>

ያልተስማማነው ጋዜጠኛ ዘብጥያ ይውረድ ፣ ጋዜጦች ይዘጉ ጥሪ አንባገነንነትን መጋበዝ ነው ! (ዘ .ተስፋዬ)

ያልተስማማነው ጋዜጠኛ ዘብጥያ ይውረድ ፣ ጋዜጦች ይዘጉ ጥሪ አንባገነንነትን መጋበዝ ነው !

ዘ .ተስፋዬ


እኛ ካለን አቋም የተለየ የሚጽፍ ጋዜጠኛ ይታሰር የማንስምማባቸው ሃሳቦች የሚያንጸባርቅ ጋዜጣ፣ ሬድዮም ሆነ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ሰላማዊ ሰልፍ ይጠራ ወይንም ይታገድ የሚሉ በርካታ ጥሪዎች ከሰሞኑ ስመለከት የህወሃት 27 ዓመት አገዛዝ ምን ያህል በሰዎች አዕምሮ ዘልቆ እንደገባና እንደመረዘው ማሳያ ይመስለኛል።

 

 የተሳሳተ ዜና ወይንም ዘገባ የሚያሰራጩ ጋዜጠኞችንም ሆነ የዜና አውታሮችን  ስህተታቸውን ነቅሶ በማውጣት ቢቻል እንዲያርሙ ማስደረግ፣ እንቢታን መርጠው ከቀጠሉ ደግሞ ለአንባቢ በማጋለጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ የመሆን እድላቸውን ማምከን ይቻላል።

 ጽሁፎቻቸው የግለሰብንም ሆነ የመንግስትን ስም አጉድፈዋል ወይንም ህዝብ ለህዝብ የሚያጋጩ ዘገባዎች ወይንም ሌላ ወንጀል ፈጽመዋል ከተባለ፣ በሀገሪቱ የፍትሃ ብሔርም ሆነ የወንጀል ክስ በአግባቡ ሊከሰሱ እንደሚችሉ እሙን ነው። 

 

ሆኖም በሃሳብ ልዩነት ላይ ብቻ ተመስርቶ የጋዜጠኛን እስር መሻት ፣ወይንም ግልጽ ባልሆነ መንገድ ያለ ፍርድቤት ትእዛዝ ወይንም መጥሪያ መንግስት ተመስገንንም ሆነ ሌሎች ላይ ያካሄደውንም ሆነ፣ በቅርቡ ደግሞ በቃሉ ወይንም መድሃኔ ላይ የሚያካሂደውን እስር በዝምታ ማለፍ ወይንም አበጀህ ማለት ከማንም በሀገራችን የዴሞክራሲ ስርዓት እንዲፈጠር እፈልጋለሁ ከሚል የሚጠበቅ አይደለም። በአንጻሩ እንዲህ ያለ አካሄድን መምረጥ  ለአምባገነናዊ ስርዓት መደላድል የሚፈጥር ስለሆነ በጽኑ ልንቃወመው ይገባል።

 

.ተስፋዬ

Filed in: Amharic