>

ጦርነቱ ከየት ወዴት . ..??? (ሰይፉ ታሪኩ)

ጦርነቱ ከየት ወዴት . ..???

ሰይፉ ታሪኩ


በሀገራችን እዚህና እዚያ የሚስተዋለው የንጹሐን ግድያና መፈናቀል ብሔራዊ ደህንነታችን የገባበትን አጣብቂኝ በጉልህ ከማሳየቱ ባልተናነሰ በትግራይ በኩል ሰሞኑን በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተቃጣውን ጥቃት ተከትሎ የፌዴራል መንግሥት በወሰደው አጸፋ ክልሉ ለሚቀጥሉት 6 ወራት በኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር መወሰኑ መጪውን ጊዜ በአስፈሪ ድባብ ውስጥ የሚጠብቁ ቀላል አይደለም፡፡ በተለይም በማዕከላዊ መንግሥቱና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ያለው አለመግባባት በሂደት አዳዲስ ቅርጽና ይዘት እየተላበሰ መሄዱ አዳዲስ ውጤቶች ማስከተሉ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት የከተቱ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሳይቀሩ ሁለቱ ኃይሎች ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ ከማሳሰብ አልቦዘኑም፡፡ በዚህም እንደ ዓለም አቀፉ የቀውስ ቡድን(Crisis Group) ያሉ ተቋማት መግለጫ እስከማውጣት ደርሰዋል፡፡ የኤርትራ መንግሥት ደግሞ ከሣምንት በፊት በይፋ ባወጣው መግለጫ የትግራይን ጉዳይ አጽንዖት በመስጠት ህወሓትን አብዝቶ ተችቷል፡፡ ከሰሞኑን ደግሞ የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ የመጪውን ጊዜ አስፈሪነት ሳይኳኩሉ ቢያስቀምጡም በሰሜን ዕዝ ላይ ቀድመው በከፈቱት ተኩስ ምክንያት ውጤቱ ሌላ ሲኾን እየተመለከትን ነው፡፡ በቅደም ተከተል እንመልከታቸው፡-

የክራይሲስ ግሩፕ መግለጫ

ፖለቲካዊ አለመግባባቶችን አስመልክቶ ሊፈጠሩ በሚችሉ ቀውሶች ዙሪያ ዓለም አቀፋዊ ትንበያና መግለጫዎችን ይፋ በማድረግ የሚታወቀው “ክራይሲስ ግሩፕ” ሰሞኑን አንድ ዘገባ አውጥቷል፡፡ በዚህም የትግራይ ክልልና የፌዴራል መንግሥቱ ውጥረት እየሰፋ መሄዱን ተከትሎ “መንግሥታቱ ቅድመ ሁኔታዎችን አለዝበው መደራደር አለባቸው” ሲል ጠንካራ ማሳሰቢያ ሰንዝሯል፡፡ ዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ በዚህ መግለጫው በትግራይ ክልል እና በፌደራል መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት አይሎ ወደ ግጭት ሊሸጋገር ይችላል ሲጋቱን ገልጹዋል፡፡ ቡድኑ በሁለቱ አካላት መካከል ያለው አለመግባባት ተባብሶ ወዳልተፈለገ ደረጃ ከመድረሱ በፊት መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን አማራጮችም ሰንዝሯል። በመፍትሔ ሐሳብነት በዋነኛነት የተቀመጠው የፌደራል መንግሥትም ሆነ የትግራይ ክልል መንግሥት ያስቀመጧቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አለዝበው ለድርድር መቅረብ እንዳለባቸው ነው። ክራይሲስ ግሩፕ የፌደራል መንግሥት በሚቀጥለው ሳምንት ለክልሎች በጀት ማከፋፈል የሚጀመርበት ወቅት እንደሆነ ይጠቅሳል። ይሁን እንጂ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የበላይ አካል በጀት አልሰጥም ማለቱን በማስታወስ፤ ይህ በሁለቱ አካላት መካከል ያለውን ውጥረት ከፍ ሊያደርገው እንደሚችል ይገልጻል። የፌደራል መንግሥት ለትግራይ ክልል የሚውለው በጀት እንደከዚህ ቀደሙ ለክልሉ በቀጥታ ሳይሆን በወረዳ እና በከተማ ደረጃ ላሉ የመንግሥት እርከኖች በጀቱ ይተላለፋል ማለቱ ይታወሳል። ሁለቱም አካላት ልዩነቶቻቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት ይኖርባቸዋል ይላል ክራይሲስ ግሩፕ።

