>

ሰላም የራቀሽ አገሬ...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ሰላም የራቀሽ አገሬ…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

“ግፍ የሚበረታው ተሸካሚውን ሲያገኝ ነው”

ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም
አዎ እወነትዎን ነው ግፍን የመላመድ ብቻ ሳይሆን የማጽናትም አቅም አለን።
አዎ አልታደልንም፤ ውብና ድንቅ አገር ሰጥቶ ጸባይ ነሳን፤
ዛሬም በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ ሮኬትና መድፍ ያጓራል፤
ዛሬም በኢትዮጵያ ምድር ታንክና መትረየስ ያፏጫሉ፤
ዛሬም የኢትዬጵያ መሬት በልጆቿ ደም እርሷል፤
ዛሬም ጫፍናጫፍ ቆመን በትቢትና በይዋጣልን እብሪት ‘ገዳይ ደግሞ’ እያን  እንፏልላለን፤
ዛሬም የኢትዮጵያ እናቶች ልጆቻቸውን አንጠልጥለው ከእብሪተኞች ጥይት ለመሸሽ አገር አቋርጠው ይሰደዳሉ፤
አዎ ደንዝዘናል፣ ሰላማችንን አጥተናል።
እሮኬት የሚወነጨፍባቸው መቀሌና ባህርዳር ያሉ ኢትዮጵያዊያን ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከአሁን አሁን ምን ይመጣ ይሆን እያለ እንቅል አጥቷል።
መከራን እና ግፍን የሚሸከም የደነደነ ትከሻ ያለንን ያህል ለጎንዮሽ ጸብም የሚያክለን እንደሌለ ዛሬም አለምን እያስደመም ነው።
ከሁሉ ከሁሉ፤ ሁሌም ባሰብኩት ቁጥር ግርም የሚለኝ እና የሚያስደንቀኝ ባህሪያችን የውጪ ወረራን፣ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘር ማንኛውንም አይነት ትንኮሳ እና ጥቃት ከመንግስት ጎን ቆመን ለመመከት የምናሳየው ወኔ፣ አስገራሚ ጀግንነት እና ጀብድ የመንግስትን አንባገነናዊ ባህሪ ለማረቅ ሲሆን ድራሹ የመጥፋቱ ነገር ነው።
ዛሬ ህውሃት ላይ የሚፎክረው ሰው ብዛቱ ብቻ ሳይሆን አጃይብ የሚያሰኘው እና አስደናቂው አንዳንዱ ስለህውሃት እኩይ እና አሸባሪ ቡድን መሆን ዛሬ ገና የሰማ መምሰሉ ነው። ጎበዝ ህውሃት እኮ አንገቷ ድረስ በወንጀል፣ በሙስና፣ በመብት ጥሰት፣ በጅምላ ጭፍጨፋ፣ በሃጢያት የተነከረች ነች።
ይህን አገር ሲደፈር የምናሳየውን ድንቅ ወኔና፣ አንድነት እና አስደማሚ ትብብር አንባገነናዊ ባህሪን ለማረቅም አውለነው ቢሆን ኖሮ ህውሃት 27 አመት ሙሉ ቁም ስቅላችንን ያሳየችን አልበቃ ብሏት ዛሬ ደግም ሌላ የእልቂት አዘቅት ውስጥ ባልዶለችን ነበር። ኢትዮጵያችንንም በጊዜ ከግፍ አዙሪት ባላቀቅናት ነበር። ወያኔ ሥልጣን ላይ እያለች የገደለቻቸው አስር ሺዎች አልበቃ ብሏት በቅርቡ በመከላከያ አባላት እና በማይክዳር ከምስት መቶ ዜጎች በላይ ባልፈጀች ነበር።
አዎ ባህሪያችን ይገርመኛል። አንባገነኖችን ወልደን፣ አሳድገን፣ አጠብድለን፣ አቀማጥለን የተፈጥሮ ሞት እስኪወስዳቸው ትከሻችንን አደንድነን እንጠብቃለን። የአንባገነን ዘመድ የለውምና መልሰው እኛኑ ይደቁሱናል። ለዛም ይመስለኛል የደም ግብር አዙሪቱ እየደጋገመ የሚጎበኘን። ለዛም ይመስለኛል በየሁለት አስርት አመታቱ መልሰን የርስበርስ ደም አፋሳሽ እልቂት ውስጥ የምንገባው።
ህውሃትን ዛሬ በተባበረ ክርን ልንገላገላት ተቃርበናል። ይህ ታላቅ ንቅናቄ ሌላ ህውሃት ላለመፍጠራችን ግን ዋስትና አይሆንም። ኩፉ እሳቤን፣ ድንቁርናን፣ አንባገነናዊ ባህሪን እና ግፍን ተጠይፈን በተባበረ ክርን ከአይምሯችንም ውስጥ ሆነ ከኢትዮጵያ ምድር ካላጠፋን እሽክርክሪቱ ይቀጥላል።
ቸር ያሰማን፤ ልቦናም ይስጠን!
Filed in: Amharic