>
5:13 pm - Wednesday April 18, 0587

የእውነት  እና የሐሳብ ጠበቃ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም (ደረጀ መላኩ - የሰብአዊ መብት ተሟጋች)

የእውነት  እና የሐሳብ ጠበቃ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም

ደረጀ መላኩ  የሰብአዊ መብት ተሟጋች

Tilahungesses@gmail.com

                                                        

መንደርደሪያ

የዝነኛው የክቡር ዘበኛ የሙዚቃ ኦርኬስትራ ድምጻዊ እና ተወርግራጊ የነበረው ሥመ ጥሩው ያ/ ጋሼ ጥላሁን ገሠሠ፡-

    ውሸት ለመናገር አትሻም ምላሴ፤

    ለእውነት እሞታለሁ አልሳሳም ለነብሴ፡፡   በማለት አዚሞ እንዳለፈው፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም  በእውነት ኑረው፣ ለእውነት ብለው፣ በእውነት ምክንያት ያለፉ፣ በክፍለ ዘመን አንዴ እንደ አንጻባራቂ ኮኮብ የሚበሩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ምሁር ነበሩ፡፡ ነበሩ ልበል ዛሬ በህይወት ስለሌሉ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን አልመነዘርም፣ በጎሳ ፣ አልሸጥም በቤሳ በማለት የሰውነት ክብርን ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተማሩ፣ በሰውነት ደረጃ ላይ ቆመው፣ በሰውነት ኑረው ያለፉ መንፈሰ ጠንካራ ሰው ነበሩ፡፡

መግቢያ

ኢትዮጵያ የአንድ ጉልበተኛ ሀገር ብቻ ናት ብዬ አላስብም፡፡ ይህቺ መሬት የተገነባችው ወይም ታፍራና ተከብራ የኖረችው በእናቶቻችንና አባቶቻችን፣ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችን በከፈሉት መስእዋትነት ነው፡፡ ማንም ሰው ከሀገሬ ሊያባርረኝ ወይም የስደት ኑሮን ( ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) እንድጋት ሊያስገድደኝ አይቻለውም፡፡ ማንም ሰው ሊያስፈራራኝ፣ የኢትዮጵያ ዜግነት መብቴን ሊገፈው አይችልም፡፡  ለወያኔዎች በግልጽ የምነግራቸው ጉዳይ ቢኖር  የእኔ ህይወት፣ የምኖርበት ቦታ፣ የምሞተውም፣ የምቀበረውም በኢትዮጵያ ምድር ነው፡፡ ከኢትዮጵያ በቀር ሌላ ሀገር የለኝም፡፡

ለወያኔ እና ሎሌዎች አንድ እውነት እነግራችኋለሁ፡፡ ዛሬ ወንጀል ከፈጸማችሁ ፣ እኔን አለ ህጋዊ አግባብ አደጋ ላይ ከጣላችሁ ነገ በታሪክ ፊት መጠየቃችሁ የማይቀር ነው፡፡ ስልጣናችሁን አለአግባብ የተጠቀማችሁ፣ ሰውን በመግደል አሸናፊ ነን ብላችሁ የምታምኑ፣ በመግደል የምታምኑ ነገ የግፍ ጽዋችሁን ትጎነጫላችሁ፡፡ ( ፕሮፌሰር መስፊን ወልደማርያም  ወዴት እንድንሄድ ይፈልጋሉ  ? እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 2015 

በፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መሞት ጥልቅ ሀዘኔን እየገለጽኩ፣ ለፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ቤተሰቦች መጽናናትን እመኛለሁ፡፡ የእውነትን ሀያልነት በመናገራቸውም ነፍሳቸው በሰላም እንድታርፍ ጸሎቴን አደርሳለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር እውነት ተናጋሪው የኢትዮጵያ ልጅ ወይም ለኢትዮጵያ ህዝብ እውነትን ሲናገር የነበረው ታላቁ ሰው ፕሮፌሰር መስፍን በማረፉ ለኢትዮጵያ ህዝብ መጽናናትን እመኛለሁ፡፡

ስለ ፕሮፌሰር መስፍን የእውነትና ሃሳብ ጠበቃነት ስጽፍ እንደው ዝም ብዬ ከመሬት እምቡር እምቡር በማለት አይደለም፡፡  ፕሮፌሰር መስፍን እኔን ጨምሮ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የእውነት መሰረትን በመያዝ ለሰብአዊ መብቶች፣ ለዲሞክራሲያዊ መብቶችና ለህግ የበላይነት እንዲቆሙ ሳይሰለቹ ፣ በብዙ መንገድ በአደባባይ ያስተማሩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ስለማውቅ ነው፡፡ በተለይም ባለፉት ሶስት አስርተ አመታት በአስከፊው እና ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የፈጸመውን የሰብአዊ መብት ጥሰት በእውቀትና ጥናት ላይ በመመስረት በአደባባይ ያጋለጡና ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተምሳሌት ነበሩ፡፡ 

የሚስተር ጆንን ቃል ልጠቀምና ‹‹ ኮቪዲ 19 በሽታ ኩራት ሊሰማህ አይገባም ›› I say to Covid 19, in the words of John Donne, “Be not proud, Covid 19  ታላቁ የኢትዮጵያ ልጅ ‹‹ በኮቪዲ 19 በሽታ ይህችን አለም ተሰናበቱ ›› ተብሎ ከተነገረ በኋላ በታላቅ ሀዘን ወድቀን የነበርን ቢሆንም፡፡ ኮቪዲ 19 በሽታ የፕሮፌሰር መስፍንን አስተምህሮን በፍጹም ሊያዳፍነው አይቻለውም፡፡ አርሳቸው በአካል ቢለዩንም ስራዎቻቸው ዝንተ አለም ሲታወሱ ይኖረዋል፡፡ 

ስለሆነም ከእናት ኢትዮጵያ ምድር ስለ ፕሮፌሰር መስፍን እናገራለሁ፡፡

ዛሬ ስለ ፕሮፌሰር መስፍን የምናገረው እንደ ተማሪያቸው ሆኜ አይደለም፡፡ የእርሳቸው ተማሪ ለመሆን አልታደልኩም ነበር፡፡

እንደ የቅርብ  ጓደኛ  ሆኜም አይደለም የምናገረው፡፡ ምክንያቱም በእኔ እና የፕሮፌሰር እድሜ መሃከል ወደ አርባአምስት አመት የሚጠጋ የእድሜ ልዩነት አለ፡፡

ስለ ፕሮፌሰር መስፍን ለመናገር ስነሳ የእርሳቸው ጓደኛ ነኝ ብዬ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በእኔና በእርሳቸው መሃከል የሰማይና የምድር ያህል ልዩነት አለ፡፡ እርሳቸውን ለማወቅ ወይም ለመረዳት እንደ ውቅያኖስ ጥልቀት እንዲኖር ግድ ይላል፡፡

ስለ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ለመናገር ወይም ለመጻፍ መንፈሳዊ ወኔ ለመታጠቅ የቻልኩት ፐሮፌሰሩ የሚታመኑ አዛውንት በመሆናቸው፣ በብዙ ሚሊዮን ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን አርአያ ስለሆኑ( መማር ለሚፈልጉት ማለቴ ነው፡፡)፣ እንዴ ለእኔ በተለይም በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በጥልቀት እንድመራመርና እንዳውቅ ከረዱኝ ስመጥር ኢትዮጵያውያን ምሁራን መሃከል አንዱ ስለሆኑ ይመስለኛል፡፡ እድሜ ልካቸውን ሙሉ ለኢትዮጵያ ሲሉ የደከሙ፣ ደጋ የወጡ፣ ቆላ የወረዱ፣ ለኢትዮጵያ ለብዙ አመታት ያነቡ፣ ስለ ኢትዮጵያ ታላቅነት፣ ታሪካዊት ሀገር ስለመሆኗ፣ የህዝቡ አኗኗር በጥልቀት ያጠኑ በመሆናቸው፣ የኢትዮጵያን ጂኦግራፊ በጥልቀት ያጠኑ ሰው በመሆናቸው፣ ለሰው ልጆች መብት መከበር በጽናት የታገሉ ታላቅ ሰው ስለሆኑ ይመስለኛል፡፡

