>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7397

ፍቅር ሃትሪኳ ቅዱስ ሥፍራ - ሑመራ፣ ተከዜ፣ ኡመሀጅር፣ ሱዳን…! (አሰፋ ሀይሉ)

ፍቅር ሃትሪኳ ቅዱስ ሥፍራ – ሑመራ፣ ተከዜ፣ ኡመሀጅር፣ ሱዳን…!

አሰፋ ሀይሉ

A Lovely City in the middle of the Desert, a River with a Bridge of Peace!
ከጀርባዬ ያለው ኢትዮጵያንና ኤርትራን የሚያገናኘው የተከዜ ድልድይ ነው! ይህ ቦታ ብዙ ድንበር የተሻገሩ ሀሳቦችን ያውጠነጠንኩበት የተቀደሰ ሥፍራ ነው! ከዚህ ወንዝ የለቀምኳቸውን ውብ ቀለማም ድንጋዮች በቤቴ ለብዙ ጊዜ አስቀምጬ እመለከታቸው ነበር፡፡ የሁለቱ የሀበሻ ህዝቦች መለያየት ትልቅ የትውልድ ማነስ እንደነበረ ደጋግሜ እንዳስብ ያስታውሱኝ ነበር፡፡
እንደ አንድ ቅን አሳቢ ኢትዮጵያዊ የሆነ ነገር ማድረግ እንዳለብኝም ይሰማኝ ነበር፡፡ ደጋግሜ ብዙ የእርቅና የሠላም መልዕክቶችን በፌስቡክ ገጼ እና ተጽዕኖ ሊያመጡ ይችላሉ ብዬ ለማስባቸው ሰዎች ሁሉ አካፍዬአለሁ፡፡ በመጨረሻም የሰሜን ኮርያና የደቡብ ኮርያ መሪዎች ለብዙ አሰርት ዓመታት ያለያያቸውን ድንበር አልፈው እጅ ለእጅ ሲጨባበጡ የሚያሳየውን ዜና ሳይ ልቤ በእጅጉ ተነካ፡፡ እና እኔም በወቅቱ በብዙ ተስፋ ሰጪ የለውጥ ሀሳቦቹ የማረከኝን የአብይ አህመድን እና የኢሳያስ አፈወርቂን ምስል ከተለያዩ ሥፍራዎች አምጥቼ፣ እጆቻቸውን በአዶቤ ፎቶሾፕ አቀናጅቼ – እጅ ለእጅ አጨባብጬ – መቼ ነው የእኛስ የአንድ እናት ልጆች ፀብ የሚያበቃውና እጅ ለእጅ፣ ልብ ለልብ የምንጨባበጠው – የሚል ከልቤ በእምባ ታጅቦ ከተጻፈ ሁልጊዜም ሳስታውሰው ከምኖር መልዕክቴ ጋር – በፎቶው አስደግፌ በፌስቡክ ገጼ አካፈልኩ፡፡ አሁንም ያንን ለፐብሊክ ያካፈልኩትን ‹‹ፖስት›› ማየት የሚሻ በቀኑ ገብቶ ማየት ይቻላል፡፡
ያ መልዕክትና ሀሳብ የእኔ ብቻ እንዳልሆነ የተረዳሁት – ብዙ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን የፌስቡክ ወዳጆቼ ሼር አድርገውት፣ በርከት ያሉ ቀና አስተያየቶችንም ሰጥተውኝ ስመለከት ነበር፡፡ ይህ በሆነ በጥቂት ሳምንታት ጊዜ ውስጥ – አብይ አህመድ ከጉራጌ ዞን ለሥራ ጉዳይ በሄደበት – ለኢሣያስ አፈወርቂ እና ለኤርትራ ህዝብ የሠላምና እርቅ ጥሪውን አቀረበ፡፡ ብዙም ሳይቆይ ከኤርትራ ቀና ምላሽ ተሰጠው፡፡ እነሆም በሑመራ የተዘጋ ድልድይ ትካዜ የወለደው፣ በተከዜ ወንዝ ውብ የውሃ ዳር ትዝታዎች አጋዥነት ያነሳሁት ሃሳብ እና የለጠፍኩት የአዶቤ የመጨባበጥ ፎቶ በአካል እውን ሆኖ – ሁለቱ መሪዎች በእውንም ሲጨባበጡ ለማየት ቻልኩ፡፡ በወቅቱ ደስታዬ ወደር አልነበረውም በእውነቱ፡፡ ይህን ስል በእኔ አሳሳቢነት ነው ሁለቱ መሪዎች የተጨባበጡት እያልኩ እንዳልሆነ ይታወቅ፡፡ ስለዚያ የማውቀው ነገር የለኝምና!
