>

የእውነት ኢትዮጵያ ወለድኩኝ ትበል ልያውም ንጉሥ ! ! ! (አሳፍ ሀይሉ)

የእውነት ኢትዮጵያ ወለድኩኝ ትበል ልያውም ንጉሥ ! ! !

አሳፍ ሀይሉ

ይህን የሚከተለውን ምስክርነት ያገኘሁት እ.ኤ.አ. በ1936 (ማለትም ፋሺስት ጣሊያን ሀገራችንን በወረረችበት ዓመት) በኒውዮርክ በታተመው የጄ. ሮጀርስ ‹‹ The Real Facts about ETHIOPIA›› በሚል መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ በወቅቱ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ – ጣሊኖች ላሳዩት ከፍተኛ መፈታተንና ዘለፋ፣ እና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የኢትዮጵያን ጥቅምና መሬት አሳልፈው እንዲሰጡ ከዓለም ኃያላን ለቀረበባቸው ግፊት ንጉሡ እንዴት ያለ ፅኑ አቋም ይዘው እንዳራመዱና፣ ምን ያህል ለሀገራቸው ክብር .. በክብር እንደታመኑ የሚገልጽ ምስክርነት ነው ጽሑፉ፡፡ በእውነት ያኮራል! በሀገር ሲመጡበት ‹‹የፈለገው ይምጣ!›› የሚል ንጉሥ! ጥሎብን እኛ ኢትዮጵያውያን – ባገራችን ሲመጡብን – ብዙ ጊዜ – እንዲህ ነን! የሮጀርስን ቃል አንብቡት፡፡ እና በማንነታችሁ ኩሩ፡፡ ለንጉሣችሁ ያላችሁ ክብር አይናወጥ፡፡ ቢያንስ በዚህ አላሳፈሩንም ነበር ጃንሆይ! ነፍስዎትን ይማር! መልካም ንባብ!  መልካም ጊዜ!
‹‹የኢጣልያው መሪ የማይነቃነቅ ቆራጥ አቋም ያለው ነው፡፡ ያገሩ ሰዎች ‹‹አርኮ›› እያሉ ነው የሚጠሩት፡፡ ‹‹እርጉም ሃዋርያው›› ለማለት፡፡ አንዴ ልክ ነው ብሎ ላመነበት ነገር ደረቱን ይሰጣል፡፡ ቅንጣት እንኳ ለሥለስ ማለት አይሻም፡፡ በመጋቢት 1928 ዓመተ ምህረት በወልወል ጉድጓዶች የተነሣ በኢጣልያና በአቢሲንያ መካከል ግጭት ሲቀሰቀስ ይሄው ሙሶሊኒ ጉዳዩ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲፈታ ለአቢሲንያው ንጉሠ-ነገሥት ጥሪ አቀረበ፡፡ ለሠላማዊው መንገድ ግን በምንም ዓይነት ወለም-ዘለም የማይሉ ያላቸውን ቅድመ-ሁኔታዎችን አስቀመጠ፡፡
‹‹አንደኛ፡- በይፋና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ አቢሲንያ ለተቀሰቀሰው ግጭት ኦፊሴላዊ መግለጫ እንድትሰጥ በማለት፡፡ ሁለተኛ፡- ይህም ይፋዊ ይቅርታ በሚነገርበት ወቅት በመዲናዋ አዲስ አበባ የኢጣልያ ባንዲራ እንድትውለበለብና ያቺን የኢጣልያ ባንዲራ የኢትዮጵያ ንጉሥ በአደባባይ ዝቅ ብሎ የክብር ሠላምታ እንዲያቀርብላት የሚል፡፡ እና ሶስተኛ፡- በወልወል ክስተት ለደረሰው ጉዳት ሁሉ የአቢሲንያው ንጉሥ ሣይውል ሣያድር በቂና ተመጣጣኝ ካሣ ለኢጣልያ መንግሥት እንዲከፍሉኝ የሚሉ ነበሩ፡፡