ስለ ፕሮፌሰር መስፍን የምናገረው የእውነትን ምንነት ስላስተማሩኝ ነው፣ በእውነት ኑሬ፣ ለእውነት ስል፣ በእውነት ምክንያት የቀራንዮን መንገድ እንድከተል ተምሳሌት ከሆኑ ኢትዮጵያውያን እንዱና ዋነኛው ምሁር ስለሆኑ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያ ምሁራን የአደባባይ ምሁራን እንዲሆኑ፣ ለእውነት እንዲቆሙ በብዙ መልኩ የደከሙ ሰው ነበሩ፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የአካዳሚክ ነጻነት እንዲሰፍን ላደረጉት አስተዋጽኦ ታሪክ ስፍራውን የሚነሳቸው አይመስለኝም፡፡

በምእራቡ አለም ታሪክ ሶቅራጥስ  የእውነትን ሃያልነት በመናገሩ ምክንያት የሞት ፍርድ ሲበየንበት በፍርሃት አልተርበደበደም ነበር፡፡

እንደ ፕላቶ ገለጻ ከሆነ ሶቅራጥስ በሚያደርጋቸው ንግግሮች ብዙዎች ሊጠሉት እንደሚችሉ፣ ብዙዎችን እንደማያስደስት፣ ሆኖም ግን ሶቅራጥስ ስለ እውነት እንደሚናገር እምነት ነበረው፡፡

According to Plato, Socrates said, “I know that my plainness of speech makes them hate me, and what is their hatred but a proof that I am speaking the truth?”

በነገራችን ላይ የሶቅራጥሥ እውነት የተመሰረተው በእውነት ላይ ነው፡፡ ሶቅራጥስ ሌሎች እውነት ነው ብለው ስለሚያምኑት ጉዳይ መጠየቅ ልምዱ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ታሪክ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በአገዛዞች አኳያ በጥሩ ጎን አይታዩም ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የእውነትን ሃያልነት በአደባባይ በመነጋገራቸው ለብዙ ግዜያት ፍርድ ቤት ተመላሰዋል፡፡ የእስርን ገፈት ቀምሰዋል፡፡ ( በተለይም ከታሪካዊው ግንቦት 1997 ዓ.ም. የምርጫ ውድድር ማብቂያ በኋላ እድሜ ልክ ተፈርዶባቸው ወደ ሁለት አመት ግድም ከታሰሩ በኋላ በምህረት ከተለቀቁት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አንዱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ነበሩ፡፡) ስለ እውነት በመናገራቸው ምክንያት በተለይም በወያኔ አገዛዝ ቂም ተረግዞባቸው ነበር፡፡

እንደ ሶቅራጥስ ሁሉ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ስለ አገዛዞች ( ጉልበተኛች)፣ ስልጣን ስለሌላቸው፣ እና የስልጣን ጥመኞችን በተመለከተ ስለያዙት እውነተ በየጊዜው ይጠይቁ ነበር፡፡ 

የእርሳቸው እውነት መጠየቅ ነበር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን እውነትን ለማግኘት ሲሉ እጅግ በርካታ ጥያቄዎችን ነሱ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር እጅግ ብዙ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እውነትን ማግኘት ይቻላል የሚል ጽኑ እምነት ነበራቸው፡፡ እውነት የምትታሰረው መጠየቅ ስናቆም ነው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ማንኛውንም ሰው ይጠይቃሉ ( ንጉስ፣ ጳጳስ፣ ፕሬዜዴንት፣ ጠቅላይ ሚኒሰትር፣ ከንቲባ፣ ፣ ፕሮፌሰር፣ በመንገድ ላይ ጠኔ የያዘው ሰው ፣ ሊጠይቃቸው የመጣውን ማናቸውም ግለሰብ ወዘተ ወዘተ ይጠይቃሉ፣ ጠይቀው እውነትን ለማግኘት ይጥራሉ፡፡)

Prof. Mesfin questioned everyone. King, pope, president, prime ministers, mayor, professor

በነገራችን ላይ እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ሁሉ ለእውነት ከቆሙ ኢትዮጵያውያን አንዱ የታወቁት የታሪክና የሰብአዊ መብት አስተማሪ ፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ ( ነፍሳቸውን ይማር )የሚዘነጉ ሰው አይደሉም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በ1984 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እንዲመሰረት ሃሳቡን ካመነጩት 28 የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን መሃከል አንዱና ግንባር ቀደሙ ሲሆኑ፣ፕሮፌሰር አለሜ እሸቴም በተመሳሳይ አመት  የኢትዮጵያውያን ሌጉ ለሰብአዊ መብቶች (Ethiopian League for Human Rights. )  የመብት አስከባሪ ተቋም በመመስረት በኢትዮጵያ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ የበኩላቸውን ጉልህ ድርሻ ሰርተው አልፈዋል፡፡ የቅርብ ጓደኞቹ የነበሩት ሁለቱም ኢትዮጵያውያን ( ፕሮፌሰር መስፍንና ፕሮፌሰር አለሜ ) ዛሬ በህይወት ባይኖሩም ሥራቸው ህያው ሆኖ እንደሚኖር ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን እንደ ሌሎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በምእራቡ አለም ስማቸው በገነኑ ታላላቅ ዩንቨርስቲዎች በአንዱ ምርምራቸውንና የማስተማር ስራቸውን ከጥሩ ክፍያ ጋር ማከናወን ሲችሉ አላደረጉትም ነበር፡፡ ፕሮፌሰሩ በኢትዮጵያ ምድር ላይ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ደስታውንም መከራውንም አብረው ያሳለፉ ታላቅ ሰው ነበሩ፡፡

ብዙዎች ኢትዮጵያን ጥለው ወደ ሌሎች ሀገራት የተሰደዱት የተሻለ ኑሮ ለመምራት፣ትምህርት ለመማር፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ዛቻና ማስፈራሪያ ስለደረሰባቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ የታሰሩ ፣ የተንገላቱ፣ የኢኮኖሚ ጥገኛ ለመሆን ወዘተ ወዘተ ምክንያት ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መቀመጫቸውን ኢትዮጵያ ላይ ያደረጉት፡፡ በፍጹም፣ በፍጹም  ስደትን ምርጫቸው አላደረጉም ነበር፡፡

የወያኔ አገዛዝ ፕሮፌሰር መስፍን አርፈው እንዲቀመጡ በብዙ ዘዴ ሞክሮ አልተሳካለትም ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን በእስር ለማንገላታተት ሞክረውም ነበር፡፡በስደት ወደ ውጭ ሀገር እንዲሄዱም ጥረት መደረጉን ከኢትዮጵያዊ ምሁራን ጽሁፍ ላይ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ ሆኖም ግን ፕሮፌሰር መስፍን ማናቸውንም የወያኔ አገዛዝ ጫና ተቋቁመው እስከ መጨረሻዋ ህቅታቸው ድረስ በኢትዮጵያ ምድር ኖረዋል፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ልበሙሉው እና መንፈሰ ጠንካራው ፕሮፌሰር መስፍን ስደትን በጽኑ ይቃወሙ ነበር፡፡ በተለይ ከኢትዮጵያ በ100000 ኪሎሜትር እርቀት ላይ ሆነው የፖለቲካ ጨዋታ ለሚጫወቱ ኢትዮጵያውያን እንደማይሳከላቸው አበክረው ይተቹ፣ ያስተምሩ ነበር፡፡

እዚች ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2015 የጻፉትን መጥቀሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የአይምሮዬ ጓዳ ያስታወሰኝን እጠቅሰዋለሁ፡፡

