>

በእስር ላይ የሚገኘው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ  የፔንን ሽልማት አሸነፈ...!!! (ይታገሱ አምባዬ)

በእስር ላይ የሚገኘው ኤርትራዊ ጋዜጠኛ  የፔንን ሽልማት አሸነፈ…!!!

ይታገሱ አምባዬ

 

ለሁለት አስርት አመታት በእስር የሚማቅቀው ኤርትራዊው ጋዜጠኛና ገጣሚ አማኑኤል አስራት አለም አቀፉን የፔን ሽልማት አሸንፏል።
ሽልማቱም በሚፅፉት ወይም በሚናገሩት ነገር የሚደርስባቸውን ጫናና ጣልቃ ገብነት ተቋቁመው የበለጠ ወኔ ላሳዩ ፀሃፊዎች እውቅናን የሚሰጥ ሲሆን አማኑኤልም “አለም አቀፉ ደፋር ፀሃፊ” በሚል ስያሜም ሽልማቱን ተቀናጅቷል።
ሽልማቱ ይፋ የተደረገው በትናንትናው ዕለት ሲሆን የፔን ፒንተር ሽልማት የዘንድሮ አሸናፊ ጃማይካዊ-እንግሊዛዊ ገጣሚ ሊንተን ክዌሲ ጆንሰን ነው ማሸነፉን በበይነ መረብ በነበረ የቀጥታ ዝግጅት ላይ አሳውቋል።
አማኑኤል አስራት ሁለት አስርታት አመት ለሚጠጋ በእስር ላይ ያለ ጋዜጠኛ ሲሆን ሽልማቱም እሱ በሌለበት ነው የተሰጠው።
በፕሮግራሙ ላይ የተሳተፈው የአማኑኤል ወንድም ከጋዜጠኛው ስራዎች አንዱ የሆነውን ግጥምም አቅርቧል።
አማኑኤል በኤርትራ ውስጥ በ90ዎቹ ላንሰራራው የግጥም አብዮትም ጋር ተሳስሮ ይጠራል።
በግጥሞቹ የተሸለመው አማኑኤል ፅሁፎቹም ጦርነት፣ ሰላምን እንዲሁም በዝቅተኛ ኑሮ ያሉ ሰዎች ዬየእለቱን ኑሯቸውን እንዴት ይገፉታል በሚልም በውብ ቋንቋ ይፅፋል ይሉታል።
በኤርትራ ያለው ማህበራዊ ችግር፣ ፍቅርና ተስፋን በጥልቀት የሚገልጹ ስራዎች ያቀርብ እንደነበር ፔን ኤርትራ በድረ ገጹ ላይ ጠቅሷል።
በወቅቱ ከነበረው የኤርትራ የጦር ግጥሞችም ለየት ባለ ሁኔታ የጦርነቱን አስከፊ ገፅታም ይፅፍ እንደነበር ፔን በድረገ-ገፁ አስፍሯል።
ከዚህም በተጨማሪ አገር በቀል የስነ-ፅሁፍ ምሽቶችን በመደገፍ ስነ-ፅሁፍ እንዲያንሰራራም የራሱን ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል።
አማኑኤል በኤርትራ የጋዜጠኝነት ስፍራ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የዘመን ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሲሆን እርሱም በሰላ ትችቱ ይታወቃል።
ይህ የሰላ ትችቱ ግን ዋጋ ያስከፈለው ሲሆን ኤርትራም የግል ጋዜጦችን ዘጋች እንዲሁም የሚቀርቡበትን ትችት ዝም ለማሰኘት በጀመረው ዘመቻም የኤርትራ መንግሥት ፖለቲከኞችን፣ ጋዜጠኞችንና ተማሪዎችን ለእስር ዳርጓል።
አማኑኤልን ጨምሮ በርካታ የግል ጋዜጣ አዘጋጆችም በጎሮጎሳውያኑ 2001 ለእስር ተዳረጉ። አማኑኤልም ሆነ ሌሎች ፀሃፊዎች ያሉበት ሁኔታ የማይታወቅ ሲሆን እስካሁንም ያናገራቸው አካል የለም።
ታሳሪዎቹ ምንም ክስ እንዳልቀረበባቸውና መንግስትም መረጃ እንደማይሰጥ የሰብአዊ መብት ተሟጓቾች ይገልጻሉ።
ከዚህም በተጨማሪ የህክምና አቅርቦት ማጣት እንዲሁም ሌሎች እንግልቶችና ስቃይ እየደረሰባቸው እንደሆነ ይታመናል።
ለሁለት አስርት አመታት የሚጠጋ በእስር ላይ የሚገኘው አማኑኤልን ጨምሮ ጥቂት ፀሃፊዎች በህይወት እንዳሉና በእስርም ላይ እንደሚገኙ ይታመናል
ገጣሚ አማኑኤል ለዚህ ሽልማት ያጨው ጃማይካዊ- ኢንግሊዛዊ ሊንቶን ክዌሲ ጆንሰን “አንድ ዜጋ ፍጹም በማይታወቅ እስር ቤት ለ20 አመታት ማጎር የአምባገነን ስርአት ማሳያ ነው። በአፍሪካዊ ዲያስፖራነቴ ትብብርና ወገንተኝነቴን ለማሳየት ደግሞ ይሄን ሽልማት ለገጣሚ አማኑኤል አስራት እንዲሸለም መርጫለሁ” ማለቱን ፔን ኤርትራ ገልጿል።
አማኑኤል አስራት በ2016 ከሌሎች ግብጻዊና ቱርካዊ ጸሃፍያን በመሆን በፔን ኦክስፋም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ሽልማት ተሰጥቶታል።
ከዚህ በፊትም ገጣሚ ለምን ሲሳይ፣ ቺማማንዳ ንጎዚ አዲቺ የሚገኙባቸው ዘጠኝ ጸሃፍያን የፔን ፒንተር ተሸላሚዎች ሆነዋል።
እንዲሁም “ደፋር ተማጓች” በሚል በፍቃዱ ሃይሉ፣ ዋሊድ ዓብዱልኬር፣ ማህቨሽ ሳበትና ሌሎች መሸለማቸውን ከፔን የተገኘው መረጃ ያስረዳል።
Filed in: Amharic