>
5:14 pm - Saturday April 20, 0126

ለጓድ ጌታቸው ጀቤሳ ስለ አብዮት ክዋክብት እና ሌሎች ነጥቦች (አናንያ ሶሪ)

ጤና ይስጥልኝ- ጓድ ጌታቸው! ባለፈው ወር ከ ‹‹ዕንቁ›› መጽሔት ልዩ ዕትም ጋር ያደረጉትን ቃለ ምልልስ ለሁለት ጊዜያት ያህል በጥልቅ ተመስጦ አነበብሁት፡፡ አንብቤም አልቀረሁ ወደ ስምጥ- ተደምሞ ውስጥ ጭልጥ ብዬ ገባሁና ድንገት ስነቃ ፃፍ ፃፍ አለኝ፡፡ ይኸውና የበኩር ልጄን ካገኘሁበት ደቂቃና ሰኮንድ ጀምሮ ላለፉት 7 ወራት የዘነጋኋት ብዕሬን እንደገና አነሳሁ፡፡
‹‹በሥራ በዕውቀት ግሎ ለመነሳት
ቆስቋሽ ይፈልጋል የሰው ልጅ እንደ እሳት››
ብለው እንደተቀኙ ክቡር የስነ-ጽሑፉ ሰው ከበደ ሚካኤል፤ እኔም በርስዎ ምናብ-ቀስቃሽ ልዩ እይታዎችና ለክርክር ጋባዥ ምልከታዎች ሳቢያ ለበለጠ ዕውቀት ስል የሁለት ትውልዶች ወግ መጀመር ፈለግሁ፡፡ መልካም ፈቃድዎ ሆኖ የኔ ትውልድ ያለበትን የዕውቀትና የታሪክ ክፍተት ለመሙላት የሚያደርገውን አጋዥ የለሽ መውተርተር በወንድም ጋሻዊ ቅርበት ቢሞሉት ዘንድ ታላቅ ምኞቴ ነው፡፡
‹‹በአብዮቱ ውስጥ ጥርሴን የነቀልኩ ሰው ብሆንም፣ ዛሬ የጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ኃብተወልድ አድናቂ ነኝ›› የሚል ዓረፍተ ነገር ከምላሽዎ መሐል በሃይለ-ቃልነት በመጥቀስ ያሰፈረችው ‹‹ዕንቁ›› መጽሔትም በሃሳብ-ጫሪነቱ በኩል የድርሻዋን ተወጥታለች- ለዚህ መጣጥፍ መፈጠር፡፡ ከዚሁም አባባልዎ ልንደርደርና ወጋችን እንጀምር…….
ምን ማለትዎ ነው ጓድ ጌታቸው? በተለይ ከተጠቀሰው ዓ/ነገርዎ ቀጥሎ ያሰፈሩት ‹‹ከእኛ በራቁ ቁጥር ታላቅነታቸው እየጎላ የሚሄዱ የታሪክ ሰው ሆነው ነው ያገኘኋቸው፡፡›› ሲሉ ምን ለማለት እንደሆነ ግልፅ አይደለም – ተፍታቶ ስላልተብራራ! እንደው በራሴ ግን እንደተረዳሁት ከሆነ፡- እኚህና ሌሎች የተጠቀሱት ግለሰቦች በግለሰብ ደረጃ መልካም ጐናቸው ቢያመዝንም፤ አካል-አምሳል የሆኑበት ‹‹ሥርዓትን›› ግን ሥርዓት-ማስያዝ ስለተሳናቸው ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ የሆኑ መሰለኝ፡፡
በዚህ ጉዳይ ሳሰላስል ትዝ ያለኝ ነገር ቢኖር በዚችው ‹‹ዕንቁ›› መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር109 ዕትም ላይ ሻምበል ፍቅረሥላሴ ወግደረስ (በልጅነቴ ‹‹አለባበስ እንደ ፍቅረሥላሴ ወግደረስ›› ሲባል ብቻ በሰማሁት በጨረፍታ የማውቃቸው) የተናገሩት፡ – ‹‹የፊውዳሉ ሥርዓት ሀገርን የፈጠረ መሆኑ የማይካድ እውነት ነው›› የሚለው ምላሻቸው ነበር፡ ፡ ይህም ምላሻቸው ሊታሰበኝ የቻለበት ምክንያቱ ደግሞ፡- እርስዎ (ጌታቸው ጀቤሳ) እና ከዚያም በኋላ በለስ የቀናቸው የበረሃ ታጋዬች ‹‹አብዮት›› ልታካሂዱ የቻላችሁባትን ሀገር ቀድሞውኑ ፈጥረው ከነእንከኖቿም ጭምር ቢሆን ያቆዮዋችሁ እነዚያው ‘ፊውዳሎች’ በመሆናቸው ነው፡፡ ወትሮስ አገር ከሌለ በማን ይለቀሳል? በማንስ አብዮት ይካሄዳል? ይህን ሳስብ ደግሞ ሌላም ሃሳብ በአይምሮዬ ትግል አሳብኩና ከሰትሁ፡፡