‹‹ የወያኔ አገዛዝ ለምን እኔን ለማሸማቀቅ እንደፈለገ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ አፓርትሜንት ላይ የሚገኘውን ቤቴን ፈልገውት ይሆን ቤቴን ከፈለጉት ሁለት ነገሮችን ብቻ ነው፡፡ የወያኔ አሽከሮች ሊያገኙ የሚችሉት ሁለት የገብረክርስቶስ ደስታን ስእሎች ብቻ ነው፡፡ እኔ ያለኝ ሀብት መጽሐፍት ብቻ ናቸው፡፡ መጽሐፍት ደግሞ ለወያኔ አገዛዝ ዋጋ የላቸውም፡፡ ስለሆነም ወያኔ እኔን የሚያስፈራራኝ ፣ የሚያበሳጨኝ ተማርሬ ሀገሬን በመልቅቅ የስደት ኑሮን እንድጋት ነው ( ኑሮ ከተባለ ማቴ ነው)፡፡ ለወያኔዎች በግልጽ የምነግራቸው ቁምነገር ቢኖር የእኔ ህይወት፣ እኔ የምኖርበት ቦታ፣ በመጨረሻም እስትንፋሴ የምትቆመውም በኢትዮጵያ ምድር ላይ ይሆናል፡፡

በእኔ በኩል የፕሮፌሰር መስፍንን በእውነት ላይ የተመሰረተ ከባድ ውሳኔ እወደዋለሁ፡፡ አከብረዋለሁም፡፡ እንደሚመስለኝ ፕሮፌሰር ለመሸለም ወይም ወቀሳ ይደርስብኛል ብለው የሚሰሩ ሰው አልነበሩም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ስለ እውነት ሲናገሩ የነበረው የሚደርስባቸውን መከራ ለመቀበል ዝግጁ በመሆን ሲሆን፣ ለህዝቡም እውነትን ለመንገር ሲሉ ነው፡፡ የፕሮፌሰሩ ብእር በማንም ሰው ላይ አድሎ አትፈጥርም ነበር፡፡ ንጉሱን፣ ፕሬዜዴንቱን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፕሮፌሰሩ ትችት አላመለጡም፡፡ ለሀገር መድህን ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦችንም አመንጭተው ነበር፡፡ በአጭሩ የፕሮፌሰሩ ብእር አድርባይ አልነበረችም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ሊሆን የሚችለውን ነገር ምክንያት አያስቀረው የሚል አመክንዮ ነበራቸው፡፡ አውጥተው አውርደው ካሰላሰሉ በኋላ መናገር የሚፈልጉትን ነገር ሳይናገሩ አያልፉም ነበር፡፡

እኔ እንደምገነዘበው እውነትን መናገር ለውጥን ሊያስገኝ ይቻለዋል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ የንጉሳዊ አገዛዝ፣ የወታደራዊ አገዛዝና መሰረቱን ጎሳ ላይ አድርጎ የነበረው የወያኔ አገዛዝ ታይተዋል፡፡ ሶስትኑም ያለፉት አገዛዞች ፊትለፊት በመተቸትና በማስተማር ከሚታወቁ በርካታ ኢትዮጵውያን መሃከል አንዱ ፕሮፌሰር መስፍን ይመስሉኛል፡፡

በእኔ የአውቀት ደረጃ ለመገንዘብ እንደቻልኩት ሶስቱንም ያለፉትን አገዛዞች ያለፍርሃት፣ ያለ ይሉኝታ ከመተቸትና ከማስተማር፣ ለሃገር መድህን ሊሆኑ የሚችሉ ሃሳቦችን ከማቅረብ አኳያ አበርክቷቸው ሰፊ ነው፡፡ ከዚህ ባሻር ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በኢትዮጵያ ምድር የባህል አብዮትን ያቀጣጠሉም ሰው ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር እውነትን ለማገልገል የአንድ ሰው አብዮት የጀመሩም ታላቅ ሰው ነበሩ ተብሎ ቢጻፍ ስህተት አይመስለኝም፡፡

ይገባኛል ወይም አውቃለሁ አንዳንድ ደካማ ሰዎች ማለትም ከእርሳቸው ጋር ለመከራከር የማይችሉ እና የእርሳቸወን አቋም የሚጠሉ ሰዎች ሥማቸውን ለማጠልሸት ይሞክራሉ፡፡ እንደ አንዳንድ ሰዎች አስተያየት ከሆነ ፕሮፌሰር የሚያቁት ነገር ቢኖር ከሌሎች ጋር አለመስማማትን ነው፡፡ ማንንም ሰው አድነቀው አያውቁም፡፡ ፕሮፌሰር የሚናገሩት የራሳቸውን እውነት ብቻ ነው የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ በፕሮፌሰር ላይ ተሰጥተው የነበሩትን ይህንና የመሳሰሉትን አስተያየቶችን ሳነብ ወይም ስሰማ ያስገርመኛል፡፡ ለራሴም ይህ የፕሮፌሰሩ ስራ ነው በማለት እነግረዋለሁ፡፡ የአደባባይ ምሁርነት የፕሮፌሰር መስፍን ስራ ነበር ብዬ አስብ ነበር፡፡

የአደባባይ ምሁር ፖሊሲዎችንና የሀገር ጉዳዮችን በተመለከተ ለማስረዳት፣ ለመተንተን  ድምጽ ለሌላቸው፣ ጉልበት ለሌላቸው ሰዎች፣ አጋዥ ለሌላቸው ሰዎች ነጻ አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እንዲህ አይነት ሰው የነበሩ ይመስለኛል፡፡ እንደ ፕሮፌሰር መስፍንን የመሰሉ እውነተኛ ምሁራን እንደ ሻማ እየቀለጡ በአንዲት ሀገር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ሌት ተቀን የሚባጁ ናቸው፡፡ የራሳቸውን እውነት ይናገራሉ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምን በመኖሪያ ቤታቸው በመገኘትም ሆነ በተለያዩ ስብሰባዎች፣ አውደ ጥናቶችና ( በተለይም በኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩቱ)፣ እርሳቸው በሰጡት አንድ ስልጠና ላይ ተካፋይ በመሆኔ ለበርካታ ጊዜያት የማግኘት እድሉ ገጥሞኝ ነበር፡፡ በእውነቱ ለመናገር ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ለሰአታት ተገናኝቶ ማዳመጥ በዩንቨርስቲ ውስጥ ለአመታት ቆይቼ ካገኘሁት የበለጠ እንደነበር ተገንዝቤአለሁ፡፡ ፕሮፌሰሩ በሚያነሱት ነጥቦች ሁሉ ጥልቀት እውቀትን የሚመገቡ ሰው ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ስለ ኢትዮጵያ የቀደመ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ወዘተ ትንታኔ ሲሰጡ ሁሉም ሰው በታላቅ አርምሞ ነበር የሚያዳምጣቸው፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ አይነት ሰው ነው በወርሃ መስከረም 2013 ዓ.ም. ያጣችው፡፡ ያሳዝናል፡፡

አንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር በጥር 2020 በህይወት ታሪካቸው ላይ የሚያጠነጥን ጥናታዊ ፊልም ‹‹ የፕሮፌሰሩ መቀስ የተሰኘ ጥናታዊ ፊልም ›› እንደተመለከትኩ አስታውሳለሁ፡፡ ፊልሙን የተመለከትኩት በብሔራዊ ቲያትር ቤት አዳራሽ ነበር፡፡ ፊልሙ ማራኪና ትምህርታዊ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በፊልሙ ሰክሪን ላይ የሚናገሩት ስለ እውነት ነበር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ነጻነትን ለመጎናጸፍ እረጅም መንገድ የተጓዙ ጎምቱ ምሁር ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻግር የፕሮፌሰር ማእረጋቸውን ከማግኘታቸው በፊት በርካታ የምርምር ጽፎችን አቅርበዋል፡፡ የምርምር ጽሁፎቻቸው ያተኩሩት በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና አለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያተኩሩ ጥልቀት ያላቸው ነበሩ፡፡ ከብዙ ሰዎች ሳይግባቡ መኖር አስቸጋሪ ነው፡፡ ብቸኝነትም ፈታኝ ነው፡፡ በነገራችን ላይ እውነት ተናጋሪዎች ጓደኞች የላቸውም፡፡ ስልጣን ያላቸው እውነቱን ፍርጥ አድረገው የሚነግሯቸውን ሰዎች ማቅረብ አይፈልጉም፡፡ ስልጣን የሌላቸው ደግሞ በፍርሃት ምክንያት ከእውነት ተናጋሪዎች ጋር መታየት አይፈልጉም፡፡ በአጭሩ በኢትዮጵያ ምድር እውነትን የሚፈልጉ፣ ለእውነት የቆሙ ሰዎች ጓደኞቻቸው በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ለእውነት በመቆማቸው ብቻ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል፣ ታስረዋል፡፡ ሆነም ግን ይሁንና ከእውነት አንዲት ጋት ፈቀቅ አላሉም፡፡ በተቃራኒው ፕሮፌሰር መስፍን እስከመጨረሻው ድረስ ህዝብን ማስተማራቸውን ቀጥለዋል፡፡ በእኔ በኩል ለፕሮፌሰር መስፍን ታላቅ አክብሮት አለኝ፡፡ እርሳቸው የአደባባይ ምሁር፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ጠባቂ፣ ጥሩ እና ታማኝ ሰው ነበሩ፡፡ አድርባይነት የእርሳቸው ባህሪ አልነበረም፡፡ ሊሆን የሚችለውን ነገር ምክንያት አያስቀረውም ባይ ናቸው፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ጨለማ በነበሩት አመታት አንጸባራቂ ኮከብ የነበሩ የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው፡፡ እርሳቸው ስለ ኢትዮጵያ የጻፉ፣ የተናገሩ፣ ያዳመጡ፣ ተምሳሌት የነበሩ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ 