ብዙዎች እንደሚያውቁኝ – ትክክለኝነቱን ያመንኩበትን እና ለሀገርና ለወገን ይበጃል፣ መሆን አለበት የምለውን ነገር ከማንም ጋር ሳልዳበል ራሴን ችዬ፣ በገዛ አዕምሮዬና አስተሳሰቤ ተመርቼ፣ ለማህበረቤም ቅርብ እንደሆነ አንድ ሰው፣ ያመንኩበትን ነገር ፊት ለፊትና በግልጽ አደባባይ አውጥቼ ለሚሰማ እና ለሚያይ ሁሉ አካፍላለሁ፡፡ ይህ በዜግነቴ እንደ አንድ ተራ ሰው የማበረክተው የሃሳብ አስተዋፅዖ ድርሻዬ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ሀሳቦች ተጠራቅመው ነው ሀገራዊ ለውጥም፣ አሻራም አሳርፈው የሚያልፉት፡፡ በዚህ በኩል በግለሰቦች ጥረትና አስተዋፅዖ ፋይዳ ላይ ከፍ ያለ እምነት አለኝ፡፡ ወደፊትም ከዚህ አስተሳሰቤ የምዛነፍ አይመስለኝም፡፡
ዛሬ ሠለጠነ፣ በለጸገ የምንለው የምዕራቡ ዓለም አብዛኛው ኗሪ፣ በአስተሳሰቡም ሆነ በብዙ ሰብዓዊ መመዘኛዎች ከኛ ብዙም የተለየ ሆኖ አይደለም፡፡ ለየት ያለን ጠቃሚ ሀሳብ ለማህበረሰባቸው የሚፈነጥቁ፣ የሚያንሸራሽሩ፣ እና እነዚያን ሀሳቦች ወደ ተሻሉ ዕድሎች ለመለወጥ የቻሉ መሪዎች ስለነበሯቸውና ስላሏቸው ነው ቱሩፋቱ ብዙሃኑን እያዳረሰ ብዙ ነገሮቻቸውን በጥበብ አቃንተው ለመኖር የተሳካላቸው፡፡ ያን በቅርበት ተገኝቼ ስመለከት ደግሞ፣ በሀገሬ ህዝብ እምቅ አቅም ላይ፣ እና በግለሰቦች አስተዋፅዖ ፋይዳቢስ አለመሆን ላይ ያለኝ እምነት እየጠነከረልኝ እንዲሄድ አድርጎብኛል፡፡ እንጂ ከቶም ‹‹አንድ ጠብታ ውሃ የውቅያኖሱን ከለር አይቀይረውም›› የሚል በግለሰቦች የማሰብ ኃይል ላይ ተስፋው የተሟጠጠ አስተሳሰብ አይነግስብኝም!
ወደ ጀመርኩት ቁምነገር ልመለስና – አሁንም ድረስ የበረሃዋን ለምለሚት ምድር ሑመራን ሳስብ፣ ተከዜን ሳስብ፣ ብዙ ተጀምረው ያልተጨረሱ ወሰን ተሻጋሪ፣ ብሔር ተሻጋሪ፣ ጥላቻና ፀብን፣ ዘመንንም ተሻጋሪ የሆኑ – ብዙ የሠላም ሀሳቦች ወደ ህሊናዬ እየተዥጎደጎዱ ይመጡብኛል፡፡ ሑመራም ሆነ ተከዜ – ይህ የተቀደሰ ሥፍራ – የህዝበ ሀበሻ የእርቀ ሠላም መጀመሪያ እንጂ መጨረሻ እንደማይሆን በእርግጠኝነት እምናለሁ፣ እናገራለሁም፡፡
ይህ ሥፍራ የኢትዮጵያና የኤርትራ ወንድማማች እህትማማች ህዝቦችን ዳግም እንዳገናኘ ሁሉ – የአማራና የትግሬ ተወላጁን ኢትዮጵያዊም፣ የተጎራባቹን ወንድማማች ህዝብም ልብ ለልብ የሚያገናኝ፣ ቂምና ጥላቻን የሚቀርፍ፣ የተጣላን የሚያስታርቅ፣ ሁሉንም አብሮ የሚያኖር፣ በተለያዩ ምክንያቶች እንዲሸረሸር የሆነውን የእርስ በእርስ እምነት የሚገነባ – ታላቅ የተስፋና የደስታ ሥፍራ እንደሚሆን እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁ፡፡
ይህ ብቻም አይደለም በዚህ አስገራሚ ሥፍራ የሚሆነው፡፡ ብዙ የአካባቢው ተወላጆች የነገሩኝ ‹‹ትሪፕ›› አለ በዚህ አካባቢ የሚዘወተር፡፡ ከሁለት አሰርት ዓመታት ከሚያንስ ጊዜ በፊት – በዚህ ሥፍራ የሚኖሩ የሁመራና አካባቢዋ ወጣት ልጆች (ነዋሪዎች) – ልክ እንደኔው – በቦርሳቸው ቤት ያፈራውን ስንቅ ቋጥረው – ለትራያንግል ትሪፕ ይወጣሉ፡፡ ትራያንግሉ እንዴት ያለ ነበር?