የኤርትራ መንግሥት መግለጫ

ሌላኛው ከሰሞኑን አነጋጋሪ ኾኖ የሰነበተው ደግሞ የኤርትራ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያወጣው መግለጫ ነው፡፡ በኤርትራ የኢንፎርሜሽን ሚኒስቴር ”የአከባቢው ሰላምና ወዳጅነት ማደላደል” በሚል ርእስ ወጥቶ አዲስ አበባ በሚገኘው የኤርትራ ኤምባሲ በኦፊስያላዊ የፌስቡክ ገጽ የተለጠፈው የአቋም መግለጫ የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያ ውስጥ እየመጣ ካለው ለውጥ ተቋዳሽ እንዳይሆን የወያኔ ቡድን እንዳፈነው ያትታል። የአቋም መግለጫው ‘”Game-over! ተብሎ የወደቀ የወያነ ቡድን ፣ ‘’ሞኝ ገበጣው እስከሚያልቅ ይጫወታል’’ እንደሚባለው የትግራይ ክልል አዲሱ ክስተት በፈጠረው በአከባቢው እየታየ ያለውን እድገትና ለውጥ ተቋዳሽ እንዳትሆን በንዴት ጨዋታ ውስጥ ገብቶ አፍኖ በመያዝ በደሎች እየፈጸመ መቆየቱን የሚታይ ነው። ይህ የጣዕረ-ሞት ቁዘማ ግን የታሪክ እሽክርክሪት ወደኋላ ሊመልስ እንደማይችል ግልፅ ነው” ሲል ይጨምራል። አሁን ያለውን ሁኔታ፣ በያዘው ቀና አቅጣጫ እንዲጓዝ፣ የአከባቢያችን ህዝቦች ራእይና ፍላጎት እንዲሰምር፣ የተጀመረውን ሰላማዊ ዝምድና ማጠናከርና ማሳደግ የሁሉም የአከባቢያችን መንግስታት ተልእኮ ነው። ሀቀኛ የአከባቢው ህዝቦቻችን ፍላጎት እንዲሳካ እና ዋስትና እንዲኖረው፣ የጋራ ጥረትና ዘዴ፣ የወደቀ የፖለቲካ ትራፊ እየጠረግን፣ አከባቢው ከግጭነትና ጠባጫሪነት፣ ወደ ሰላምና መተጋገዝ ለመቀየር በከፍተኛ መተባበርና ትጋት መስራት ይጠበቅብናል።” ሲል ህወሓትን በጽኑ ኮንኗል፡፡

የዶ/ር ደብረጽዮን ጋዜጣዊ መግለጫ

ከአንድ ወር በፊት የፌዴሬሽን ም/ቤት “ሕገወጥ” ባለው ምርጫ ተመርጠው “የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር” የኾኑት ዶክተር ደብረፂዮን ገ/ሚካኤል ሰሞኑን በትግርኛና አማርኛ ቋንቋዎች ሰፋ ያለ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ የጋዜጣዊ መግለጫቸው ሙሉ ትኩረት ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ከገቡበት ፍጥጫ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥትም የአንድን ሀገር ሉዓላዊነት ጥሶ በትግራይ ላይ ጦርነት ሊከፍት መኾኑን ጠቁመዋል፡፡ “ውጊያ ውስጥ ከገባን ፈልገን ሳይኾን ተገድደን ነው” ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ “የምናሰልፈው ልዩ ኃይልና ሚሊሻ ሳይኾን ሕዝብ በመኾኑ አሸናፊ እኛ ነን” ብለዋል፡፡ የመግለጫው የትኩረት ነጥብ ከኾኑት ጉዳዮች መካከል መቀሌ የሚገኘው የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝም ተጠቃሽ ነው፡፡ ዶ/ር ደብረጽዮን ሠራዊቱን አስመልክቶ የሰነዘሩት ሃሳብ አነጋጋሪ ነው፡፡ ሰሜን ዕዝ ከትግራይ ጋር ኾኖ መስዋዕት እንደሚከፍል አስረግጠው ገልጸዋል፡፡ በዕዙ ላይ የተደረገው የሰራዊት ዝውውርና አዲስ ስምሪት የሚደገፍበት ምንም ዐይነት ተጨባጭ ምክንያት ባለመኖሩ እንደማይቀበሉት ገልጸዋል፡፡ “አሃዳዊ” እና “አምባገነናዊ” የሚሉ ቃላትን ደጋግመው መጠቀምን በመግለጫቸው የመረጡት ርዕሰ መስተዳድሩ በመጪዎቹ ጊዜያት ጦርነት ለመኖሩ አብሪ ጥይቶች ማየታቸውን እርግጠኛ በመኾን ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ ለኹሉም የመከላከያ ሠራዊት ዕዞች የ”ተጠንቀቅ” ትዕዛዝ መተላለፉን በመግለጽም “ከሕግ ውጭ ሥልጣን ላይ ያለው አሃዳዊውና አምባገነናዊው ቡድን በትግራይ ህዝብ ላይ ሲፈፅመው የነበረውን ሴራ ወደ ኃይል እርምጃ በመሸጋገር ላይ ስለ ሆነ ሕብረተሰቡ ዝግጅቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል” ጥሪ እስከማቅረብ ደርሰዋል፡፡ “ትግራይን ለማንበርከክ የሚደረገው ርብርብ” በማዕከላዊ መንግሥቱና በኤርትራ መንግሥት ጣምራነት የሚካሄድ ነው የሚሉት ዶ/ር ደብረጽዮን ጦርነቱ የአህጉር፣ ከዚያም ሲያልፍ የዓለም ችግር በመኾኑ ዓለማቀፉ ማኅበረሰብ መላ እንዲፈልግ ለተለያዩ ሀገራት ጥሪ ማቅረባቸውን አንስተዋል፡፡ “ሕገመንግሥታዊነትና ሰላም ያለው ትግራይ ውስጥ ነው” ያሉት ዶ/ር ደብረጽዮን የሀገር መከላከያ ሠራዊት በምንም መልኩ የክልላችንን ሰላም የሚያደፈርስ ነገር ውስጥ መግባት የለበትም ሲሉ አሳስበዋል፡፡ ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ነው የሚያሻቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ሠራዊቱን ተጠቅሞ ለማንበርከክ የሚደረግ ማንኛውም ሙከራ አይሳካም ብለዋል፡፡

