>

የአለቃ ዘነበ የህይወትን የስራ ውጣ ውረድ  ከ1817-1869 ዓ.ም  (ሳሚ ዮሴፍ)

የአለቃ ዘነበ የህይወትን የስራ ውጣ ውረድ  ከ1817-1869 ዓ.ም 

ሳሚ ዮሴፍ

“ቅቤ ለመጽሐፍ ዘመዱ አይደለም፤ መጽሐፍ ግን ለሰው ቅቤ ነው” (መጽሐፈ ጨዋታ)
 
* በ1924 ዓ.ም “መጽሐፈ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ” የተባለ አንድ ወግ- አዘል ድርሰት በአዲስ አበባ ከተማ ታተመ። 
የመጽሐፉ አሳታሚ በብላቴን ጌታ ህሩይ ወልደ ሥላሴ የተቋቋመው “ጎህ ጽባህ ማተሚያ ቤት” ነበር። ደራሲው ደግሞ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመን ጽሑፎቻቸው የታወቁት አለቃ ዘነበ ነበሩ። መቶ ሃምሳ ዓመት በላይ ያስቆጠረው ይህ የአለቃ ዘነበ ድርሰት እስከዛሬ ድረስ የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ እድገት መነሻ ተደርጎ ይታያል።
አለቃ ዘነበ በ1810ዎቹ አጋማሽ (አንዳንድ ሰነዶች 1817) በሸዋ በይፋት አካባቢ ተወለዱ። በ1820ዎቹ የልጅነታቸውንና የትምህርት ዘመናቸውን በዚያው በሸዋ ወይም በሌላ ቦታ እንዳሳለፉ መረጃው የለም። ቢሆንም በአካል ያገኟቸው ሰዎች እንደሚመሰክሩት አለቃ ጠለቅ ካለ የማወቅ ጉጉት በተጨማሪ የግዕዝ ሰዋሰው፣ የአቡሻክር
 (ቀን አቆጣጠር) እና የጽሕፈት ሙያ ነበራቸው። አለቃ ዘነበን የያዛቸው ይህ የትምህርት እና የቋንቋ እውቀት ጥማትም፣ ወደፊት እንደምናየው በብዙ የድርሰት መስኮች (ታሪክ፣ ወግ፣ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም) ፈር-ቀዳጅ እንዲሆኑ ያገዛቸው ይመስላል።
ደብተራ ዘነበ በ1830ዎቹ እንደመነኮሱ የተወሰኑ የውጭ ሰነዶች ይናገራሉ። ነገር ግን ይህ መጠሪያቸው አንድም ከመነኩሴነታቸው፣ አንድም ደግሞ የባህር ማዶ ሰዎች የሀገራችንን የባህልና የማዕረግ ሥርዓት በሚገባ ካለመረዳቻው የመነጨ ሊሆን ይችላል። “አባ ዘነበ” ባዮችም በደብረ ታቦር አካባቢ ጋፋት የሰፈሩት መድፍ ሰሪ ሚሲዮናውያን (st. Chrischona pilgermision) ነበሩ።
በ1840ዎቹ ደብተራ ዘነበ በማናውቀው ሁኔታ እጣቻው ከአባ ታጠቅ ካሣ ጋር መጣመር ይጀምራል። የቋራው ደጃዝማዥ ካሣም አፄ ቴዎድሮስ ተብለው በ1847 ዓ.ም ሀገሪቱን ሲገዙ ዜና መዋዕላቸውን እንዲፅፉ የሾሟቸው ደብተራ ዘነበን ነበር። ደብተራ ዘነበም ከልጅነት ጀምሮ እስከ 1852 ዓ.ም ድረስ ያለውን የቴዎድሮስን ታሪክ (በመቅደላ ከመሞታቸው ከስምንት ዓመት በፊት) ውብ በሆነ አማርኛ ጽፈውታል። ይህም ፈር- ቀዳጅ ድርሰታቸው ቀዳሚው የአማርኛ ዜና ወዋዕል ተደርጎ በሰፊው ይጠቀሳል።
ከደብረ ታቦር እስከ መቅደላ (ከ1847_ 1860)
“ዝናም ከዘነመ በኋላ ቡቃያ ያበቅላል፤ ንጉሥም ከወደደ በኋላ ይሾማል።” (መጽሐፈ ጨዋታ)
