>
5:13 pm - Wednesday April 20, 9960

የተፈጥሮ አደጋና  አደጋውን ለመቆጣጠር ኢትዮጵያ የምትወስደው እርምጃ ( ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

የተፈጥሮ አደጋና  አደጋውን ለመቆጣጠር ኢትዮጵያ የምትወስደው እርምጃ

                                      

ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)


በኢትዮጵያ የተፈጥሮ ቁጣን ለመቀነስ ወይም ለመቆጣጠር ስራ ከተጀመረ ከአስራ አምስት አመት በላይ አለፈው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የተፈጥሮ ቁጣን ለመቀነስ አልሆነልንም፡፡ ነገሩ ‹‹ አድሮ ቃሪያ ›. ወይም ‹‹ ከርሞ ጥጃ ›› የተሰኘውን የአባቶች ብሂል ያስታውሰናል፡፡ አባቶቻችን ያለምክንያት አልነበረም ፡፡ ምንም የህይወት ለውጥ ማምጣት የተሳነው ግለሰብ ሲያጋጥማቸው የተጠቀሰውን አባባል ይጠቀማሉ፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ በኢትዮጵያ ልክ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተከሰተ የተፈጥሮ ቁጣ አይነት አንድ የተፈጥሮ ቁጣ  ደግሞ ደጋግሞ ይከሰታል፡፡ ኢትዮጵያን በየጊዜው እያሰለሰ ተመሳሳይ የተፈጥሮ አደጋ ያደባያታል፡፡በጣም አስገራሚው  መራሩ ሁነት ግን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት የሚለው መንግስታዊ ተቋም ሁልግዜ መኖሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ከብዙ አመታት በፊት ወይም ከጥቂት አመት በፊት ከተከሰቱት የፖለቲካ ውድቀታችን መማር እንዳልቻልን ሁሉ፣ ከደረሰብን የተፈጥሮ ቁጣ መአት መማር አልቻልንም፡፡ ሳዝናል፡፡ እውን ኢትዮጵያውያን ከአመታት በፊት የተፈጸሙ ሁነቶችን የማስታወስ ብቃት የላቸውንም በፍጹም በፍጹም ሀሰት ነው፡፡ Do Ethiopians have short memories? Absolutely not በእኔ አስተያየት በመንግስት ስልጣን ላይ የተቀመጡ አንዳንድ ሹመኞች ከእነርሱ በፊት በስልጣን ማማ ላይ የተቀመጡ ሹመኞች ከጥቂት አመታት በፊት የሰሩትን ስህተት በመርሳት እነርሱ ደግመው ደጋግመው ስህተት ሲሰሩ ይሰተዋላል፡፡ ከዚህ ባሻግር በሃብት ማማ ላይ የተቀመጡ በርካቶች ትላንትን የሚዘነጉ ናቸው፡፡ እነማን እንደነበሩ ማስተወስ አይፈልጉም፡፡ ከትቢያ ተነስተው ሳይሰሩ፣ ሳይደክሙ አዱኛ ቤታቸው የገባችላቸው የከንቱ ከንቱዎች፣ትላንት ምን እንደነበሩ በፍጹም ማስታወስ አይፈልጉም፡፡ ወይም የማስታወስ ችሎታ የላቸውም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ተራ ዜጎች ኑሮአቸው የተናጋ ነው፡፡ የሚወዱትን ወዳጅ ያጡም ናቸው፡፡ እነርሱ የቅንጦት ኑሮ ለመኖር አልታደሉም፡፡ ስለሆነም ትላንትን በፍጹም የሚዘነጉ አይደሉም፡፡ የደረሰባቸውን ጉዳት በአይምሮአቸው ያሰላስላሉ፡፡ ነገም ተስፋ ይዞላቸው እንደሚመጣ የሚያውቁት ነገር የለም፡፡ ባለስልጣኖችም ሆነ ባለወረቶች በተፈጥሮ ቁጣ ምክንያት በሚከሰቱ ጉዳቶች ለአብነት ያህል ችጋር ወይም የኑሮ ውድነት ወዘተ የሚደርስባቸው ጉዳት ወይም የህይወት መናጋት ዝቅተኛ ነው፡፡ ስለሆነም አውቀውም ይሁን ሳያውቁት ያ የመከራ አመት ካለፈ ከጥቂት አመት በኋላ ይረሱታል፡፡ ወይም ይዘነጉታል፡፡ እነርሱን በተለየ ሁኔታ ፣ በግል ደረጃ የነበረው ጠኔ ወይም ችግር ስላልደቆሳቸው በአይምሮአቸው ማስታወስ አይፈልጉም፡፡ ለአብነት ያህል በ1977 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ድርቅና ጠኔ ተከስቶ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ የሰሜን ኢትዮጵያ ገበሬዎችን እንደ ቅጠል ባረገፈበት በዚያ ክፉ ግዜ በኑሮ የተደቆሰው ተራው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ነበር፡፡ በማናቸውም ግዜ የተፈጥሮ አደጋ ወይም የእህል እጥረት ሲከሰት በይበልጥ ተጎጂው ተራው ዜጋ ነው፡፡ የኮቪዲ ቫይረስ በሽታ ተከሰተ ከተባለ ወዲህ በኢትዮጵያ ምድር እነማን መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እንደተቸገሩ ማስተዋሉ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ .”Shoe-nail pinches the wearer

