሓት ከሚባለው ድርጅት ውስጥ በጁንታነት የተፈረጁ ጥቂት ግለሰቦችን በሕግ ቊጥጥር ሥር ለማዋል በየትኛው አገር የተሟላ ጦርነት (full-scale war) አይካሄድም፡፡ እውነታው ይሄ አይደለም፡፡ በደሀው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት ተገዝቶ አገርን ከማናቸውም ጠላት ለመከላከል የተያዘን ትጥቅ እንዲቆጣጠር የተደረገ የጥፋት ኃይል የኢትዮጵያ ጠላት በመሆኑ ለአገር ህልውና አስጊነቱ አያጠያይቅም፡፡ በሰው ኃይል፣ በስንቅና ትጥቅ ዓመታት ወስዶ ለጦርነት ሲዘጋጅ ከቆየ አሸባሪ ኃይል ጋር ሊደረግ የሚችለው ተራ የሕግ ማስከበር ሥራ ሳይሆን ጦርነት መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ቊጥሩ ወዲፊት የሚገለጽ ሆኖ፣ በአገዛዙ ‹ትዕግሥት› ሳይሆን ንዝህላልነት በዚህ ጦርነት አእላፍ ኢትዮጵያውያን ተሠውተውበታል፤ በውጭ ምንዛሬ የተገኘ አገራዊ ሀብት ወድሞበታል፡፡ በዚህም አገራችን ያላት የመከላከያ ኃይል በሰው ኃይልም ሆነ በመሣሪያ የተዳከመ አቋም ላይ የሚገኝ መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ዐቢይ በለውጥ መንፈስ እንደገና አደራጅቼዋለሁ ያለው የመከላከያ ኃይል ክፍተት ጎልቶ የታየበት ጦርነት መሆኑም ተስተውሏል፡፡ የአማራ ሕዝባዊ ኃይል በደጀንነት ሳይሆን በፊታውራሪነት ባይደርስለት ኖሮ መጣፊያው ባጠረ ነበር፡፡

ዐቢይ በብዙ አገራዊ ጉዳዮች ውሳኔ አሰጣጥ ረገድ በአመራር ቆራጥነት አለመኖር የወደቀባቸውን ፈተናዎች ሁሉ በትዕግሥት ወይም በወያኔ ሊያሳብብ አይችልም፡፡ የአገርን ህልውና ሥጋት ላይ የጣለና ሕዝብን (አገዛዙ ከለላ በሰጣቸው) በወንበዴዎች ያስጨረሰ ነው፡፡ የሱ ‹ትዕግሥት› የኢትዮጵያ ህልውናና የሕዝቧ ደኅንነት አደጋ ላይ መውደቅ ጋር የተያያዘ እንዳልሆነ አሁንም ከዚህ ቀደምም በተደጋጋሚ ታይቷል፡፡ ባለፉት 3 ዓመታት ዜጎች በማንነታቸውና በሃይማኖታቸው ሲጨፈጨፉ፣ ከቤት ንብረታቸው ሲፈናቀሉ እንኳን ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ዘመቻ ሊወስድ ቀርቶ እንደ አንድ አገር መሪ ድርጊቱን በስሙ አምኖ ዜጎችን ለማጽናናትና ባስቸኳይ ለማቋቋም እንቅስቃሴ ሲያደርግ አላየንም፡፡ በዜጎች ደም ተራ የቋንቋ ፌዝ ሲያፌዝ ከመስማታችን በቀር፡፡ ታዲያ የመሪ ተግባሩ ምንድን ነው? ይልቁንም እሱ ያደራጃቸው የመከላከያና የፖሊስ እንዲሁም ልዩ ኃይል በሚል በየክፍላተ ሀገሩ በሕገ ወጥ መልኩ የተደራጁት ኃይሎች ለዚህ ተባባሪ ሆነው ሲያገለግሉ መቆየታቸው የዐደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ አሁንም የሽብር ድርጊቶቹ በተለይ በጎጃሙ መተከል፣ በወለጋና በኮንሶ ቀጥሏል፡፡