አዳፍኔ በተሰኘው መጽሃፋቸው ላይ ‹‹ ኤመርሰን ›› የአለም አይን መሆኑን እንዳሳየው እርሳቸውም የኢትዮጵያ አይን መሆናቸውን አሳይተዋል፡፡ በመጽሃፋቸው ላይ የኢትዮያን ታላቅነት አብራተዋል፡፡ አሁን ያለው ትውልደ የአባቶቹን ታሪክ በመዘንጋቱ የትውልድ መቆራረጥ ሊከሰት እንደቻለ በሀዘን አስፍረዋል፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን የእኛ አቅጣጫ ጠቋሚያችን ነበሩ፡፡ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን የት እንደነበሩ፣ ወደፊት ምን ሊሆኑ እንደሚችሉ ያሳዩን ሰው ነበሩ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ለኢትዮጵያ ወጣት በእጅጉ የሚጨነቁ፣ የሚጠበቡ ሰው ነበሩ፡፡

እንደሚመስለኝ ‹‹ አዳፍኔ ›› የተሰኘው መጽሀፋቸው ማስታወሻነቱ ለኢትዮጵያ ወጣቶች ነው፡፡ 

ፕሮፌሰር መስፍን ወጣቱ ትውልድ በብዙ የአፍሪካ ሀገሮች እንደሚስተዋለው ወጣቱ ትውልድ በማንነት ቀውስ ውሰጥ እንዳይዘፈቅ ፣ የኢትዮጵን ታሪክ በቅጡ እንዲረዳ በብርቱ አስጠንቅቀውት ነበር፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ለወጣቱ ትውልድ በርካታ ሃላፊነቶችን ሰጥተውትም ነበር፡፡ ለአብነት ያህል እንደሚከተለው ለማስታወስ እሞክራለሁ፡፡

  • ኢትዮጵያን ከሞት ማዳን የምትችሉት ከጎሰኝነትና መንደርተኝነትነ እሳቤ ገሸሽ ለማለት መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ ስትችሉ ብቻ ነው፡፡
  • ኢትዮጵያን ማዳን የምትችሉት የተቋረጠውን የትውልድ ቅብብሎሽ ለማስቀጠል ስትችሉ ነው
  • ኢትዮጵያ የምትድነው ወጣቱ ትውልድ ለሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለህግ የበላይነት መከበር ሲል በሰውነት ደረጃ መቆም ሲችል ነው፡፡

ስለሆነም የኢትዮጵያ ወጣት የጎሰኞችን እና የጎሳ አምበሎችን የሴራ ገመድ በጣጥሶ  ኢትዮጵያን ከሞት መታደግ አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን በአንድ ወቅት በውጭ ሀገር የተሻ ኑሮ ስለሚመሩ ኢትዮጵያውያን ሲናገሩ ፣ በአሜሪካን ያለው ህይወት መልካም ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እንደ ኢትዮጵያ ያለ  ሀገር ማግኘት አይቻላችሁም፡፡ አንድ ቀን ኢትዮጵያን ተስፋ አደርጋለሁ ብለው ነበር፡፡ አንዳንድ የህሊና ሚዛናቸው ያልተሰበረ በውጪ ሀገር የሚኖሩ ( ኑሮ ከተባለ ማለቴ ነው) ኢትዮጵያውያን የፕሮፌሰሩን ፍልስፍናዊ ትንቢት ለመረዳት ይሞክራሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

በእኔ አስተያየት የአንድ ሰው ታላቅነት የሚለካው ጉልበት ለሌላቸው፣ ለተራቡ፣ ለታረዙ፣ ለተጠሙ ሰዎች የእውነትን ሃይል መናገር ሲቻለው ይመስለኛል፡፡

ማናቸውም ሰው ይኖራል፣ ኋላም ይሞታል፡፡ ይህ የተፈጥሮ ህግ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እረጅም እድሜ ለመኖር የታደሉ ይመስለኛል፡፡ ምክንያታዊ ህይወት ኖረዋል፡፡ ስልጣን ለሌላቸው፣ ለተራቡና ለተጠሙ ኢትዮጵያውያን የእውነትን ሃይል በተመለከተ እድሜ ልካቸውን ተናግረው አልፈዋል፡፡

ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ እንደጻፈው ‹‹ የአንድ ሰው ማንነቱ መለኪያው በተመቻቸ እና በጥሩ ሁኔታዎች ውስጥ ሳይሆን፣ በአስቸጋሪ እና አወዛጋቢ ጊዜያቶች በሚሳየው አቋሙ ነው፡፡ እውነተኛ ጎረቤት ለሌሎች ደህንነት ሲል የራሱን ስልጣን፣ ክብር እና ህይወቱን ጭምር አሳልፎ የሚሰጥ ነው፡፡

 

.

Dr. Martin Luther King, Jr. wrote, “The ultimate measure of a man is not where he stands in moments of comfort and convenience, but where he stands at times of challenge and controversy. The true neighbor will risk his position, his prestige, and even his life for the welfare of others.”

ፕሮፌሰር መስፍን እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ያሳለፉ ይመስለኛል፡፡ በብዙ ፈተናዎች እና አደጋ ውስጥ ያለፉ ሰው ናቸው፡፡ ህይወታቸው፣ነጻታቸው፣ ንብረታቸው፣ ክብራቸው፣ ወዘተ በአደጋ ውስጥ ብዙ ግዚያትን አልፏል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና  ነጻ ሆነው ኖረዋል፡፡ በነጻነትም ሞተዋል፡፡ ስለሆነም ‹‹ በነጻነት መኖር፣ በነጻነት መሞት››  ፕሮፌሰር መስፍን ትተውልን ያለፉት አስተምህሮ ነው፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሚያዚያ 2015 ‹‹ የት እንድንሄድ ይፈልጋሉ ? ›› በሚል ርእስ ባቀረቡት አስተያየት፡

  • የትም እንደማይሄዱ ለወያኔዎች አሳይተዋቸዋል ( አረጋግጠውላቸዋል)፡፡
  • በኢትዮጵያ ምድር በነጻነት ኑረው በነጻነት እንደሚሞቱ አሳይተዋቸዋል፡፡
  • በሞት ማሸነፍ እንደሚቻል ጽፈው አልፈዋል፡፡
  • ፐሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም በሞታቸው ድልን ተጎናጽፈዋል፡፡

የኢትዮጵያ አይን፣የኢትዮጵያ ጸሃፊ፣ስለ ኢትዮጵያ ተናጋሪ፣ስለ ኢትዮጵያ አድማጭ፣ የኢትዮጵያውያን ተምሳሌት፣ለእኔ ተምሳሌት በመሆኖ አመሰግናለሁ፡፡ ለሁሉም ሥራዎቾ አመሰግናለሁ፡፡ የእውነትን ሃያልነት ተናጋሪው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ነፍሶ በሰላም ትረፍ፡፡

የፕሮፌሰር መስፍን ማስታወሻ  ( ከ 1922- 2013 ዓ.ም.)