አለቃ ዘነበ በአፄ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግሥት ስመ ጥር የቤተመንግሥት ቧለሟል የነበሩ ይመስላሉ። በጸሐፌ ትእዛዝነታቸው እስከ 1950ዎቹ መጀመሪያ ድረስም አገልግለዋል። ከ1852 አጋማሽ እስከ መጋቢት 1860 ዓ.ም ደግሞ የመዝገቤት ሹም ሆነው በመቅደላ ቆይተዋል።
የዘመኑን ታሪክ ከፃፉት መሀል አንዱ የሆኑት አለቃ ወልደ ማርያም እንደሚሉት አለቃ ዘነበ የድርሰት ብቻ ሳይሆን ሌላም ሙያ ነበራቸው።
“በዚህ ዘመን በሰው ሁሉ ብዙ መከራ ነበረበት። በየሀገሩም በመቅደላ ሌሊት እየገባ ጅብ ሲበላ ሰዉን ሁሉ አስጨነቀ። በዚህም ጭንቅ ነፍጠኛ ሁሉ መክሮ በየደጁ ሲተኩስ ብዙ ጅብ አለቀ። አለቃ ዘነበ የሚባልም ለአፄ ቴዎድሮስ የተወደደ ጸሐፊ የሸዋ ሰው ለብቻው ከዳጁ ላይ 11 ጅብ ገደለ።”
(የቴዎድሮስ ታሪክ ገጽ ፵፮)
ከላይ የሚነበበው ቃልም በተራው “መጽሐፈ ጨዋታ” ላይ አለቀ ዘነበ በነፍጥ ዙሪያ ያነሷቸውን ወጎች በመጠኑ ያስታውሰናል።
“ተጌጥ መልካም ነው ወርቅና ብር፤ ለሰልፍስ መልካም ባሩድና አረር…ለሰውስ መልካም ነው ሀገር፣ ለወገብስ መልካም ነው ዝናር…ካረር ማን ይውላል ነፍጠኛ፤ ከሜዳ ማን ይውላል ፈረሰኛ…ፍቅር ዘውድ ነው፣ መልካም ጠባይ ዝናር ነው።” (መጽሐፈ ጨዋታ)
እንዳጋጣሚ ሆኖ ከ1850 ዎቹ እስከ 1869 ዓ.ም ባሉት ዓመታት ስለ አለቃ ዘነበ በርከት ያሉ መረጃዎችን እናገኛለን።
ለዚህም ዋናው ምክንያት ከ1850 ዓ.ም መባቻ ጀምሮ አለቃ ዘነበ በሚሲዮናውያኑ ሰንድ ውስጥ መጠቀስ መጀመራቸው ነው። በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩት የተለያዩ ኃይማኖት ሚሲዮኖች በቀላሉ ለመንቀሳቀስ አይችሉም ነበር። በአንድ በኩል ወንጌልን በአደባባይ መስበክ ስለማይፋቀድላቸው በየቤታቸው ትምህርት በመስጠትና በሀገሪቱ የታተሙትን ወንጌሎች በማከፋፈል ይሠሩ ነበር። በሌላ በኩል ደግሞ አዳዲስ አማኞችን ወደ ሚሲዮኑ እምነት
(ወንጌላዊ ወይም ካቶሊክ)  ሳይሆን ወደ ኦርቶዶክስ ክርስትና ማስጠመቅ ይገደዱ ነበር። እና ሰነዶቹ እንደሚገልጹት በ1850 ዓ.ም መባቻ አፄ ቴዎድሮስ በጋፋት ያሉትን ባለሙያ ሚሲዮናውያን አማርኛ የሚያስጠና አንድ ሊቅ ይመድባሉ። መምህር ሆነው የተመረጡትም የያኔው ደብተራ/አለቃ ዘነበ ነበሩ። እሳቸውም እኒህን ሚሲዮናውያን ቋንቋ በማስታማር ሳሉ እግረ መንገዳቸውን በቅርቡ ታትሞ የተሰራጨውን የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ በጥልቀት ማንበብ ሳይጀምሩ አይቀርም። በዚህም ምክንያት ብዙ ሳይቆዩ ወንጌልን የመስበክ ጠንካራ ፍላጎት አድሮባቸው ከ1861 ዓ.ም ጀምሮ ይህንን ተልዕኮ የተያያዙት ይመስላል።
