>

ጉዞ ዓፄ ምኒልክ - ከወረይሉ እስከ መቀሌ! - ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ (አሰፋ ሀይሉ)

 
 

ጉዞ ዓፄ ምኒልክ – ከወረይሉ እስከ መቀሌ!

(የአባቶቻችን ታሪክ ተረስቶ እንዳይቀር…)

– ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ
አሰፋ ሀይሉ

… ደጃዝማች ባሕታ ሐጎስ የአክለ ጉዛይ ሹም በታኅሣሥ ወር 1887 ዓ.ም.  አክለ ጉዛይ ከውጭ ኃይል ነፃ መሆኑን አወጀ፡፡ በሦስተኛው ቀን በቶዞሊ የሚመራ የኢጣሊያ ጦር ዘመተበትና ደመሰሰው፡፡ ራስ መንገሻም የኢጣሊያንን መስፋፋት ለመግታት ኮአቲት ሰነዓፌ አጠገብ ጥር 3 ቀን 1887 ዓ.ም. ተዋጋና ተቸነፈ፡፡ ጀኔራል ባራቲየሪ ቅኝ ግዛቱን በማስፋፋት የመረብን ወንዝ በ1887 ዓ.ም. በማለፍ ራስ መንገሻን ወግቶ እስከ ዓድዋ ተቃረበ፡፡ የዚህን ጊዜ ነው ራስ መንገሻ እንዲህ ሲል ጥሪ ወደ ምኒልክ የላከ፤
እሪ በሉ ትግሮች ለየጁ ንገሩ
የጆች እሪ በሉ ለጎንደር ንገሩ
ጎንደሮችም እሪ በሉ ለወሎ ለጎጃም ንገሩ
እሪ በሉ ጎጃሞች እሪ በሉ ለክስስሱ ብረት ሐረር ለቃኘው ንገሩ
እሪ በሉ ሐረርጌዎች እሪ በሉ ለንጉሠ ነገሥት ለዳኘው ንገሩ
ይቆጣ የለም ወይ ሲሰማ ላመሉ፡፡
እንዲህ ካለ በኋላ በዚያ አካባቢ ለመቆየት አልቻለም፡፡ ዘመናዊ ትጥቅ ያለው የኢጣሊያ ጦር እያየለ ሔደ፡፡ ራስ መኮንን ቀዳሚ ጦር ይዞ ተጉዞ አምባላጌ ሰፍሮ ነበረና ከእርሱ ዘንድ ሒዶ ተቀላቀለ፡፡ የዚህን ጊዜ እንዲህ ብሎ ለአቅራሪ ግጥም ነገረ ይባላል፤
ለየጁ ለጎንደር ለወሎ ለጎጃም ብነግረው ዝም አለኝ
ከባሕር ዳር ወጥቶ መኮንን አዳነኝ፡፡
ከራስ መንገሻ ጦር በተጨማሪ የራስ ወሌም እዚያ ነበረ፡፡ ራስ መኮንንና አብረውት የነበሩት የሁለቱ ራሶች ጦር በትክክል የሰፈረው ደባር ከሚባል ስፍራ ሲሆን እርሱም ከአምባላጌ 15 ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ በስተ ደቡብ በኩል ይገኛል፡፡
ባራትየሪ ዋናውን የጦር ሰፈር አዲግራት ላይ አድርጎ ወራሪ ጦር እስከ አምባላጌ ከመቀሌ 70 ኪሎ ሜትር ያህል ደቡብ ምሥራቅ ወደ ውስጥ ከሚርቀው ገብቶ እዚያ ላይ ሻለቃ ቶዞሊ መሽጎ ተቀመጠ፡፡ የአምባው ከፍታ 3,411 ሜትር ከባሕር በላይ ይሆናል፡፡
ዓፄ ምኒልክ ክተት ዐዋጅ በመስከረም 1888 ዓ.ም. አስነገሩ
 የዐዋጁ ቃል እንዲህ ይነበባል፤
 
