>

ተዛዝበናል ይህም ቀን ያልፋል!!! (ብርሃኑ ተክለያሬድ)

ተዛዝበናል ይህም ቀን ያልፋል!!!

ብርሃኑ ተክለያሬድ

መንግስት ሲፈቅድልህ ፊትን እያጨፈገጉ አልያም ፈገግ እያሉ አደባባይ መውጣት ስሙ “አድርባይነት” እንጂ “ሰብዓዊነት” አይደለም። አርቲስትነቱ ቲያትር ቤት አልያም ክሊፕ ላይ እንጂ በህዝብ ላይና በሀገር ላይ ሲሆን ያስተዛዝባል።
ተዛዝበናል!!!
እናንተኮ አማሮች/ኦርቶዶክሳውያን ምንም በማያውቁት ቤታቸው ቤንዚን እየተርከፈከፈበት ሲነድ ሚሊየነሮች የነበሩ እስካሁን ለማኝ ሆነው ሲቀሩ ሌላውን ረስታችሁ የሃጫሉ ሀዘን ላይ ደረት መቺዎችና ሀውልት መራቂዎች ነበራችሁ። ወገናችሁ እንደበግ ሲታረድ ለእርዳታ መሰባሰብ ቀርቶ ባሌና አርሲ ለጉብኝት የሄዱ አርቲስቶችን ያገለላችሁ ጉዶች ናችሁ።
ይህም ቀን ያልፋል!!!
ወለጋ ለስብሰባ የተጠሩ ንፁሐን ህፃናትና እናቶች ላይ ሳይቀር የጥይት እሩምታ ሲዘንብና ደማቸው እንደውሻ ፈሶ ሲቀር የቀሩትን እንርዳቸው ብሎ ሀሳብ ያቀረበ አንድም ሰው አልነበረም። እስከዛሬም ህፃናቱ ምግብ ምግብ እያሉ በየሜዳው ወድቀው እያለቀሱ ነው።
ተዛዝበናል!!!
መተከል ምስኪናን እንደ አውሬ ሲታደኑ አንዱ በቀስት ሌላው በጥይት መድረሻ ሲያሳጣቸው፣ አስከሬን እንኳን መቅበር ቅንጦት በሆነ ጊዜ “ኧረ ወገን ናቸው እንርዳ” ያለ አንድም ጎበዝ አልነበረም።
ይህም ጊዜ ያልፋል!!!
ማይ ካድራ ላይ ነፍሰ ጡሮች ሳይቀሩ በቢላ ሲቀረደዱ ንፁሐን ሲበለቱ ካየን ቀናት ተቆጠሩ። ተራፊዎች “አሞራ ይብላን እንጂ ዳግም ማይ ካድራን አናይም” እያሉ ሲቅበዘበዙ የዛሬዎቹ ሰብዓዊነትን አቀንቃኞች ባላየ አልፋችኋል።
ተዛዝበናል!!!
ዛሬ ለምን ወገኖቻችንን ረዳችሁ አንልም። ይሁንና መንግስት ሲፈቅድ ሙሾ አውራጅ መንግስት ሲፈቅድ ሳቅ መንግስት ሲወድ እርዳታ መንግስት ዝም ሲል ዝምታ በእውነተኛ ስሙ ሲጠራ አንድም “አሽቃባጭነት” አንድም “አድርባይነት” ነው።
አድርባይነትና አሽቃባጭነትን ነፍሴ አጥብቃ ትፀየፋቸዋለች
(አንድ ሁለት ከዚህ በፊት በሰብአዊነት የምናውቃቸውን አርቲስቶች አይመለከትም)
Filed in: Amharic