ይኸውም ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም ‹‹ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?›› በሚለው መጽሐፋቸው ውስጥ ያኖሩት ሃሳብ ነው፡፡ ያም ‹‹የቤቴ መቃጠል ለትኋኑ በጀኝ›› እንዳለው ቂል አንሁን፤ የኢትዮጵያ ችግር ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን አምባገነንነት ነው›› ያሉት ሃሳብ ነው፡፡ በግል ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ባደረኳቸው ውይይቶች እንደተገነዘብኩት እነራስ አበበ አረጋይን የመሰሉ ለሀገር ታላቅ-ውለታ የሠሩ አርበኞች በደርግ መገደል ስህተት እንደነበር ነው፡ ፡ ይህም ማለት፡- ለኢትዮጵያና ለምትወከልበት የባዕድ ቅኝ አገዛዝን የመከተ ኢትዮጵያዊ የነፃነት ትእምርት (An Ethiopian Symbol of freedom from colonizers) በአርበኝነት ተጋድሎ ለፈፀሙ ኢትዮጵያዊ ይህን የመሰለ አፀፋ መስጠት፤ እጅግ ታላቅ ታሪካዊ-ስህተት እንደነበር እና ለትንኝ ለኩሶ ቤት እንደማቃጠል ያለ ቂልነት (ብልሀት-አልባነት) መሆኑን ነው፡፡
ሀገር ፈጣሪዎቹ ወይም በራሳቸው ዘመን አባባል ሀገር-አቅኚዎቹ ያጐበጡት ባለ ሀገር፣ የቆረጡት ጡት፣ የሰበሩት ቋንጃ፣ የፈነገሉት ‹‹ባሪያ››፣ ያሳረሱት ጭሰኛ…. መኖሩ የታሪክ አስቀያሚ ሃቅ ቢሆንም፤ ይህ የሠሩት እኩይ ተግባር የሠሩትን ሰናይ ተግባር ሁሉ ደምስሶ እነርሱንም በፍፁም ሰይጣንነት አስፈርጆ ለጭፍን ጥቃት ሊዲርጋቸው ባልተገባ ነበር፡፡ ስሜታዊ ካልሆንንና ሚዛን ካልሳትን በቀር ከሰው ስህተት (ኃጢአት) ከብረት ዝገት እንደማይጠፋ ባልተሠወረብን ነበር! የእውቀት ብርሃን ካለመስፋቱም የተነሳ የጠፉት ነገሮች ጥቂት ተብለው የሚታለፉ አይደሉም፡፡
ይሁንና፡- እነዚህን ሁሉ ሰዋዊ እና የማኀበረሰብ የዕድገት ሂደትን የተመለከቱ ውስብስብ ጉዳዮች በጥሞና አስተውለን ሳናይ ቀርተን የችኮላ እርምጃ ከወሠድን፤ በኋላ መዘዙም ፀፀቱም የከበደ ይሆናል፡፡ በተለይ ‹‹እርምጃው›› አብዮታዊ ሲሆንና መተኪያ የሌለውን የሰው-ልጅ ውድ ሕይወት የሚነጥቅ ሆኖ ከተፍ ሲል፤ እንደሀገርና እንደ ሕዝብ የሚያስከፍለንም ዕዳ ከትውልድ-ትውልድ እንደሚተላለፍ መርገምት አሽመድማጅ ነው፡ ፡ ደግሞውንስ፡- የሰውን መጥፎ ስራ እንጂ ሰውን ራሱን መጥላት፣ ጠልቶም መግደል ያንን መጥፎ- ስራ ይገድለዋል?! ታዲያ፡- መጥፎው ስራ ላይሞት ነገር መጥፎ ስራ ሠሪውን መግደል መፍትሄ ይሆናል?!
