>

ነገረ ለማ እና ነገረ አብይ - የጠቅላዩ የፓርላማ ውል!  (ሥርጉተ ሥላሴ)

ነገረ ለማ እና ነገረ አብይ – የጠቅላዩ የፓርላማ ውል!  

ሥርጉተ ሥላሴ
አብይ ወ ለማ….,!
አብይወለማ በኮንፊዩዝድ እና በኮንቢንስ መርህ ከነዱን በኋላ መለዬት አህዱ ያለው መቼ ነው?
1) ጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ እንደ ልጅ እያሱ ዘመን ስለሚያደርጋቸው ያንጊዜ ወደ ተፈጠረው የሴራ ሙልሙል ሰተት ብለው ገቡ ደጃች ይሁኑ አይሁኑ ማዕረጉ ይስተካከልኝ ተሰማ ናደው የሄዱበት የሴራ መስመርን ደገሙት።
 ቀንበጥ ብሎጌ ላይ በዝርዝር ሰርቸዋለሁ። ይኽውም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በግል አቶ ለማ መገርሳ ሳይኖሩበት የመከሩበት ወቅት የጠቅላላ የነበረው ተስፋ መፈንቅል የተከወነበት የታሪክ ክስተት ነበር።
ጠቅላዩ ኦህዴድን አውልቀው ወይ ቀይጠው የግንቦት 7 መንፈስ በውስጣቸው ችግኙን የፈቀዱበት። አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ የማድመጥ አቅም ያላቸው በሳል ፖለቲከኛ ናቸው። ጠቅላዩ የአቶ አንዳርጋቸው የብቃት ርዕይ ምርኮኛ ናቸው።
ከሳቸው ጋር እኔ ሁለት ጊዜ በመድረክ ተገናኝተናል።
1.1 ሲዊዝ የቅንጅት ድጋፍ ሰጪ አካል ሲመሰረት፣ እሳቸው ከለንደን፣ ዶር አሰፋ ነጋሽ ከሆላንድ፣ ሥርጉተ ሥላሴ ከሲዊዘርላንድ አቶ ሚስጢረ ኃይለሥላሴ በጄኔባ ዩንቨርስቲ አዳራሽ ባዘጋጁት የወርኃ ሚዚያ ጉባኤ በገላጭነት አብረን ተገኝተናል።
 ያገደውን ቪዲዮውን አንድ ቀን አዘጋጁ አካል የራሱም ታሪክ ነውና ይፋ ያደርገው ይሆናል።
2.2 የጀርመን ፍራንክፈርት አማይን የግንቦት 7 መሥራች ጉባኤ ላይ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ከለንደን በገላጭነት፣ ሥርጉተ ሥላሴ ከሲዊዘርላንድ በሰብሳቢነት በድጋሚ ተገናኝተናል።
 ቪዲዮውን የሰማያዊ ድህረ ገፅ አዘጋጅ ጉዲት ብለው በሞገቱኝ ፔጃቸው ላይ ይገኛል። እኔም ሽንፍላ ብዬ የሞገትኳቸው ጡሁፍ ደጉ ዘሃበሻ ላይ ይገኛል። ደግመው አልሞከሩትም። ስለተግባባን  ይመስለኛል።
ይህን ያነሳሁት ያለምክንያት አይደለም። ጠቅላዩ በአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አቅም ምርኮኛ ቢሆኑ እኔ አልፈርድባቸውም።
እኔንም ማርከው እስከተፈቱበት ጊዜ ከድርጅታቸው በላይ በብራና ህዋህትን ሞግቸዋለሁ። መፈናፈኛ ነስቼ። ሲታሠሩ ሁለት ወር ጥቁር ለብሻለሁ። ኢትዮጵያ ህሊናዋን እንዳጣች ይሰማኝ ነበር።
ዕድሉን ካገኙ ለበጎም፣ ለመጥፎም መሥመር ማህንዲስ ናቸው። የኢትዮጵያ መከራ ያለው በዚህ ውስጥ ነው።
የጠቅላዩ እና የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ዝግ ስብሰባ ያ ቀን የአቶ ለማ መገርሳ እና የጠቅላይ ሚር አብይ አህመድ የመንፈስ ጋብቻ ስንጥቅ የገጠመው ዕለት ነበር። የጠቅላዩ የተቀባይነት መሸርሸር ስልታዊ የውድቀት አህዱም ነበር። የኦሮማራ ቃልኪዳንም ንደት በር የተንኳኳበት።
