>

ህወሓት ሆይ እጅሽን ስጪ !! (ዘመድኩን በቀለ)

ህወሓት ሆይ እጅሽን ስጪ !!

ዘመድኩን በቀለ

• ምስኪኖችን አታስጨርሺ፤  እጅሽን ስጪ !!
– እግዚኦ ሰላምከ ሀባ ለሀገር ወጽድቀከኒ ለቤተክርስቲያን፤ አግርር ፀራ ታህተ እገሪሃ እቀብ ህዝባ ወሃይማኖታ ለሃገሪትነ ኢትዮጵያ፡፡
•••
ውድ ጓደኞቼ ሆይ !! የላካችሁልኝና በየ እርሻው፣ በየመንገዱ የወዳደቁ የወንድሞቼን አስከሬኖች በሙሉ አየሁ። ተመለከትኩም። አዘንኩ፣ አለቀስኩም። ከጦርነት የሚጠበቀውም ይሄው ነው። የሚገርመው እና የሚደንቀው ግን እኒህን ምስኪን ታጣቂዎች ወደ ውጊያ የላከው አካል ጫፉ አይነካም። የቴዎሮስን ሞት እንኳ አይሞቱም። ፈሪ ናቸው። በመጨረሻም ካረፉበት ሆቴል ሳይወጡ፣ ከሞቀ ቤቱም ሳይንቀሳቀስ፣ ከሚስቱ ጋር አሸሼ ገዳዬ ሲል  ነው መጨረሻ ላይ በቁጥጥር ስር ዋለ የሚል ዜና የሚሠራለት። ከዚያ አዲስ አበባ በአውሮጵላን ወይ በኢሊኮፍተር ዘና ብሎ ይመጣል። ከዚያ ፍርድ ቤት ቀርቦ ይሟገታል። እንደ አብዲ ኢሌ ዘና ብሎ ፈታ ብሎ ይኖራል። ከዚያ ወይ ይፈረድበታል። አልያም በዋስ ወይም በምህረት ይፈታል። የሚጎዳው ግን ምስኪኑ ነው። ደሙ ደመ ከልብ ሆኖ የሚቀረው ግን ምስኪኑ ነው። የምትጎዳው እናት ናት። ሚስትና ልጆቹ ናቸው። አዎ ጉዳቱ እዚያ ላይ ነው።
•••
የህወሓት ሹማምንቶች ሆይ እባካችሁ እናንተ የማትሳተፉበትን ጦርነት አትምሩ። ህጻናትን ለውጊያ አትመልምሉ። ነውረኞች ሆይ የእናንተን ልጆች አሜሪካና አውሮጳ አንደላቃችሁ እያኖራችሁ በሰው ልጆች በንጹሐን ህይወት በምስኪኑ ገበሬ ልጅ ነፍስ  አትቀልዱ። እጃችሁን ስጡና ሃገር ትረፍ።
•••
ህወሓት ሆይ የምትዋጊው ከዐቢይ አሕመድ ጋር አይደለም። የምትዋጊው ከኢትዮጵያ ጋር መሆኑን እወቂ። ከኢትዮጵያ ጋር ተዋግቶ ያሸነፈ ደግሞ የለም። ትደቂያለሽ፣ ትወጊያለሽ፣ እናም ውጊያውን አቁሚና እጅሽን ስጪ። ብዙ የጎዳሻቸው፣ ያቆሰልሻቸው፣ ያረድሽ ያሳረድሻቸው፣ ቂም የያዙብሽ ሚሊዮኖች አሉ። እናም መቃብር እስክትወርጂ አይፋቱሽምና በጊዜ እጅሽን ስጪና ነገሩን አብርጂ። ራያ፣ ወልቃይት፣ ፀገዴ ምናምን ያንቺ ያልሆነውን ምድር ሁሉ በጊዜ መልሺ። መልቀቅሽ ላይቀር በጊዜ ልቀቂ። ሰውም አይለቅ። ንብረትም አይውደም። ለትውልድም አስቢ። ይሄ ምክሬ ነው።
•••
አስታውሺ ጋዳፊን አስታውሺ፣ ሳዳም ሁሴንን አስታውሺ። አስታውሺ ፈርኦንን፣ ናቡከደነጾርን አስታውሺ። ኢትዮጵያን በድለሻል፣ አሳዝነሻል፣ አስለቅሰሻል። ቤተሰብ በትነሻል። በዘር በጎጥ ከፋፍለሻል፣ ቤተሰብ በትነሻል። በክልል በረት ውስጥ አስረሽ ፍዳ መከራ ሃገር ምድሩን አብልተሻል። እናም በሌላው የፈሰሰው ደም ይብቃ። ትግራይን በደም አበላ አታጥምቂ። እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል ማለትሽን ተዪ። እጅሽን ስጪ።
•••
የትግራይ አክቲቪስቶች እረፉ። የተለየ ሃገር ተቀምጣችሁ በባዶ ሜዳ አትፎክሩ። ህዝብ አታስጨርሱ። ትእቢት ነው ወሬ ፉከራ አቁሙ። ከቻላችሁ ራሳችሁ ገብታችሁ ተዋጉ። ራሱን መግቦ ማደር የማይችል ምስኪን ህዝብ በጦርነት አትማግዱ። በባዶ ሆዱ አታዋጉት። የትግሬ ኩራቱ ኢትዮጵያዊነቱ ነው። እናም ተፋቱት። ኢትዮጵያዊነቱን መልሱለት። የኢትዮጵያ ጠላት፣ ኢትዮጵያ ላይ ተቀምጦ ኢትዮጵያን ተሰደበ፣ የተራገመ፣ የሸጠ፣ የለወጠ፣ ያሳዘነ፣ ያስከፋ፣ ያዋረደ፣ አንገት ያስደፋ፣ የሰረቃት፣ ያስለቀሳት ሁሉ ዋጋውን ያገኛል። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ዋጋውን ያገኛል። እያያችሁትም ነው።
•••
አስታውሱ እግዚአብሔር እናንተ ህወሓቶችን፣ እረኛና የገበሬ ጦረኞችን የሆናችሁትን አስነስቶ ግዙፉንና እግዚአብሔር የለሹን የደርግ ከሃዲ ሠራዊት ቀጣው። እሱ ትምህርት ሊሆናችሁ ሲገባ በተራችሁ ጠገባችሁ፣ ጎረራችሁ፣ በምድር ላይ ማን ይችለናል አላችሁ። ያዙኝ ልቀቁኝ አላችሁ። ወበራችሁ። ረከሳችሁ። ትዕቢታችሁ ጣሪያ ነካ። እግዚአብሔር አያችሁ፣ ተመለከታችሁ። እንዳስነሣችሁ ሊያስቀምጣችሁም ፈለገ።
•••
ትናንት ፉከራችሁን፣ ቀረርቶአችሁን ሁሉ ውኃ በላው ዛሬስ የተለየ ይሆናል ብላችሁ ነው?
 
