>

ኢትዮጵያ በታሪኳ ካየቻቸው የስጋት ደመናዎች የአሁኑ ተወዳዳሪ ያለው አይመስለኝም ! (ታዬ ቦጋለ አረጋ)

ኢትዮጵያ በታሪኳ ካየቻቸው የስጋት ደመናዎች የአሁኑ ተወዳዳሪ ያለው አይመስለኝም !

ታዬ ቦጋለ አረጋ

በቅድሚያ ፦ በአማራነታቸው ምክንያት በጉራ ፈርዳ ህይወታቸውን በአስከፊ የጅምላ ጭፍጨፋ ላጡ የአማራ ሰማዕታት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልፃለሁ…!!!
 
ትላንት አብሮ ለታገለ ለሞተ እና በወንድማማችነት መንፈስ ለወደቀ ወገን ምላሹ ይህ መሆኑ ያሳዝናል…!!!
በመቀጠል ፦ ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ ሳይወጡ በፍጥነት ማስተካከል ካልተቻለ ፤ ኢትዮጵያ በቋፍ ላይ ለመሆኗ የሚከተሉት ሁለት መልዕክቶች የሚናገሩት እውነት አላቸው ፦
1. የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በፌስቡክ ሠሌዳቸው የሚከተለውን ጠንከር ያለ አስተያየት አስፍረዋል ፦
“ዛሬም በጉራ ፈርዳ… የአማራ ህዝብ ለፍትህ ፣ ለነፃነት እና ለአብሮነት ሲታገል ቢኖርም እስካሁን በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም፣ ፍትህና የህግ የበላይነት ሰፍኖ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በየትኛውም የአገራችን ክፍል በሰላም ፣
በነፃነት እና በደስታ መኖር የሚቻልባት አገር ባለቤት መሆን
አልተቻለም ። ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ግፍና መከራው አየተጠናከረ በአሰቃቂ ሁኔታ መጨፍጨፋና በገፍ መፈናቀሉ ተስፋፍቶ ቀጥሏል። ይህንን ሁኔታ ለመረዳት ብዙም ሩቅ ሳንሄድ ይህንን አንድ ዓመት ብቻ ወስዶ አዝማሚያውን መገምገሙ ከበቂ በላይ ነው ። ከጥቅምት እስከ ጥቅምት ያለው አንድ ዓመት ብቻ በግልፅ የሚነግረን ግፍና መከራው
ተጠክሮ መቀጠሉን ነው። ማለቂያ የሌለው የጅምላ ጭፍጨፋ ፣ በገፍ መፈናቀል፣ የዘመናት የልፋት ውጤት የሆነ ንብረት ውድመት የየሳምንቱ መርዶ መስማት የተለመደ እየሆነ መጥቷል ። ስለሆነም ነገሩን ላለማባባስ ሲባል በዝምታ ማለፋ የሚጎዳ መሆኑን በተግባር እያየነው በመሆኑ ያገባናል ባዮች በሙሉ ልንነጋገርበት ይገባል ። ይህ በአማራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈፀመ ያለው በማንም ህዝብ
ሳይሆን በጥቂት ቡድኖችና ግለሰቦች ሴራ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉንም የኢትዮጵያ ህዝብ በአጋርነት የሚያሰልፍ የትግል አቅጣጫ ነድፎና ስትራቴጅያዊ ግብ ወስኖ በጋራ መንቀሳቀስ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም ። በክስተት ላይ ያነጣጠረ ጩኸት አልቃሻ ከማድረግ
የዘለለ ጥቅም የለውምና ። “
2. ሌላው ከፍተኛ የብልጽግና አመራር ክቡር አቶ ዮሐንስ ቧያለው በተመሳሳይ የሚከተለውን ጠንከርና መረር ያለ መልዕክት አስተላልፈዋል ፦ ” ዓመታትን ያስቆጠረው በአማራ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ተጠናክሮ የቀጠለው ችግሩን ላለማባባስ በሚል በዝምታ መታለፉ ነው ። በመሆኑም በችግሩ ስፋት ላይ ለመፍትሔው ውይይት ክፍት ማድረግ
ይገባል ። ይህንን ማድረግ ካልቻልን የቅደም ተከተል ጉዳይ ካልሆነ የነገ ተረኞች ሁላችንም ነን፤ ፖለቲከኞች፤ ልሂቃን፤ ሁሉም አማራ መምከር አለበት…? ዛሬ ላይ ሆነን በኢትዮጵያ የተበተነውን አማራ ደህንነት መጠበቅ ከማይቻልበት የብልፅግና ውህደት Exit የሚያደርግበትን መላ ለመዘየድ ዓለማቀፋዊ የአማራ ጠቅላላ ጉባዔም ሳያስፈልገው
አይቀርም ።
.
NB:- እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ህዝቦችን ይባርክ።”
የሁለቱም ከፍተኛ አመራሮች ፅሑፍ ይዘት በብልፅግና አመራሮች መሀከል፤ በተለይም በኦሮሚያ እና በአማራ አመራሮች ጎራ የለየ ከፍተኛ ክፍተት እየተፈጠረ ለመሆኑ በጉልህ አመላካች ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ ይህንን ልዩነት ማጥበብና የቀደመውን መልካም ጓዳዊ ግንኙነት እና ወንድማማችነት ማደስ ካልቻሉ፤ በተጨባጭም በኦሮሚያ ብልፅግና የተወሰኑ አመራሮች የሚታየውን የከፋ የብሔረሰብ ጥላቻና ሀገርን ለከፋ እልቂት የሚዳርግ የትንኮሳና ስውር ሴራ አካሄድ ማስቆም ካልቻሉ ፤ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ያለጥርጥር ከድጡ ወደ ማጡ ይሰምጣል ። የመጨረሻው መጀመሪያም ይሆናል ። ለላይኛው ቤትም ሠርግና ምላሽ መሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነው። ትላንት አብሮ ለታገለ ለሞተ እና በወንድማማችነት መንፈስ ለወደቀ ወገን ምላሹ ይህ መሆኑ ያሳዝናል ።
እግዚአብሔር የንፁሀንን ዕንባ ዐይቶ ይፍረድ!
Filed in: Amharic