‹‹አርሶ መራብና ተኩሶ መሳት
እያደር ይፈጃል እንደ እግር እሳት››
እንዲል ያገሬ ገበሬ እርስዎ-ጓድ ጌታቸው ጀቤሳም የዚህ ‹‹አብዮት›› አንዳንድ ነገረ-ሥራ እያደር እንደሚከነክንዎ ተሰማኝ-ከአመላለስዎ! ፕሮፌሰር መስፍን ከእንዲህ ያለው እያደር የእግር- እሳት ከሚሆን ፈተና መውጪያ መንገዱንም ጠቁመዋል-በውይይታችን ዘመን! የቲቶን ቼኮዝሎቫኪያ በአስረጂነት ያነሳሉ፡፡ አሁን ለጊዜው በስም የማላስታውሰውን የቼኮዝሎቫኪያ አርበኛ፤ ቲቶ አብዮት ሲያካሂድ በርዕዮተ-ዓለም ምክንያት እንዳልገደለው በማስረዳት ፤ የሥርዓት ለውጥ ቢፈለግም የአገርን ምሰሶና ማገር ግን ሳያናጉና ሳይነቀንቁ መሆን እንዳለበት ዛሬም በ84ዓመት ዕድሜያቸው ሳይታክቱ ያስተምራሉ፡፡ ከንባብም ከተመክሮም ያገኙትን ዕውቀት ቀምረው እንካችሁ የሚሉን ጉምቱው አሰላሳይና መምህር ፕሮፌሰር መስፍን ወ/ማርያም!
ታዲያ ምን ዋጋ አለው? አብዮቱ ስር-ሰደድ (deep-rooted) መሆን ሲገባው በተውሶ መነፅር ከሶቪየት ሩሲያ ባገኘው የንድፈ-ሃሳብ መመልከቻ (a theory as an eye glass) የተነሳ ሥር-ነቀል (Radical) ሆነና ፤ ሁሉን ከስሩ መነጋግሎ ጥሎ የኢትዮጵያዊነት ትእምርት ወይም አርአያ-ምሳሌ (Symbols) የሆኑትን የአገር ባለውለታዎችን ከነወከሉት ሃሳብም ጭምር ገደላቸው፡፡ ቀጣዩ ትውልድም እንደመነሳሻ-እሳት (Inspiration) የሚያቀጣጥሉትን ቀዳሚ-ነበልባሎች አጥቶ እና ከሥሩ ተነቅሎ በኦና ምድረ-በዳ ላይ ያለ ክቡር ዓላማ ለከንቱ መብልና ውሀ ብቻ መዋተት ጀመረ፡፡
እነሆም እስከ የኔ ትውልድ ድረስ መስተሐልይ (Mind) እንደሌለው እንስሳ ሁሉን ከአልቦ (ዜሮ) ለመጀመር ተገደደ፡፡ ከቀደመው ታሪኩ ጋርም ክፉኛ በመቆራረጡ የተነሣ አውነቱን ከቅጥፈት-ሰበካው መለየት ተስኖት ሚዛን ስቶ ግራ ተጋባ፡፡ እየፈጩ ጥሬ፣ ታጥቦ ጭቃ፣ ከርሞ ጥጃ፣ ውኃ-ቅዳ ውሃ-መልስ (አሁን አሁን እንኳ ውኃውም በፈረቃ ስለሆነ የሚቀዳም የሚመለስም የለ¡) ….የሆነ የአዙሪት ኑሯችንን ኖረን ኖረን ኖረን ይኸው ቀጣይቷን ትውልድም መውለድ ጀምረናል፡፡