በተፈጥሮ አደጋ የተደቆሱ ዜጎች የገፈቱ ቀማሽ ስለሆኑ የተከሰተውን መራር ሁነት አይረሱትም፣ ሁል ግዜ በአይምሮአቸው ቀርጸው ያስቀምጡታል ፡፡ የጠፈጥሮ አደጋው እንዴት እንደተከሰተ፣ ቀኑን፣ ሰአቱን፣ ድርቁ በየትኛው አመተምህረት እንደተከሰተ፣ የአንበጣው ወረራ መቼ እንደተከሰተ፣የጎርፍ አደጋው በየትኛው አመት  እንደተከሰተ በታላቅ ሀዘን ያስታውሱታል፡፡ ለአብነት ያህል የዛሬ ስልሳ አመት በአንበጣ ወረራ የተጠቃ፣ ወይም የዛሬ ስልሳ አመት በጎርፍ አደጋ የቅርብ ወዳጆቹን ያጣ ግለሰብ የዛ መጥፎ ትዝታ እድሜ ልኩን በአይምሮው ጓዳ ይደውልበታል፡፡ በምንም አይነት አይዘነጋውም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ1956 ዓ.ም. በትግራይ ድርቅና ጠኔ ያጠቃቸውን ኢትዮጵያዊ ዜጎችን በአይናቸው በብረቱ ስለተመለከቱ የዛ መጥፎ ትዝታ እስከ ህይወታቸው ፍጻሜ ከአይምሮ ጓዳቸው እንዳልጠፋ ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ዶክተር ዮሃንስ አበራ  የተባሉ የጂኦግራፊ ተመራማሪ በአንድ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ እንደጠቆሙት የዛሬ ስልሳ አመት በአደጉበት መንደር የአንበጣ መንጋ ያደረሰውን አስከፊ ጉዳት ዛሬም ያስታውሱታል፡፡ ‹‹ ጸሊም በርበር›› በተባለች መንደር የአንበጣ መንጋ ተከስቶ እጅግ በጣም የምወደውን ዛፍ በአንድ ለሊት የአንበጣው መንጋ አወደመው፡፡ ክስተቱ በጣም አስፈሪ ነበር፡፡ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1973  ደግሞ በቆቦ በርካታ ህይወት በድርቅና ጠኔ ምክንያት እንደ ቅጠል ረግፎ ተመልክቻለሁ፡፡ ያ የተፈጥሮ ቁጣ አሁን ድረስ ከአይምሮዬ አልጠፋም ሲሉ ነበር መራሩን እውነት ያስታወሱት፡፡