ሲነግሩኝ፡- ቁርሳቸውን ሑመራ ላይ ይቀማምሱና ወንዙን ተሻግረው ወደ ኤርትራ ይገባሉ፡፡ ምሳቸውን ደሞ ኤርትራ ላይ ከዚህ ከተከዜው ድልድይ ከፍ ብላ በእግር በምታስኬድ ኡመሀጅር በተባለች ከተማ ቀማምሰው አርፈው፣ እየተጨዋወቱ ይቆያሉ፡፡ መጨረሻ ላይ ደሞ መቅሰሳቸውን ፀሐይ ሳትጠልቅ ጥቂት ተጉዘው ወደ ሱዳን ይሻገሩና ይቀማምሳሉ፡፡ የትሪፕ ሃትሪክ፡፡ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሱዳን፡፡
እውነትም ሑመራ – ወደፊት በማነሳሳቸው ጥቂት ምክንያቶች የተነሳ የሥጋትና የጥርጣሬ ዳመና ያደረባት ከተማ ሆናም እንኳ –  የኢትዮጵያ፣ የሱዳን፣ እና የኤርትራ ህዝቦችን በጋራ የምታስተናግድ የፍቅር መናኸሪያ መሆኗን ያላቆመች አስገራሚ የፍቅር ከተማ ሆና አሳልፋለች፡፡ ሱዳኖች ድንበር ተሻግረው በሑመራ ያርፋሉ፡፡ አንዳንዶቹን እጠይቃቸዋለሁ፡፡ ለምንድነው እዚህ የምትመጡት? – እየተገረምኩ ነዋ፡፡
አንዳንዴ እኮ ሁመራ በ47 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሙቀት ግላ ጉልቻ ላይ እንደተጣደ ድስት ስትለበልብህ ታገኛታለህ፡፡ ወበቁም ከባድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ተከዜ ጋር ደጋግመህ የምትሄደው፡፡ ከሙቀቱ ለመፈወስ፡፡ ከወበቁ ለመዳን፡፡ ንጹህ ቀዝቃዛ አየር ለመሳብ፡፡ እና ሱዳኖቹ ምን ብለው ይመልሱልኛል? አሁን ሱዳን በጣም ሙቀት ስለሆነ ነው እዚህ ልናሳልፍ የመጣነው! እንዴ? ሱዳን ከዚህም ይብሳል ማለት ነው?!! – የባሰ አታምጣ! ብዬ እብስ፡፡ በእርግጥ ሱዳኖች ሌላም የሚስባቸው ነገር አለ፡፡ ከሀበሻ ሁሉነገር በፍቅር የወደቁም ይመስለኛል፡፡ ዝርዝሩን ወደፊት በጨዋታ ስለማነሳው ልተወው፡፡ ብቻ በሁሉም የምትመረጥ የበረሃ ለምለም ነች፣ ሁሉንም ስታስተናገድ የኖረች፡፡ ብዙው አሉታዊ ነገሮቿ እንደተጠበቁ ሆነው ማለት ነው፡፡ አላፊ ናቸው በእውነቱ፡፡ ወደፊት የምናየው ነው፡፡
እና ሑመራ የሶስት ህዝቦች መናኀሪያ ነበረች፡፡ ሶስት ባህሎችን ቀይጣ የያዘች፣ እንደ ብዙ ጠረፋማ ከተሞች በማህበራዊ መስተጋብር የበለፀገች፣ ሰው ሰው የምትሸት ምርጥ የተቀደሰች ሥፍራ ሆና ቆይታለች፡፡ ወደፊትም የማይቀርላት ታላቅ የሶስት ጎረቤታም ህዝቦችን የምታገናኝ ምድራዊ ደሴት የምትሆንበት ጊዜ ደግሞ እጅግ ቅርብ ይመስለኛል፡፡
ሑመራ፣ እና ተከዜ፣ እና የአካባቢው ቀጣና በሙሉ – ከዚህ የሚያልፍ ስጋትና ውጥረት ተላቀው – የጋራ ወዳጅነት፣ የሠላም፣ የእርቀ ሠላምና የትብብር ቀጣና እንደሚሆን ሙሉ እምነቴ ነው፡፡ ፈጣሪ ይርዳቸው፡፡ የፈጣሪ ቅን መንፈስ ያደረበትን የሰው ልጅ ዕለት በዕለት ያብዛላቸው፡፡ እንደ ውሃው፣ እንደ ልምላሜው፣ እንደ ውብ ቀለማም ድንጋያቱ – ውብና መልካም ህልምን ያሳያቸው፡፡ እውን ያድርግላቸው ፈጣሪ፡፡ እያልኩ ሁልጊዜ እመኛለሁ ከልብ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ሁሉ አብዝቶ ይባርክ! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!
Filed in: Amharic