ከዛሬ አርባ ዓመት በፊት ከነበረችው ኢትዮጵያ ያነሠች፣ በዓለሙ ፊት ዜጎቿ የተዋረዱባት፣ የተማሩ ዶክተሮቿ እና ፓይለቶቿ ጥለዋት ወይም ጠልፈዋት የሚጠፉባት፣ ታፍና የምታቃስት፣ ታማ የምታጣጥር የውሁዳን- ገነት የብዙሃን-ሲዖል ሆና የማሽቆልቆል ጉዞዋን በሙሰኞች ፎቅና በቀለበት መንገዶች ከፍና ወደ ቤርሙዳዋ እየገሰገሰችው አለች-ያቺ ከአራት አሥርት በፊት እንደዘበት አብዮት ያካሄዱባት- ኢትዮጵያ! ዛሬም በውስጧ የሚብላላው የብሶት እሳተ-ገሞራ በጨዋ ዜጎቿ ገመና ከታችነት የተደበቀላት የምስኪን-ኃያሎች አገር ኢትዮጵያ!
ተቃርኖዋን በሆዷ ያረገዘችው ኢትዮጵያ፡ – በባለ-ሁለት አሀዝ የገዢዎች ዕድገት መዝሙሯ ተገዢዎችዋን እያዝናናች፣ በብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ካድሬዎች አበል-ወለድ ጉዋይላና ጃሎታ ጮቤ እየረገጠች፣ ከውጭ ለሚመጡ እንግዶቿ ታሪካዊ ቅርሶቿን ሳይሆን እንስት ልጆቿን እያስጐበኘች፣ ለም መሬቷን እየቸበቸበች፣ ድሃ ዜጐቿን በኮንዶሚኒየም እያቆረች፣ ከቀዬያቸው እየነቀለች፣ በአርቴፊሻል ውበቷ ተንቆጥቁጣ፣ በቻይና ሜክ-አፓች ገፅታዋን እየገነባች ክፉ ገዢዎቿ በተገዢዎቿ ማጅራት ላይ በመረማመድ ወደ ተድላ ዳገት ሲወጡ፤ ምስኪን ተገዢዎቿ ደግሞ በገዢዎች በመረገጥ ወደአዘቅት ቁልቁለት የሚወርዱባት የጥቂት ሞልቃቆች እና የአያሌ ጐስቋሎች አገር ሆናለች፡፡
ጓድ ጌታቸው! ታዲያ-የአክሊሉ ሀብተወልድ ኢትዮጵያን እና የበረከት ስምዖንን ኢትዮጵያ ሲያስተያዩዋት ምን ይሰማዎታል? ኢትዮጵያስ ተሻላት ወይስ ባሰባት? ‹‹አብዮቱስ›› አከማት ወይስ አዳከማት? ሰንኮፏስ መች ይነቀላል? መቼስ ያሽራል? ዛሬ ላይ፣ ለአርባ ዓመታት የተጓዝንበትን መንገድ መለስ ብለው ሲያዩት፤ በጉብዝና ወራታችሁ የቀመራችሁትና የመራችሁት ‹‹አብዮት›› ግቡን መትቷል ይላሉ? ወይስ ‹‹አብዮቱ›› እግረ መንገዱን ባስገኛቸው ተረፈ-ምርቶች (by-products) ወይም ንዑሳን-ግቦች እየተፅናናን ነው? ‹‹አብዮቱስ›› ለሀገሩና ለህዝቡ በምልዓት የተለመውን ትሩፋቶች በተጨባጭ አስገኝቷል? ወይስ ለአዲሶቹ ‹‹ገዢ መደቦች›› አደላድሎ ሲያበቃ፤ ለእንደኔ ዓይነቱ ተርታ ሰው ግን መሬት ሰጥቶ መብትና ነፃነትን ገፏል?!