በነገራችን ላይ ተራ ዜጎችና የተፈጥሮ አደጋው ግንባር ቀደም ገፈት ቀማሽ የነበሩት ዜጎች በአንድ ወቅት የተከሰተውን የተፈጥሮ አደጋ ያስታውሱታል፡፡ የደረሰባቸውን ችግር አይዘነጉትም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የሚያመጡት ፋይዳ የለም፡፡ ምክንያቱም እነርሱ የችግሩ ገፈት ቀማሽ እንጂ የመፍትሔው አካል አይደሉም፡፡  ምናልባት ካለፈው ፣ ካጋጠማቸው የተፈጥሮ አደጋ ልምዳቸው በመነሳት የተፈጥሮ አደጋን ለመከላከል የሚያስችል መፍትሔ ሊያመነጩ ይቻላቸዋል፡፡ ሆኖም ግን ዘዴው ወይም መሳሪያው የላቸውም፡፡ በችግር ምክንያት ያገኙት ልምድ ብቻውን የትም አላደረሳቸውም፡፡ የተፈጥሮ አደጋን  ለመከላከል ወይም ለመቀነስ ዘዴው፣ አቅሙና መሳሪያው የሚገኘው በመንግስት ተቋማት ወይም በሌሎች መንግስታዊ  ባልሆኑ ተቋማትና በአለም አቀፍ ተቋማት ተቀጥረው በሚሰሩ ባለሙያዎች ዘንድ ነው፡፡ በእነኚህ በተጠቀሱት ተቋማት የሚሰሩ በርካታ የሥራ ሃላፊዎችና ሰራተኞች ግን ዳተኝነት ይታይባቸዋል፡፡ በብዙ የአለም ክፍሎች የተፈጥሮ አደጋ መከሰቱ ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ ከእኛ ሀገር በብዙ መልኩ በሰፋ ሁኔታ ብዙ ሀገራት በተፈጥሮ አደጋ መደቆሳቸው ተፈጥሮአዊ ነው፡፡ በተለይ በሰለጠነው አለም የሚከሰተው አውሎ ነፋስ ወይም ከባድ ጎርፍ አስከፊ ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በተለይ በሰው ህይወት ላይ የሚያደርሰውን ከባድ መቀሰፍት በብዙ መልኩ መከላከል ይችላሉ፡፡ በአጭሩ የተፈጥሮ አደጋውን አስከፊ ቅስፈት ከመፍጠሩ በፊት መከላከል ይችላሉ፡፡ የተፈጥሮ አደጋን አስከፊ የህይወትና ንብረት እንዳያስከትል መከላከል ምክንያታዊና በብዙ ሀገራት ተሞክሮ ውጤት ያመጣ ነው፡፡ አጠቃላይ ማህበረሰቡ ዝምታን ካልመረጠ በቀር የተፈጥሮ አደጋ የከፋ ጉዳት በሰው ልጆች ላይ ማድረስ አይቻለውም፡፡ ለአብነት ያህል ድርቅ፣ የቁጥቋጦ እና ደን ቃጠሎ በአውስትራሊያ እና በተባበረችው አሜሪካ፣ ጎርፍ በአውሮፓ ምድር የተፈጥሮ አደጋዎች ናቸው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በተጠቀሱት የምእራብ ሀገራት የተፈጥሮ አደጋ የተፈጥሮ መቀሰፍት መሆን አይቻለውም፡፡ በኢትዮጵያ ግን የተፈጥሮ አደጋ መቀሰፍትን ይዞ ነው የሚመጣው፡፡ በሰለጠነው አለም የሚገኙ መንግስታት ህብረተሰቡን በማሳተፍና እራሳቸውም ጣልቃ በመግባት ከተፈጥሮ አደጋ ጋር ግብግብ በመግጠም የተፈጥሮ አደጋ መቀሰፍትን እንዳያመጣ መከላከል ችለዋል፡፡ ለአብነት ያህል የምጽአት ቀን የሚመስል ከባድ አውሎ ነፋስ ከተሞቻቸውን ሲመታ፣ ወጀቡ እስኪያልፍ አብዛኛው ህዝባቸውን የሚደብቁበት መከላከያ ስላበጁ በሰው ህይወት ላይ የሚደርሱ ጉዳቶችን በእጅጉ ቀንሰውታል፡፡ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው የኤሌክትሪክ ሽቦዎችና መስመሮች፣ በአጠቃላይ የአገልግሎት መስጫ ድርጅቶች በአጭር ግዜ ውስጥ ተጠግነው ወደ ቀደመው አገልግሎታቸው ይመለሳሉ፡፡ እነርሱ ሁል ግዜ ሃያ አራት ሰአት ዝግጁ ናቸው፡፡ ተኝተው አያድሩም፡፡ በሰለጠነው አለም ‹‹ መከላከል ከማከም ›› ይሻላል የሚል መርህ አለ፡፡ (The magic rule here is “Prevention is better than cure) የተፈጥሮ አደጋ ወደ ተፈጥሮ መቅሰፍት እንዳይቀየር ከተፈለገ ሳይንሳዊ ቅድመ ትንበያ ግድ ይላል፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ከመከሰቱ በፊት የሚመለከተው ተቋም ቅድመ ማስጠንቀቂያ ለህብረተሰቡ ማስተላለፍ ግድ ይለዋል፡፡ የሰለጠነው አለም ከባድ ጎርፍ፣ አውሎ ነፋስ፣ የመሬት መንቀጥቀጥ ሳይቀር በአንድ ህዝብ በሚበዛበት ስፍራ ከመከሰቱ በፊት ቅድመ ትንበያ ስለሚሰጥ የተፈጥሮ መቅሰፍትን መከላከል ወይም በእጅጉ መቀነስ ችለዋል፡፡ ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ወይም ከሌላ የውሃ አካል የሚሳውን አውሎ ነፋስና ከባድ ዝናብ ዝም ብለው ቁጭ ብለው አይጠብቁትም፡፡ ተዘጋጅተው አስበውበት ስለሚጠበቁ ያ አስፈሪ የተፈጥሮ አደጋ ወይም ቁጣ ከባድ የህይወት ፍጅት በእጅጉ ይቀንሱታል፡፡ ባሳለፍነው በሱዳን ካርቱም እና በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረውን የጎርፍ አደጋ ያስከተለውን የተፈጥሮ መቅሰፍት ማስተዋሉ እኛና የሰለጠነው አለም ምን ያህል ሰፊ ልዩነት እንዳለን መረዳት ያስችለናል፡፡ ( የተፈጥሮ አደጋን ከመከላከል ያለንን የብቃት ደረጃ ማለቴ ነው) እጅግ በብዙ እጥፍ ከእኛ ሀገር በበለጠ ግዝፈት በተፈጥሮ አደጋ የሚደቆሰው የምእራቡ አለም፣ ከእኛ በብዙ እርቀትና በላቀ ደረጃ የተፈጥሮ አደጋ የሚያስከትለውን መቅሰፍት መከላከል የመቻላቸው ሚስጥር ሲስተዋል አስደናቂ ነው፡፡ እኛም በብዙ መልኩ ወደኋላ የቀረን ስለመሆኑ ማሳያም ነው፡፡

በኢትዮጵያ ባልተጻፈ ህግ መሰረት ማከም ወይም አደጋ ከደረሰ በኋላ ለአደጋ የተጋለጡትን ግፉአን መልሶ ለማቋቋም እንደ ደንብ ይቆጠራል፡፡ In Ethiopia the tacitly agreed rule seems to be “cure is better than prevention

