>
5:13 pm - Thursday April 19, 6260

የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) ክሱን ወደ ዓለም አቀፍ  የወንጀል ፍርድ ቤት ለምታቀርቡ ወገኖች (ከይኄይስ እውነቱ)

የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) ክሱን ወደ ዓለም አቀፍ  የወንጀል ፍርድ ቤት ለምታቀርቡ ወገኖች

ከይኄይስ እውነቱ


የዘር ማጥፋት ክሱን በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዳይቀርብ ለማድረግ ማናቸውንም ዓይነት መደራደሪያ ቢያቀርቡላችሁ መቀበል የለባችሁም፡፡ በሕፃናትና በንጹሐን ደም ላይ ለመደራደር ማንም ውክልና አልተሰጠውም፡፡

የእናንተ ውግንና ፍትሕን ከተጠማው የኢትዮጵያ ሕዝብና ያለምንም ጥፋታቸው በማንነታቸው በጭካኔ ከተጨፈጨፉት ወገኖቻችሁ ጋር ብቻ ይሁን፡፡

 

በዚህ አጭር ጽሑፍ መልእክት የማስተላልፍላችሁ ወገኖቼ በዕውቀት፣ በልምድ፣ በማዕርግ ከሁላችሁ የማንስ ኢትዮጵያዊ ወንድማችሁ ብሆንም ትኩረት ሰጥታችሁ/ልብ ብላችሁ ገንዘብ እንድታደርጉት በቅድሚያ በአክብሮት እጠይቃችኋለሁ፡፡ 

በቅርቡ በኢኦተቤክ ሥር የዘር ማጥፋት መከላከያ ድርጅት መቋቋሙ የሚታወስ ነው፡፡ ድርጅቱ በውጭና ባገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ምሁራንን፣ የኢኦተ. ሃይማኖት አባቶችን እና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለሙያዎችን በማስተባበር በኢትዮጵያ ለበርካታ ዓመታት ሲፈጸም የቆየውንና አሁንም እየተፈጸመ ያለውን በአማራ ሕዝብ እና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ  ዘርን እና ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ የዘር ፍጅት (ጄኖሳይድ) ወንጀል ክስ ለዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ለማቅርብ እንቅስቃሴ እንደጀመረ እየሰማን ነው፡፡ እንቅስቃሴው ዘገየ ከሚባል በቀር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የሚወድ ዜጋ ሁሉ ሲጠብቀው የቆየ ነው፡፡ ይህንን ጥረት ከግብ ለማድረስ መረጃ፣ ማስረጃ፣ ሃሳብ፣ ዕውቀት፣ ገንዘብ፣ ጊዜ፣ የሚጠቅመውን ሁሉ በመስጠት የምንሳተፍ ወገኖችን በሙሉ የኢትዮጵያ አምላክ እንዲረዳን አጥብቄ እጸልያለሁ፣ እመኛለሁም፡፡ ይህን የምለው ብዙ ጅምሮች ባጭሩ ሲቀጩ በማየቴ ነው፤ ከውስጥም ከውጭም የሚነሱ የጨለማው ኃይሎች ለበጎ ከሚሰባሰቡት የብርሃን ኃይሎች በበለጠ ለጥፋት ተግተው እንደሚሠሩ በማስተዋሌ ነው፡፡ መለስ ዜናዊ በ1997 ዓ.ም. ‹አልጋው› ሲነቃነቅበት ከሰማይ በታች ባለ ጉዳይ ሁሉ ለመደራደር ዝግጁ ነኝ ካለ በኋላ በጠራራ ፀሐይ ወደ 300 የሚጠጉ ኢትዮጵያኖችን በአረመኔ ኃይሉ እንዳስጨረስና መላ አገሪቱን ወኅኒ ቤት እንዳደረገ የማንዘነጋው ነው፡፡ 

በዚህ ረገድ የምናከብራቸው የአፍሪቃ የስትራቴጂና የደኅንነት ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር የሆኑትና በአፍሪቃ የዘር ማጥፋት ወንጀሎችን ለማየት በተሰየሙ ዓለም አቀፍ ፍ/ቤቶች ልምድ ያላቸው ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ በቅርቡ በርዕዮት ሜዲያ ባደረጉት ቃለ መጠይቅ በውጭ የተሰማሩ የአገዛዙ ኃይሎች፣ የኦነግና የሕወሓት ደጋፊዎች የዘር ማጥፋት ክሱ ዓለም አቀፉ ወንጀል ፍ/ቤት እንዳይደርስ ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡ በመሆኑም ድርጅቱና አባላቱ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ፣ በዘር ፍጅት ላለቁት ወገኖቻችን በተለይ ያለንን ታማኝነትና ተቆርቋሪነት የምንገልጸው ለዚህ ተጽእኖ ባለመንበርከክ ይሆናል፡፡ እምቢ!!! በማለት የሚደርስብንን ማናቸውንም ፈተናዎች (የንዋይ/የሥልጣን) ለመቀበል ዝግጁ መሆንን ይጠይቃል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱ አስተዳደር ግብስብሶች ሁሉ ሠርገው ስለገቡባት አንድነቱን አጥቶ ለአገዛዞች ፈቃድ ውሎ ካደረ እነሆ 45 ዓመታት ተቈጥረዋል፡፡ በተለይም በቅርቡ ተነጥለን የራሳችንን ቤተክህነት እናቋቁማለን ያሉ አፈንጋጮች ‹ተመልሰናል› በማለታቸው ተገቢው የይቅርታ ሥርዓት ሳይፈጸም ዕርቀ ሰላም እንደወረደ ተነግሯል፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ጉዳይ የራሴ ተዐቅቦ (reservation) ስላለኝ ሰዎቹን በጥንቃቄ መመልከት ያስፈልጋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ባንድ ጀምበር ፍጹም ሊቀየሩ አይችሉምና፡፡ ዛሬ ሁሉንም ነገር ለመንፈስ ቅዱስ እንዳንተወው መንፈሳዊነቱ የለንምና፡፡ 