ታዲያ ‹‹አብዮቱ›› በቃል እና በመፈክር የህዝብ፤ በተግባር የ‹‹ጥቂት ገዢ መደቦች›› አልሆነምን? አንድ ሁለት ተብሎ ሊቆጠር የሚችለውን ፍሬ-ነገርስ በስተመጨረሻ በዜሮ አላባዛውምን? እንግዲያስ፡- አንድ ወደፊት ሁለት ወደኋላ የሆነው እንቅስቃሴ ብቻውን እንደ እርምጃ ተቆጥሮ፤ ወደፊት የሄድንበትና ወደ ኋላ የተጐተትንበት ጉዞ ሂሳቡ ሳይሠላና በትክክል ሳይወራረድ ትርፋችንን ከኪሳራችን መለየት እንችላለን? የተሻለ ለውጥ እናመጣበታለን ብላችሁ እንደለውጥ መሣሪያ የተገለገላችሁበት ‹‹አብዮት››ስ ዛሬ ላይ ሲያስተውሉት ያለማው ይልቃል ወይስ ያደማው? ሌላ የለውጥ መንገድ/መሣሪያ መርጣችሁ ኖሮ ቢሆንስ ኪሣራውን መቀነስ ይቻል ነበር? እንዲያው በደፈናው፣ ልክ እንደ አረጀና እንደ አፈጀ ዋርካ ውስጥ-ውስጡን ብልና ምስጥ ሲቦረቡረው ኖሮ ቀፎውን የቀረውን የሺህ ምናምን ዓመት ዘውዳዊ-ሥርዓት በግራ እጅ መፈክር ነቅንቃችሁ ግብዓተ-መሬቱን በማፋጠናችሁ ብቻ ለተለማችኋት ኢትዮጵያ አለመገኘት እንደማካካሻ /ማስተዛዘኛ ሊወሰድ ይገባዋልን?
ከዚህ፡- በመሠረቱ ‹‹ስር-ነቀል›› ከሆነ እና ሀገር-በቀል አእማዶችን በሙሉ ያለልዩነት ከገረሠሠ (Iconoclastic) ‹‹አብዮትስ›› ከቶ ስኬት ሊገኝ ይቻላልን? /ይቻልስ ነበርን? እዚህ ጋር ከእውቅነቱም በላይ አዋቂነቱ የሚጐላብኝ የጥበብ ሰው ኃይሌ ገሪማ ያነሳው ሃሳብ ትዝ አለኝ፡ ፡ ‹‹የጠላኸውን ነገር መግደል እንጂ መለወጥ አትችልም፤ የወደድከውን ነገር ነው ልትቀይረው ዘንድ የሚቻልህ….›› ዓይነት አንድምታ ያለው ንግግሩ! ሁሉን ነገሩን የተጠየፋችሁትና የተንገሸገሻችሁበት ያ የፊውዳል-ስርዓት፤ አንዲትም መልካም ነገር ፈልጋችሁ አጥታችሁበት ነበርን? የናንተን የምቾትና የብሩህ ተስፋ የወደፊት ዕድል ወደ ጐን ብላችሁ፤ ‘ለጭቁኑ’ ሰፊ ጭሰኛ ስትሉ የከፈላችሁት መራር ዋጋስ የጭቆናውን ቀንበር ሰብሮለታል ወይስ አፅንቶበታል? የኢኮኖሚ፣ ማኅበረ-ባህላዊ፣ የፖለቲካ፣ የሃይማኖት፣ የስነ- ልቦና ሥርዓቱን በሙሉ ነቅፋችሁና ጠልታችሁ ባካሄዳችሁት ‹‹አብዮት›› ጭቁኑን ጠቅማችሁታል? ወይስ ተጠቅማችሁበታል?