የመንፈሰ ጠንካራውን፣ አይበገሬውን እና ልበ ሙሉውን ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም መስከረም 19 ቀን 2013 እኩለ ለሊት ላይ ህልፈታቸው ሲሰማ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በከባድ ሀዘን ውስጥ ጠዱለው ነበር፡፡ ከመገናኛ ብዙሃን እንደተሰማው የ 90 አመቱ መስፍን በኮቪዲ 19 በሽ ምክንያት ነበር ያረፉት፡፡  ይህ ማስታወሻ የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘኋቸው ከ35 አመታት በፊት አዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ ኤኔሪኮ ኬክ ቤት ውስጥ የሚወዱትን ቡና ሲያጣጥሙ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍንን ኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ የሚለው ጽሰ ሃሳብ ብቻ የሚገልጻቸው አይመስለኝም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ኢትዮጵያዊ አርበኛ ይመስለኛል፡፡ እድሜ ልካቸውን ሙሉ ለኢትዮጵያ የደከሙ ናቸው፡፡ ኑሮአቸውን በምእራቡ አለም ካናዳ ያደረጉት ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚሊኪያስ የተባሉ ኢትዮጵያዊ በፕሮፌሰር መስፍን ከዚች አለም መለየት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ካሰፈሩ በኋላ  የፕሮፌሰርን የአርበኝነት ስሜት እንዲህ ሲሉ ነበር ያሰፈሩት፡፡

‹‹ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም የኢትዮ- አሜሪካን የካርተና ጂኦግራፊ ተቋም( at the Ethio-American Mapping and Geography Institute, )ተጠባባቂ ዳይሪክተር በነበሩበት ጊዜ እኔ የጄኔራል ዊንጌት ተማሪ ነበርኩ፡፡ እኔን ጨምሮ ሌሎች ሶስት የጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ተማሪዎች በተጠቀሰው ተቋም ተቀጥረን እንድንሰራ በፕሮፌሰር መስፍን በመመረጣችን በጊዜው የፕሮፌሰርን ኢትዮጵያዊ ስሜት ለመገንዘብ ችዬ ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መሰፍን በጊዜው ለነበሩት የተቋሙ ሃላፊዎች አሜሪካውያን ፍላጎትና አላማ አልተነበረከኩም ነበር፡፡ የነጮችን የበላይነት ለመቀበል አይምሮአቸው አልተቀበለውም ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት በግዜው የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ሚንስትር ክቡር ልጅ እንዳልካቸው መኮንን ትእዛዝ  ፕሮፌሰር መስፍን ከነበረቡት ሃላፊነት ተነስተው በአዲስ አበባ ዩነቨርስቲ ኮሌጅ በጂኦግራፊ የትምህርት ክፍል መድበዋቸዋል፡፡ እኔ እና ሶስቱ ጓደኞቼም ተቋሙን ለቀን ወደ ትምህርት ገበታችን ተመልሰናል፡፡ ( ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም. )

የአዲስ አበባ ዩነቨርስቲ ተማሪዎች ህብረት በእነ ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስና በበሌሎች በጊዜው በነበሩ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ከተመሰረተ በኋላ ይዘው የተነሱት መፈክር ‹‹ መሬት ላራሹ ›› የሚለው ነበር፡፡ በጊዜው የነበሩት የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ከሰሜን ኢትዮጵያ በድርቅና ጠኔ የተሰቃዩ ኢትዮጵያዊ ዜጎች አዲስ አበባ ሾላ ተብሎ በሚታወቅ ቀደምት ሰፈር ተጠልለውበት የነበረው መጠለያ በአጼ ሀይለስላሴ መንግስት ሲፈርስ ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ፕሮፌሰር መስፍን የተማሪዎችን ድምጽ አሰምተዋል፡፡ የመንግስት ተግባርም ትክክል አይደለም በማለት መሞገታቸውን ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ታሪክ መማር ይቻላል፡፡ ከዚህ በሻግር የዩንቨርስቲ ኮሌጅ ተማሪዎች ‹‹ ታገል ›› የተሰኘ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች መጽሔት በሚያዘጋጁበትም ጊዜ ተማሪዎች የሃሳብ ነጻነታቸውን ተተቅመው ሃሳባቸውን እንዲያሰሙ በረታቱ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ፕሮፌሰር መስፍን በዩንቨርስቲ ቅጥር ግቢ ውስጥ የአካዳሚክ ነጻነት እውን እንዲሆን እድሜ ልካቸውን ሙሉ ደክመዋል፡፡ ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ በጽሁፋቸው እንዳሰፈሩት እርሳቸውን ጨምሮ ( ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ )፣ ደክተር ሀይሌ ፊዳ፣ ብርሃነ መስቀል እረዳ፣ ዋለልኝ መኮንንና ለሌሎች ተማሪዎች ፕሮፌሰር መስፍን  ምክረ ሃሳብ አቅራቢ ነበሩ ወይም አስተማሪ ነበሩ፡፡ ከዚህ ባሻግር የዩነቨርስቲ ተማሪዎች ፕሬዜዴንት ጥላሁን ግዛው በአጼ ሀይለስላሴ ወታደሮች ሲገደልም በመቃወም የተማሪዎችን ትግል ደግፈው አንደነበር ከታሪክ እንማራለን፡፡

በ1954 ዓ.ም. ተካሄዶ በነበረውና በከሸፈው የእነ ጄኔራል መንግስቱ ንዋይ እና ወንድማቸው አቶ ግርማሜ ንዋይ መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ጊዜ የአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተማሪዎች ድጋፋቸውን ለማሳየት ከአራት ኪሎ እስከ ለገሃር ድረስ በአካሄዱት አመጽ ከፋኩሊቲው ተማሪዎቹን ተከትለው የሄዱት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ነበሩ፡፡ በመጨረሻም ፕሮፌሰሩ ለተማሪዎቹ በሰጡት ምክር የሀገሪቱን ህግ እንዲያከብሩ ስላሳሰቧቸው ተማሪዎቹ በወታደሮች ጥይት እንዳይገደሉ አድርገዋል፡፡ ( ፕሮፌሰር ጳውሎስ ሚልኪያስ)

It is important to note that a few years before, when during the abortive coup d’état lead by Mengistu and Germame Neway, the university college students demonstrated in support of the uprising, Mesfin was the only faculty member who accompanied the demonstrators from Arat Kilo to La Garre tendering advice to the young demonstrators as to what they should or should not do. At the end of the day, he saved the student demonstrators from a certain massacre by warning them not to disobey the orders of the pro-monarchist soldiers led by General Merid Mengesha,

ፕሮፌሰር መስፍን የዩንቨርስቲ ተመራማሪና አስተማሪ በነበሩበት ጊዜም ሆነ አሁን በስተመጨረሻ ጡረታ ከወጡም በኋላ ቢሆን ስለ ኢትዮጵያ ሀዝብ መናገራቸውን ፣ መጻፋቸውን አላቋጡም፡፡ እርስቻው ምንግዜም ቢሆን ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ የጻፏቸው በርካታ መጽሐፍት ፍንትው ብለው የሚያሳዩት ጥልቅ እውቀታቸውን ነው፡፡ የደርግ ጭፍጨፋ አሳምሟቸዋል፡፡ ወያኔ የፈጸመው ግፍ የበለጠ አሳምሟቸዋል፡፡ ሁለቱንም መጥፎ አገዛዞች ፊትለፊት ሞግተዋቸዋል፡፡ በተለይም የወያኔን የጎሳ አገዛዝ ክፉኛ ተችተውታል፡፡ ስለ ጎሳ ፖለቲካ አደገኝነት አይናቸው ደም እስኪመስል፣ እጃቸው እስኪዝል ጽዋል አስተምረዋል፡፡ ሰሚ ጆሮ አግኝተው ይሆን መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ትቼዋለሁ፡፡

