>

በኢትዮጵያ ‹‹ፖለቲካ›› ከታጋይ ለገሠ (መለስ) ዜናዊ በላይ - የትግራይን ህዝብ ያሳነሰ ሰው ከየት ተፈልጎ ይገኛል?!  (አሰፋ ሀይሉ)

በኢትዮጵያ ‹‹ፖለቲካ›› ከታጋይ ለገሠ (መለስ) ዜናዊ በላይ – የትግራይን ህዝብ ያሳነሰ ሰው ከየት ተፈልጎ ይገኛል?! 

አሰፋ ሀይሉ

 

«በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለየብሔሩ የተሰጣቸው የመቀመጫ ኮታ ይሄን ይመስላል:-
1. ኦሮሚያ 178
2. አማራ 138
3. ደቡብ 123
4. ትግራይ 38
5. ሶማሌ 23
6. ቤኒሻንጉል 9
7. አፋር 8
8. ጋምቤላ 3
9. ሐረሪ 2
10. ድሬዳዋ 2 [በልዩ ሁኔታ የሚታይ]
11. አዲስ አበባ 23 [በልዩ ሁኔታ የሚታይ]»
       (-የኢፌዲሪ ሕገመንግሥት)
ላለፉት ሃያ ምናምን ዓመታት በቀጠለው ‹‹የብሔር ብሄረሰቦች›› እየተባለ በሚጠራው በዘር ላይ የተመሠረተ የጎሳ ሥርዓት ዘመን – የትግራይ ህዝብ ቁጥር አንድ ጠላት – ሌላ ማንም ሳይሆን – ማን እጅ እንደሚገባ፣ ማን እንደሚተኩሰው፣ እና ማንስ እንደሚሞትበት በማይታወቅ ግዑዝ ጠብመንጃ ተመክቶ – ‹‹ክላሻችን እስካለ ማንም ምንም አያመጣም!›› በሚል ትዕቢት ተወጥሮ – መጥፊያ ገመዱን በትግራይ ህዝብ ላይ ያጠለቀው መለስ ዜናዊ ነው!
መለስ ዜናዊ ሀገርን በወንዴ ዘር ርጭትና በዲኤንኤ ምርመራ እየተለየ – ጎሳ ከጎሳ ጋር እየተቧደነ ከሚፈነጭባት የዱር እንስሳት ‹‹ፖለቲካ›› ይልቅ – በአይዲዎሎጂዎች፣ ወይም ወሳኝ በሆኑ ሀገራዊ ሀሳቦች፣ ወይም ሌላው ሀገር እንዳለው ዲሞክራትና ሪፐብሊካን፣ ፕሮግሬሲቭና ኮንሰርቫቲቭ፣ ህዝባዊና ብልጽግናዊ፣ ወዘተ ወዘተ በሚሉ በሀገራዊ አጀንዳዎች ዙሪያ የተደራጁ፣ በፓርቲ አባልነት መስፈርታቸው ለየትኛውም ኢትዮጵያዊ ክፍት የሆኑ፣ ዘመናዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነፃ ሃሳባቸውን አቅርበው ተወዳድረው፣ በሀሳባቸው ላይ ተመሥርቶ በመረጣቸው ህዝብ ሥልጣን የሚይዙበትና፣ ህዝብን የሚያስተዳድሩበት ፖለቲካ ፈጥሮ ቢሆን ኖሮ – የትግራይ ህዝብ (እና ወያኔ) ዛሬ ከጠብመንጃ ሌላ ምንም አማራጭ የሌላቸው፣ ቢጮሁ ሰሚ የሌላቸው፣ ከታሪካቸውም ከሁለነገራቸውም አንሰው የተዋረዱ የፖለቲካ አናሳዎች ሆነው አይቀሩም ነበር፡፡
የትግራይ ጎሳ የሚባል ካለ (የለም እንጂ!) የሌሎቹ የትልልቆቹ ጎሳዎች (ብሔሮች ብለው ራሳቸውን የሚጠሩት ህዝቦች) መጫወቻና ማላገጫ አድርጎ ያስቀረው – ሌላ ሳይሆን ይሄው መለስ ዜናዊ ጽፎ ያነገሰው – በዘር ላይ የተመሠረተ ህገመንግሥት ነው!! አሁንም ደግሜ እናገረዋለሁ፡- የትግራይን ህዝብ የፖለቲካ አናሳ አድርጎ ያስቀረው፣ የአማራና የኦሮሞ እና የ‹‹ደቡብ›› ሕዝቦች የፖለቲካ መጫወቻ እንዲሆን ቸንክሮ ያስቀረው – ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን – መለስ ዜናዊ ፅፎት ያለፈው ህገመንግሥት ተብዬው የኢትዮጵያ የዘረኝነት አገዛዝ ሰነድ ነው!!
መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያን በጎሳ ከፋፍሎ ለመሸንሸን ካለው ጉጉት የተነሳ – በትግራይ ህዝብ ላይ የማይወጣውን የአናሳነት ሸምቀቆ በአንገቱ ላይ አስገብቶበት ሞተ፡፡ የትግራይ ልሂቃንና ፖለቲከኞች መረዳት ያለባቸው ነገር – እንዲህ ሰሚ ያጣ አናሳ አድርጎ ያስቀራቸው ነገር – ሌላ ማንም ሳይሆን – ራሱ መለስ ዜናዊ በቃል እየመራ አፈሙዝ ደግኖ ያስፃፈው ህገመንግሥቱ ራሱ መሆኑን፡፡ ይህ የጎሳ ‹‹ፖለቲካ››ን (በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ – ምክንያቱም በጎሳ የተደራጀ ነገር በትክክል ይጠራ ከተባለ ‹‹ፖለቲካ›› ለመባል ስለማይበቃ!) በኢትዮጵያ ምድር ያሰፈነው ህገ አራዊት (ወይም ህገመንግሥት) ከኢትዮጵያ ምድር ተወግዶ – በዘር መቧደን ላይ የተመሠረተው የመለስ የክላሽ ፖለቲካ በዘመናዊ የአስተሳሰብ ፖለቲካ እስካልተቀየረ ድረስ – ወያኔም ሆነ (በህይወት ካለ ወደፊት ማለቴ ነው)፣ አጠቃላዩ የትግራይ ተወላጅ የሆነው ህዝብ – እስከ ዝንተዓለሙ አናሳ ሆኖ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡
ይህን የምናገረው ምናልባት አሁን ለ1000ኛ ጊዜዬ ቢሆንም፣ አሁንም ግን አዕምሯቸውን ለእውነት ለመክፈት ለሚፈቅዱና ለፈለጉ የትግራይ ልሂቃን ወዳጆቼ – ሰክነው በአስተውሎት እንዲያጤኑት ስል ደጋግሜ እወተውታለሁ፡፡ በዚህም የጭንቅ ሰዓታቸው ላይ ቆም ብለው ደጋግመው እንዲያስተውሉት በአክብሮት እጠይቃቸዋለሁ! እንደ ጅል መላልሼ እያስረገጥኩ የምናገረው እውነቱን አሁንም አሁንም ደጋግመው እንዲያስተውሉት ነው፡፡
የምናገረው ነገር ግልጽ ነው፡፡ የትግራይን ህዝብ የሌሎች ተላላኪ፣ ታዛዥ፣ ሎሌና ጭፍራ ሆኖ እንዲቀር ያደረገው ወይም ይህ እንዲሆን የደነገገው – ሌላ ምንም ነገር ሳይሆን – ራሱ መለስ ዜናዊ አስቦ አሰላስሎ የቀመረው ወይም የቆመረው – እና በህይወትም እያለ በስም ካልሆነ በቀር በትክክል ለመተግበር ሲተናነቀው የቆየው ወይም አፈሙዝ ደግኖ ባሻው መልኩ ሲዘውረው የቆየው – ህገመንግሥት ነው! ህገመንግስቱ የትግራይ ህዝብ የውርደት ምንጭ ነው! ህገመንግሥታዊ ሥርዓቱ የትግራይን ህዝብ አሽከር አድርጎ ያስቀረ ዘረኛ ህገመንግሥት ነው!
