>

ጦርነቱ ተከፍቶአል፤ የእኛ ድርሻ ምንድነዉ? (ክፍል ሶስት/መጨረሻ -ሃራ አብዲ)

 ጦርነቱ ተከፍቶአል፤ የእኛ ድርሻ ምንድነዉ?

ክፍል ሶስት/መጨረሻ 

«,,,ምቾት ማጣቴን ዋጥ አድርጌ ፤ወያኔን እስከነወዲያኛዉ ከላይዋ ላይ አሽቀንጥራ ለመጣል ሀገሬ የመልስ ምት የምትሰጥበትን ጦርነት መደገፍ  ግን ምርጫዬ ነዉ»

 ሃራ አብዲ

ወደ ጽሁፌ ማጠቃለያ ስገባ፤ የትግራይ ስመ-ምሁራንና የፖለቲካ ቡድኖችን በአንድ ወገን፤ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይን መንግስት የምንቃወመዉን በሌላ ወገን አቁመን የሁለቱን ጎራዎች ሀቅ እና ወገናዊነት እንድንፈትሽ እፈልጋለሁ።

* የትግራይ ልሂቃን የሚባሉትም ሆኑ ትግራይን በመወከል ፓርቲ የመሰረቱ የፖለቲካ አመራሮች ጉዳይ 

 

የትግራይ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችም ይሁኑ ስመ-ምሁራን ፤ፈጽሞ የአሳ ጅራት የመሆናቸዉ ነገር አጃኢብ ያስብላል። ሆኖም እነሱ የሚጠቅማቸዉን ያዉቃሉ። በመሀል ሀገር እና በዉጭ ሀገር የሚኖሩትን የትግራይ ተወላጆችን ማለቴ እንጂ፤እዚያዉ ትግራይ ዉስጥ የሚኖሩትንማ ምን ማለት ይቻላል?።

(የፖለቲካ ሳይንስ ምሁር የሚባለው ፖለቲካዉን በሳይንሳዊ መንገድ ተንትን ከምትለዉ፤ በካሜራ ፊት ክላሽ ፈትተህ ግጠም ብትለዉ የሚቀለዉ ነዉ ፤ያሳፍራል)

ወደፖለቲከኞቹ ስንመጣ በቅድምያ አብርሀ ደስታ ትኩረቴን ስቦታል። ሲጀምር ኢትዮጵያዊ ነኝ በማለት ጀመረ። ደግ አደረግህ፤ አበጀህ አልነዉ። ሰሞኑን ሸርተት እያለ ከእጃችን ማምለጥ ጀመረ። ህዝቤ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ከቀጠለ እሰየዉ ኢትዮጵያዊ እሆናለሁ፤ ከተገነጠለም አብሬዉ እገነጠላለሁ ማለቱ ሳያንስ፤ህዝቤ ገደል ከገባ ገደል እገባለሁ ብሎ አረፈዉ። (ምንጭ ኢትዮ ሬፈረንስ እትም 11/09።2020) ይህን ያህል ምን መጣ? ኢትዮጵያ የትግራይን ህዝብ ምን አደረገችዉ?