በ1852 ዓ.ም አለቃ ዘነበ የአፄ ቴዎድሮስ ጸሐፌ ትእዛዝነታቸው አበቃ። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም እሳቸው የደረሱት “የቴዎድሮስ ታሪክ” በዚሁ ዓመት ዘገባ የሚያቋርጠው። አፄ ቴዎድሮስም በተራቸው አለቃ እንግዳን አዲሱ ጸሐፌ ትእዛዛቸው አድርገው ሲሾሙ አለቃ ዘነበን ደግሞ (በግዞት ይሁን በሹመት) የመዝገቤት ሹም አሰኝተው ወደ መቅደላ ላኳቸው። መቅደላም በነበሩባቸው ዓመታት (ከ1852-1860 ዓ.ም) አለቃ ዘነበ ለአምባው ወታደሮች ወንጌልን በአማርኛ መስበክ የጀመሩ ይመስላል።
አለቃ ዘነበ መቅደላ ሳሉ ከመዝገቤት ኃላፊነታቸው ባሻገርም
በጸሐፊነት ሙያቸው ቀጥለዋል።  በጊዜው ከቀዷቸው በርካታ ብራናዎችም ቢያንስ አንዱ ለትውልድ ተርፏል።
ይህንንም የዳዊት ብራና በመቅደላ ሳሉ በእጃቸው የጻፉት አለቃ ዘነበና መልአከ ገነት ወልደ መስቀል ሲሆኑ ወቅቱም በ1852 ዓ.ም ነበር። አለቃ ዘነበ መቅደላ ሳሉ በርካታ ድርሰቶችን ሥነ ጽሑፍ አበርክተዋል።
* የቴዎድሮስ ታሪክ (1852 ዓ.ም)
* መጽሐፈ ጨዋታ (1856 ዓ.ም)
* የኦሮምኛና አገውኛ መዝገበ ቃላት (1860 ዓ.ም)
በዚህም ዘመን አለቃ ዘነበ ከሚሲዮናውያኑ Martin Flad እና Johannes Meyer እንግሊዝኛ መማር ጀምረው ነበር።
በተራቸውም ኦሮምኛን ያስተምሩ ነበር። የዘመኑ ሰነዶች እንደሚሉት አለቃ ወደፊት ወንጌልን በኦሮምኛ ለመስበክ እንዲችሉ እየተዘጋጁ የነበረ ይመስላል።
ከመቅደላ እስከ አድዋ (ከ1860-1864)
“በርበሬ ላይን ቀይ ሆኖ ይታያል፤ ምነው ቢሉ በብልሃት ገብቶ ሊለበልብ። ክፉ ሰውም ቀስ ብሎ ገብቶ ኋላ ነገሩን ያመጣል።” (መጽሐፈ ጨዋታ)
ብዙም ሳይቆዩ አፄ ቴዎድሮስ በመቅደላ አረፉ። አለቃ ዘነበም የደጃዝማች ዓለማየሁ ሞግዚት ሆነው በእንግሊዙ ጦር ተመደቡ። በሞግዚትነት የተመረጡበትም ሁኔታ በወቅቱ የእንግሊዝን መንግሥት ወክሎ በአስተርጓሚነት ያገለግል የነበረው ሶርያዊው ራሰም (Hormuzd-  Rassam) ሲገልጽ…
“በእኔው አመልካችነት አለቃ ዘነበ የሚባለው ኢትዮጵያዊ ጻድቅ ክርስቲያን የአፄ ቴዎድሮስ የመዝገብ ቤት ኃላፊ የነበረው፣ ለዓለማየሁ ሞግዚት ሆኖት አብሮት እንዲሄድ ተፈቀደ። በኋላ ግን በየምክንያቱ አብሮት ሊሄድ አልቻለም”
(ተክለፃዲቅ መኩሪያ)
ምክንያቱም እንዲህ ነበር አለቃ ዘነበ ከእንግሊዞች ጋር የጌታቸውን ልጅ ተከትለው ሰንአፈ ድረስ ተጓዙ። ሰንአፈም ላይ ከደጃች ዓለማየሁ ጋር በመርከብ ተሳፍረው በግብጽ የስዊዝ ካናል ሊደርሱ ሲሉ አንድ ችግር ተፈጠረ።
 ካፒቴን ስፒዲ (ባሻ ፈለቀ) ዓለማየሁ እሳቸውን እንደማይፈልጋቸው ከነገራቸው በኋላ እቃውን ተቀብሏቸው ዓለማየሁን ይዞ ተጓዘ።
“ታላቅ በደልና ግፍ ደርሶብናል። በሀገራችን አንድን ሰው ማባበል ነውር አይደለምን? ምንም እንኳን ሐበሻ ጥቁር ቢሆን በአርአያ ሥላሴ አልተፈጠረምን? በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነፃ አልወጣም?…ይህንንም አሁን የጻፍኩት የእንግሊዝ ሕዝበ ክርስቲያን እንዲያውቀው ብዬ ነው።
