>

ትብብር እና ቅንጅት የሚፈጠርበት ጊዜ አሁን ነው (ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ)

ትብብር እና ቅንጅት የሚፈጠርበት ጊዜ አሁን ነው

ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ


ጠቅላዩ  በቤኒሻንጉል ጉምዝ የሚካሄደውን ጭፍጨፋ እና ግድያ  እንደሚቀጥል ተናግረዋል (ጠ/ሚ/ ለፓርላማ ከተናገሩት የተወሰደ)፡፡  ይህ ንግግር ለቤኒሻንጉል ጉምዝ ብቻ የተነገረ ሳይሆን በሌሎችም ክልሎች አማራን የማጥቃት ስልት እንደሚቀጥል በስውር ማስታወቃቸው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሀገርን የሚመራ መሪ የህዝቡን ጥቃት ይታደጋል እንጅ ጥቃቱ ይቀጥላል ብሎ ሲናገሩ መስማት ይህ ንግግር መሪውን የመጀመሪያ ያደርጋቸዋል፡፡ መንግስት የተባለ አካል በተበየነበት ሀገር፤ መንግስት የዜጎችን ደህንነት መጠበቅ ግዴታው መሆኑ እየታወቀ እንዲህ መነገሩ እጅግ ያሳዝናል፡፡ እጅግም ያሳፍራል፡፡ 

የመከላከያ ሰራዊታችን ብቃት እንኳን ለዜጎቹ ለጉረቤት ሀገራትም እንደሚበቃ በተግባር የተፈተነ ጉዳይ ነው፡፡ እውነታው ይህ ሁኖ እያለ የዜጎች ግድያና ጭፍጨፋ እንደሚቀጥል መነገሩ ጉዳዩ ግድያውን ለማስቆም የአቅም ማጣት ሳይሆን ፍላጎቱ እንደሌለ ማሳያ ነው፡፡ አማራ በራሱ ሀገር ይገደል፣ ይገለል እና ይሸማቀቅ ዘንድ  ህገ – መንግስታዊ ድንጋጌ ተጥሎበታል፡፡

ጎሳቸውን ተጠቅመው ወደ ስልጣን ለመውጣት የሚፈልጉ ብሄርተኞች ህገ – መንግስቱን እና የጎሳ ፖለቲካን ሙጥኝ ያሉበት ምክንያት ይኸው ነው፡፡ ብሄርተኞች ወደ ስልጣን ለመውጣት ይመቻቸው ዘንድ ህገ – መንግስቱን እና የጎሳ ፖለቲካውን እንዳይቀየር ሲሟገቱ እንሰማለን፤ ዳሩ ግን ህገ – መንግስቱ እና የጎሳ ፖለቲካው የአንድነት ፀር ከመሆኑም ባሻገር በዜጎች መካከል መቃቃርን እና ግጭትን እንደሚጋብዝ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናግረዋል፡፡ ሁኖም ግን ሰሚ የለም፡፡ ምክንያቱም ይህ ብሄር – ተኮር ጥቃት ስልታዊ በሆነ መንገድ እንዲቀጥል ይፈለጋል፡፡ የሽመልስ አብዲሳ ንግግር ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ በዚህ ሁሉ ዘር – ተኮር ግድያዎች ጠቅላዩ ምንም አይነት ማፅናኛ አለመስጠታቸው ሌላው ማረጋገጫ ነው፡፡

ስለዚህ መላው አማራ እና ግፍን የሚፀየፉ ውድ ኢትዮጲያውያን በሙሉ በአንድ ድምፅ በጋራ በመቆም ይህንን ዘረኛ ስርዓት ልንታገለው ይገባል፡፡ በጥቃቅን ጉዳዬች መለያየትን አቁመን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተባብረን ይህንን የብሄርተኛ ስርዓት ልናስቆመው ግድ ይላል፡፡ ከብሄር ይልቅ በዜግነት እና በሀገር አንድነት ላይ የሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥምረት፤ ህብርት፣ ትብብር እና ቅንጅት የምንፈጥርበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ጉዳዩ ለፖለቲካ ስልጣን የምንራኮትበት ሳይሆን ሀገርን እና ህዝብን ለመታደግ ኃላፊነታችንን የምንወጣበት ጊዜ ነው፡፡ እኛ ህብረት ፈጥረን ግድያና ግፍን ማስቆም እስካልቻልን ድረስ ሰቆቃው ይቀጥላል፡፡ 

Filed in: Amharic