የፌዴራሉ መንግሥት አጸፋ

በያዝነው ዓመት ከመተከል አንስቶ እስከ ሰሞነኛው የምዕራብ ወለጋው የዜጎች ዘግናኝ ጭፍጨፋ ድረስ ማዕከላዊ መንግሥቱ በችግሮቹ ስፖንሰር አድራጊነት የሚከስሰው ኦነግ ሸኔንና ህወሓትን ነው፡፡ በተለይም ህወሓት በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚፈጸሙት ጭካኔ የተሞላባቸው ግድያዎችና መፈናቀሎች በየስፍራው በሚገኙ ጉዳይ አስፈጻሚዎቹ በኩል መሳርያና ሎጂስቲክ በማቅረብ ጥቃቶቹን እንደሚያስፈጽም ሰሞኑን በተለያየ የመንግሥት አካላት ከወጡት መግለጫዎች መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህም አልፎ ባሳለፍነው ማክሰኞ በተካሄደው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ አንዳንድ የም/ቤት አባላት ህወሓት በአሸባሪነት እንዲፈረጅ ከረር ያለ ጥያቄ ሲያሰሙ እንደነበር ተሰምቷል፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት ለሰሜን ዕዝ አዳዲስ የጦር መኮንኖች በኃላፊነት መሾማቸውን ተከትሎ “ሹመቱ ተፈጻሚ አይኾንም” ያለው የትግራይ ክልል መቀሌ የሚገኘውን የሠራዊቱን ካምፕ ስለማገቱ ተነግሯል፡፡ የመከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም የክልሉ መንግሥት እየነዛቸው በሚገኙ አፍራሽ ፕሮፓጋንዳዎች ላይ ማሳሰቢያ ሰጥቷል፡፡ እነኚህና ሌሎች አካሄዶች ሲዳመሩ የትግራይ ክልልና የመሪው ድርጅት ህወሓት ጉዳይ አዳዲስ ተላውጦዎችን በቀጣይ ይዞ እንደሚመጣ እየተጠበቀ ባለበት ሁኔታ ማክሰኞ ምሽት የትግራይ ልዩ ኃይል መቀሌ በሚገኘውን የመከላከያ ሠራዊት ላይ ተኩስ ከፍቷል፡፡ ይኽንን ተከትሎም በማዕከላዊ መንግሥቱ በተላለፈ የሃገርን ሉዓላዊነት የመታደግ ትዕዛዝ ክልሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ በፌዴራል ፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውሎ በኮማንድ ፖስት ሥር ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት እንዲተዳደር በሚኒስትሮች ም/ቤት ተወስኗል፡፡

ቀጣይ ሂደቶች ምን ውጤት ይኖራቸዋል? የሚለውን እንመለሳለን፡፡

Filed in: Amharic