ቄሮን እያስጮኸ ብዙ ለመናችሁ። እምቢ ስትሉ ፋኖን አስነስቶ ውቃቢያችሁን፣ ቆሌያችሁን ገፈፈው። እንዴት መቀሌ እንደተደበቃችሁ ሳታውቁት ራሳችሁን መቀሌ አገኛችሁት። ፉከራችሁ፣ ቀረርቶአችሁን ሁሉ ውኃ በላው። እናም ከዚህ መማር ሲገባችሁ አሁንም ትፎክራላችሁ። እንዴት ሰው ከእናቱ ጋር ጦር ልግጠም ይላል? ይሄ እብደት ነው።
•••
መብራት ከኢትዮጵያ እየሄደልህ፣ እህል ከዐማራ እየተጫነልህ፣ ስልኩ፣ ኢንተርኔቱ ቋቱ አዲስ አበባ ሆኖ እንዴት ነው የተሰወረባችሁ? አውሮጵላን ከኢትዮጵያ፣ ወደብ የላችሁ። ከኤርትራ፣ ከዐማራ ተናክሳችሁ። ከዐፋር ተቧቅሳችሁ እንዴት ትችሉታላችሁ? ለትግራይ ህዝብ ጠላት አታብዙበት። ምስኪኑን ህዝብ በእናንተ ነውርና ጥጋብ አታስፈጁት። ምክሬ ነው።
•••
ተረጋጉ “ከህወሓት ጋር ጠበኞች አይደለንም !” እያሏችሁ ነው
•••
” ግጭቱ ከመላው የህወሓት መዋቅር ጋር የተፈፀመም አይደለም። ይልቁንም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከሚፈልግ ህወሓት ውስጥ ከተሸሸገ ቡድን ጋር ነው። የመከላከያ ሠራዊቱ ደርሶበት የነበረውን ጥቃት በማካካስ አሁን ላይ የሕግ የበላይነትን የማስከበር ተግባር እና ቦታዎችን የመቆጣጠር ሥራዎችን በመሥራት ላይ ይገኛል። “
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ሴክሬታሪያት ኃላፊ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ለጋዜጠኞች ከሰጡት መግለጫ የተወሰደ። 
•••
ተረጋጉ ከህወሓት ጋር ጠበኞች አይደለንም እያሏችሁ ነው። ሁለቱም መግለጫ የሰጡት ህወሓት ኮትኩታ ያሳደገቻቸው የማደጎ ልጆቿ ናቸው –
 ደመአ እና ሬዲ !!
ይልቅ ይህችን ነገር በደንብ አንብቧት። በወለጋ ዐማራውን እያጸዱት ነው የሚመስለው። በመትረየስና በቦምብ ተረሽነው ወላጆቻቸውን ያጡ የዐማራ ህጻናት በረሃብ እያለቁ ነው ይላል የራሱ የዓማራ መገናኛ ብዙሃን።
•••
የዐማራ መገናኛ ብዙሃን በስልክ ያናገራቸውና ከጥቃቱ ያመለጡ አንድ አዛውንት “መከላከያ ደርሶላችኋል ወይ?” ተብለው ሲጠየቁ “መጣ የተባለውም የክልሉ ልዩ ኃይል ነው። ‘አዬ…እሱ ቀርቶ.… ‘እኛ አስከሬን በየጫካው እያፈላለግን ነው፣ እናቶቻቸው የተገደሉባቸው ህጻናት ከሦስት ቀን በላይ የሚቀምሱት አጥተው እየሞቱ ነው። እና እባካችሁ በህይወት እንዲተርፉ ቢያንስ ለህጻናቱ ምግብ ላኩላቸው። አጎራባች ቀበሌዎች በፍርሀት ገበያም ሱቅም ዘግተዋልና ልጆች በረሃብ እያለቁ ነው…” ሲሉ ተናግረዋል።