የጎሳ ፖለቲካ አካሄድ ለኢትዮጵያ እንደማይጠቅማት በማስተማራቸው፣ ለነጻና ፍትሃዊ የምርጫ እውን መሆን በእውነት መሰረት ላይ በመቆማቸው፣ ለእኩልነት በመሟገታቸው፣ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች፣ ለህግ የበላይነት መከበር ሌት ተቀን በመድከማቸው የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ በተለያዩ ጊዜያት ዘብጥያ ወርውሯቸዋል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን የቅንጅት ለአንድነትና ዲሞክራሲ ( ቅንጅት) አንዲመሰረት ሁነኛውን ሚና የተጫወቱም ሰው ነበሩ፡፡ እንደ አውሮፓዊቷ አና ጎሜዝ የህሊና ፍርድ ከሆነ በታሪካዊው የግንቦት 1997 ዓ.ም. የምርጫ ፌሽታ አሸናፊ የነበረው ቅንጅት የተሰኘው የተቀዋሚዎች ስብስብ ነበር፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዜናዊ ግን ምርጫውን ያሸነፈው መንግስታቸው እንደሆነ የግፍ አገዛዘቸውን መቀጠላቸውን በታላቅ ሃዘን እናስታውሰዋለን፡፡ ሆኖም ግን  ፕሮፌሰር መሰፍን እና የትግል አጋሮቸቸቸው የወያኔ አገዛዝ  ምርጫውን አሸንፍኩ  ብሎ ያወጀው በተጭበረበረ ሁኔታ ስለሆነ ይህን ፌዝ ህሊናችን ሊቀበለው አይቻለውም በማለታቸው አለምበቃኝ እስር ቤት መወርወራቸው የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር በአለምበቃኝ ለሁለት አመት ቆይተዋል፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር ይሄን ስቃይ የተቀበሉት ለውዳሴ ከንቱ አልነበረም፣ ታላቅ ሰው ለመባልም አልነበረም፡፡ ለስልጣን ወይም ሀብት ጥማታቸውን ለማርካትም አልነበረም፡፡ እርሳቸው ስቃይን የተቀበሉት ከልብ በሚወዷት ሀገራቸው ኢትዮጵያ የሰለጠነ መንግስት እንዲቆም፣ ኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ሀገር እንድትሆን፣ ኢትዮጵያውያን አንገታቸውን ቀና አድርገው እንዲሄዱም ነበር፡፡ 

ፕሮፌሰር መስፍን ዛሬ ተለይተውናል፡፡ በአጼ ሀይለስላሴ መንግስት የመጨረሻ አመታት ፕሮፌሰር መስፍን የወሎ ርሃብ በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲታወቅ በማድረጋቸው ታሪክ ስፍራን አይነሳቸውም፡፡ በወያኔ አገዛዝ ደግሞ የሰብአዊ መብቶች እንዲከበሩ ላደረጉት ታላቅ ሥራ ሻምዮንነቱን ማንም ሊነጥቃቸው አይቻለውም፡፡ ከዚህ ባሻግር በኢትዮጵያ የዲሞክራቲክ ባህል እንዲዳብር በህትመት ውጤቶችም ሆነ በማህበራዊ ሚዲያ እስከ ህልፈተ ህይወታቸው ድረስ ሃሳባቸውን በማካፈል የሚታወቁ ብርቱ ሰው ነበሩ፡፡ ለእነኚህና ለሌሎች ጊዜ ለማይሽራቸው አብርክቶቻቸው የአለም ኖቤል ሰላም ተሸላሚ መሆን የሚገባቸው ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡

ፕሮፌሰር መስፍን ቢያልፉም በርካታ ማስታወሻዎችን ትተውልን አልፈዋል፡፡ ህልማቸው ዘላለማዊ ሻ ሆኖ ሲንቀለቀል ይኖራል፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን በወያኔ አገዛዝ የጨለማ ዘመን ኢትዮጵያዊነትን በልባችን ውስጥ ያስቀመጡ፣ ኢትዮጵያ ዲሞክራቲክና የነጻነት ሀገር እንድትሆን የራሳቸውን ሻማ የለኮሱ ዝንተ አለም የሚወሱ፣ የኢትዮጵያ አርበኛ ተብለው የሚጠሩ ሰው ናቸው፡፡ 

በአንድ የስብሰባ አዳራሽ ለተሰበሰበው ህዝብ ንግግር ሲያሰሙ፣ ወይም ለተመራማሪዎች በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ንግግር ሲሰሙ ድምጻቸው ጉልህ፣ ለኢትዮጵያ የሚደማ ልብም ያላቸው የኢትዮጵያ ልጅ ነበሩ፡፡ ስለሆነም የእርሳቸውን አርአያነት መከተል ውዴታ ብቻ ሳይሆን የህልውና ጉዳያችን ነው፡፡

.

Whenever Mesfin spoke of his people’s plight, in lectures or in political fora, his voice rang with valour, and boldness, and hope, and rocky conviction. Indeed, there has been no nationalist of his stature during our own lifetime. Instead of grieving, therefore, we must strive to be worthy of his example.

May God bless Professor Mesfin Wolde Mariam, and may he rest in eternal peace.

የኢትዮጵያ መልክአ ምድራዊ  አባት (The “Father of Geography of Ethiopia” )

ዶክተር ዮሃንስ አበራ በባህርዳር ፔዳጎጂካል ሳይንስ የጂኦግራፊ ዲፓርትመንት ተመራማሪና መምህር የነበሩ ሲሆን፣ ለጸሃፊው በርካታ የጂኦግራፊ ኮርስ ትምህርት ሰጥተውታል፡፡ ዶክተር ዮሃንስ የፕሮፌሰር መስፍንን አካዴሚክ ብቃት በተመለከተ አንደሚከተለው ጽፈዋል፡፡ 

‹‹ ባለፈው ሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም. በአማርኛ ቋንቋ ለመጀመሪያ ጊዜ ያዘጋጀሁትን የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ መጽሐፍ ኮፒ ለፕሮፌሰር መስፍን በመላክ አስተያየታቸውን ለማግኘት ሞክሬ ነበር፡፡ የመጽሐፉን ኮፒ ከመላኬ በፊት ፈቃደኝነታቸውን በኢሜይል ጤቄአቸው ነበር፡፡ አንድ ሰው በዘጠና አመቱ የተላከለትን መጽሐፍ አንብቦ ጥልቅ አስተያየት ለመስጠት አስቸጋሪ ሁኔታ ሊገጥመው እንደሚችል ይገባኛል፡፡ ከእርሳቸው ( እርሱ) የምጠብቀው ምላሽ የኢትዮጵያ ጂኦግራፊ አባት የሚለውን መጠሪያ እንዲቀበሉኝ ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ለላኩላቸው የመጽሀፉ ኮፒ ይህቺን አለም ከመሰናበታቸው በፊት ሊልኩልኝ አልቻሉም ነበር፡፡

Last July I sent the manuscript of my book on the Geography of Ethiopia, written for the first time in Amharic, to Professor Mesfin Woldemariam to review it and give me his blessings. I did that after a prior exchange of email messages asking him for his willingness to do so. I know that at the age of 90 it is difficult for him to go through my manuscript and give me detailed comments. What I expected from him was just a blessing as the “Father of Geography of Ethiopia”. He did not manage to return my manuscript before he passed away. (Dr. Yohannes Aberra
October 1, 2020 )

በፕሮፌሰር መስፍን ሞት ጥልቅ ሃዘን የተሰማኝ በኢትዮጵያ ውሰጥ ከሚገኙ ጥቂት ገለልተኛ እና ነጻነታቸውን ያስከበሩ አሳቢ ስለነበሩ ብቻ አይደለም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ያለኝን እምቅ ችሎታ በማየት ( በመረዳት) ህይወቴን ሙሉ በኖርኩበት የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል ገብቼ ጥናትና ምርምሬን እንድቀጥል ጥበባዊ ምክር ለጋሼ ስለነበሩ ነው፡፡ (he is my mentor who saw the potential in me and pulled me into the field of geography which became my life long profession )