ጓድ ጌታቸው ጀቤሳ! ከቅን-ልቦና የተነሳውን እና ማኅበረሰብን በበጐ ለመለወጥ/እንደ አዲስ ለማዋቀር የከፈላችሁትን ከራስ ወዳድነት በፍፁም የራቀ (Selfless or Altruist) ድርጊት ከጥንስሱ አሉታዊ /አፍራሽ የነበረ አድርጌ መውሰዴ ሳይሆን፤ በፍፁም ሃሳባዊ-ተምኔታዊነት (Utopian Idealism) ያለማችሁት ‹‹ያ ያማረ ህልም›› በሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ጉድለት የተነሣ በሂደቱና በውጤቱ ያስከሰተውን ወይም ያስከተለውን አሰቃቂና አሳዛኝ የደም-ጐዳና ከነ ያልተፈለገ አምባገነን-ወለድነቱ ጭምር ለመሞገት በማሰቤ ብቻ መሆኑን ይረዱልኝ! ከቶውንስ፡- ሰው አምሳሉ የሆነውን ሌላኛውን ሰው ‹‹ነፃ›› ሊያወጣው ይችላልን? በሕግ እና በአዋጅ አካላዊ-ባርነቱን ማስቀረት ቢቻል፤ ከአእምሯዊ- እስራቱና ከመንፈሳዊ-ሠንሠለቱ የሚፈታውስ ማን ነው? የሰውስ ምክንያታዊነት እና ለመሰሉ ተቆርቋሪነት፤ ከራሱ ጥቅምና ድንበር ምን ያህል ርቀት ሊሻገር ይችላል?
ጥቂት ስለ አብዮት ከዋክብት እና አብዮታውያን ሰብዓ-ሰገሎች***
‹‹አብዮት፣ አቅደህ ዓልመህ የምታደርገው ፍጻሜ ሳይሆን፤ እንዲሁ አንድ ቅጽበት ላይ ሕዝብ ‹‹አሁንስ በዛ!›› ሲል፣ የአብዮት ከዋክብት ሲገጣጠሙ የሚሆን ይመስለኛል›› ሲሉ ምላሽ የሰጡበት የየካቲት 66ቱ አብዮት መንስኤ ጉዳይ እጅጉን በጥልቅ እንዳስብ ያነሳሳኝ አንደኛው ምናብ ቀስቃሽ ምልከታዎ ነው፡፡ ይህን እይታዎን እስከተወሰነ ድረስ ብጋራም፤ ከተወሰነ መንገድ በኋላ ግን እለያለሁ፡፡ ይኸውም፣ የአብዮት በተግባር መነሳት የብዙ ተዋንያንና ድርጊቶቻቸው የተቀናጀ ድምር-ውጤት በመሆኑ ላይ ከሃሳብዎ ጋር ሥምም ነኝ፡፡
የ66ቱን አብዮት እንደ አብነት ብንወስድ፤ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች (አራሾች፣ ተማሪዎች፣ ወታደሮች፣ ሹፌሮች፣ ሙስሊሞች…) በተለያዩ የትግል ግንባሮች ላይ ተሰልፈው ሥርዓቱን ለመገርሰስ ያካሄዱት ባለ ብዙ ግንባር ፍልሚያ ያስገኘው ድምር ውጤት፤ ‹‹የአብዮት ከዋክብት›› መግጠማቸውን እና ለአንድ የስኬት ምዕራፍ መብቃታቸውን አብሳሪ ይሆናል፡፡ በዚህ ረገድም፡ – ‹‹የአብዮት ከዋክብት›› መግጠምን እንደ አንድ ብሔራዊ የአብዮት መነሻ ምክንያት ብንወስደው ትክክል ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ግን ፋና ወጊ ሆነው መንገዱን የጠረጉት ወይም ‹‹እርሾ›› ሆነው ትልቁን አብዮት በማፋፋም ለተግባር ያንቀሳቀሱና ያበቁት የመጀመሪያ ረድፍ ወጣኒዎች የማይናቅ ስፍራ አላቸው፡፡