‹‹የአቢሲንያው ንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ደግሞ ለዚህ የሙሶሊኒ የዲፕሎማሲያዊ ሠላማዊ ጥሪ እና ቅድመ-ሁኔታዎች ለራሱ ለሙሶሊኒ መልስ አልሰጡትም፡፡ ያደረጉት ነገር በቀጥታ የፕሬሱን ማህበረሰብ በሙሉ ጠርተው መግለጫ መስጠት ነበር፡፡ ያን ማድረጋቸው ደግሞ ለሙሶሊኒ ምንም ማምለጫ አማራጭ የሚሰጥ መንገድ አልሰጠውም፡፡ የእርሱንም የማይናወጥ ያለውን የድርድር ቅድመ-ሁኔታ፤ የንጉሡንም እምቢተኝነት ያደመጠውን የኢጣልያ ሕዝብ ደባብቆ የሚያመልጥበት ምንም ክፍተት አልነበረውም፡፡ በፊት ለፊት በቃሉ መሠረት ከመጋፈት ውጪ፡፡
‹‹ጆርጅ በርናርድ ሾው ነገሩን ለማለሣለስና በሽምግልና ለመፍታት በአቢሲንያው ንጉሥ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ ቀርቦ ሣለ ንጉሡን ሁሉን ለእዝጌሩና ጉዳዩን በአፅንኦት ለሚከታተለው ወዳጅ የዓለም ሃገራት ትተው ሙሶሊኒ ባቀረበላቸው ሃሳብ መሠረት አቢሲንያ በኢጣልያ ሞግዚት አስተዳደር መሆኗን ብቻ በማወጅ ሁሉንም ነገር በእርቀ-ሠላም ይፍቱት እባክዎ ልለምንዎት ብሎ በሠላም እንዲደራደሩ የሙጥኝ ባላቸው ጊዜ ንጉሡ የሰጡት መልስ ይህን ነበር፡-
‹‹እኔ በኢጣልያ መንግሥት ሥር በሎሌነት ያደርኩ አሻንጉሊት ልዑል ከምሆን ይልቅ፤ ያለጥርጥር ልክ ከ60 ዓመታት በፊት እንደነበረው የሃገሬ ንጉሥ እንደ አፄ ቴዎድሮስ፤ ራሴን ባጠፋ እመርጣለሁ…
‹‹ያን ባደርግ ከሠሎሞን ጀምሮ… እኔን ወደዚህች ምድር ባመጡኝ ዘር ማንዘሮቼ፣ ባያት በቅድመ-አያቶቼ፣ ከሥር መሠረቴ ፊት… ለኢጣልያ ሎሌ አሽከር ሆኜ አድሬ ቢያገኙኝ.. ምን ያህል የተዋረድሁ ሆኜ በፊታቸው እንደምቀልል አንዳች ጥርጥር የለውም፡፡ እንኳን ለኢጣልያ ይቅርና… እኔ የዚህች በዓለም ሁሉ ቀደምት መንግሥት የሆነች… ከኖህ የጥፋት ውሃ አስቀድማ የተመሠረተች ታላቅ ሉዓላዊት ሃገር ንጉሠ-ነገሥት ሆኜ ሣለ… የብሪታንያንም ሞግዚታዊ አስተዳደር ሆነ የአንግሎ ፈረንሣዮች የሞግዚታዊ አስተዳደር አሊያም የማናቸውም ምድራዊ መንግሥት አገዛዝ በምንንም ዓይነት የምቀበለው ጉዳይ አይደለም፡፡
‹‹እኛ የእነርሱን መልካም ፊት ለማግኘትና ጥርሣቸውን ለማጣፈጥ ስንል… ኢትዮጵያን እንደ ኬክ ቆራርጠን፣ ጥሩ ጥሩውን ጣፋጭ ጣፋጩን እምቡጧን… ለዚህ ወይም ለዚያኛው ሃገር አሣልፈን የምንሠጣት ምድር አይደለችም ሃገሬ፡፡
‹‹ኢንግላንድ ወይም ሌላው ሉዓላዊ ሃገርና ሕዝብ በፈቃደኝነት የትኛውንም የግዛቱን ቅንጣት በፈቃዱ ቆርጦ ይሰጣልን? በፍፁም አያደርገውም! እኔም ለዚህች ሃገርና ለሕዝቤ በታላቁ ምኒልክ ስም የፈጸምኩት ታላቅ የምድር የሠማይ ቃልኪዳን አለብኝ፡- ፈጣሪ በሚል ቀን ወደ እርሱ እስኪጠራኝ ድረስ በፍፁም ለአፍታም ቢሆን በፈቃዴ ከሃገሬ ላይ ቅንጣት እንኳ ለማንም ቢሆን ላልሠጥ!››
ኃያሉ ፈጣሪ አምላክ የቃልኪዳኑን ምድሩን ኢትዮጵያን ሁልጊዜም በግርማው በቸርነቱ ከጠላት ሁሉ ሸሽጎ እንደሚያቆያት እናምናለን፡፡
አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡ 
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ 
Filed in: Amharic