>

ኧረ ታዛቢም ፍሩ...!!! (መሐመድ አሊ መሐመድ) 

ኧረ ታዛቢም ፍሩ…!!!

መሐመድ አሊ መሐመድ 

ጠቅላይ ሚ/ሩ “ዛሬ እዚህ የጠራናቸው ፓርቲዎች ተካፋይ ያልሆኑና በሀገር ጉዳይ ላይ የማይደራደሩ ናቸው” አሉ። ኧረ ይሉኝታ ፍሩ! ዛሬ በጠ/ሚ/ሩ ጥሪ ከታደሙት አብዛኞቹ፣ ትናንት የፌዴራሊስ ኃይሎች በሚል በህወሓት አስተባባሪነት መቀሌ ላይ ሲታደሙና ውስጣችንን ሲያደሙን የነበሩ አይደሉም እንዴ? አንዳንዶቹ ቀደም ሲል ገዥውን ፓርቲ ሊገዳደሩ የሚችሉ ጠንካራ ፓርቲዎችን ያፈረሱና የደህንነት ተከፋዮች እንደነበሩ በግልፅ የሚታወቅ አይደለም እንዴ? ወይስ ዛሬ ህወሓት መክፈል በማይችልበት ሁኔታ ላይ ስለሆነ ይሆን “ተከፈይ አይደሉም” የተባሉት?
በዚህ ውይይት ላይ critical ሀሳቦች ሲነሱ አልሰማሁም። ሚዛን የሚደፋ ሀሳብ ያላቸው ሰዎች ሲናገሩም አላየሁም። ይልቁንም ጠቅላይ ሚ/ሩ ፓርቲዎቹን እንደልጅ ሲመክሩና ሲያስተምሩ ታዝቤያለሁ። ፓርቲዎች በተመጣጣኝ ደረጃ (on equal footing) ሳይሆኑ እንዴት ተፎካካሪ መሆን ይቻላል? ጠቅላይ ሚ/ሩ “በምርጫ ሳይካሄድና ሳትወዳደሩ ሥልጣን ትፈልጋላችሁ” ብለው መሳለቃቸውስ የጤና ነው? የምር ግን እንዲህ የሚያስብ ፓርቲና ፖለቲከኛ አለ?
በዚህ አስተሳሰብ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን መገንባት እንዴት ይቻላል? በጠ/ሚ/ሩ እይታ “ዴሞክራሲ በሂደት የሚገነባው ነው” የሚባለውስ እስከመቼ ነው? ይኸ ነገር ለ30 ዓመታት እስከሚሰለቸን ተደሰኮረኮ። ይልቁንስ ለእውነተኛና ትክክለኛ ምርጫ አመች ሁኔታዎችን ለመፍጠር በአጭር ታጥቆ መሥራት አይሻልም? እስቲ የምር እንነጋገር፣ አሁን ባለው የሀገራችን ሁኔታ፣ የተለያዩ አማራጭ ሀሳቦች ያሏቸው ፓርቲዎች በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች እስከታች ወርደው ሀሳባቸውን ለህዝብ ማቅረብ ይችላሉ ወይ? ህዝቡስ የተለያዩ ሀሳቦች ቀርበውለት የተሻለውን መምረጥ የሚችልበት ዕድል አለ ወይ? ካልሆነ የህዝብን የሥልጣን ባለቤትነት ማረጋገጥ የሚቻለው እንዴት ነው?
በግሌ ጠቅላይ ሚ/ሩ ኢትዮጵያዊነትን የምር እስካቀነቀኑ ድረስ በሥልጣን ላይ ቢቆዩ ችግር የለብኝም። ነገር ግን በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ተወዳድረው መሆን አለበት። ለውድድር ደግሞ ተወዳዳሪ ያስፈልጋል። ጠንካራ ተወዳዳሪዎችን ከዙሪያህ አርቀህ ስለነፃና ፍትሃዊ ምርጫ ብታወራ አጉል ምፀት ነው የሚሆነው። ጠ/ሚ/ሩ “በ97 ምርጫ ተቃዋሚዎች የሸጡት ሀሳብ አሁን ለመጣው ለውጥ እርሾ ሆኗል” ማለታቸውን ወድጀዋለሁ። ግንኮ በ97 ምርጫ ጉልህ ሚና የነበራቸው ሰዎች ዛሬም ከነሀሳባቸው በህይወት አሉ። ወይስ ለእናንተ የሚቀርብ አንድ ግለሰብ ብቻ ነው የሚታያችሁ?
በነገራችን ላይ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶ/ር ጌዲዮን ያቀረቡት ጽሁፍስ ቢሆን አግባብነት ያለው (relevant) ነው ወይ? ማለትም የምርጫ ህጉንና ህገ-መንግሥቱን የማሻሻል ዕቅድ ከሌለ፣ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ስላሉ (በእኛ ሀገር ተፈፃሚነት ስለሌላቸው) የምርጫ ሥርዓቶች ማውራት ፋይዳው ምንድነው? ይልቁንስ ከፊታችን ያለው ምርጫ 2013 ምን መልካም ዕድሎችና ተግዳሮቶች አሉት? በሚለው ላይ የምር (critically) መነጋገር አይሻልም ነበር ወይ?
ይህም ሆኖ፣ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ የተለያዬ አስተሳሰብና አመለካከት ያላቸውን ወገኖች ቀረብ ብለው ለማነጋገር ያላቸውን ተነሳሽነትና ሰውኛ ባህሪ ሳላደንቅ አላልፍም። ይህም ለተራ የፖለቲካ ፍጆታ እንደማይሆን ተስፋ አደርጋለሁ!!
ሌላው ከተወሰኑ ሳምንታት በፊት ምርጫ ቦርድ በፌስቡክ ገፁ ላይ “ስለ ምርጫ ስርአት ያስጠናሁት ጥናት” በሚል የለቀቀውን ሰነድ ካየሁ በኋላ ለአንድ ወዳጄ :-
“ይህ ሰነድ ብርቱካን ሚደቅሳ ‘ተቃዋሚዎች ሆይ አንብቡትና በጉዳዩ ላይ ራሳችሁን አብቅታችሁ በቀጣይ በሚኖረኝ ትግል አግዙኝ’ ያለችበት ሰነድ ነው ግን የትኛው ተቃዋሚ አንብቦ ይሄድ ይሆን? ብዬው ነበር።”
የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሲያሰራጭ ንግግራቸውን የቆረጠባቸው ሰዎች ስለመኖራቸው አላውቅም። በተላለፈው ፕሮግራም ላይ ግን ተቃዋሚዎች ስለ ጉዳዩ አዲስ ሆነው ቁልጭ ቁልጭ ሲሉ እና እዚህ ግባ የማይባል ቅጥ አምባሩ የጠፋ ሀሳብ ሲያነሱ ነው የዋሉት።
ራሷ ብርቱካን ሰነዱን አንስታ ነው ለመሞገት የሞከረችው። በአብዛኞቹ ተቃዋሚዎች ሊነሳ ይገባው የነበረውን ሀሳብም ያነሳችው እሷው ብቻ ናት።
Filed in: Amharic