አለቃ ዘነበ ለkrapf ኅዳር 8 1861 ዓ.ም ምፅዋ።
በዚህም ምክንያት አለቃ ዘነበ ግብጽ ድረስ ደርሰው ደጃች ዓለማየሁን ሳይሰናበቱ ኢየሩሳሌምን ሳይሳለሙ በመመለስ ለበርካታ ወራት በምፅዋ ለእንግልት ተዳረጉ። በምጽዋ ቆይታቸውም ከፈረንሳይ ምክትል ቆንስሉ ሙንዚንገር ዘንድ አርፈው የተወሰኑ መጻሕፍትን የጻፉ ይመስላል። በሙንዚንገር ገፋፊነትም (እስከ ዛሬ ሊገኝ ያልተቻለ) ሁለተኛውን የአፄ ቴዎድሮስ ታሪክን ሳያዘጋጁ አይቀርም። በመቀጠልም ለሚሲዮናዊ ሥራ እንዲሆን አራቱን ወንጌላት ወደ ኦሮምኛ በትጋት ተርገመው ወደ ጀርመን ሀገር ላኩ። ለዓመት ያህል ምፅዋ ከቆዩም በኋላ በመጋቢት 1861 ዓ.ም ከሁለት ሚሲዮናውያን ጋር በመሆን በእንግሊዝ የታተመውን የአማርኛ ወንጌልን ለማሰራጨት British Foreign Bibel Society
ሥር ተቀጥረው ወደ አድዋ አመሩ። በአድዋ ቆይታቸው ውስጥ (ከ1861- 1864 ዓ.ም) አለቃ ዘነበ የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎችን ለአካባቢው ነዋሪዎች በማሰራጨትና የኦሮምኛ ቋንቋ እውቀታቸውን በጥናት በማዳበር ጊዚያቸውን ያሳለፉ ይመስላል። ብዙም ሳይቆዩ  እሳቸው ተርጉመው (ወይም የመጽሐፉ ሽፋን እንደሚለው ጽፈው) የጨረሱት ኦሮምኛው ዳዊት አድዋ ሳሉ ታተመ።
መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ኦሮምኛ የመተርጎም ሥራ በማስፋፋት ከሌሎች የቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር (ዋሬ፣ ሩፎ፣ ሾለን፣ ጀገን እና ገብረ ሚካኤል)  በመተባበር ሙሉውን አዲስ ኪዳን ወደ ኦሮምኛ ተርጉመው በሰኔ 1862 ዓ.ም አገባደዱ። ይህም ትርጉማቸው ለኦሮምኛ ሥነ ጽሑፍ የመጀመሪያው አዲስ ኪዳን መሆኑ ነው። ከጥቂት ዓመታት በኋላም ሚሲዮኑ ክራፍ
(J.L Krapf) በ1869 በራሱ ስም  ያሳተመው ይህ የአለቃ ዘነበን ሥራ ነበር።
ታዲያ የአለቃ ዘነበና የባልደረቦቻቸው ትርጉም እንደ ፈር ቀዳጅነቱ ያህል በአንዳንድ የቋንቋው ምሁራን ብዙውን የተወደደ አይመስልም። ሙሉውን መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ኦሮምኛ የመለሰው ታታሪው ኦነሲሞስ ነሲብ ሥራውን ሲጀምር የነ አለቃ ዘነበን ትርጉም መሠረት ለማድረግ ሞክሮ ነበር። ሆኖም የነ አለቃ ዘነበ የአዲስ ኪዳን ትርጉም በርካታ የፊደል ስህተቶች፣ የቃላት አመራረጥ፣ የግስ እርባታ አካሄድ ችግሮች ስለነበሩት ኦነሲሞስ መጽሐፍ ቅዱስን ከእንደገና ወደ ኦሮምኛ ለመተርጎም እንደተገደደ ይናገራል።
አለቃ ዘነበ አድዋ በገቡ በዓመታቸው (ሚያዝያ1862 ዓ.ም)
ያልጠበቁት ደብዳቤ ከምኒልክ ደረሳቸው።
ይቀጥላል….
Filed in: Amharic