>

‹‹ጥቁር ፋሽስቱ የህወሓት ቡድን የፈጸመው ተግባር የውጭ ወራሪዎች እንኳን ያልፈጸሙት ነው...!!!››  (አርቲስት ደበበ እሸቱ)

‹‹ጥቁር ፋሽስቱ የህወሓት ቡድን የፈጸመው ተግባር የውጭ ወራሪዎች እንኳን ያልፈጸሙት ነው…!!!››

– አርቲስት ደበበ እሸቱ

ጥቁር ፋሽስቱ የህወሓት ቡድን በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ያደረሰው ጥቃት የክህደት ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም የሀገሪቱን ህዝቦች ለማንበርከክ የሞከሩ ወራሪዎች እንኳን ያልፈጸሙት ተግባር መሆኑን አርቲስት ደበበ እሸቱ አስታወቀ።
አርቲስት ደበበ እሸቱ ፋሽስቱ የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመውን ትቃት አስመልክቶ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቀው ፤ ከሃዲው ቡድን ለ21 ዓመታት ክልሉንና ህዝቡን ሲጠብቅ በነበረው የመከላከያ ሰራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የከሃዲነት ተግባር ከመሆኑም ባሻገር ትውልድም ይቅር የማይለው ነው።
‹‹ተስፋ የቆረጠ ሰው ብዙ ነገር ያደርጋል። ተስፋ ባይቆርጥ ኖሮ፣ አብሮት ሲሰራና አብሮት ሲበላ የቆየ ወንድሙን አይገድልም ነበር። መከላከያ ሠራዊቱ ከኋላዬም ከፊቴም ያለው የራሴው ወገን ነው ብሎ ወገኑን ተማምኖ በተኛበት በሌሊት ክህደት መፈጸሙ ቡድኑ የመጨረሻ ዘመኑ ላይ መድረሱን የሚያመላክት ነው ።
“አርቲስት ደበበ እንደሚለው፤ የህወሓት ቡድን በመከላከያ ሠራዊቱ ላይ የፈፀመው ክህደትና ጭካኔ የውጭ አገር ጠላትና ወራሪ እንኳን ያላደረገው ነው። ጣሊያን አላደረገውም፣ ደርቡሾች አላደረጉትም፣ እንግሊዞች ዳግማዊ አጼ ቴዎድሮስን ለመያዝ በመጡበት ጊዜ እንዲህ አይነት አፀያፊ ድርጊት አልፈጸሙም።
 የራሳችን ወገን የተባለው ግን እንዲህ አይነት ዘግናኝ ድርጊት ፈጸመ። የሠራዊቱ አባላት ሲወጣ ‹‹ለማን ጥላችሁን ነው የምትሄዱ፣ እባካችሁ ቆዩልን›› ያለ አካል ይሄን ክህደት መፈጸሙ የግድያ ቀን እያመቻቸ ነበር ማለት ነው። ሠራዊቱ ይህ ክህደት እንደሚፈጸምበት ቢያውቅ ጥሪውን ሳይቀበል ይወጣ ነበር። የወገን ጥሪ ሆኖበት ግን ቆይልኝ ሲባል እዚያው ቆየ። ወገን በወገኑ ላይ እንዲህ ሲጨክን ቅስም ይሰብራል።ኢትዮጵያዊ መሆኑንም እንድንጠራጠር አድርጎናል ብሏል።
 ‹‹እንዲህ አይነት የአውሬነት ባህሪ ያላቸው ሰዎች ነበሩ ለካ ሲመሩን የቆዩት›› ያለው አርቲስት ደበበ፤ እነዚህ ሰዎች የፈጸሙት አጸያፊ ተግባርም መላውን ኢትዮጵያዊ ያሳዘነና ያስቆጣ መሆኑንም ጠቁሟል።
እንደ አርቲስት ደበበ አስተያየት፤ ፋሽስቱ የህወሓት ቡድን ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት ለጥፋት የሚሆኑትን ገንዘብና ሌሎች ነገሮችን ቢያከማችም ሊያዛልቀው ግን አይችልም። አቅም ይሳነዋል። አሁን ላይ ማድረግ የሚችለው የመሰረተ ልማት ውጤቶችን ማውደም ብቻ ነው። ከአዲስ አበባ ጋር ግንኙነቱ ስለተቋረጠ የገንዘብ ምንጩም ይደርቃል። እስከ አሁን ግን ከዚህ በፊት በሰበሰበው ገንዘብ አፈ ቀላጢዎችን ቀጥሮ በውጭ መገናኛ ብዙኃን ብዙ እያስወራ ነው።
“የውጭ መገናኛ ብዙኃን የሚወሰደውን ህግ የማስከበር ሥራ የእርስ በርስ ጦርነት አስመስለው የሚያቀርቡት የፋሽስቱ አፈ ቀላጤዎች የሚነገ ራቸውን መሆኑን የገለጸው አርቲስት ደበበ፤ ኤምባሲዎች እውነታቸውን መናገር እንዳለባቸው አሳስቧል። ቡድኑ በውጭ አገር ወንጀል በሚሰራባቸው ባንኮች ባስመጠው ገንዘብ ‹‹ሎቢስት›› ቀጥሯል። እነዚህ ተቀጣሪዎች ተደማጭነት ያላቸው ናቸው፤ ነጭ ለነጭ ደግሞ ይተማመናሉ። እነዚህ ተቀጣሪዎች ግን የጁንታው ገንዘብ ሲቋረጥ ይከስማሉ። አሁንም ሀሳባቸውን የቀየሩ አገራትና መሪዎች ታይተዋል። በተለይም ኤርትራ ላይ ሮኬት ከተኮሰ በኋላ የቡድኑ ጠብ ፈላጊነት ዓለም በሙሉ ተረድቶታል” ብሏል።
አሁን መንግሥት እያደረገ ያለው ህግ የማስከበር ሥራ የትግራይ ህዝብ ላይ የተነሳ ጦርነት ሳይሆን የትግራይን ህዝብ መደበቂያ አድርጎ የተቀመጠ ወንጀለኛን መፈለግ ነው ያለው አርቲስት ደበበ እሸቱ፣ ወንጀለኞቹ ለፍርድ እስኪቀርቡ ድርስም የኢትዮጵያ ህዝብ ከመንግሥት ጎን ቆሞ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አሳስቧል።
‹‹እንደ ትግራይ ህዝብ የኢትዮጵያን ባንዲራ
 የሚያከብር አላውቅም፤ እኔ ባየሁት፤ ልጅ ሲወለድ የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው ከቤታቸው የሚሰቀለው፣ ሰርግም፣ ክርስትናም፣ ለቅሶም ሲሆን የኢትዮጵያ ባንዲራ ነው የሚውለበለበው›› ያለው አርቲስት ደበበ፤ የትግራይ ህዝብ በህወሓት ቡድን ለደረሰበት በደል የኢትዮጵያ ህዝብ ከጎኑ ሊቆም እንደሚገባም አሳስቧል።
አዲስ ዘመን ህዳር 12/2013
Filed in: Amharic