    እግዚአብሔር በቸርነቱ እስካሁን ጠላት አጥፍቶ አገር አስፍቶ አኖረኝ፡፡ እኔም እስካሁን በእግዚአብሔር ቸርነት ገዛሁ፡፡ እንግዲህ ብሞትም ሞት የሁሉ ነውና ስለ እኔ ሞት. አላዝንም፡፡ እንግዲህም ያሳፍረኛል ብዬ አልጠራጠርም። አሁንም አገር የሚያጠፋ ሃይማኖት የሚለውጥ ጠላት እግዚአብሔር የወሰነልን ባሕር አልፎ መጥቷል፡፡ እኔም ያገሬን
ከብት ማለቅ የሰውን መድከም አይቼ እስካሁን ዝም ብለው ደግሞ እያለፈ እንደ ፍልፈል መሬት ይቆፍር ጀመር፡፡
     አሁን ግን በእግዚአብሔር ረዳትነት አገሬን አሳልፌ አልሰጠውም፡፡ ያገሬ ሰው ካሁን ቀደም የበደልሁህ አይመስለኝም አንተም እስካሁን አላስቀየምኸኝም፡፡ ጉልበት ያለህ በጉልበትህ እርዳኝ፡፡ ጉልበት የሌለህ ለልጅህ፣  ለሚስትህ፣ ለሃይማኖትህ ስትል በሐዘን እርዳኝ፡፡ ወስልተህ
የቀረህ ግን ኋላ ትጣላኛለህ፣ አልተውህም ማርያምን፡፡ ለዚህ አማላጅ የለኝም፡፡ ዘመቻዬም በጥቅምት ነውና የሸዋ ሰው እስከ ጥቅምት እኩሌታ ድረስ ወረይሉ ከተህ ላግኝህ፡፡
ለሌሎች ክፍለ ሀገሮች በየአቅራቢያቸው እንዲከቱ ትእዛዝ ተላልፎአል፡፡ የምኒልክ ጦርም ጥቂት ቆይቶ ተንቀሳቀሰና ወረይሉ ደረሰ፡፡ እዚህ ሆኖ ነበር የአምባላጌውን ድል የሰማው፡፡ ነገርን ትንቢት ይቀድመዋል እንደሚባለው ስለሚመጣው ጦርነት የሚነገረው ክፉ አልነረበም፡፡ በኢትዮጵያ እረኛ በአረኽ ከብት ሲያግድ ምን ብሎ እንደሚዘፍን ይደመጥ ነበር፡፡ በዚያን ዓመት ይዘፍን የነበረው፤
በየካቲት እንበል እንክት እንክት
በመጋቢት እቤታችን ክትት፡፡
… የአላጌ ያገፈቱ ድል ቀማሽ ፊታውራሪ ገበየሁ ነበር፡፡ በዕለቱ ታሞ ስለነበረ ዱላ እየተመረኮዘ ነበር ገደሉን የወጣው፡፡ ግን ይህ ሁናቴው ድልን ከመቀዳጀት አልከለከለውም፡፡ ስሙን ትንሹም ትልቁም ወዲያው ዐወቀውና እንዲህ ይል ነበረ፤
… ገበየሁ
ጎበዝ አየሁ፡፡
ከነፍጥ ጎበዛየሁ
ከጀግና ገበየሁ፡፡
የንጉሥ ፊታውራሪ የጎራው ገበየሁ
አላጌ በሩ ላይ ማልዶ ቢገጥማቸው
ለምሳም አልበቁም ቁርስ አደረጋቸው፡፡
በዚያኑ ጊዜ ጀኔራል አሪሞንዲ የሚባለው ኢጣልያዊ የጦር አዛዢ 5,000 ወታደር አስከትሎ 8 መድፎች ጭኖ አላጌ የነበረውን የኢጣሊያ ጦር ለመርዳት ወደ ስፍራው እየተቃረበ ነበር፡፡ አዲራቅ ከሚባል ቦታ ሲደርስ የተኩስ ድምፅ ሰማ፡፡ ወዲያው ወታደሩን ለውጊያ ስፍራ ስፍራ አሲዞ መድፎቹን አልሞ ይጠባበቅ ጀመር፡፡ ብዙም ሳይቆይ ኢትዮጵያውያን አባራሪ ኢጣሊያኖች ተባራሪ ሆነው አዲራቅ ሲደርሱ በተከፈተው ተኩስ ብዙ የኢጣሊያ ወታደሮች ወደቁ፡፡ የአሪሞንዲ ፈረስም በጥይት ተመትቶ ወደቀ፡፡ ጥይቱ የታለመው በአሪሞንዲ ላይ ነበር፡፡ አሪሞንዲ ነገሩ ከአቅሙ በላይ መሆኑን ስለተረዳ ወታደሩ እንዲሸሽ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ጊዜው መሸና ለአባራሪ አልመች አለ እንጂ ከዚህ የበለጠ ለማድረግ ይቻል ነበር፡፡ ጋሊያኖን መቀሌ ትቶ እርሱ አዲግራት ዘለቀ፡፡
እንዲህ ቀኑ በድል ከተሟሸ በኋላ አሸናፊውን የወይራ ጉንጉን አይደለም የጠበቀው፤ ለእጆቹ ሰንሰለት እንጂ፡፡ ገበየሁ ትእዛዝ አላከበርክም ተብሎ ሰንሰለት ጠለቀለት፡፡ ደግነቱ በዚህ ሁናቴ ብዙም አልቆየም፡፡ ጥቂት ቆይቶ ሰንሰለቱ ወለቀለት፡፡ ይህ ያልተጠበቀ አጋጣሚ ከፍተኛ ስሜቱን አላቀዘቀዘበትም፡፡ ወደፊት እንደምናየው የሀገር ፍቅሩን በደሙ ጠብታ አቅልሞታል፡፡
የአምባላጌ ውጊያ በኢትዮጵያውያን አሸናፊነት ከተደመደመ በኋላ ወደ መቀሌ አመሩ፡፡ በዚያን ጊዜ የዓፄ ምኒልክ ጦር ትግሬ ደርሷል፡፡ በሻለቃ ጋሊያኖ የሚመራ 1,300 የኢጣሊያ ጦር እንዳ ኢየሱስ ኮረብታ ላይ መቀሌ አጠገብ መሽጎ ተቀምጦ ነበረ፡፡ እዚያ የኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ነበረ፡፡ ያንን የተቀደሰ መካን ኢጣሊያን ወደ ምሽግነት ስለ ለወጠው እንዲህ ተባለ፤
እንዳ ኢየሱስን ጠላት አረከሰው
እባክህ ገበየሁ ግባና ቀድሰው ፡፡
እንዳ ኢየሱስ ከከፍተኛነቱም በላይ (2,225 ሜትር) ዙሪያውን በድንጋይ ካብ በጥብቅ ስለተሠራ በቀላሉ የሚደፈር ምሽግ አልነበረም፡፡ አንድ ጉድለት ነበረው፡፡ ይኸውም የውሀው ኩሬ ከምሽጉ ውጭ ነበር የሚገኘው፡፡ ይህ የመጠጥ ውሀ ኢትዮጵያውያን እጅ ከገባ በውሀ ጥም የመፈታት ዕድል የኢጣልያንን ሰራዊት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡ ይኸውም አልቀረ፡፡ ኢትዮጵያውያን ምንጩን ያዙና በዘብ ያስጠብቁት ጀመር፡፡ (በነገራችን ላይ ይህ ብልሃት የእቴጌ ጣይቱ ምክር መሆኑን ልብ ይሏል – አቅራቢው)፡፡
ከአሁን ወዲያ የኢጣሊያ ወታደር ውሀ ሊቀዳ አልቻለም፡፡ ከዚህ በፊት ለአስቸኳይ ጊዜ በበርሜል ሞልቶ በአምባው ላይ ያከማቸውን ውሀ በቁጠባ ያከፋፍል ጀመር፡፡ እሱም ቢሆን ብዙ የሚያወላዳ አልነረም፡፡ ይህን አስመልክቶ አቅራሪ እንዲህ አለ፤