•••
እናም የዝሆኖቹን ጠብ ለዝሆኖቹ ተዉትና ይልቅ በኦሮሚያ እየጸዳ ላለው ዐማራ መላ ፈልጉለት። አይናችሁንም ከዚያ አታንሱ። እነ አቢቹ ህወሓትን ለራሳቸው ሲሉ ምንም አያደርጓትም። ያለበለዚያ ጠላት ነው የሚያጡት። የጦስ ዶሮ ማሳበቢያ ነው የሚያጡት። ጦርነቱ ከምር ከህወሓት ጋር ቢሆን መልካም ነበር። ግን አይደለም። ደጺን አገዙት አይደል ያለው አቢቹ። እንደዚያ ነው የሚሰማኝ።
•••
ትራንፕና ባይደንም እየተቦጣበጡ ነው። “ በአሜሪካም ይኸው ምርጫ እየተጭበረበረ ነው ለሚሉ አምባ ገነን ገዢዎችም ትምህርት የሚሰጥ ተግባር ከአሜሪካ እየኮመኮምን ነው።” ሊፈሳፈሱ ይሆን እንዴ?
•••
ሚጢዬ ምክር ቢጤም አለችኝ። 
•••
የዓባይ ሚዲያ ጋዜጠኞቹ እነ መዓዛ መሐመድ እና ብርሃኑ ተክለ ያሬድ ከነ ሙሉ ቲሙ። ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ፣ መምህርት መስከረም አበራና አስቴር በዳኔ። እንዲሁም የኢሳቱ የአዲስ አበባ ጋዜጠኛ ጎበዜ ሲሳይ ከፈጣሪ ጋር ራሳችሁን ብትጠብቁ። ሙያችሁን ተዉት ማለቴ አይደለም። የቆሰለ ነብር አደገኛ ነው ብዬ ነው። ብልጽግና በደንፉ እስኪያስራችሁ ድረስ በሌላ እንዳይተናኮላችሁ በጊዜ ወደ ቤታችሁ ለመግባትም ሞክሩ። አታምሹ። አሁን አቢቹ ነፍሴ ጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያምን የሚያስንቅበት ጊዜ እየመጣ ስለሆነ ትንሽ ራሳችሁን ጠብቁ።
ወንድማዊ ምክሬ ነው። 
• ኢትዮጵያ ግን ታሸንፋለች፣ ትነሣለችም። ይኸው ነው። የኢትዮጵያ እናቶች ሆይ !! እግዚአብሔር ይሁናችሁ። የኃዘን ዳርቻ ያድርግላችሁ። ምህረቱንም ያቅርብልን። የሞቱትን ነፍስ ይማርልን።
•••
¶ ድልና ትንሣኤ ለኢትዮጵያ ሀገሬና ለተዋሕዶ ሃይማኖታችን ! ውድቀትና ጥፋት፤ ለሁለቱም ጠላቶች። አራት ነጥብ።
• ይህንንም ራሴው በእጄ ጻፍኩት። +49 1521 5070996 ደግሞ የቴሌግራም፣ የቫይበር፣ የኢሞና የኋትስአፕ መልእክቶችን የምቀበልበት የእጅ ስልኬ ነው።
• ኢትዮጵያ ግን ታሸንፋለች፣ ትነሣለችም። ይኸው ነው።
• ደኅና እደሩልኝ  !!
•••
ሻሎም !   ሰላም !
ጥቅምት 25/2013 ዓም
ከራየን ወንዝ ማዶ።
Filed in: Amharic