በሌላ መልኩ ዐቢይ ትዕግሥቱ የሚያልቀው ሥልጣኑ ሲነካ ብቻ መሆኑን ከቡራዩው ጭፍጨፋ በኋላ ወታደሮች ወደ ቤተመንግሥት ሲመጡና በዙሪያው ያሉ ልዩ ዞኖች የሚገኙ ዘመዶቹ መንግሥታችን ተነካ ብለው ይመጣሉ ሲል፣ የቡራዩውን ጭፍጨፋ በመቃወም የአዲስ አበባ ወጣቶችን ተቃውሞ ለማፈን ሲያስገድልና በርሃ ሲልክ፣ እስክንድርና ጓዶቹን ከማኅበረሰብ  ተቋምነት እስከ ፖለቲካ ማኅበርነት በሚያደርጉት ሰላማዊ እንቅስቃሴ በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘታቸው ምክንያት ይህች ባቄላ ያደረች እንደሆነ በሚል ለራሱ ያደራጀውን ፖሊስ እና የፀጥታ ሠራተኞች እየላከ ባለማቋረጥ ሲያዋክብ÷ሲያስፈራራና ሲያስደበድብ÷በመጨረሻም ያለምንም ጥፋታቸው ወኅኒ ቤት ሲወረውራቸው፣ ከሀጫሉ ግድያ በኋላ ጀዋርና ተከታዮቹ ቤተመንግሥቱን ለመቆጣጠር ያላቸውን ዱለት ሲረዳ፣ የወላይታ ሕዝብ ወያኔ እና የዐቢይ አገዛዝ በደምና ባጥንት የተገኘ ያሉት አገር አፍራሽ ‹ሕገ መንግሥት› በፈቀደለት መሠረት የክፍለ ሀገርነት ጥያቄ ሲያቀርብ፣ አሁን ደግሞ ወያኔ አልጋውን ሊነጥቅ ጦርነት ሲጀምር ምን ድረስ እንደሄደ አስተውለናል፡፡ 

ወያኔ ዝግጅት ሲያደርግ የዐቢይ መደበኛና የመከላከያ ደኅንነት ኃይል ምን ይሠሩ ነበር? ላገር ተቆርቋሪ የሆኑ ሜዲያዎች መረጃና ማስረጃዎችን መሠረት አድርገው ደጋግመው የሰጡት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያስ ለምን ማንቂያ አልሆናቸውም? በሰሜን ዕዝ አባላት እና በማይካድራ የተፈጸመው ዘግናኝ የጦር ወንጀልና የዘር ማጥፋትን መቀልበስ አይቻልም ነበር? አንዱን የመንግሥት ተቋም ሌላው የሚቆጣጠርበትና የሚከታተልበት አሠራር ያለበት አገር ቢሆን፣ ማንም ወንበዴ ቡድን እየተነሳ ዜጎችን በጠራራ ፀሐይ በጅምላ እየፈጀ ተጠያቂነት የሌለበት አገር ባይሆን ኖሮ የዐቢይ አገዛዝና ግለሰቡ እልል ሊባልለት ቀርቶ ከተጠያቂነት ጋር ከሥልጣኑ በገዛ ፈቃዱ መልቀቅ አልነበረበትም? ጎበዝ! እናስተውል እንጂ፡፡ ወተት ከመጋት አልፈን ጥሬ መቈርጠም ላይ አልደረስንም እንዴ? ሁሌም ሕፃነ አእምሮ መሆን ያስተዛዝባል፡፡ ይህንን የምለው ብልሃት ለጎደላቸው እንጂ ዐውቀው ለሚያጠፉት አይደለም፡፡ 