ነዳናቸው መቀሌ ከግንቦ ወስደን አጎርናቸው
ካህያ ከፈረሱ ሬሳ አስተቃቀፍናቸው
ውሀውን ከልክለን ፈርስ አሸናናቸው
ምኒልክ መሐሪ ነው ከደሴ ገሥግሦ ፈቶ ሰደዳቸው
ዓድዋ ደርሰው ከዱ ባያልቅ አበሳቸው
ወጨፎ ነበረ ያዷው ብረታቸው
በጎበዝ አየሁ ነው ድል ያደረግናቸው፡፡
ኢጣልያኖችን ያጋጠመው ችግር ከቀን ወደ ቀን እየባሰ ነበር የሚሔደው፡፡ በዚህም ላይ እነ ሊቀ መኳስ አባተ እያሸጋገሩ በመድፍ ያጣድፉት ጀመር፡፡ እንደውም አንድ ጊዜ አባተ የተኮሰው የመድፍ ጥይት ተሻግሮ በኢጣልያኖቹ መድፍ አፈ ሙዝ ተቀረቀረ፡፡ የዚህን ጊዜ እንዲህ ተባለ፤
አባተ አባ ይትረፍ ነገረኛ አዋሻኪ ሰው
ይኸን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው፡፡
አበሻ ጉድ አለ ጣሊያንም ወተወተ
ዓይነ ጥሩ ተኳሽ ቧያለው አባተ፡፡
ስለ ሊቀ መኳስ አባተ ቧያለው ከፍ ያለ የጉብዝና ሙያ ጸሐፌ ትእዛዝ ገብረ ሥላሴ እንዲህ ሲል ጽፎለታል፤
    በነጋም ጊዜ ሊቀመኳስ አባተ ዕቃቸው ያለበትን
ምግባቸውን የሚበሉባትን ቤት በመድፋቸው የታለመበትን እሱ
በግራ በጅሮንድ ባልቻ በቀኝ ሆነው ተኮሱባቸው፡፡ ሊቀ መኳስ
አባተም ኢጣሊያው ከጉድባው እስኪወጣ ድረስ እንቅልፍ
አልተኛም፤ ወገቡን አልፈታም፡፡ እንዳይንቀሳቀሱ አስጨንቆ
አስጠብቦ በመድፍና በመትረየስ ይጠብቃቸው ነበር፡፡ በዚያን
ሰሞን ሊቀ መኳስ አባተ የሠራውን ሥራ ሰው ሊያደርገው
አይችልም (ገጽ 247)፡፡
እዚያ ኢትዮጵያውያን ሲደርሱ ፋታ ለማግኘት ጣልያኖቹ ድርድር ጀምረው ነበረ፡፡ የዘመኑ አዝማሪ ምናልባት ጣድቄ ሳትሆን አልቀረችም ያን ድርድር ውትፍትፍ ብላዋለች፡፡ ከዚህ የተሻለ አገላለጥ አይገኝለትም፤
አውድማ ይለቅለቅ በሮቹ አይራቁ
ቀድሞም ያልሆነ ነው ውትፍትፍ ነው እርቁ፡፡
በአንድ በኩል በውሀ ጥም በሌላ በኩል ደግሞ በጥይት ድብደባ የኢጣልያ ወታደር ስለተ ጎዳ ከእዚያ ነቅሎ ለመሔድ ፈቃድ ጠየቀ፡፡ ጥያቄው ተሟላለትና ጓዙን ጠቅልሎ አዲግራት ገባ፡፡ የዓፄ ምኒልክም ጦር ወደ ዓድዋ አልፎ እዚያ ወሳኙን ውጊያ ለመፋለም ይዘጋጅ ጀመረ፡፡
         – ዶ/ር ሥርግው ሐብለ ሥላሴ፣ «ዳግማዊ ምኒልክ — አዲሱ የሥልጣኔ መሥራች»፣ ገጽ 227-232፣ 1992 ዓ.ም.፡፡
 
Filed in: Amharic