ደጋግሜ እንደተናገርኹት እግዚአብሔርን ፈርታችሁ፣ የቤተክርስቲያኒቷ ሀብት የሆነውን ምእመን አክብራችሁ፣ በነፍስም በሥጋም መተዳደሪያ የሆነችውንና በመንፈስ ቅዱስ ጭምር አደራ የተቀበላችሁላትን ቤተክርስቲያን እንድትጠብቁ እማፀናችኋለሁ፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ምናልባትም ለመጨረሻ ጊዜ ፈተና አቅርቦላችኋል፡፡ ድርጅቱ ውስጥ የተሰባሰቡትን አባላት ማንነት በሚገባ ዕወቁ፣ ውስጣችሁን አጥሩ፡፡ ማንም የድርጅቱ አባል ከጉባኤው ፈቃድ ውጭ ከ‹መንግሥት/አገዛዙ› ሰዎች ጋር ክሱን በሚመለከት መነጋገር የለበትም የሚል አቋም አለኝ፡፡ 

ሕፃናት፣ እናቶችና አረጋውያን የኛን ሞት እየሞቱ እስከ መቼ እንዘልቃለን፡፡ እውነተኛ መንፈሳውያን አባቶች በተለይም ለዚህ ዓለም ምዉት ነን ያላችሁ መነኰሳት ማንን ነው የምትፈሩት? ምን እንዳይቀርባችሁ?

እዚህ ላይ ማሳሰብ የምፈልገው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሀብት በመጠቀም የተቀደሰ ዓላማን በማጨናገፍ የታወቁት አገዛዙና ባለሟሎቹ እንዲሁም ሽብርተኞቹ ኦነግና ሕወሓት ለዚህ ተልእኳቸው የሚጠቀሙት አንዱ ስልት የዘር ማጥፋት መከላከያ ድርጅቱ ውስጥ ያሉ ግለሰቦችን በሚያውቋቸውና ለአገዛዙ ባደሩ ታዋቂነትና ተሰሚነት ባላቸው ሰዎች መቅረብ በመሆኑ፣ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ገብተው፣ ቤተክህነቱ ውስጥ ገብተው፣ በልዩ ልዩ የማኅበረሰብ ተቋማት ውስጥ ገብተው ልዩነትን መፍጠርና መከፋፈል የለመዱት እኩይ ተግባር ነውና፡፡ የዘር ማጥፋት ክሱን በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዳይቀርብ ለማድረግ ማናቸውንም ዓይነት መደራደሪያ ቢያቀርቡላችሁ መቀበል የለባችሁም፡፡ በሕፃናትና በንጹሐን ደም ላይ ለመደራደር ማንም ውክልና አልተሰጠውም፡፡ ለምሳሌ አገዛዙ ወልቃይት፣ ጠገዴ፣ ጸለምት፣ ሁመራ እና ራያን ለመደራደሪያ ሊያቀርብ ይችላል፡፡ እነዚህ በጭራሽ መደራደሪያ ሊሆኑ አይችሉም፡፡ የዘር ፍጅት ተፈጽሞ በኃይል የተወሰዱ ቦታዎች እንደሆኑ ሁሉ ባለ ርስቱ ሕዝብ ራሱ ያስመልሳቸዋል፡፡ ሌላው የያዛችሁትን አጀንዳ በሚመለከት ማናቸውም በውጭ ያሉ ‹የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች› ጋር ኅብረትና ግንኙነት መፍጠር የለባችሁም፡፡ ላለፉት 27 ዓመታትም ሆነ የወያኔ ወራሽ የሆነው የዐቢይ አገዛዝ ዘመን ‹የኢትዮጵያ ኤምባሲዎች› አገዛዙን የተቆጣጠረው የዘር ፖለቲካ ድርጅት ቅጥያዎች መሆናቸውን ለአፍታ መዘንጋት የለባችሁም፡፡ አንዳንዶች ለስላሳና ባንፃራዊነት ከቀደሙት ‹የተሻሉ› የሚመስሏችሁ ‹አምባሳደሮች› የበግ ለምድ የለበሱ ተኩላዎች በመሆናቸው እጅግ ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ በአገር ቤት የነበራቸውን የኋላ ታሪክ በሚገባ እናውቀዋለን፡፡ ለሕወሓት ሎሌ በነበሩበት ዘመን ወይ በግድያ ወይ በዝርፊያ ሕዝባችንን ቁም ስቅሉን ሲያሳዩ የነበሩ መሆናቸውን ጥቂት ብትመረምሩ ትደርሱበታላችሁ፡፡ ልዝብ ሰይጣኖች መሆናቸውን ከዐቢይ ልትማሩ ይገባል፡፡ የእናንተ ውግንና ፍትሕን ከተጠማው የኢትዮጵያ ሕዝብና ያለምንም ጥፋታቸው በማንነታቸው በጭካኔ ከተጨፈጨፉት ወገኖቻችሁ ጋር ብቻ ይሁን፡፡ 