ይህ በእንዲህ እንዳለ ገብሩ አስራት ነኝ የሚል ፖለቲከኛ ተነስቶ ለይስሙላ ያህል «መገንጠል በየትኛዉም መንገድ መፍትሄ አይሆንም» በሚል  ቱባ ርእስ ስር ወደ ገደለዉ ሲገባ፣ «አሁን ላይ የምንሰማዉ ግፋ በለዉ መልካም አይደለም፤አሁንም ማእከላዊ መንግስት ጉዳዩን በጥበብ መፍታት መሞከር አለበት,,,መንግስት በተለያዩ አካባቢዎች ያፈነገጡ ሃይሎች ችግራቸዉ ምንድን ነዉ? ብሎ መመርመር አለበት,,, ምናምን እያለ ሲዘበዝብ ሳየዉ BS ከማለት ሌላ ምንም አላልኩም። መቼም ሰዉ የተለያየ የአስተሳብ ዘይቤ አለዉ። ሰዎች በአስተሳሰባቸዉ Synthesists, Idealists, Pragmatists, Analysts, and Realists thinking mode ይኖራቸዋል። አንዳንዱ ሁለትም ሶስትም የአስተሳሰብ ዘይቤ በጥምር ሊይዝ ይችላል። በአንድ ጉዳይ ላይ አንድ ሽህ አንድ ሀሳቦች የሚመነጩት ከነዚህ የአስተሳሰብ ሞድ ልዩነት በመነሳት ነዉ።ይሁንና የተንሻፈፈ ሃሳባቸዉን በድፍረት ለመናገር ያላዋቂ ድፍረታቸዉ ቢያግዛቸዉም ፤ባለአእምሮ ዜጋ ሃሳቤን እንዴት ያየዋል ብለዉ አያስቡም።ያለዉን የማለት መብቱ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ አሁን ማን ይሙት ገብሩ አስራት የወያኔ እኩይነት ጠፍቶት ነዉ?አረመኔዋ የጦር ወንጀለኞች ክምችት በሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን ላይ የፈጸመችዉ የሀገር ክህደት ጠፍቶት ነዉ? የትግራይን ህዝብ ሲንከባከብ አብሮአቸዉ አረም ሲያርም እህል ሲሰበስብ የኖረን የወገን ጦር እንደ ባእድ ወራሪ ከጀርባዉ ወግታ ሙትና ቁስለኛ ማድረግዋ ጠፍቶት ነዉ? የመጀመሪያዎቹን የጥይት እሩምታ ወያኔ እንዳርከፈከፈችብን አልሰማም?  የሰሜን እዝን አብረዉት የበሉት ፤ከሀዲያን የትግራይ ወታደሮች በጉዋዶቻቸዉ ላይ መሳሪያ አነጣጥረዉ እንደረሸኑዋቸዉ አልሰማም? አልሰማም ወይ?/ What is he talking about, then? ድንገት ሰምቶ ከሆነ ግን ኢትዮጵያ የተከፈተባትን ጦርነት እንዴት እንድትመክተዉ ይመክረን ይሆን?? በሽምግልና ምናምን የሚለዉ የኢትዮጵያ መንግስት ቀደም ባለዉ ጊዜ፤ ከሃይማኖት መሪዎች ፤ከሀገር ሽማግሌዎች ከእዉቅ አትሌቶችና ታዋቂ ሰዎች የተዉጣጣ መልእክተኛ ቢልክባት ሽምግልና የፋራ ነዉ ብላ ወያኔ ሽማግሌዎቹን የዉሻ በትር አስይዛ በሄዱበት አዉሮፕላን አንከሳክሳ እንደመለሰቻቸዉ ገብሩ አስራት አያዉቅም? BS.

ሌላዉ ስዬ አብርሃ ነዉ። ሌላዉም ስዩም መስፍን።

ወያኔ ከመከላከያ ሚኒስትርነቱ ላይ ጋማዉን አንቃ ስዬ አብርሀን ፍርድ ቤት ገትራዋለች። ኢትዮጵያዊትዋ ዳኛ ብርቱካን ሚደቅሳ ክሱን ዉድቅ አድርጋ ነጻ ብትለቀዉም ወያኔ ድጋሚ ማንቁርቱን ይዛ ስዬን ለስድስት አመታት ዘብጥያ አሽታዋለች። መጨረሻ ላይ ግን  ስዬ ከወንጀል ግብረ አበሮቹ ጋር መቀሌ መሽጎ ኢትዮጵያን ለማድማት ወያኔ ለምትፈልገዉ ጦርነት አዘጋጅቶአት አሁን እግሬ አዉጭኝ ብሎ ወደ አሜሪካ አቅንቶአል። 