የወያኔ/ሕወሓት ከኢትዮጵያ ገፀ-ምድር መጥፋት ከኦነግና ከጥቂት ግብረ አበሮቹና ግብረ በላዎቹ በስተቀር የኢትዮጵያ ሕዝብ የዘመናት ጸሎቱ ነው፡፡ የአገዛዙ ፍላጎት ግን ይህ እንዳልሆነ በግልጽ ነግሮናል፡፡ ሕወሓት እና አሁንም በአሸባሪነት ተግባሩ የቀጠለው ኦነግ የኢትዮጵያ ደመኛ ጠላቶች ናቸው፡፡ ግዑዛኑ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ ዓላማውን ዐውቀውና ተረድተው የመሠረቷቸውና አባላት የሆኑት በሙሉ እንጂ፡፡ የዚህ ድርጅት አባል መሆኑ በራሱ በገዛ ፈቃድ የሰይጣን ክልብ ውስጥ መቀላቀል ነው፡፡ ሥር የሰደደ በሽታ ነው፡፡ እኔ በግሌ መሥራቾቹንም ሆነ ዐውቀው ፈቅደው አባላት የሆኑትን በሙሉ ሰውነቴና ነፍሴ አጥብቀው ይጸየፏቸዋል፡፡ ልቡሳነ ሥጋ አጋንንት ለመሆን መርጠዋልና፡፡ አጋንንትን መጥላት ደግሞ ሰዋዊ ነው፡፡ ከጦርነቱ ማግስት የዐቢይ አገዛዝ በነዚህ የኢትዮጵያና ሕዝቧ ጠላት በሆኑ ድርጅቶች ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው? በሽሽት ያለፋቸው ጉዳዮች መሆኑን የሕዝብ ባልሆነው ምክር ቤት በነበረው ውሎ ተረድተናል፡፡

ሕወሓት በዚህ ጦርነት አማካይነት በተከፈለ መሥዋዕትነት ድል እንደሆነ እናምናለን፡፡ ቀሪ ርዝራዦች ቢኖሩም፡፡ ወያኔ የተከለው የአስተሳሰብ/የአመለካከት ነቀርሳና መዋቅሮቹ ግን በመላው ኢትዮጵያ ተንሠራፍተው ይገኛሉ፡፡ ይህ መርዝ በኢትዮጵያ የሠራ አካላት ናኝቶ ይገኛል፡፡ ዐቢይ አስተሳሰባቸውን እንጂ ሰዎቹን አልጠላም ካለ (እስክንድር ሰውየውን ካልጠላው በስተቀር ኢትዮጵያን በሚመለከት ምን የሚጠላ አስተሳሰብ ኖሮት ነው ደመኛ ጠላቱ ያደረገው?) ይህን ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ (በጦርነቱ ምክንያት ሕይወቱን ገብሮ) የሰጠውን ዕድል ለምን ሊጠቀምበት አልፈለገም? ከወያኔ አስተሳሰብ መገለጫዎች መካከል ዋናዎቹ አገር አጥፊው ‹ሕገ መንግሥት› (በየክፍላተ ሀገራቱ ወያኔ የጻፈላቸው ‹ሕግጋተ መንግሥታት›ን ጨምሮ)፣ በዚህም መሠረት የተተከለው የጐሣ ፌዴራሊዝም፣ የጐሣ ፖለቲካና ‹ክልል› የተባለው አፓርታይዳዊ የአትድረሱብኝ አጥር ይገኙበታል፡፡ ዐቢይ የኢትዮጵያን ሕዝብ አምኖና ይዞ እነዚህን ርምጃዎች ለመውሰድ ለምን ቆራጥነቱን አጣ? የምርጫ ማኅበራዊ መሠረቴ የሚለውን ሕዝብ ስለሚያጣና ራሱ የሚያራምደው የኦሮሙማ ፕሮጀክት ስለሚጨናገፍበት? አይመስለኝም፡፡ ሥልጣኔን ላጣ እችላለሁ የሚለው ሥጋት ግን የቀረበ ምክንያት ይመስለኛል፡፡ 