በኢትዮጵያ ጤና ጥበቃ ሚንስትር የቆየ ፖሊሲ መሰረት ደግሞ ‹‹ ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ ›› የሚለው መርህ ተቀባይነትን ያገኘ ነው፡፡ ከዚህ የምንረዳው ቁምነገር ቢኖር ቅድሚያ የሚሰጠው በሽታን ለመከላከል ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ቀላሉን ወይም ርካሹን ዘዴ ለመምረጥ አይደለም፡፡ መከላከል ከማከም በብዙ መልኩ ከፍተኛ  መዋለንዋይ እና ጥረትን ይጠይቃል፡፡ መከላከል ከማከም ወይም ከማዳን የሚመረጥበት ምክንያት፣ አንድ ሰው ክፉኛ ታሞ ድንገት ቢድን እንኳን ቋሚ የጤና ችግር ሊያጋጥመው ይችላል ከሚለው ሳይንሳዊ እሳቤ ይመስለናል ፡፡ ለአብነት ያህል የስኳር በሽታ  ወይም የልብ ጤና ችግር ያለባቸውን ሰዎች ማንሳት ይቻላል፡፡ በተፈጥሮ አማካኝነት ከቤተሰብ ከሚወርሱት ከሚሊዮኖች ጥቂቶች በቀር የተጠቀሱትን በሽታዎች መከላከል እንደሚቻል ሃኪሞች ይመክራሉ፡፡ የአመጋገብ ዘዴአችንን ጤናማ ከሆነ፣ በየቀኑ ለተወሰኑ ደቂቃዎች አካላዊ እንቅስቃሴ ወዘተ ካደረግን እዳው ገብስ ይሆናል፡፡ ይህን ማድረግ ከተሳነን እድሜ ልካችንን ከመድሃኒት ጋር መኖር ውዴታ ሳይሆን የህልውና ጉዳይ ይሆናል፡፡ ስለሆነም ቅደመ ጥንቃቄ ካለማድረግ የተነሳ በርካታ ሰዎች የስኳር በሽታ ታማሚ ከሆኑ በኋላ እድሜ ልካቸውን ከስኳር ጋር ይኖራሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ  አንድ ሰው የቀዶ ጥገና ከተደረገለት በኋላ ከበሽታው ፈውስ አገኘ ቢባልም ሌሎች የጤና ጠንቆች ያጋጥሙታል፡፡ አንድ የጤና ችግር ከተቃለለ በኋላ ሌላ የከፋ የጤና ችግር ሊከሰት ይቻለዋል፡፡ በመድሃኒት ውስጥ ያሉ ኬሚካሎች በሰውነታችን ውስጥ ካለው ተፈጥሮአዊ ኬሚስትሪ ጋር ሲዋሃዱ የሚያመጡት ጣጣ እና ዳፋ በርካታ ነው፡፡ መድሃኒቶች ጠቀሜታቸው አሌ ባይባልም የጎንዮሽ ጉዳታቸው ደግሞ መዘንጋት የለበትም፡፡ ስለሆነም የተፈጥሮ አደጋ ተከስቶ የከፋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ፣ እንዲሁም የተፈጥሮ መናጋት ከማስከተሉ በፊት ቅድመ ዝግጅት ማድረጉ አማራጭ የለውም፡፡ ለአብነት ያህል የአንበጣ መንጋን መከሰት ማስቀረት ባይቻልም የአንበጣው መንጋ በበረሃማ አካባቢዎች ተፈልፍሎ ወደ ደጋና ወይና ደጋ ወይም የቆላ አየር ንብረት ያለባቸው አካባቢዎች ደርሶ ተክሎችን ከማዳበየቱ በፊት ብርቱ የመከላከል እርምጃ መወሰድ አለበት፡፡ የገበሬውን እህል ሙልጭ አድርጎ ካጠፋው በኋላ ለገበሬው የእርዳታ እህል ማቅረቡ ገበሬውን ከሞት ይታደገው እንጂ ዘለቄታዊ መፍትሔ ለማምጣት አይቻለውም፡፡ ስለሆነም የተፈጥሮ አደጋ ተከስቶ መቅሰፍትን ከማስከተሉ በፊት የመከላከያ እርምጃ መውሰዱ ለማህበረሰቡም ሆነ ለተፈጥሮ አካባቢዎች ጤናማ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ በእያንዳንዱ የገበሬ ቤት በቂ የገንዘብ አቅምና የእህል ክምችት ከሌለ ድርቅ በሚከሰትበት ጊዜ፣ የአንበጣ መንጋ አካባቢውን ሲወር፣ የሚከተሉት ችግሮች መከሰታቸው አይቀሬ ነው፡

  • ችጋር እና ጠኔ ይከሰታል
  •  ተክሎች ይደርቃሉ፣ አፈሩ ይሸረሸራል፡፡
  • የአካባቢው የውሃ ቦታዎች(ውሃ ጠገብ ስፍራዎች ) ይደርቃሉ
  • ከፍተኛ የጤና ቀውስ ይከሰታል
  • በመጨረሻም የሰው ህይወት እና እንሰሳት ይቀጠፋሉ

 ድርቅ የአለም አየር እንቅስቃሴ አንዱ አካል ስለሆነ መከላከል አይቻልም፡፡ Drought cannot be prevented. It is an integral part of the natural global air circulation.) ስለሆነም የሚያዋጣው ድርቅ የሚያመጣውን መዘዝ ለመከላከል መሞከር ነው፡፡ በአንድ ሀገር ድርቅ ተከስቶ መቀሰፍትን እንዳያመጣ ከተፈለገ የሚከተሉት ቁምነገሮች በሀገሬው መንግስት መሰራት እንዳለባቸው የመልክአምድር አጥኚዎች የሚከተሉትን ምክረ ሃሳባቸውን ያቀርባሉ፡፡

  • ድርቅ በሚያጠቃቸው የውሃ ማቆር ተግባራትን በሰፊው ማከናወን፡፡
  • የተፈጥሮ ሀብት እንክብካቤና የውሃ ብክነትን መከላከል ( ውሃን ደግሞ ደጋግሞ ጥቅም ላይ ማዋል)
  • ድርቅን መቋቋም የሚችሉ ሰብሎችን በስፋት ማልማት
  • ከእርሻ ስራ ውጪ ሌሎች የሥራ አይነቶችን ማስፋፋት ( ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋት )

ለአብነት ያህል በደረቅ የአየር ንብረት ውስጥ እየኖሩ የተሻለ ኑሮ ለመምራት የቻሉት የሰለጠኑት ሀገራት ተፈጥሮን ለመግራትና የተፈጥሮ ቁጣን ለመቀነስ ስለቻሉ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ጎርፍ፣የአንበጣ መንጋና እምቦጭ የመሳሰሉ የተፈጥሮ አደጋዎችን ከመከሰታቸው በፊት መከላከል እንደሚቻል ባለሙያዎች ምክረ ሃሳብ ያቀርባሉ፡፡ ለአብነት ያህል የበርሃ አንበጣ  ወደ አንበጣ መንጋ ከመቀየሩ በፊት መራቢያ አካባቢው መድረስ ከተቻለ መከላከል ይቻላል፡፡ ( አንበጣው የሚፈለፈልበትን አካባቢ በመለየጥ መቆጣጠር እንደሚቻል የመስኩ ተጠባቢዎች በየጊዜው የሚያስተምሩት ቁምነገር ነው፡፡ ሰሚ አድማጭ ጆሮ ያለው ሃላፊነቱን የሚያውቅና የሚፈጽ የመንግስት አካል ከተገኘ ማለቴ ነው፡፡ )ከዚህ ባሻግር በጣና ሃይቅ ላይ የእምቦጭ አረም ከመከሰቱ በፊት ወደ ሀይቁ የሚገቡ ማዳበሪያዎች፣ ኬሚካሎች፣ ፕላስቲክ ወዘተ ወዘተ እንዳይገቡ መከላከል ቢቻል ኖሮ  የጣናን ሃይቅ በእምቦጭ አረም እንዳይወረር መከላከል ይቻል ነበር፡፡ ከ15,000 ስኩዌር ኪሎሜትር ስፋት ባለው የጣና ሀይቅ ላይ ከአፍንጫቸው አርቀው የማያስቡ ባለወረቶች ከሆቴሎቻቸው የሚወጡ ቆሻሻዎችን እንዳይደፉ ጥብቅ ቁጥጥር ካልተደረገ፣ ከገበሬው የእርሻ መሬት ላይ ማዳባሪያ እየታጠበ ወደ ሃይቁ እንዳይገባ የደን ልማት ፕሮዤ በአካባቢው ካልተከናወነ ወዘተ ወዘተ ጸረ አረም ማሽን መኪና በመግዛት ወይም በአንድ ሰሞን ሆይሆይታ የጣናን ሃይቅ ከእምቦጭ አረም ለመታደግ ዘበት ነው፡፡ ወይም ከፕሮፓጋንዳ ጩሀት አያልፍም፡፡ የጣናን ሃይቅ ከእምቦጭ አረም በርካታ የዘመቻ ስራዎች የተከናወኑ ቢሆንም ውጤታማ አልሆኑም፡፡ የእምቦጭ አረም አድማሱን አሰፋ እንጂ አልቀነሰም፡፡ እንደው ለነገሩ ላለፉት አርባና ሃምሳ አመታት ውስጥ የተለያዩ ዘመቻዎች ቢደረጉም የሀገሪቱን ችግሮች መፍታት አልተቻለም፡፡ በባህርዳር ጣና ዙሪያ የተገነቡ የሰውን መንፈስ የሚያድሱ ሆቴሎችም ሆኑ መናፈሻዎች የቆሻሻ አወጋገድ ዘዴያቸው ህሊና በፈጠረባቸው ባለሙያዎች መፈተሸ አለበት፡፡ ከብዙ አመታት በፊት የጣናን ሃይቅ ተጎራብቶ የተሰራው የፈለገ ህይወት ሆስፒታል በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች የህክምና አገልግሎት የሚሰጥ የሕክምና ተቋም ቢሆንም    የቆሻሻ አወጋገድ ስልቱ ግን እጅግ ዘመናዊ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ  የአዋሽ ተፋሰስ አካባቢዎችን በዛፍ መሸፈን ቢቻል ኖሮ የአፋር አካባቢን ከከፍተኛ የጎርፍ አደጋ መታደግ ይቻልም ነበር የሚል የግል አስተያየት አለኝ፡፡ የአፋር አካባቢን በተክሎች መሸፈን ቢቻል የአካባቢውን ህብረተሰብ ከአስከፊ የጎርፍ አዳጋ መቅሰፍት መከላከል ይቻል ነበርም ብዬ አምናለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ባሳለፍነው ክረምት የአፋር አካባቢ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ በከፍተኛ ሁኔታ በጎርፍ የተጠቃው በእግዛብሔር ቁጣ አይደለም፡፡ የሰው ልጅ ስግብግብነት በአስከተለው መዘዝ የአካባቢው ደን ያለርህራሄ ስለተጨፈጨፈ እንጂ፡፡ ስለሆነም አካባቢው በከፍተኛ ደረጃ በጎርፍ አደጋ ከተጥለቀለቀ በኋላ ለተጎጂው ህዝብ የዕለት ደራሽ እርዳታ ( እህል፣ ብርድ ልብስ፣ ጊዜያዊ መጠለያ ወዘተ) ማቅረብ ለግዜው የሰውን ልጅ ህይወት ለመታደግ ይረዳ ይሆን እንጂ ብቻውን ትርጉም የለውም፡፡ ይህ የተፈጥሮ ቁጣ ካለፈ በኋላ የአካባቢው ህዝብ የኑሮ ደረጃ ሊሻሻል ቀርቶ በቀደሙት አመታት ከነበረው ኑሮው የበለጠ ያሽቆለቆለ ይሆናል፡፡