ትልቁን ሀገራዊ ሥዕል በማየትና የተሻለች ኢትዮጵያን በመተለም፤ የተበታተነውን የሕዝብ ሮሮ እና የዕለት ተዕለት ሕይወት መከራ፤ በንድፈ-ሃሳባዊ መነጽር ደርዝ በያዘና ትርጉም በሚሰጥ መልኩ ለሁሉም ቅርብና ድርስ በሆነ መንገድ መንስኤውን ከመፍትሔው መተንተን ቀዳሚው ሥራ ይመስለኛል፡፡ ለአንድ፣ በሀገሩ ላይ ባለሀገር ሳይሆን ጭሰኛ ባሪያ ለተደረገ ምስኪን ገበሬ ሊገባ በሚችል መልኩ፤ የመከራው ምንጭ ፊታውራሪ አሰጌ አልያም ቀኛዝማች ጉደታ ራጉ ሳይሆኑ ሁለቱም አካል-አምሳል የሆኑበት በመሬት ላይ የተገነባ የባላባት ፖለቲካ-ወ-ኢኮኖሚያዊ (ፖለቲካል ኢኮኖሚ) ሥርዓት እንደሆነ በጥበብና በፖለቲካዊ ጽሑፎች የገለጡ ‹‹አሳቢያን›› ያላቸው የብርሃን አብሪነት ሚና ወሳኝ ነው፡፡
‹‹ትንቢት ይቀድምዎ ለነገር›› እንዲሉ አበው እናንተም በማርክስኛ፡- ‹‹ንድፈ-ሃሳብ ሲሠርጽ ቁስ-አካል ይሆናል›› እንደምትሉት፤ ህሊናዊ ሁኔታዎችን ምቹ በማድረግ ረገድ እና ባለአገሩን ለለውጥ እንዲነሳሳ በመቀስቀስ ብዙ የማይዘመርለት ግን ቁልፍ የሆነውን የዜግነት ድርሻ ተወጥተዋል፡ ፡ በፈረሰው ምትክም ሊተካ ስለሚገባው የሥርዓተ- መንግሥት ዓይነት ርዕያቸውን አካፍለዋል፡፡ ነገሮችን በ‹‹አብዮት›› መቀየር ምርጫ የለሽና አይቀሬ ከሆነ ዘንዳ ደግሞ፤ ቢያንስ ሊመጣ ያለው ‹‹አብዮት›› ግብታዊ ሆኖ ከሚበጀው የሚፈጀው እንዳይበልጥ ሲባል ሊከተለው ስለሚገባው አቅጣጫና ሊያርፍበት ስለሚገባው ዳርቻ በማመላከት ሊያሰክኑት ይገባል- እነዚህ አሳቢያን! ይህንን የሞከሩት ግን፤ በወቅቱ ሰሚ ጆሮ እንዳላገኙ ብዙዎች አርፍደውም ቢሆን እማኝነት የሰጡበት ጉዳይ ሆኗል፡፡
ዶ/ር የራስወርቅ አድማሴ በዕንቁ መጽሔት ቅጽ 6 ቁጥር 112 ላይ በሰጡት ቃለ-ምልልስ የትግል ጓደኛቸው አቶ አሰፋ ሀብቱ የአብዮቱን ድንገተኛ አመጣጥ አስመልከቶ የነገሯቸውን ሲገልጹ፡- ‹‹የኛ ነገር ሳይሞቅ ፈልቶ ነው ለአሳላፊው ያስቸገረው›› አለኝ በማለት ‹‹ሁኔታችንን በአጭሩ የሚገልጽ ትልቅ አባባል ነው›› ሲሉ ሥምምነታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በዚህ አባባላቸው ላይ በማከልም፡ – ‹‹በአብዮታውያኑ ላይ አብዮቱ የደረሰባቸው ገና ትጥቃቸውን በበቂ ሳያጠባብቁና ሳያሰማምሩ ነው ማለት ይቻላል›› በማለት እንደደራሽ ድንገት ከተፍ ያለውን አብዮት መግራት ወይም መከተርና በታለመ ቦይ ውስጥ እንዲፈስ ለማድረግ ያለመቻላቸውን በፀፀት ይዘክሩታል፡፡