ከፍ ብዬ የጠቀስኳቸውን ወያኔና ኦነግ የተከሏቸውን አገራዊ ሳንካዎች ለማስወገድ ፈቃደኝነቱን ቢያሳይ በመላው የኢትዮጵያ ግዛት የሚገኙ ዜጎችን ማኅበራዊ መሠረቱ ማድረግ አይችልም? ይህን ለማድረግ ዝግጁነቱን ገልጾ የሚገጥመው ተግዳሮት ካለና አስፈላጊም ከሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ በድጋሚ ሕይወቱን ለመስጠት ዝግጅነቱን አልጠራጠርም፡፡ ታዲያ ዐቢይ የሚፈልገው ምንድን ነው? መደበኛ ትምህርትም ሆነ ሕይወት ያስተማራቸው በርካታ ዐዋቂዎችና ጠቢባን ባሉባት አገር እሱ የተሻለ መፍትሄ ስላለው ነው? ወይስ በጎ መካር በማጣቱ?

ሌላው በዚህ አስተያየት ሳላነሳው የማላልፈውና ዐቢይ ከሚመራው ኦሕዴድና የኦሮሙማ ፕሮጀክት አራማጆች በተደጋጋሚ የምሰማው አባባል አለ፡፡ ኦሮሞ በወርድና ቁመቱ ልክ በኢትዮጵያ የተለየ ቦታ ሊያገኝ ይገባዋል የሚል፡፡ ይህ አባባል በየትኛውም ነገድ/ጐሣ ቢነገር ከፍተኛ የሕማም ምልክት ነው፡፡ በጨቋኝ-ተጨቋኝ ትርክት ላይ የተመሠረተው የጐሠኞች አስተሳሰብ ዓላማ በኢትዮጵያ ነገዶች/ጐሣዎች መካከል እኩልነትን መፍጠር ነው ወይስ በሕዝብ ብዛት (ሊያውም በትክክል ቊጥሩ በማይታወቅበት፤ ቢታወቅም ለውጥ በማያመጣው) ብልጫ ብቻ ለአንዱ የተለየ ጥቅምና መብት ለመስጠት ያለመ ነው? ከሆነ ጭቆና/ባርነት ማለት ሌላ ትርጕም የለውም፡፡ የምን ወርድና ቁመት ነው? ወርዱም ይስፋ÷ቁመቱም ይንቀዋለል በኢትዮጵያዊ ዜግነት ረገድ ሁሉም እኩል መብትና ግዴታ ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን አስተሳሰብ ይዞ ስለ መንግሥተ ሕዝብ (ዴሞክራሲ) ማውራት አይቻልም፡፡ ለመብት፣ ለነፃነት፣ ለብሔራዊ ሀብት ተጠቃሚነት መሠረቱ የኢትዮጵያ ዜግነት ነው ብለን የምናምን ከሆነ የኢትዮጵያን ሀገረ መንግሥት በማስተዳደር ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ነገዶች/ጐሣዎች የቊጥራቸው ብዛት እንዲሁም የሚኖሩበት ግዛት ጥበትና ስፋት ግምት ውስጥ ሳይገባ እኩል ውክልና ሊኖራቸው ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ዴሞክራሲ የአብዛኛውን አስተዳደር የሚቀበል÷የውኁዳን መብት ደግሞ የሚያስጠብቅ ሥርዓት ነው ስንል ዜግነትን መሠረት አድርጎ እንጂ በጐሣ ሂሳብ አይደለም፡፡ በሌላ አነጋገር ከየትኛውም ነገድ/ጐሣ ይሁን የአብዛኛውን ሕዝብ ድምጽ የሚያገኝ ፓርቲ ወይም ግለሰብ አገርን ለመምራት እኩል ዕድል የሚያገኝበት ሥርዓት ማለት ነው፡፡ በየደረጃውም ባሉ የሥልጣን አካላት ይኸው መርህ በወጥነት ተግባራዊ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ዐቢይ ‹የራሳችን ዴሞክራሲ› የሚለው ‹የወርድና ቁመት ዴሞክራሲን› ይሆን?

