>

ተጠያቂው ማነው? ፍትህ ለኢትዮጵያ!  (ያሬድ ሀይለማርያም)

ተጠያቂው ማነው? ፍትህ ለኢትዮጵያ!   

ያሬድ ሀይለማርያም

በአገሪቱ ውስጥ በግራም በቀኝም በሕዝብ ላይ ለሚፈጸሙ ጭፍጨፋዎች እና የአገር ሃብት ውድመቶች የመንግስት ባለሥልጣናት የሚሰጡዋቸው መግለጫዎች የጥቃቱን ያህል ሂሊናን የሚያቆስሉ ናቸው። የትላንቱን የወለጋው እልቂት ተከትሎ የጠቅላዩን የሃዘን መግለጫ ተከትሎ የክልሉ ፕሬዚደንት አቶ ሽመልስ አብዲሳም “በኦነግ ሸኔ እና በወያኔ የጥፋትና የሽብር ሴራ ኢትዮጵያ አትፈርስም” በሚል መልዕክት ሃዘናቸውን ገልጸዋል። አቶ ሽመልስ ሆይ፤ ኢትዮጵያ ከፈረሰችም የምትፈርሰው በወያኔ እና በኦነግ ሴራ ብቻ ሳይሆን በእርሶ እና በፓርቲዎት በብልጽግና እንዝህላልነት፣ ዳር ቆሞ ተመልካችነትም ነው።
በሃጫሉ ሞት ማግስት ሕዝብ ሲጨፈጨፍ እርሶ እና ያሰለጠኑት የክልል ጦር በሩን ዘግቶ ሲያንቀላፋ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በአሰቃቂ ሁኔታ በዘራቸው እና በኃይማኖታቸው ተለይተው ሲታረዱ እና ከተማ ሲነድ አደረ። እርሶና ባልንጀርዎችዎት፤ ጠቅላይ አቃቤ ሕጓን ጨምሮ ወደ አደባባይ ወጥታችሁ ይሄንኑ የተለመደ እዮዮ፤ የአዞ እንባ እያነቡ ከጥቃቱ ጀርባ ወያኔ እና ኦነግ ናቸው አላችሁን። ታዲያ ስንቶቹን የወያኔ እና የኦነግ አመራሮች በወንጀል ከሰሳችሁ? የወያኔ ባለሥልጣናት በእነዚህ ወንጀሎች ውስጥ እጃቸው ካለበት ለምን በሌሉበትስ አትከሷቸውም? ‘አዲስ አበባ የተቀመጠው የኦነግ አመራር ጫካ ካለው ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት አለው፤ ይሄንንም በማስረጃ አረጋግጫለሁ’ ብሎ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር መግለጫ ከሰጠ አመት አለፈው። ነገር ግን የአዲስ አበባው ኦነግ ዛሬም አዲስ አበባ ላይ ቁጭ ብሎ መንግስት ባመቻቸለት ቢሮ፣ ሹማምንቱም እንዲሁ በተመቻቸላቸው ምቹ ሁኔታ ተቀምጠው ሥራቸውን በሰላም እያከናወኑ ነው። ታዲያ ስለየትኛው ኦነግ ነው እየነገሩን ያሉት?
ዛሬም በወለጋ መከላከያ ሠራዊቱ የስጋት ቀጠና የሆነውን አካባቢ ለቆ እንዲወጣ ትዕዛዝ ሰጥታችሁ ስታበቁ ሕዝብ በነፍሰ በላው ኦነግ ሰራዊት ሲጨፈጨፉ ያንኑ የለመደባችሁን የውንጀላ እና ከአንገት በላይ ለቅሶ ይዛችው ወደ አደባባይ መውጣት እውነትም ማፈር ድሮ ቀረ ያስብላል።
መንግስት ዜጎቹን ከማንኛውም ጥቃት የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበትም የዛሬዎቹ ሹማምንት የገባችው አልመሰለኝም። ባለፉት ሁለት አመታት ከቡራዩ ጥቃት ጀምሮ ለተፈጸሙት ዘር ተኮር ጥቃቶች ሁሉ ወያኔን እና ኦነግን በመግለጫ ተጠያቂ በማድረግ ከኃላፊነት ነጻ ለመውጣት የምታደርጉት ጥረት ብዙ እርቀት ይዟችሁ የሚሄድ አይመስለኝም። እነዚህ ጥቃቶች እስካልቆሙ ድረስ ከኦነግ እና ከወያኔ እኩል ብልጽና ፓርቲ እንደ ድርጅቱ እና አመራሮቹም እንደየ ኃላፊነታችሁ ልክ እኩል ተጠያቂዎች ናችሁ።
ባለፉት ሁለት አመታት ለተፈጸሙት ዘር ተኮር ጥቃቶች ሁሉ ከወያኔ እና ከኦነግ እኩል፤
+ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ፣
+ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንትና አመራሮች
+ የአማራ ክልል ፕሬዚዳንድ እና አመራሮች
+ የቤኒሻንጉል ክልል ፕሬዚዳንድ እና አመራሮች
+ የመከላከያ ሹማምንት እና የፌደራል የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች
+ የኦሮሚያ ክልል የጸጥታ ዘርፍ ኃላፊዎች
ሁሉ ኃላፊነት መውሰድ እና ተጠያቂነትንም አለባቸው። በሕግም ተጠያቂዎች ናችሁ። በአገሪቱ ውስጥ በዜጎች ላይ ለሚፈጸሙ የመብት ጥሰቶች እና ጭፍጨፋዎች እነ እገሌ ናቸው እያሉ ጠአት እየጠነቆሉ ነጻ መውጣት አይቻልም። በሕግ ፊት ዜጎችን ጨፍጭፎ በሚገለው የኦነግ ሠራዊት እና ዜጎች ሲገደሉ እና ንብረታቸው ሲወድም የመከላከል ኃላፊነቱን ሳይወጣ ዳር ቆሞ በሚያይ የመንግስት አካል መካከል ልዩነቱ ጠባብ ነው። አንዱ ሕገ ወጥ ድርጊት በቀጥታ በመፈጸም፤ ሌላው በሕግ የተጣለበትን ዜጎችን ከጥቃት የመከላከል ኃላፊነቱን ባለመወጣት ተጠያቂዎች ናቸው።
ትልቁ ጥያቄ እነዚህ ባለሥልጣናት ማን እና የት ቦታ ነው በፍርድ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉት የሚለው ነው። ለዚህ መልሱ ቀላል ነው። ትላንት በወያኔ ዘመን እነ አቶ በረከት በአገር ላይ ተገልጾ የማያልቅ ጥፋት ሲያደርሱም ይሄ ጥያቄ ይነሳ ነበር። የህውሃት ጀንበር ስትጠልቅ ግን ጥያቄው መልስ አግኝቷል። እነ አቶ በረከት አሰልጥነውና ኮትኩተው ያሳደጓቸው ካድሬዎች፤ የዛሬዎቹ አገር መሪዎች ከአለቆቻቸው የተማሩ አይመስለኝም። የብልጽግና ጀንበር ሳትወጣ ልትጠልቅ ይመስላል። ዛሬ ባትጠየቁ ነገ ለፍርድ እንደምትቀርቡ ቅንጣት ታክል አልጠራጠርም።
ፍትህ ለኢትዮጵያ!
Filed in: Amharic