17 ዓመት ሙሉ ከደርግ ጋር ስታገል ደሜን አፍስሼያለሁ ለሚለው – እና የተለየ የተሻለ መብት ይገባኛል ለሚለው የወያኔ ህዝባዊ ሠራዊትና – ለአጠቃላዩም የትግራይ ህዝብ – መለስ ዜናዊ የዋለለት ብቸኛ ውለታ ቢኖር ህገመንግሥቱን ከሠማይ የወረደ ሥጦታ አስመስሎ ማበርከቱ ብቻ ነው፡፡ ያውም እስከ ፍጻሜው በትግራይ ህዝብ ደም ተጠብቆ እንዲኖር ከአደራ ጋር ጭምር አስረክቦትና ተናዝዞ ማለት ነው!! መለስ በህገመንግሥቱ በጥቂት እፍታ የትግራይን ህዝብ ጠቅሞታል ከተባለ… ምናልባት (እሱም ከሆነ ነው!) ከነሶማሌና ቤኒሻንጉል ወዘተ በላይ የትግራይ ህዝብ ከቁጥሩ አንፃር ብልጫ የሚታይበት ጥቂት የፓርላማ ወንበሮች ያለአግባብ እንዲኖሩት ማድረጉ ብቻ ነው!
እነ ደብረ ጽዮን፣ እነ አዲስዓለም ቤሌማ፣ እና ሌሎች ብዙ ዶክትሬትን ያህል የዕውቀት እርካብ ላይ የወጡ የህወሃት ነባር ታጋዮች፣ እና በሺህ የሚቆጠሩ በሥርዓቱ የአካዳሚክ ኢንተረስታቸው ተጠብቆላቸው ጥሩ ጥሩ በሆኑ ዓለማቀፍ ተቋሞች ውስጥ ላቅ ያለን ዕውቀት ለመገብየትና በአካዳሚ ከፍ ያለ ደረጃን ለመቀዳጀት የቻሉ የህወሃት ወጣት አባላትና ደጋፊዎችስ… እንዴት ይህን ፍጥጥ ያለ እውነታ ማወቅ እና ማየት ተሳናቸው? እንዴት ህዝባቸውን በገዛ ሀገሩ፣ ዘር እየቆጠረ፣ ከሌሎች ህዝቦች ያነሰ መብትና ድምጽ የሚሰጠውን፣  የለየለት አናሳ አድርጎ የሚያስቀረውን ይሄን ህገመንግሥት እንደ ዳዊት ጧት ማታ እያነበነቡ የሚኖሩ የመለስ በቀቀኖች ሆነው እንዴት ሊቀሩ ቻሉ? ምን ዓይነት ድግምት ቢያስነካቸው ነው እነዚህ ሁሉ አዋቂዎች የመለስ የውርደት ካባ የሆነውን ህገመንግሥት ለብሰው በመለስ የውሸት መንገድ ዕድሜያቸውን ለመፍጀት፣ ህይወታቸውን ለመባጀት የመረጡት? ምን ዓይነት እውነትን የማያሳይ፣ ዳፍንታም ልክፍት ነው?
በአሁን ወቅት የምፈራው ነገር ቢኖር – ይህን የትግራይን ህዝብ የሌሎች ዘሮች (የእነ አማራ፣ ኦሮሞ፣ ‹‹ደቡብ››!) ተላላኪ ጩሎ አድርጎ ያስቀረ የትግራይ ህዝብ የአናሳነት ማረጋገጫ የሆነው ዘረኛ ህገመንግሥት – የትግራይ ልሂቃን አዕምሯቸው በርቶ የተገለፀላቸው ቀን – እና ህገመንግሥቱ ይቀየርልን፣ ህገመንግሥቱን አንፈልገውም፣ ህገመንግሥቱ ለትግራይ ህዝብ በደሎች ሁሉ ምንጭ ሆኗል፣ ህገመንግሥቱ የትግራይ ህዝብ ዕድሜ ልኩን በሌሎች ሰጥ ለጥ ብሎ እንዲገዛ ሁኔታዎችን ያመቻቸ የባርነት ምንጭ የሆነ ህገመንግሥት ነው – ብለው በሆታ የተነሱ እለት – ሌሎቹ ደግሞ… ‹‹ኖኖኖ… በህገመንግሥቱማ ቀልድ የለም! አሁን ገና በዓይናችን መጣችሁ!›› እንዳይሏቸው ብቻ ነው የምፈራው!!!