2) ጠቅላዩ ከድነውት ያለፋት ሌላው አመክንዮ የ16/2010 የምስጋና ቀን ነው። ይህ ቀን ኦህዴድም ያቀደው ነበር። በዛ የሴራ ጉንጉን ድርጅታቸው አለበት።
አቶ ለማ መገርሳ አልተገኙም። ይህም ብቻ ሳይሆን የተጎዱትን ለመጠዬቅ ሆስፒታል ሲገኙ በጣም ዘግይተው፣ በዛለ ስሜት ሰውኛ ጣዕም በሌለው ቃና የሰይጣን ሥራ ሲሉ ገልጠውታል። የህዝቡ ድጋፍ አስደንግጧቸዋል። እሳቸውን ብቻ አይደለም አጤ ግንቦት 7፣ ኦፌኮን ጭምር።
የአቶ ለማ መገርሳ የቅናት እርሾ በዚህ ቀን የተጠነሰሰ ይመስለኛል። ከዛ በኋላ ላም ጣም ያለው ሁነት አላዬሁም።
3) ጉዞ አሜሪካ። አብረው ተጓዙ። በሚኒሶታው ንግግር ብቻዬን ነበርኩ እንኳን ኖራችሁልኝ አይነት ምት ነበረው ሞቅ ደመቅ ያለው ንግግራቸው።
ከዛ በፊት የኢትዮጵያ ህዝብ ለሳቸው የሰጠው ክብር እስር ቤት አድርገው ነበር ያዩት። አቶ ለማ መገርሳ ከኦሮሞ ፖለቲከኞች ከኮ ገመቹ አያኖ ባልተናነሰ ሁኔታ የሰከኑ፣ ጭምት መሪ ናቸው።
4) ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ነበር ጠቅላዩ። ፕ/ አለማርያም አክ ወሬ ቢሉትም፣ የሆነ የመመረዝ ገጠመኝ ግን ነበር። ይህን ከዕውነተኛ ቤተሰብ እኔ ሰምቻለሁ። እሳቸውም ህልም ሳያዩ አልቀሩም።
 ይህ በማን ተከወነ? ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ በኦሮሞማ ማህበርተኞች የገጠመው ቀውስ አይነኳትም። ለምን?
5) ከአሜሪካ መልስ ጠቅላዩ ታግተው ነበር እስከ ቤተሰባቸው? በማን ታገቱ? እማስታውሰው አንድ ዓለም ዓቀፍ የሴቶች ጉባኤ የከፈቱት ወሮ ሮማን ተስፋዬ ነበሩ። ለምን?
በዛ ወቅት ጠቅላዩን ፎቷቸውን ብቻ እንጂ ድምፃቸውን መስማት አይቻልም ነበር? ሞቱ ሲቀር ዕገታውን ማን ከወነው? አብረዋቸው የተጓዙት አቶ ለማ መገርሳ ነበሩ።
6) አሜሪካ እያሉ ስለ ኦነግ ሲጠዬቁ በቅርቡ ኤርትራ ሄጄ አገኛቸዋለሁ ብለውን የተፈቀደላቸው ግን አቶ ለማ መገርሳ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ብቻ ነበሩ። የሚገርመው ሲሄዱ የመንግሥት ሚዲያ ዘግቦት ሲመለሱ ግን የውሽማ ሞት ነበር። ለብዙ ቀናት አቶ ለማ መገርሳ ተሰውረዋል።
 ከዚህ ጋር አያይዤ እማነሳው በአማራ ታጣቂዎች ለማደራደር የተላኩት አቶ ደመቀ መኮነን፣ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ ዶር አንባቸው መኮነን እያሉ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ነበሩ። ለምን? እስካሁን ድረስ አቶ ደመቀ መኮነን ኤርትራን አያውቁትም። ለማሟያ ጊዜ ብቻ ነው የሚፈለጉት።
7) የቡራዩጭፍጨፋ፣ የአዲስ አበቤ እስር እና ጭፍጨፋ የተመራው በኦህዲድ እና በኦነግ ነበር ብዬ አምናለሁ። ያንጊዜም አቶ ለማ መገርሳ የክልሉም፣ የኢትዮጵያም ስውር መሪ ነበሩ። ድምጣቸው ግን አይወጣም።
ይህንንም ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ አህመድ ሳይነካኩት ያለፋት ጉዳይ ነው። ለምን?