ስዩም መስፍን፤ አንድ ጊዜ የኢትዮጵያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ሌላ ጊዜ በቻይና የኢትዮጵያ (የህወሀት) አምባሳደር እየሆነ በህልሙ እንኩዋን ያላየዉን ስልጣን ሲቀማጠልበት ቢኖርም በመጨረሻዉ ኢትዮጵያን ለመዉጋት ለማድማትና ለመበታተን ሸሚዙን ሲጠቀልል ከርሞአል። ኢትዮጵያ የቱንም ያህል ከአመድ ላይ አንስታ በወሳንሳ ተሸክማ የሀገር መሪነት እድል ብትሰጣቸዉም እነሱ የልባቸዉ አይደርስም። አይረኩም። ወያኔዎች እና ሰዉን አስገድደዉ የሚደፍሩ (rapists) ነፍስ የራቃቸዉ ወንጀለኞች  ናቸዉ። ስነልቦናቸዉም አንድ ነዉ። አስገድደዉ ይደፍራሉ፤ያሰቃያሉ፤በመጨረሻም ይገድላሉ። (This is the hallmark of rapists-the hallmark of TPLF gangs as well)

እስከዛሬ ድረስ ሙሉ የእምነት ቃሌን የምሰጥላቸዉ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊ  የትግራይ ተወላጅ አቶ ገብረመድህን አርአያ ናቸዉ።( ምስጋናዬ ለአቶ ገብረመድህን ይድረስ)

 

የተቀሩት የትግራይ ስመ-ምሁራንና ፖለቲከኞች ከሳምንት ዉስጥ ሁለቱን ቀኖች ኢትዮጵያዊ ሆነዉ መግለጫ ቢጤ ያወጡና አምስቱን ቀናት በመደዳዉ «ወላዲት አደይ ትግራይ ወይእካ ክርትም» ሲሉ የሚገኙ ናቸዉ። የትግራይ ልሂቃንና ፖለቲከኞች እዉነተኛ ኢትዮጵያዊ መንፈስ ይኑራቸዉ አይኑራቸዉ ለማወቅ ጥቂት አፕቲቱዩድ ቴስት መስጠት በቂ ነዉ።

U, ወልቃይት፤ጠገዴ፤ ሁመራና ራያ የማን ግዛት ነዉ?

ለ, ራስ ዳሽን ተራራ በስርቆት ወደ ትግራይ የሄደዉ መቼ ነበር? ሌቦቹስ እነማን ነበሩ?

ሐ, የአሰብ ወደብ ለኢትዮጵያ አይገባም ብላችሁ በብረት ክንድ ትገዙዋት የነበረችዋን ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ለማድረግ የፈለጋችሁበት እዉነተኛ ምክንያት ምን ነበር?

 

*ህወሃት በኢትዮጵያ ላይ በከፈተችዉ ጦርነት የተነሳ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድን ተጠያቂ ማድረግ 

 ወደዚህኛዉ የሃሳብ ጎራ ስንገባ፤ ከላይ ካነሳነዉ ወገናዊነት ፈጽሞ በተቃርኖ የቆመ ነዉ። ይህ ሃሳብ በአሁኑ ጊዜ ለኢትዮጵያ የሚጠቅማት እንዴት ነዉ? የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርና የጦሩ ጠቅላይ አዛዥ ለዉጊያዉ አመራር መመሪያና ዉሳኔ ማስተላለፋቸዉን ትተዉ ፍርድ ቤት እንዲቆሙ ነዉ የሚፈለገዉ?

ለነገሩ በግሌም ብጠየቅ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወያኔን አመራር ጥግ ለማስያዝ ይጠቅማል ብለዉ የተከተሉትን መንገድ አላመንኩበትም፤ አላምንበትምም። ወያኔ ከሁለት አመት የበለጠ ጊዜ አግኝታ የዘረፈችዉን አጣጥማ እየበላች፤ ቅልጥሙን በዊስኪ አያጠበች በተረፈዉ ጊዜ ጦርዋን እንድትወለዉልና አቅምዋን እንድትገነባ ባላዬ ባልሰማ ታልፋለች። ወያኔ የተሰጣትን እድል አሽቀንጥራ ጥላ ፤በእብሪት ተወጥራ የከፈተችብንን ጦርነት በድል ካጠናቀቅን በሁዋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩንም ሆነ መንግስታቸዉን ለመውቀስ ፤ተጠያቂም ለማድረግ መብቱ አለን። ጊዜዉም ይኖረናል። በኔ አስተያየት፤ ጊዜዉ አሁን አይደለም።