በኢትዮጵያ ስለሚከሰተው የተፈጥሮ አደጋ በተመለከተ ከህይወት ልምድ እና ከንባብ እውቀቱ በመነሳት ነገሮችን መመርመር እና ማሰላሰል ለሚችል ህሊና የፈጠረበት ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ምድር ላለፉት ሃምሳ (50) አመታት ተመሳሳይ ጥያቄዎች እንደሚቀርቡ፣ተመሳሳይ መልሶች እንደሚሰጡ መገንዘብ ይችላል፡፡ ለአብነት ያህል በ1965 ዓ.ም. ከተከሰተው አስከፊው ድርቅ በኋላ የድርቅ መንስኤና ውጤት አጥኚዎችና ሪፖርተሮች የመንግስት ሃላፊዎችን ድርቁ ከመከሰቱ በፊት ማስጠንቀቂያ ሰጥታችሁ ነበርን ብለው ላቀረቡት ጥያቄ በሰጡት መልስ አዎን ተናግረናል ሆኖም ንጉሱ ልደታቸውን ለማክበር ነበር ትኩረት የሰጡት ሲሉ ነበር የተደመጡት፡፡ በ1977 ዓ.ም. በተመሳሳይ መልኩ አስከፊ ድርቅ ሲከሰት ተመሳሳይ ጥያቄ ለእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን የሥራ ሃላፊዎች ቀርቦ በሰጡት መልስ ለመነግስት አሳውቀናል፡፡ ሆኖም ግን የጊዜው መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የነበረው 10ኛውን አብዮት በአል ለማክበር፣ ኢሰፓአኮን ለመመስረት እና የከለር ቴሌቪዥን ፕሮግራም በኢትዮጵያ ለማስጀመር ነበር፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮት ሲፈነዳ በኢትዮጵያ ምድር ድርቅና ጠኔን፣ ችጋርን ታሪክ እናደርገዋለን ተብሎ በብዙ መልኩ ተደስኩሮ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አስቂኙ እና መራሩ እውነት ግን 10ኛው የአብዮት በአል ሲከበር በኢትዮጵያ ምድር ችጋር ታሪክ መሆኑ ቀርቶ በገሃድ ይታይ ነበር፡፡ በእውነቱ ያማል፡፡ ያሳዝናል፡፡ የወታደራዊውን የደርግ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ትብብርና በውጪ ሃይሎች ድጋፍ ገርስሶ የጣለው የኢህአዲግ ድርቅና ጠኔን ለመከላከል አገዛዝ በርካታ ፖሊሲዎች ቢያዘጋጅም ተቋማት ቢያቋቁምም የተፈጥሮ አደጋዎች ወደ ተፈጥሮአዊ መቅሰፍት እንዳይቀየሩ ማድረግ አልተቻለውም፡፡ ከተግባራዊ እንቅስቃሴ ይልቅ ጩሀቶች ይበዛሉ፡፡ የመልክአ ምድር ተጠባቢው ዶክተር ዮሃንስ አበራ በእንግሊዝኛ ያቀረቡት የምርምር ጽሁፍ የበለጠ ገላጭ በመሆኑ እጠቅሰዋለሁ፡፡

For the last 50 years the same question is asked and the same answer given. After the horrors of the 1973 drought-induced famine reporters asked officials “Weren’t you warned about the hazard?” They answered “Yes, but…”; they were busy with the cakes. After the 1984 tragic famine reporters asked officials “Weren’t you warned about the hazard?” They answered “Yes, but…”; they were busy with 10th anniversary of the revolution, the formation of WPE, and the launching of colour TV. The irony is that the 1974 revolution was aimed at making famine history.  (Dr. Yohanness Aberra)

