>

መደመር ከሠላም ይወግን !!! (ከመንግሥቱ ደሳለኝ)

መደመር ከሠላም ይወግን !!!

 

ከመንግሥቱ ደሳለኝ


ግብፅ አመታዊ የምርት መጠ /GDP/ 251 ቢሊዮን ዶላር ነው፤የኢትዮጵያ አመታዊ የምርት መጠን 84.4 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡በእዚህም ደረጃቸው ግብፅ 45ኛ ደረጃን ስትይዝ ኢትዮጵያ ደግሞ 68ኛ ናት – ከአለም፡፡ ከአፍሪካ ግብፅ ከናይጄሪያ እና ከደቡብ አፍሪካ በመቀጠል 3ኛ ኤኮኖሚ ስትሆን ኢትዮጵያ 8ኛ ናት፡፡  

ግብፅ በአየር ሃይል ከአለም 7ኛ ነች፤ ኢትዮጵያ 28ኛ ነች፡፡ግብፅ በታንክ 4145 በመያዝ 4ኛ ነች፤በአጠቃላይ ወታደራዊ ቁመናዋ ከአለም 9ኛ ነች፡፡ 900 ተዋጊ አውሮፕላኖችን በመያዝ  ግብፅ ከአለም 3ኛ ስትሆን ኢትዮጵያ 48ኛ ናት፡፡ በብዙ መንገድ እንበለጣለን ማለት ነው፤ለማንኛውም ውሳኔ የተገዳዳሪ ሃይልና የራስን ሃይል ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቃል – ‘’ ራሱን አያውቅ ‘’ እንዳንባል፡፡ኢትዮጵያ ከአለም ደካማ መንግሥታት / failed or collapsing states / ከሚባሉት 25 ሀገራት ዝርዝር ተርታ ትገኛለች፡፡የተሻለ የመንግሥት አስተዳደር፤ የኤኮኖሚ አቅም ወዘተ. በመያ  ግብጽ በእዚህ ዝርዝር አልተካተተችም፡፡

ኢትዮጵያ በርካታ የቤቱ ውስጥ ችግር አለባት፤የትግራይ ክልላዊ መንግሥት እና ፌደራል መንግሥቱ የሚያሳዪት አለመግባባት ለሃገር ጥሩ ምልክት አይደለም፤15 ሚሊዮን ህዝብ ቀጥተኛ ተረጂ ይሆናል ማለት ጥሩ ዜና አይደለም፤አንበጣና ጎርፍ ደቁሰውን ሄደዋል፤እስከ 15 ሚሊዮን ወጣት ስራ ፈላጊ አለን፤የጎንዮሽ ቁርቁሱ ዛሬም እንደበረታ ነው፤የኮሮና ጣጣ ገና አልተወጣነውም – በኤኮኖሚውም በጤናውም አዳክሞን ሊሄድ ይችላል፡፡በአዲስ አበባ ዙሪያ ብቻ በልዩ የኦሮሚያ ዞኖች በጣም በርካታ ወጣቶች የባንክ ስሊፕ ሞልቶ ገንዘብ ለማስወጣትና ለማስገባት የሌላ ሰው ዕገዛ ይፈልጋሉ – የማንብበና የመፃፍ ዕድል በመንፈጋችን፡፡ ‘’ትምህርት ሕይወት ነው’’  ብለን ብዙዎቹን ሕይወት ነፍገናቸዋል፡፡ equity የለም፤ ጣጣችን ብዙ ነው፡፡የማያስፈልገውን አናስብ፡፡ ያልበላን አንከክ፡፡ ከሰላምና ልማት ውጪ ማሰብ ለኢትየጵያ ቅንጦት ነው፡፡መስመር ከሳትንም ከአዙሪቱ አንወጣም፡፡ 

በኮሚኒስቱ ንቃ፣ተደራጅ፣ታጠቅ ስሜት መንጎድ ዛሬ ኪሳራ ሊያመጣ ይችላል፤የማኪያቬሊን የሴራ ፖለቲካ /the-not-be-good/ ሙጥኝ ማለት ቅራኔ ከማስፋት፣ገንዘብ ከማጥፋት፣ቁልቁል ከመውረድ ብዙ አይታደግም፡፡ችግርን ለነገ ማሳደር ነው፤እነዚህ ዕሳቤዎች ኮትኩተው የሚያሳድጉት ቅራኔን እና ክፋትን ነው፡፡የየዕለት ንግግራቸው ደግም ያው የለመድነው ‘’ ወድር፣ውጋ፣ንቀል፣አምክን፣ሸምቅ፣እሰር፣ሰልል፣አጥፋ፣ዝረፍ፣ግደል፣ከፋፍል፣ውገር …’’ ናቸው፡፡ እነዚህ ወረት ያጠፋሉ፣ሃገር ያድፋፋሉ፡፡እስኪበቃን ስላየናቸው ሊናፍቁን አይገባም – ሌላውን እንሞክር፡፡ቁርቁሱን የሚመክሩን፣ግብግቡን አይዞህ! የሚሉን ከጉዳዩ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚጠቀሙ ናቸው፡፡ጥቅሙን እነርሱ ያውቃሉ፡፡  

  

ምክረ ሃሳብ፡-

  1. ከትግራይ ክልላዊ መንግሥት ጋር ያለውን አለመግባባት በተቻለ መጠን በሰላማዊ ውይይት ብቻ መፍታት፤
  2. በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያሉትን አለመግባባቶች በጋራ ተጠቃሚነት መንፈስ በሰላም መጨት፤
  3. በቤት ውስጥ ያሉትን ፖለቲካዊ ክፍተቶች በመወያየት ከስኬት ማድረስ – ለሃገርና ለህዝብ ህልውና ሲባል፤ብልፅግና የሚወለደው በእጅጉ ከሰላም ውስጥ ነው፡፡  
  4. መጪውን ምርጫ ትርጉም ባለው መልኩ ተፎካካሪዎችን በማሳተፍ መፈፀም፤ያ ቢከብድ እንን በሃሪፉ ለመምሰል እና ለማስመስል መሞከር – ‘Fake it before you make it’ እንዳሉት፡፡ይህን በመፈፀም ፋታ ካገኘን የብልፅግናው መንገድ በግማሽ ተሳካ ማለት ነው፡፡ነቃ እንበል፤ መደመር ከሰላም ይወግን – አስገዳጅ ሁኔታዎች ካልመጡ በስተቀር፡፡/Good fence makes good neighbor/ – ጠንካራው የጉርብትና አጥር ሰላምና ፈታ ያለ ፖለቲካዊ ሰጥቶ መቀበል መሆን አለበት፡፡

ያልተረጋጋ የቤት ፖለቲካ ለግብፅ ቁርስ፣ምሳና እራት ነው፤ኢትዮጵያን ለመውጋት ግብፅ በአካል መምጣት አይጠበቅባትም፡፡ እንደወትሮው ሁሉ በወኪል መስራት ትችላለች፡፡ወኪል ነፍ ነው !!!

Filed in: Amharic