ይሄ ዘረኝነትን በምድራችን ህጋዊ ዕውቅና ሰጥቶ ያነገሠ፣ ዜጎች ዲኤንኤያቸውን በመቁጠር ብቻ – ሳይሰሩ፣ ሳይዘሩ፣ ሳያጭዱ፣ በስፐርም ርጭትና በዲኤንኤ ምርመራ ብቻ – የሀገሪቱን የፖለቲካ ወንበር እንዲቆጣጠሩ የሚያስችላቸው – የተወሰኑት የሀገሪቱ ህዝቦች በደማቸው እየተለዩ የሀገሪቱን ፖለቲካ በአዛዥነትና በበላይነት እንዲመሩ፣ እንደ ትግራይ ያሉ አናሳዎች ደግሞ እነርሱን ደጅ እየጠኑ፣ እየተለማመጡ፣ ሲልኳቸው ወዴት – ሲጠሯቸው አቤት እያሉ አንገታቸውን ደፍተው እንዲኖሩ የሚያደርገው – ይህ ዘረኛ ህገመንግሥት ሥልጣን የሰጣቸው ትላልቆቹ ብሔሮች (ጎሳዎች ወይም ነገዶች) – ህገመንግሥቱማ የደም ሥራችን ነው! ህገመንግሥቱ ከሚለወጥ – ሠማይና ምድር ቦታቸውን ቢለዋወጡ ይሻላል – ህገመንግሥቱ የመጨረሻው ምሽጋችን ነው፣ ለህገመንግሥቱ መከበር እስከዘለዓለም ዘብ እንቆማለን – ብለው እንዳይነሱና – ትግራዮች (ወይም ህወሃቶችና ደጋፊዎቻቸው) የህገመንግሥት ተቃዋሚዎች፣ ሌሎቹ እነ አማራና ኦሮሞ ደግሞ ህገመንግሥቱን በደማችን እናስከብራለን ባዮች ሆነው እንዳናየቸው ብቻ ነው የምፈራው!
እንዴ! በዘርህ አማራ ወይም ኦሮሞ ሆነህ በመገኘትህ ብቻ ትግሬንና አደሬን እንደ ጩሎ ያሻህን እያዘዝካቸው የሚፈጽሙ ተላላኪ የማድረግ መብትን የሚያጎናፅፍህ፣ አንተን ጌታ፣ ሌላውን ሎሌ የሚያደርግልህ የመለስ ህገመንግሥት እያለልህ – ጌትነትን መተው እኮ ከባድ ነው! አያደርጉትም አይባልም! አይሆንም አይባልም! ሁሉንም አይተናልና ከፀሐይ በታች የማይሆን ነገር ምን አለ? ማየት ብቻ ነው!
አይ መለስ! እንዲያው ሰው እንዴት በገዛ ህዝቡ ላይ ይሄን ያህል ህገመንግሥታዊ ሸር ቀምሮ ይሞታል? ወይስ የዘረኝነት ልክፍት፣ የዘረኝነት አባዜ ነው የተጸናወተው? እና ዘረኝነትን ሳላነግስ ከምቀር… የትግራይ ህዝብ የአማራ ተላላኪ፣ የኦሮሞ ጩሎ፣ የኢትዮጵያ አናሳ ሆኖ ጥንቅር ብሎ ይቅር – ብሎ ወስኖ ነው?? ግራ ያጋባል!
አፈር ቅሞ፣ አፈር ልሶ፣ አፈር መስሎ… በመራኸው መንገድ ነጉዶ… ደሙንና አጥንቱን ከስክሶ… ገና ለገና ጥሩ ጭንቅላት አለህና አንተ ትሻላለህ የሚበጀንን አምጣልን ብሎ ነፍሱን ሳይሳሳ የሰጠህን የገዛ ህዝብህን… ‹‹አፈር ላበደረ ጠጠር›› አድርገኸው… የሌሎች ቋሚ ጩሎ እንዲሆን ፈርደህበት… በህገመንግሥት ቀፍድደኸው.. ወደምትሄድበት ተቀየስክ!? አሁን ነፍስህ ይማራል አንተ? አንተንስ የእውነት ኃጢያት ባይሆን እንዲያው – እውነት እግዜር ካለ… ነፍስህን አይማረው – ማለት ነበር! በእግዜሩ ሥራ አታስገባኝ ብለን እንጂ – ስንት ያስመኛል!!!
ሰው ጮሆ ጮሆ ጮሆ… ልሳኑ እንደሚዘጋው፣ እኔም ቸክችኬ፣ ቸክችኬ… ከመቸክቸክ ብዛት የተነሳ ጣቶቼ ደረቁ!! በምን ቃል ብናገር፣ በምንስ ቋንቋ ብንናገር ነው ግልጽ ያለውን እውነት ለሰው በጥሞና ማስረዳት የሚቻለው ይሆን? ፈጣሪ ይወቀው! ችግር ነው! ጌትነት! በቃኝ አሁንስ!
Filed in: Amharic