8) ከህወሃት ጋር የአብረን እንሥራ ጥሪ በቀውሱን በማደራጀት፣ በመምራት የራሳቸው ድርጅት ስላለበት መድፈር ተሳናቸው። አንችላቸውም የእንታረቅ ጥሪ የቀረበው ከአቶ ለማ መገርሳ ነው።
በዚህ ውስጥ እስትንፋሻቸውን የአማራን ህዝብ በመካድ እረገድ ጠቅላዩም አቶ ለማም አቋማቸው አንድ ነው። መቼውንም አማራ ከዚህ አሪዎስ መንፈስ መታመንን አያገኝም።
ቦንዳ ጆከር።
ቦንዳው ጆከር አቶ አባ ዱላ ገመዳ ናቸው። በሁለት መንትዮሽ ህወሃትን በተኃድሶ የማስቀጠል ህልም ነበር። ሁለቱ ግራ እና ቀኝ ጎኖች አቶ በረከት ስምዖን እና አቶ አባ ዱላ ገመዳ ነበሩ። ታስታውሳላችሁ የሥራ መልቀቂያው ቲያትር እና የገበጣ ጨዋታው።
የሴራ ቸረቸራው የአቶ በረከት ስሞዕን እስርም ከዚህ አመክንዮ ጋር የሚያያዝ ነው። የታሠሩት አማራን ስለበደሉ ሳይሆን የአጤ አባ ዱላ ገመዳ ሽርብ መንፈስ እንዳይቀጭ የተከወነ ነው።
ሦስት ጠቅላይ ሚኒስተር ኢትዮጵያ ነበሯት። ጠቅላዩ ይፋ አቶ ለማ መገርሳ እና አቶ አባ ዱላ ገመዳ በሥውር። አሁን በአቶ ለማ መገርሳ ትክ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ናቸው። የዚህ ጉልህ ባለድርጃ የፖለቲካ ሲቃ ሊቀ መኳስ ደግሞ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ናቸው።
በዚህ ውስጥ ብዙው አብይዝም እንዳይረሳ። የራሱ አርት እና ቀለም ያለው ሰብዕና ነውና። እራሱን የቻለም ሌሰን ነው።
የጃዋር ንቅናቄ።
በዚህ የለውጥ ንጥ ቀላል የማይባለው የሞገድ አብዮት የአቶ ጃዋር መሃመድ ንቅናቄ ነበር። ጠቅላዩን የፈተነም የፈተለም። የእሱን ኃያል መንፈስ ጥሶ ለመውጣት በሙከራም፣ በስኬትም ሁለት ጊዜ ሞክረው ጠቅላዩ አሳክተዋል።
 ከሁሉም ትቢያ ያለበሰው ግን አቶ ኤርምያስ ለገሰ ነው። በቃ ቀብሮታል። ከጠቅላዩ ጋር መቼውንም ቢሆን እርቀ ሰላም እንዳይወርድ አድርጎ ገንዞታል።
አቶ ጃዋር መሀመድ ግራጫማ ሲቃ ሰብዕና ያለው ሰው ነው። በስፋት ብሎጌ ላይ ፅፌዋለሁኝ። ወደዛ አልመለስም የተስፋውን አሟሟት ቃሬዛ አልባ ያደረገው አቶ ኤርምያስ ለገሰ ነው።
አቶ ኤርምያስ ለገሰን ጎልጉሎች፣ የግንቦት 7 ሰዎች ሲያብጠለጥሉት አስተውላለሁ። ትናንትም ዛሬም ላመነበት አመክንዮ ሞተር ነው። ከትልልቆቹ ፖለቲከኞች አይመድቡትም። አቅሙም ሆነ የትግል ስትራቴጂ እና ታክቲኩ ዒላማውን ስቶ አያውቅም። ጀርመኖች ፑንክትልሽ ይሉታል ሰብዕናውም።
ለመናድም ለመገንባትም አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ያላቸውን ሙሉ አቅም ሳይሸራረፍ ያለው ፖለቲከኛ ነው። ለበጎ፣ ለጤናማ ሁነት ክህሎቱን ቢውለው፣ ጥሩ አማካሪ ቢያገኝ ጉልህ ሦስት ድክመቶችን አርሞ ፈጣሪን ቢጠይቅ፣ ንሰኃ ቢገባ፣ የጥሞና ጊዜ ቢኖረው መሪ የመሆን አቅሙ አንቱ ነው።
እሱን አጀንዳቸው በአወንታዊም በአሉታዊም የሚያደርጉ ሰዎች ጭፍጫፊ ተኮር ነው ዕይታቸው። ያልተገባ ሪኮመንዴሽን ነው። እሱንም አያውቁትም።
ለማወቅም አጀንዳቸው አይደለም።  ንቀት ይሁን ምን አላውቅም። አሁን ባለው የግራ ቀኝ ፖለቲካ ወሳኝ ሚና እዬተጫወተ ያለ ሰው ነው።
ክወና።
ጠቅላዩ ሰው አለኝ ብለው ያስባሉ። አይሰቡት። መለመላቸውን ይቆሙ ዘንድ የአንዲ ፕሮጀክት ለድል በቅቷል። ወደ ገደሉ አሁንም እዬገሰገሱ ነው።
ያን የመሰለ የሰማይ መላዕክት የረበበት ፍቅር ባፍ ጢሙ ደፍተውታል። የተሰማሩት ወዘተረፈ ሚዲያዎች አቅም የሳሙና አረፋ ነው። በድንግልና የተቀበሏቸው መንፈሶች እኔን ጨምሮ ዛሬ የለም።
የሰከነ፣ የጠራ፣ የበሰለ፣ ምንም ቅምጥ ፍላጎት ያላንጠለጡ ሰብዕናዎች ድጋፍ ማጣት አለመታደል ነው። ይቀጥላል። እግዚአብሔር ይስጥልኝ።
ኢትዮጵያዊነት ተፈሪ ማንነት።
Filed in: Amharic