ለማጠቃለል ጥቂት ሀብታሞች የበለጠ ሀብታም፣ አብዛኛው ድኆች የበለጠ ድኆች በሚሆኑበት ኢፍትሐዊ በሆነው ዓለማቀፋዊ ሥርዓት ውስጥ እንደ አገር ህልውናን፣ ብሔራዊ ጥቅምን፣ ክብርንና ኩራትን አስጠብቆ ለመቀጠልና ማናቸውንም ጫናዎች በብሔራዊ ስሜት ለመቋቋም ከሁሉም አስቀድሞ የጋራ በሆኑ ዐበይት አገራዊ ጉዳዮች ላይ ተስማምቶ፣ ብሔራዊ ሀብታችንን በፍትሐዊነት ለጋራ ጥቅም በማዋል፣ ልዩነታችንን ተቀብሎ ባንድ አገር ጥላ ሥር ልዩ ልዩ ቋንቋ÷ ባህል÷ሃይማኖት ይዞ ተከባብሮ መኖር የጥንካሬ ምንጭ ከመሆኑም በላይ ሊውጡን ካሰፈሰፉ ኃይሎች ባርነት መውጫው ሁነኛ መንገድ ነው፡፡ በመሆኑም ከተዘፈቅነበት ድንቁርናና ጨለማ መውጫ ጊዜው እጅግ ዘግይቷል ከሚባል በቀር አሁን ነው፡፡ በዚህ ጦርነት የተገኘውን ድል ሳናባክን ለዚህ ቅዱስ ዓላማ ብናውለው ኢትዮጵያና ሕዝቧ በእጅጉ ያተርፋሉ፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ ቅድሚያ አጀንዳ ምርጫ አይደለም፡፡ ከተዘፈቅንበት ‹ማጥ› ውስጥ ሳንወጣ ስለ ምርጫ ማውራት ዕብደት ነው፡፡ እባካችሁ እምነት ካላችሁ ስለ እግዚአብሔር ብላችሁ፣ እምነት ከሌላችሁ ስለ ኅሊናችሁ ብላችሁ ያባከናቸው የማይመለሱ ጊዜያት ቆጭተውን አገራችንን በመታደግ ለትውልድ የሚተርፍ ሥራ ላይ እንሠማራ፡፡ ዐቢይ በቅኔ ሊነግረን እንደሞከረው የእሱ ‹ብልጽግና› መጥፊያችን እንጂ ታዳጊያችን አይሆንም፡፡ 

ወገን በወገኑ ላይ ጥቂቶች በልተው አብዛኛው ጦሙን የሚያድርበት የግፍ ሥርዓት የሚጭን ከሆነ፤ ፈረንጆቹስ (የራሳችንን ስግብግቦች በመያዝ) በርጥባን፣ በብድር፣ ይህን ፕሮጀክት ልሥራላችሁ በሚል ሽፋን አገርን በአራጣ ይዘው በባርነት ከሚያኖሩበት ዓለምአቀፋዊ ሰይጣናዊ ሥርዓት በምን እንለያለን? ወደ አእምሮአችንና ኅሊናችን ሳንመለስ ባሳለፍናቸው 30 ዓመታት በመጣንበት መንገድ እንቀጥል ካልን አገርን ልናጣ ወደምንችልበት አሸናፊ የሌለው የርስ በርስ እልቂት ውስጥ እንደምንዘፈቅ አሳቢ አእምሮ፣ አስተዋይ ልቡና እና በጎ ኅሊና ብቻ በቂ ነው፡፡ ጆሮ ያለው መስማትን ይስማ!!!

Filed in: Amharic