የዘር ማጥፋቱ ሃሳብ ከዛሬ 45 ዓመታት በፊት ታቅዶ ተግባራዊ መሆን የጀመረ ሲሆን፣ ላለፉት 27 ዓመታት የቀጠለ፣ በተለይ ደግሞ ላለፉት 3 ዓመታት እጅግ ተጠናክሮ አገራችን በደም አበላ እንድትታጠብ ያደረገ፣ በታሪካችን – ከግራኝ አህመድ እና ከኦሮሞ ወረራዎች ጋር ባንድነት የሚታይና ተወዳዳሪ የማይገኝለት የጭካኔ ተግባር ነው፡፡ ይልቁንም የዘር መድልዎ የነገሠበት (አፓርታይዱ) የዐቢይ አገዛዝ ከመጣ ወዲህ ላለፉት 3 ዓመታት ገደማ የዘር ማጥፋቱ ተግባራት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ግዛቶች በአማራው ሕዝብና በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች ላይ ተፈጽሟል፡፡ አሁንም አላባራም፡፡ ይህንን ጽሑፍ እያዘጋጀሁ እያለሁ በመተከልና አካባቢው 50 የሚደርሱ አማራ ኢትዮጵያውን መገደላቸው ተነግሯል፡፡ የዘር ፍጅቱ ግንባር ቀደም ተዋናዮች ኦነግ እና ሕወሓት ቢሆኑም፣ በአባሪ ተባባሪነት ከማዕከላዊው ‹መንግሥት› ጀምሮ እስከ ወረዳ ባለሥልጣናት/ ካድሬዎች ተሳታፊ የሆኑበት እንደሆነ ከዜና አውታሮች ተሰምቷል፡፡ ማስረጃዎችም አሉ፡፡ 

በነገራችን ላይ በቅርቡ ባወጣሁት ጽሑፍ ኦነግ እንጂ ሸኔ የሚባል የለም እንዳልሁት÷ በክሱ ዝግጅት በርካታ ዐዋቂዎች እንዳላችሁ ባምንም ለጥንቃቄው ያህል ኦነግን (ሸኔ የሚለው ማጭበርበሪያ ሳይጨመር) ያለምንም ቅጽል እንዲጠራ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ በአንፃሩም በሜዲያዎች ረገድ እንደ ኦ ኤም ኤን ያሉ ሜዲያዎች በግልጽና ዋና ተዋናይነት የሚታዩ ሲሆን፣ የመንግሥት ሜዲያዎችና ሌሎች ለመንግሥት ቅርብ የሆኑና ድጎማ የሚሰጣቸው የተወሰኑ የ‹ግል› እና ማኅበራዊ ሜዲያዎች ደግሞ በሚያስደነግጥ ዝምታና አንዳንዶችም በቀጥታ ለፍጅት/እልቂት የሚያነሳሱ ወሬዎችን በማሰራጨት አባሪ ተባባሪ መሆናቸውም ሊታወቅ ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ አንዳንዶች በፌስ ቡክ እና በዩ ቲዩብ በጽሑፍ እና በድምጽ ያስተላለፏቸውን ፕሮግራሞች ለማንሳት እየተንደፋደፉ ስለሆነ፣ ውጭ ያላችሁ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ ምንጩ ድረስ ዘልቃችሁ እነዚህን ፕሮግራሞች በማስረጃነት መያዝ እንደሚገባ ልጠቁማችሁ እወዳለሁ፡፡

ኰናኔ በጽድቅ ፈታሔ በርትዕ የሆነው እግዚአብሔር አምላክ በግፍ የተጨፈጨፉ ወገኖቻችንን ፍትሕ ለማየት ያብቃን፡፡ ለግፉአን ጥብቅና ለመቆም የቆረጣችሁ ወገኖቼ በሙሉ የእውነት አምላክ ይርዳችሁ፡፡

Filed in: Amharic