በመሆኑም ታቅዶና ታልሞ አቅጣጫ ያልያዘ፣ ብሎም መድረሻውን በትክክለኛ ሥፍራው ላይ ያላጠናቀቀ ‹‹አብዮት›› የማይፈልገውን በመገርሰሱ ሲሞገስ፤ የሚሻውን በቅጡ ባለማወቁ ወይም የሚሻውን እንዴት እንሚጨብጥ ዝርዝር ስልት ባለመንደፉ የተነሳ ስላከሸፈው (ስላስነጠቀው) ውጥኑ ሊወቀስ ይገባል፡፡ የቤት ሥራውም በከፊል እንጂ በሙሉ እንዳልተጠናቀቀ አስረጂ ነው፡፡ ልክ አንድ አውሮፕላን አነሳሱ (take off) መልካም ሆኖ ጉዞው እጅግ የታወከና አቅጣጫ የሳተ ቢሆንና፤ በአጓጉል ሁኔታ ያልፈለገው ቦታ ላይ ተንገጫግጮ ሲያርፍ (not safe landing) እንደማለት ነው- አብዮቱ፡፡ ሊያሳካ ከፈለገው ግብ አንጻር ሲገመገም ‹‹አብዮቱ›› ዛሬም መንገድ ላይ ያለ ታካች-ተጓዥ መስሎ ይታየኛል፡፡
በአጠቃላይ፡- ‹‹አብዮቱ›› ያልፈለገውን የባላባት ሥርዓት በመናድ በኩል ሲሳካለት፤ የፈለገውን የ‹‹ሕዝባዊ መንግሥት››፣ የ‹‹ዕኩልነት››፣ የ‹‹ነጻነት››፣ የ‹‹ታላቅ ሀገርነት›› ህልም ዕውን በማድረጉ ረገድ ግን ክፉኛ ከሽፏል፡፡ በመሆኑም፡- ይህንን ያላለቀ የቤት ሥራ በሦስተኛው ትውልድ ትግል በድል ምዕራፍ መደምደም የኔ ትውልድ ዘመነኞች የቤት ሥራ ሆኗል፡፡ ለዚህ ደግሞ፡- የእርስዎ ዘመን ትውልድ ያካሄደውን ‹‹አብዮት›› ተፈጥሯዊ ባህሪና አነሳስ፣ ርዕዮተ- ዓለማዊ መሠረት፣ ጥንካሬና ድክመት፣ ስኬትና ውድቀት በቅጡ መገምገም ግዴታ ይሆንብናል፡፡ አለበለዚያ እንደ አንዳንድ የዘመኑ ብዕረኞች እንዲሁ በአጉል ጀብደኝነት ነገረ-አብዮትን ከጠዋት እስከ ማታ ስናላምጠው ብንውልና በአደባባይ ስንለፍፈው ብንከርም፤ በተግባር ጠብ የሚል ነገር አይኖርም፡፡ ጣዕሙ እንዳለቀ ማስቲካ ኦና ኦና ከማለት ውጪ ሌት ተቀን ‹‹አብዮት አብዮት ከወዴት አለሽ?›› ብንላት ከቶም አቤት አቤት ልትለን አትችልምና፡፡
ጓድ ጌታቸው- ሃሳቤ አላለቀም፡፡ ገና ሲሶው እንኳን አልተነካም፡፡ ይህ ጽሑፍ ግን በዚሁ ይብቃው፡፡ ምላሾን ለማግኘትም በጉጉት እጠብቃለሁ፡፡ እስከዛው ግን በአማርኛ ትርጉሙ በማውቀው አንድ የኦሮምኛ ምርቃት ልሰናበትዎ

‹‹የሰማይ ኮከብ ገድ ይሁነን!››

Filed in: Amharic