ለአሁኑ መደረግ ያለበት

ቀደም ሲል የትግራይን ፖለቲከኞችና ስመ-ምሁራን የጠቀስኩት ለዚህ ነዉ። ክፉ ቀን ሲመጣ እያንዳንዱ ወያኔን ከብቦ አላስነካም ይላል። ምንም ያህል በወንጀል ቢጨማለቁ ወገንተኝነታቸዉን አይነፋፈጉም። ከህዝቤ ጋር ገደል እገባለሁ ሲሉ ይደመጣሉ።ምንም እንኩዋን ጦርነቱን የጀመረችዉ ወያኔ ብትሆንም። ምንም እንኩዋን የኢትዮጵያ መንግስት ገደቡን የጣሰ ትእግስት እንዳደረገ ቢያዉቁም፤ «ጦርነት ይቁም መንግስት ጉዳዩን በጥበብ መፍታት መሞከር አለበት እያሉ ያደነቁሩናል።

እኛ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁን ተጠያቂ መሆን አለባቸዉ እንላለን። (We need to prioritize our affairs. Let’s not die on every hill)

 ሀገራችን የክህደት ጦርነት ተፈጽሞባታል።(We need to deal with this un just war first and for most)!

ጊዜዉ ሲደርስና ሀገር ስትረጋጋ ወደ ቤት ስራችን እንመለሳለን።ጦርነቱ በኢትዮጵያ አንድነትና ድል አድራጊነት ሲጠናቀቅ ሃሳቦች ተንሸራሽረዉ የማይጠቅመዉ ተበጥሮ ለሀገራችን የሚበጃትን ሃሳብ ለማዳበር አሁን በዚህ ክፉ ቀን አብረን መቆም ካልቻልን ወደፊት ለዉይይት አብረን መቀመጥ አንችልም።።

ማጠቃለያ

በህወሃት ጀማሪነት የተከፈተዉ ጦርነት በአጭሩ እንዲጠናቀቅ የምንፈልግ የህወሀትን የጦር ወንጀለኞችና የሃያ ሰባት አመታት አፓርታይድ አገዛዝ ቁንጮዎችን ወደ ህግ በማምጣት እንተባበር። ነቀፋና መጎነታተሉን ጋብ አድርገን ወደ ተቀራራቢ ሃሳብ እንምጣ። ለስነ-ልቦናዉ ጦርነት ሰልፋችንን እናስተካክል። አብርሃ ደስታ ከህዝቡ ጋር ገደል ከሚገባ ወንጀለኞቹ ከተደበቁበት  የክህደት ገደል ወጥተዉ ወደ ህግ እንዲመጡ ይምከራቸዉ። ሽምግልና ይሻላል የሚለዉ ገብሩ አስራት ወንጀለኞቹ እጃቸዉን በሰላም እንዲሰጡ ይሸምግላቸዉ።

ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ለዚህ ተጠያቂ ናቸዉ የምንል ጥቂት እንታገስ። በወያኔዎች የምንበለጥበትን ምስጢር እንለማመደዉ። በአንድነት ካልቆሙ እንደሚጠፉ ስለሚያዉቁ ነዉ እንጂ ወያኔን እኮ አብርሃ ደስታ ፤ገብሩ አስራትና ስዬ አብርሃ ወደዋቸዉ አይደለም ወገናዊነታቸዉን የሚያሳዩት። ግርፊያዉ ይብዛ ይነስ እንጂ ሶስቱም በእስር ቤት ትንሽ ሳይቀምሱ አልቀሩም።

 እኛም እልሃችንንና ሃቃችንን በልባችን ይዘን ይህ ጦርነት በድል እንድናጠናቅቅ ለሰራዊታችን፤ ለመንግስታችንና ለህዝባችን አጋርነታችንን ልናሳይ ይገባል።መወነጃጀሉ ጋብ ይበል።

 

እግዚአብሄር ኢትዮጵያንና ህዝብዋን ይባርክ

Filed in: Amharic