>
5:13 pm - Thursday April 20, 0180

" በምርጫ ቦርድ አዋጅ መሰረት ህውሓት መታገድ ወይም መሰረዝ ነበረበት...!?!"  (አቻሜለህ ታምሩ)

” በምርጫ ቦርድ አዋጅ መሰረት ህውሓት መታገድ ወይም መሰረዝ ነበረበት…!?!” 

አቻሜለህ ታምሩ 

“በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት”  ጸደቀ በተባለው የምርጫ ቦርድ አዋጅ  አንቀጽ ፺፰ ንዑስ አንቀጽ ፪ ላይ የተጠቀሰውን ጥፋት ፈጽሞ የአዋጁ ቅጣት ተፈጻሚ የማይሆንባት ሕወሓት!
በብርቱካ ሜዴቅሳ የሚመራው ምርጫ ቦርድ ከሁለት ዓመት በፊት  “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ” የሚል አዋጅ አርቅቆ  “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” እንዲጽድቅ ካደረገ በኋላ ባለፈው ዓመት ጥቅምት ፭ ቀን ፪ ሺ ፲፪ ዓ.ም በወጣው ነጋሪት ጋዜጣ ላይ “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” የጸደቀውን የምርጫ አዋጅ ታትሞ እንዲወጣ አድርጓል። ዛሬ በስራ ላይ ያለው ይህ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አንቀጽ ፺፰ የሚያወራው የፖለቲካ ፓርቲን በቦርዱ ውሳኔ ከምዝገባ ስለመሰረዝ ነው።
የአንቀጹ ንዑስ አንቀጽ ፪ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በቦርዱ ውሳኔ ስለሚሰረዝበት ሁኔታ ሲደነግግ እንዲህ ይላል፤
“ቦርዱ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ (፩) ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ጋር ተመጣጣኝ የሆኑ የዚህ አዋጅ ድንጋጌዎችን ጥሷል ብሎ ሲያምን ፓርቲው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ስህተቱን እንዲያስተካክል የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል፡፡ በማስጠንቀቂያው መሠረት ያላስተካከለ እንደሆነ እንደ አግባብነቱ ከምዝገባ ሊሰርዘው ይችላል፡፡”
ይህን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ  አንቀጽ ፺፰ ንዑስ  አንቀጽ ፪ ይዘን ባለፈው ዓመት መጨረሻ ላይ በትግራይ ክልል ተካሄደ በተባለው ምርጫ የተሳተፉ ፓርቲዎች ይህን የምርጫ ቦርድ አዋጅ መጣስ አለመጣሳቸውን ስንመረምር ምርጫ ቦርድ ራሱ የትግራይ ክልል ምርጫ “ኢ-ሕገ መንግስታዊ” እንደሆነ እና የፌደረሽን ምክር ቤት ተብዮው ደግሞ  “የትግራዩ ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠር፣ የማይጸናና ተፈፃሚነት የሌለው ነው” በሚል የተሰጡ መግለጫዎችን እናገኛለን። ይህ ማለት በትግራይ ክልል ውስጥ ተካሄደ በተባለው ምርጫ የተሳተፉ ፓርቲዎች ሁሉ “ኢ-ሕገ መንግስታዊ” የተባለ ምርጫ አካል በመሆን የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አንቀጽ ፺፰ ንዑስ አንቀጽ ፪  ላይ  የፖለቲካ ፓርቲ በቦርዱ ውሳኔ እንዲሰረዝ ያደርጋሉ  በሚል የቀረቡ ጥሰቶችን ሁሉ ፈጽመዋል ማለት ነው።
ምርጫ ቦርድ ግን  “ሕገ መንግሥቱን ጥሷል” በተባለው ምርጫ በመሳተፍ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አንቀጽ ፺፰ ንዑስ አንቀጽ ፪ ላይ የተጠቀሰውን ጥፋት የፈጸሙ  የፖለቲካ ፓርቲዎችን  እስከዚህ ሰዓት ድረስ አልሰረዘም!
ወይዘሪት ብርቱካን ሜዴቅሳ  የምትመራው ቦርድ የሚተዳደረው “የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር” በሚል በተረቀቀውና  “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት” በጸደቀው አዋጅ መሆኑን በተደጋጋሚ ነግራናለች። ይህ ወይዘሪት ብርቱካን ቦርዱን የምታስተዳድርበት አዋጅ አንቀጽ ፺፰ ንዑስ  አንቀጽ ፪ “ኢ-ሕገ መንግስታዊ” የተባለ ተግባር ላይ የተሰማራ ፓርቲ በምርጫ ቦርድ ውሳኔ እንደሚሰረዝ ይደነግጋል። ትግራይ ክልል ተካሄደ የተባለ ምርጫ “ኢ-ሕገ መንግስታዊ” ነው ከተባለ በዚህ “ኢ-ሕገ መንግስታዊ” ነው በተባለው ምርጫ ላይ ተሳትፈው  የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አንቀጽ ፺፰ ንዑስ አንቀጽ ፪ ላይ  የተጠቀሰውን ጥፋት የፈጸሙትን እንደ ሕወሓት አይነት ፓርቲዎች በአዋጁ መሰረት ለምን ምርጫ ቦርድ አልሰረዛቸውም? ነው ወይስ “ኢ-ሕገ መንግስታዊ” ነው በተባለው ምርጫ ላይ ተሳትፎ የኢትዮጵያ የምርጫ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ሥነ ምግባር አዋጅ አንቀጽ ፺፰ ንዑስ አንቀጽ ፪  ላይ  የተጠቀሰውን ጥፋት የፈጸሙ ሕወሓት ድርጊት ምርጫ ቦርድ  የተቋቋመበትን አዋጅ እንደጣሰ አይቆጠርም?
Filed in: Amharic