በነገራችን ላይ በኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋ የሚያስከትለውን ጉዳት ለመክላት ወይም ለመቀነስ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1975 ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አገዛዝ የነበረው ደርግ የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽንን ካቋቋመ በኋላ እንደተጀመረ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ይህ የመንግስት ተቋም ይንቀሳቀስ የነበረው በኮሚሽነር ሽመልስ አዱኛ እና በምእራባውያን ቸርነት ነበር፡፡ ኮሚሽር ሽመልስ በመላው አለም እየዞሩ እምባቸውን በማንባት ለተረጂ ወገኖቻችን እርዳታ ያሰባስቡ እንደነበር ታሪክ የሚዘነጋው አይመስለኝም፡፡ ከዚህ ባሻር ሌላው ኮሚሽር የነበሩት ሻለቃ ዳዊት በምእራቡ አለም እየዞሩ ድርቅ በኢትዮጵያ ውስጥ አስከፊ ጉዳት ከማድረሱ በፊት በማሳወቃቸው ታሪክ ስፍራውን የሚነሳቸው አይመስለኝም፡፡ የእርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽን በህይወት ለመኖርና ለመስራት የቻለው በምእራባውያን እርዳታ ነበር፡፡ ስለሆነም የተቋሙ ህልውና የተመሰረተው በለጋሽ ሀገሮች ቸርነት ላይ ነበር፡፡ ተቋሙ በኢትዮጵያውያን የሚረዳ አልነበረም፡፡ ለዚህም ነበር እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1984 የተከሰተው ድርቅና ጠኔ ያስከተለውን አሰቃቂ መቅሰፍት መቋቋም የተሳነው፡፡ የኢህአዲግ አገዛዝ በሽግግር መንግስቱ ዘመን የመጀመሪያውን የአደጋ መከላከል ፖሊሲ እንዳወጣ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ የምእራባውያን ፈጣን እርዳታ ታክሎበት በዘመነ ኢህአዲግ ቀደም ባሉት አገዛዞች የተከሰቱ የሰው እና እንሰሳት እልቂት አልተከሰተም፡፡ ድርቅና ችጋር ግን  በተወሰኑ አመታት ልዩነት ግን መከሰቱ አይቀሬ እውነት ሆኖ አሁን ድረስ ዘልቋል፡፡ ከዚህ ባሻግር በችጋር የሚሰቃየው ኢትዮጵያዊ ዜጋ በአስደንጋጭ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ የምእራባውያን እርዳታ ስለሚጎርፍ የህይወት መጥፋት ግን ቀንሷል፡፡ የችጋር አሳዛኝ ገጽታዎች አይታዩም፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ከተከሰተ በኋላ የሚወሰዱ እርምጃዎች እየተሻሻሉ የመጡ ይመስላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የምእራባውያን እርዳታ እንደ ግዴታ የተቆጠረ ይመስላል፡፡ የምእራባውያኑ አፋጣኝ እርዳታ ባይቀርብ ኖሮ የሚከተለውን ሰብአዊ ቀውስ ለመተንበይ አስቸጋሪ ነው፡፡ ሌላው የኢትዮጵያ የዘመናት ችግር ዛሬም አልተቀረፈም፡፡ ሁል ግዜ በእርዳታ ላይ መንጠልጠላችን አሳሳቢ ነው፡፡ የተፈጥሮ አደጋን ወይም ድርቅን ማስቀረት አዳጋች ቢሆንም የተፈጥሮ አደጋ ከተከሰተ በኋላ አስከፊ ጉዳት ሳያደርስ ለመከላከል የምንጠቀምበት ዘዴ ዛሬም ደካማ እና ወደኋላ የቀረ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ኢትዮጵያ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በ2013 የተፈጥሮ አደጋ የሚያደርሰውን መቅሰፍት ያስችላት ዘንድ የአደጋ መከላከል ፖሊሲ አውጥታ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የአደጋ መከላከል ዝግጁነት ኮሚሽን የተባለው ተቋም የተረጋጋ አይመስልም፡፡ በመጀመሪያ ተቋሙ ሲቋቋሙ በኮሚሽን ደረጃ በመቀጠል ደግሞ በምክትል ሚኒስትር ደረጃ ሲቋቋም በማሰለስ ደግሞ ወደ ቀድሞ ስሙ ኮሚሽን የሚል ስያሜ እንዲይዝ ተደርጓል፡፡ ሌላው መሰረታዊ ችግር የፖሊሲ መቀያየር ይመስለኛል፡፡ የፖሊሲ መቀያየር ሰራተኞችን ግራ ሊያጋባ ይችላል፡፡ የሰራተኞች ሞራልንም ጭምር ይገላል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ፖሊሲው የማይረባ ከሆነ የፖሊሲ አውጪዎችና የፖሊሲ አስፈጻሚዎች ስራ በእጅጉ ይደናቀፋል፡፡ ለተቀሱት ችግሮች ደግሞ የሚከተሉት ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላ፡፡

  • የቁሳቁስ እጥረት መሰረታዊ ምክንቶች ናቸው፡፡
  • በርካታ ሰራተኞች ከልብ የመነጨ የስራ መንፈስ ስለሌላቸው ( ምን ህሉ ሰራተኛ ነው ያለ ቀን አበል ክፍያ ለተቀጠረበት ተቋም ነጻ አገልግሎት መንፈሳዊ ወኔ የታጠቀው ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡

በነገራችን ላይ የተለያዩ አማላይ ፖሊሲዎች እና ከፍተኛ ባለሙያዎች መኖር ብቻቸውን ትርጉም የላቸውም፡፡ በመሬት ላይ የሚታየው ኋላቀር ስራ ከሆነ የፖሊሲ እና ከፍተኛ ባለሙያዎች ከወረቀት ነብርነት የሚዘሉ አይመስሉኝም፡፡ የተፈጥሮ አደጋ የሚያስከትለውን መቅሰፍት ለመከላከል የሚከወኑ ተግባሮች አትራፊ አይደሉም፡፡ የፖለቲካ መሳሪዎቸም አይደሉም፡፡ ስራው የሰብአዊ ስሜትና መንፈሳዊ ወኔን የሚጠይቅ ነው፡፡ በዚህ ስራ ላይ የሚሰማሩ ሰዎች የአምላክ ልብ ሊኖራቸው ግድ ነው፡፡ ሰይጣናዊ ስሜትና የጎሰኝነት ስሜት ያላቸው ሰዎች በዚህ ተግባር ላይ መሰማራት የለባቸውም፡፡ የተፈጥሮ አደጋ ተጠቂዎችን በጎሳ በመከፋፈል ልዩነት የሚያደርጉ፣ ወገኔ ለሚሉት ተገቢውን የሰብአዊ የሚሰጡ፣ ሌሎችን ችላ የሚሉ ደግሞ በአንደኛው ወገን ላይ የሞት ፍርድ እንደሰጡ መታወቅ አለበት፡፡ እስቲ  የተፈጥሮ አደጋ የሚያስከትለውን መቅሰፍት የሚያጠኑ ተመራማሪዎች አሁን ላለው የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች ያቀረቡትን ሶስተኛውን ጥያቄ ላስታውሳችሁ፡፡ (ጥያቄው በሰሜን ኢትዮጵያ ምድር በሰብል እና እጽዋት ላይ ከባድ ውድመት እያስከተለው የአንበጣ መንጋ በር፡፡) ጥያቄው የሚከተለውን ይመስላል፡፡