ይህ የሆነው እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1973  ፕሮፌሰር መስፍን የጂኦግራፊ ዲፓርትመንት ሃላፊ በሆኑበት ጊዜ በቢሮአቸው በዛን ግዜ የአርት ህንጻ ዛሬ ኦሲአር በዛሬው አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ነበር፡፡ በአንደኛው ሴሚስተር ፕሮፌሰር መስፍን ( በአብዛኛው ተማሪ የሚታወቁት ጋሼ መስፍን በሚለው ስም ነበር ) የኢትዮጵያን ጂኦግራፊ አስተምረውኝ ነበር፡፡ ( taught me the Course Geog. 101 (Geography of Ethiopia). ) በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ይህን መጽሐፍ ያዘጋጁት እንደጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1972 የነበረ ሲሆን የዩንቨርስቲ ተማሪዎች የመማሪያ መጽሀፍ ሆኖ አገልግሏል፡፡ ጸሃፊው የአንደኛ አመት የዩንቨርስቲ ተማሪ በነበረበት ጊዜ የፕሮፌሰር መስፍንን መጽሐፍ ተምሮበት እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ከ1991ዎች መጀመሪያ ጀምሮ ግን የወያኔ አገዛዝ የፕሮፌሰር መስፍን የአይምሮ ጭማቂ መጽሀፍትን ከዩንቨርስቲ ቤተመጽሐፍቶች ውስጥ አውጥቶ እንደነበረ በሃዘን እናስታውሰዋለን፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ይህን መጽሐፍ ከማዘጋጀታቸው በፊት መላውን የኢትዮጵያ ግዛቶች በአካል በመገኘት ጥናትና ምርምር ማድረጋቸውን ዶክተር ዮሃንስ የህሊና ምስክርነታቸውን አስፍረዋል፡፡ ስለ ፕሮፌሰር መስፍን አስደናቂ የማስተማር ችሎታ በጠቀሱት ጽሁፋቸው ላይ ደግሞ ፕሮፌሰር መስፍን የኢትዮጵያን ጂኦግራፊ ትምህርት ለተማሪዎቻቸው ሲያስተምሩ መላውን ኢትዮጵያ ሲፈትሹ፣ ሲያጠኑ ያጋጠማቸውን አስደናቂ እና እውነተኛታሪኮች ስለሚያክሉበት በታላቅ ጉጉት እንደሚከታተሉ፣ ከሌሎች ኮርሶች ይልቅ ለፕሮፌሰር ኮርስ ብዙ ግዜ እንደሚሰጡ አስታውሰዋል፡፡  በውጤቱም ኤ “A”. አገኘሁ፡፡ ውጤቱ አስደናቂ ነበር፡፡ ምክንያቱም በካምፓሱ በሰፊው የሚነገር ወሬ ነበር፡፡ ጋሼ መስፍን ኤ ለእግዚአብሔር፣ ቢ፣ ለመስፍን፣ ሲ ለጎበዝ ተማሪ የሚል ውሳኔ አላቸው የሚል ነበር፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ለእግዚአብሔር ይሰጣል የተባለው የመስፍን ኤ ውጤት ለእኔ ተሰጠኝ በዚህም መንፈሴ ጠነከረ፣ ሞራሌ ተነሳሳ፣ የጂኦግራፊ ተማሪ ለመሆን ውሳኔ ላይ ደረስኩኝ፡፡ የአንደኛ አመት ተማሪ እያለሁ ያገኘሁት አጠቃላይ ውጤት የህግ፣ የምጣኔ ሀብት፣ ንግድ ስራ ወዘተ ተማሪ ለመሆን የሚያስችለኝ የነበረ ቢሆንም እኔ ግን የጂኦግራፊ ተመራማሪና አጥኚ ለመሆን ወሰንኩ በዚሁ መሰረት የመጀመሪያ ዲግሪ፣ ሁለተኛና ሶስተኛ ዲግሪዬን የጨበጥኩት በመልክአ ምድር ጥናት ነው፡፡ በነገራችን ላይ የጂኦግራፊ ተማሪ ለመሆን ፍላጎቴ የተጫረው በልጅነቴ ነበር፡፡ አንዳንድ ገንዘብ አምላኪ ምሁራን  የመልክአ ምድር ጥናት ዋጋ የለውም ማለታቸው ከባድ ስህተት ነው፡፡ የጂኦግራፊ ባለሙያዎች እውቀት ሰፊ እና ጥልቀት ያለው ነው፡፡ አለም ዛሬ ለገባችበት ከባድ ችግር የመልክአ ምድር ትምህርት ዘርፍ ሁነኛ መፍትሔ ያለውም ነው፡፡

 

The result I got for the Course was “A”. The result was a surprise because the widespread gossip in campus was Gashe Mesfin says: “A for God; B for Mesfin; and C for a bright student”. If Gashe Mesfin gives me A, which is Mesfin’s grade for God, I thought, then I am destined to be a geographer. My three Degrees (BA, MA, PhD) are all in Geography! Although my CGPA in the Freshman Programme was sufficient for others like law, business, etc fields I decided to join geography also motivated by my interest in the environment since childhood. Casting aside the business minded scholars who think that geography is a valueless field it has to be known to everyone that geography endows a broader and integrative mentality which is what the world needs now to solve its problems. (Dr. Yohannes Aberra
October 1, 2020  )

በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያ በአካዲሚክ የምርምር ስራዎች ላይ ( በተለይም በጂኦግራፊ የትምህርት መስክ ) ያበረከቱትን እጅግ ጠቃሚ እና ለሀገር መድህን የሚሆኑ ሃሳቦችን ገቢራዊ ለማድረግ የፖለቲካ ልዩነት ጋሬጣ መሆን የለበትም፡፡ በተለይም በድርቅና ጠኔ ምክንያትና ውጤት ላይ ያደረጉት ምርምር እጅግ ጠቃሚ ነው፡፡ በተለይም በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያዘጋጁት መጽሐፍ ‹‹ His seminal work on Famine Vulnerability ›› ጌዜ የማይሽረው እና ኢትዮጵያን በተወሰኑ አመታት እያሰለሰ የሚደቁሳትን ድርቅና ጠኔ ለመከላከል የሚረዳ መጽሀፍ በመሆኑ የመንግስት አካላት እና ጉዳዩ የሚያሳስባችሁ ምሁራን ለተመራማሪዎች መጽሐፉን በብዛት ቢያሳትሙት፣ በወያኔ አገዛዝ ውሳኔ ከዩንቨርስቲ ቤተመጽፍቶች ተለቃቅመው የት እንዳሉ የማይታወቁ መጽፍቶቻቸው እና የአይምሮ ጭማቂ የምርምር ውጤቶቻቸው ተመልሰው ለተመራማሪዎች የሚደርሱበት መንገድ ቢፈለግ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ የፕሮፌሰር መስፍንን ልእለ ስራዎች ህያው የሚሆኑት በአንድ ሰሞን ሆይሆይታ ሳይሆን መስፍን የምርምር ማእከል በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ተከፍቶ ስራዎቻቸው ለወጣት ተመራማሪዎች ምቹ ሁኔታ ሲፈጠር ብቻ ይመስለኛል፡፡ ሌላው ጥልቀት ያለው የምርምር ውጤታቸው ” Suffering under God’s Environment ›› የሚለው መጽሐፋቸው ይጠቀሳል፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር መስፍን ፖለቲከኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ብቻ ሳይሆኑ ሃይማኖተኛም እንደነበሩ ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም ፡፡ ስለሆነም ሶስቱንም ማንነታቸውን ሚዛናዊ በማድረግ በራሳቸው መንገድ ለመሄድ ምን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር አንባቢው ይረዳል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

 የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አባት

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የተመሰረተው እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በወርሃ መስከረም 1984 ነው፡፡ መስራቾቹም ወደ ሃያ ስምንት የሚጠጉ ኢትዮጵውያን ሲሆኑ፣ ከሙያ አኳያ የዩነቨርስቲ ምሁራን፣ ነጋዴዎች፣ የህግ ባለሙያዎች፣ አስተማሪዎች፣ ተመራማሪዎች ይገኙበታል፡፡ የሰብአዊ መብት አስከባሪ ድርጅት፣ ኢሰመጉን ለመመስረት የሃሳቡ አመንጪ ከሆኑት ግንባር ቀደም ሰዎች አንዱ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንደሆኑ ከተለያዩ ምሁራን ጽሁፎች ላይ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ለኢሰመጉ መወለድ የ28ቱ ሰዎች ጊዜ የማይሽረው፣ ጊዜ የማይከዳው ስራቸው ዘላለማዊ ሆኖ እንደሚቀጥል ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ የፕሮፌሰር መስፍንን ልእለ ሥራዎች ለየት የሚያደርገው ነገር ቢኖር፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ አባት በማለት የግል አስተያየቴን ለማቅረብ የደፈርኩት ላለፉት ሃያ ስምንት አመታት ያለመታከትና ያለመሰልቸት፣ እንዲሁም ያለፍርሃት፣በልበ ሙሉነት፣ በእውነት መሰረት ላይ ሆነው በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በተለይም ሃሳብን በነጻነት ስለ መግለጽ መብት፣ ስለ የሰብአዊ እና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ የህግ የበላይነት መከበር ወዘተ ወዘተ በመጻፋቸው ነበር፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን እስከመጨረሻው ድረስ ኢሰመጉን እንደ ልጃቸው ያዩ የነበሩ፣ ከዚህ ባሻግር የኢሰመጉ መጻኢ እድል በብርቱ የሚያሳስባቸው ሰው ነበሩ፡፡ ኢሰመጉን የስራ ሃላፊዎችና አባላት በሚያገኙበት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ኢሰመጉ አጠቃላይ ስራዎች ሳይጠይቁ አያልፉም ነበር፡፡ ምክንያታዊ መልስ ካላገኙም ፊትለፊት ይገስጹ፣ ይመክሩም ነበር፡፡

በነገራችን ላይ ኢሰመጉ መንግስታዊ፣ ፖለቲካዊና አትራፊ ያልሆነ ለሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር፣ ለህግ የበላይነት የቆመ የሰብአዊ መብቶች ተከራካሪ ድርጅት መሆኑን ማስታወሱ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡

የታላቁ ሰው ህልፈተ ህይወት በተሰማ ማግስት የኢሰመጉ ቦርድ አባላትና እና የጽ/ቤት ሃላፊ በስማቸው አመታዊ ሸልማት ለማዘጋጀት፣ የኢሰመጉ ቤተመጽሐፍት ቤት በስማቸው እንዲሰየም መወሰናቸውን አቶ አመሃ መኮንን የኢሰመጉ የቦርድ ሊቀመንበር ለመገናኛ ብዙሃን ከሰጡት መግለጫ ተሰምቷል፡፡ በእውነቱ ለመናገር ለኢሰመጉ ቤተሰቦችና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ሁኔታ ለሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን ሁሉ የመንፈስ ብርታትን የሚሰጥ ነበር፡፡

እንደ መደምደሚያ

ከልጅነት እስከ እውቀት፣ ማለትም እድሜ ዘመናቸውን ሙሉ በዩንቨርስቲ ተመራማሪነት፣ ፖለቲከኛነት፣ የሰብአዊ መብት ተሟጋችነት፣ የእውነት ሃያልነትን በመናገር ያሳለፉት ፕሮፌሰር መስፍን ዛሬ በህይወት አጠገባችን የሉም፡፡ ሁላችንም ወደማንቀርበት ሞት ነጥቆናል፡፡ ወደር የማይገኝለት ስራቸው ግን ህያው ሆኖ ይቀጥላል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ለእውነት ኖሮ በዘጠና አመት ከዚህ አለም መለየት ክብር ነው

ፕሮፌሰር መስፍን ታላቅ ምሁርና ዋርካ ነበሩ ። ማንንም የማይፈሩ ለሀቅ የቆሙ የመብት ተሟጋች ነበሩ ። በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ተማሪዎችን ላለፉት ስልሳ አመታት ካገራቸው ጋር ጥብቅ የሆነ መተዋወቅ ኖሯቸው ያገር ፍቅር እንዲኖራቸው አድርጓገዋል ። ፕሮፌሰር መስፍን አመመኝ ደከመኝ ሳይሉ ሳያቋርጡ ሁሌ ፕሮጄክቶች አሏቸው ። ሳይደክሙ ይጽፋሉ ። ሀሳቡቸውን ያጋራሉ ። ይሟገታሉ ። ይከራከራሉ ። ይጣላሉ ።  ቂም ግን አይዙም ። ጠባቸውም ሳይቀር ለማስተማር ነው ።

ፕሮፌሰር መስፍን ጥልቅ ተመራማሪ ነበሩ ። የሚወዱትን የኢትዮጵያን ጆግራፊና የገጠር ኢኮኖሚ መረጃ የሚሰበስቡት በየአካባቢው በመሄድ በግና ፍየል በመቁጠር ብቻ ሳይሆን ፣ ኩበትና ጭድ ፣ ወዘተ በመቁጠር ላይ የተመሰረተ እስካሁን ቤታቸው መረጃው የሚገኝ ጥናት ላይ የተመሰረተ ጥናት መሰረት ያደረገ ነው ። ምርምራቸው የጂዎግራፊ ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ የሆነ የአማርኛ የቃላትን ጥንታዊ አመጣጥና አጠቃቀም በተመለከተ ለወደፊቱ ምሁራን የሚመራመሩበት ገና ያልታተሙ ብዙ ስብስብ ቦታ በጠባብ ቤታቸው እንዳለ ተማሪያቸው የነበሩት ዶክተር አበበ ሀረገወይን በአንድ ጽሁፋቸው ላይ አስቀምጠውታል፡፡ 

ለእኔ የሚዸንቀኝ ጉልበታቸውንና  ጽናታቸውን ከየት እንደሚያመጡት ነው ። የአእምሮው ላንድ ሰከንድ አለማረፍና ምንም እድሜ የማይወስነው አዲስ ነገር ለመማር ያላቸው ሌላው ልዩ ተሰጥኦው  እንደሆነ በርካታ ምሁራን የሚስማሙበት ነው ። ፍራቻ የሚባለው እርሳቸው ዘንድ ይርሽ ብላ አታውቅም ። የሰው አምበሳ ናቸው ። እውነትን የያዘ ፍርሀት የለውም ። በመታሰርና በመንገላታት ከፍለውበታል ።

ፕሮፌሰር መስፍን የዘመናዊ ትውልድ መቋጫና በልዩ መልኩ መደምደሚያ ናቸው ። ያገራችንን ታላላቅ አርበኞችና ባለውለታዎች በልባችን ህያው እንደሆኑት እርሳቸውም መምሕራችንና አባታችን ህያው ይሆናሉ ። 

ፕሮፌሰር መስፍንን የሰጠን ቸሩ አምላካችን ይክበር ይመስገን ።

 

 ይህ እውን እንዲሆን ግን የሚከተሉት ተግባራት በመንግስትና ኢትዮጵያዊ ወዳጆቻቸው እንዲከወን ስጠይቅ በታላቅ አክብሮትና ትህትና ነው፡፡

  • ለአካዳሚክ ነጻነትና በጂኦግራፊ የትምህርት ዘርፍ ላበረከቱት ታላቅ አስተዋጽኦ ሲባል የስድስት ኪሎ ዋናው ካምፓስ በስማቸው እንደሰየም የግል ሃሳቤን አቀርባለሁኝ
  • የነጻነት አደባባይ በሚል ስያሜ  ሃውልታቸው ቆሞ ወጣቱ ትውልድ የነጻነት ትርጉም ቢረዳ የሚለው ሌላው የግል አስተያየቴ ነው፡፡
  • የፍትህ መጽሔት ዝግጅት ክፍል ባልደረቦች ብርርቱ እንዳሰሰበውና በአክብሮት እንደጠየቁት እኔም ለብዙ አስርተ አመታት የኖሩበት አፓርትሜንት ላይ የሚገኘው የቤት ቁጥር 1 መኖሪያ ቤታቸው ሙዚየም እንዲሆን የኢትዮጵያን መንግስት እማጸናለሁ፡፡

እስቲ  ብሔራዊ ተምሳሌቶቻችንን ማክበር፣ ከእነርሱ መማር እንጀምር፡፡

እንደ ፕሮፌሰር መስፍን ተማሪ፣ አድናቂ፣ ተከታይ፣ አክባሪ፣ ወዘተ የእርሳቸውን ሌጋሲ ለማስቀጠል ሁላችንም ለህሊናችን ቃል እንግባ፡፡ As to us, his students, we will carry on his legacy

May God bless Professor Mesfin Wolde Mariam, and may he rest in eternal peace

Filed in: Amharic