የአንበጣ መንጋ ስለሚያስከትለው መቅሰፍት ቅድመ ማስጠንቀቂያ አልሰጣችሁም ነበርን ? የሚል ነበር፡፡ ባለስልጣኖቹ በሰጡት መልስ ደግሞ  እንደ ቀደሙት አገዛዞች ባለስልጣኖች ተመሳሳይ በሆነ መልኩ ( በደርግና በወያኔ ዘመን ከነበሩት ባለስልጣኖች ማለቴ ነው፡፡ ) አዎ አሰጠንቅቀናል የሚል ነበር፡፡ ሆኖም ግን ባለስልጣኖች የፖለቲካ ቼዝ ጨዋታ ላይ ነበሩ፡፡ ርብርቦሹ የተጀመረው ዘግይቶ የአንበጣው መንጋ  በሰብል ላይ ጉዳት ማድረስ ከጀመረ በኋላ ስለመሆኑ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን የተዘገበ ጉዳይ ነው፡፡ ነገሩ ከባድ አውሎ ነፋስ አካበቢውን ካናወጠው በኋላ እንደሚሰራ ወደብ መሆኑ ነው፡፡ (“A port after the storm!”.)  በኢትዮጵያ የተፈጥሮ አደጋ መቅሰፍት የሚያስከትለውን ጉዳት ለመክላት የሚመረጠው ቀላሉ መንገድ ነው፡፡ ይሄውም የተፈጥሮ አደጋው ከደረሰ በኋላ ጉዳት ለደረሰባቸው ሰዎች ከእርጥባን የተገኘን እርዳታ ማደል ነው፡፡ የተፈጥሮ አደጋው የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚደረጉ ጥረቶች አጥጋቢ አይደለም፡፡ የተፈትሮ አደጋዎችን ቅድመ ትንበያ ለማድረግ ገና ብዙ ዳገት ይቀረናል፡፡ በእውነቱ ለመናገር ይህቺ ሀገር በሌላት ጥሪት በሚያማምሩ ህንጻዎች ቢሮ ውስጥ ተቀምጦ በተሸርካሪ ወንበር መንፈላሰስ መፍትሔ አያመጣም ዘመናዊ ተሸርካሪዎች ለባለስልጣናቱ የሚመደቡት፣ የተሻለ ክፍያ የሚያገኙት የመፍትሔ አመንጪዎችን በማበረታተት ሀገሪቱን ከችጋር ለመገላገል ይመስለኛል፡፡ ባለስልጣናቱ አደጋ ለደረሰባቸው ሰዎች 15 ኪሎግራም በቆሎ ወይም የስንዴ ዱቄት እና አንድ ጀሪካን ዘይት ለተጎጂዎች ማቀረቡ የሚቀል ስራ ነው ብለው የሚያስቡ ይመስላሉ፡፡ ሆነም ግን ይሁንና ዋነኛ ስራቸው በጎርፍም ሆነ በሌላ የተፈጥሮ አደጋ የሚጠቁ ሰዎች ከአደጋው በፊት ራሳቸው በራሰቸው መንገድ በቂ የምግብ ክምችት ወይም የገንዘብ አቅም እንዲኖራቸው አቅም እንዴት መፍጠር እንዳለባቸው ማሰላሰል ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ለአብነት ያህል በየአመቱ የአዋሽ ወንዝ እየሞላ የተፈጥሮ መቅሰፍት የሚደርስበት የአፋር ገበሬ አካባቢውን እንዴት ከጎርፍ መከላከል እንዳለበት ገና ክረምት ሳይገባ ትምህርት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በቂ የኢኮኖሚ አቅም እንዲፈጥር መንግስት መርዳት አለበት ባይ ነኝ፡፡ የኢትዮጵያ አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሽን ተቋም የተፈጥሮ አደጋ ከመከሰቱ በፊት የሚያከናውናቸው ተግባራት አመርቂም ውጤታማም አይመስሉም፡፡ በእውነቱ ለመናገር በብርቱ መታሰብ ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር የአንድ አካባቢ ህዝብ በጎርፍ ስለተጠቃ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚገመቱ መድሃኒቶችና እህሎች በአስቸኳይ መድረስ አለባቸው የሚሉ ሪፖርቶች ወይም ማሳሳቢያዎች የኢትዮጵያን ገበሬ ችግር ዘለቄታዊ በሆኑ መንገድ የሚፈቱ አይመስለኝም፡፡ ከተሳሳትኩ ልታረም ዝግጁ ነኝ፡፡ ለአብነት ያህል በቅርቡ የሰሜን ኢትዮጵያን ገበሬ ስጋት ውስጥ የዶለውን የአንበጣ መንጋ ለመከላከል የሚወሰዱ እርምጃዎች ዘመናዊነት ይጎለዋል  በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ቀርበው ቃለምልልስ ካደረጉ ባለሙያዎች መሰማቱ አሳሳቢ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በሳይንስና ቴክኖሎጂ አለመራመዳችንን የሚያመላክት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የተፈጥሮ አደጋ ከተከሰተ በኋላ የሚሰጡ ህይወት አድን ስራዎች፣ ልክ የህመም ስሜት ሲሰማን እንደምወስዳቸው መድሃኒቶች የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶች የእኛ ብርቱ ጓደኞች ሆነው የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ ለራስ ምታት ወይም ቁርጥማት የሚወሰዱ መድሃኒቶች አንድ ግዜ ብቻ ወስደን የምናቆማቸው አይደሉም፡፡ እንደውም ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠናቸውን እየጨመርን መውሰድ ግድ ይለናል፡፡ እስከ ህይወታችን ፍጻሜ ድረስ የህመም ማስታገሻ መድሃኒቶችን እንወስዳለን፡፡ የበሽታውን ምንጭ ለማድረቅ የምንወስደው መድሃኒት ከበሽታው የሚገላግለን መሆኑን ማወቅ ብልህነት ነው ፡፡ ሰላም፡፡

Reactive response limited to relief aid is like taking drugs to relieve pains. The pain comes back and you need more potent drugs. The more you take the more you need until you fall dead! Eliminating the source of pain must be the most effective remedy.

Filed in: Amharic