>

አቶ ልደቱን ባየሁት ጊዜ ....!?! (የሺዋስ አሰፋ፣ የኢዜማ ሊቀ መንበር)

አቶ ልደቱን ባየሁት ጊዜ ….!?!

የሺዋስ አሰፋ፣ የኢዜማ ሊቀ መንበር
——-

* …የአገዛዝ መጥፎ ባህሪው የኃይማኖት፣ የባህል እና የሽምግልና ተቋማትን ጨምሮ ያረክሳቸዋል። ሲብስበትም የፍትህ ተቋማትን ይገድላቸዋል። በመጨረሻም ለዜጎችና ለሃገር ብቻ ሳይሆን ለራሱም የሚያስታርቀው፣ የሚዳኘውና የሚያድነው ያጣል…!
 
ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ጋር ለሁለት ቀናት ደብረዘይት/ቢሾፍቱ የውይይት ፕሮግራም ነበረን። እንደጨረስንም ሳናየው ብንሄድ አምላኩ ያየናል ብለን አቶ ልደቱ ወደታሰረበት ጣቢያ ከአቶ አዳነ ጋር ተከታትለን ሄድን።
ከጣቢያ እንደደረስን ወዲያው ጠሩልን። ሳሳ፣ ነጣ ያለች ሸሚዝ አጥልቆ፣ ጠቆር ባለች ማስክ አፉን ሸብ አድርጎ ብቅ ሲል ባየሁት ጊዜ…ከስቷል…ጠቁሯል… አዘንኩ። እግዚአብሔር ያስፈታህ አልኩት፣ አሜን አለ… ጥቂት ስለ እስሩ፣ ሰለጤናው፣ ስለ ፍ/ቤት ትዕዛዝ ጠየቅሁት። አልጠበቀም። እኛም ማዕከላዊ፣ ቂሊንጦ እና ቃሊቲ እያለን እንደዚሁ ድንገቴ ጠያቂዎች ይመጡልን ስለነበር ስሜቱን ተረድቸዋለሁ።
ስለህመሙና ማግኘት ይገባው ስለነበረው የውጭ አገር ህክምና ሲናገር ግን በጣም አሳስቦኛል። የአገዛዝ መጥፎ ባህሪው የኃይማኖት፣ የባህል እና የሽምግልና ተቋማትን ጨምሮ ያረክሳቸዋል። ሲብስበትም የፍትህ ተቋማትን ይገድላቸዋል። በመጨረሻም ለዜጎችና ለሃገር ብቻ ሳይሆን ለራሱም የሚያስታርቀው፣ የሚዳኘውና የሚያድነው ያጣል።
ከአቶ ልደቱ ጋር ሁለት ጊዜ ሚዲያ ላይ ስንገናኝ በስትተቀር የቀረበ ትውውቅ የለንም። በሩቁ ባለኝ ትዝብት በሁለት ጎን የሚዋጋው የአገራችን የፖለቲካ ጦር ልቡ ድረስ ዘልቆ ያደማው ይመስለኛል። ሆኖም በወትሮውም፣ በአሁኑም የአገራችን ፖለቲካ አቋሙ፣ ትንታኔው እና እልህ በሚገፋው አገላለፁ አልስማማም። ይህ ግን የግል አቋሜ ነው። የፍትህ ተቋማት ከግለሰብ በላይ ናቸው። በግለሰብ ፍቅር አይጠቅሙም በግለሰብ ፀብ አይጎዱም። አቶ ልደቱ ትክክል አይደለም፣ ህገወጥ ነው ብለው ወደህግ ፊት ያቀረቡት ሰዎች የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ የማያከብሩና የራሳቸውን ስሜት የሚተገብሩ ከሆነ መጀመሪያውኑ ለምን ዳኛ ፊት አቀረቡት? ይሄ መንገድ በቅርብ ጊዜ አሳብሮ እነሱ ቤት እንደሚገባ ማስተዋል እንዴት ተሳናቸው?
ይህ እንዴት ቅርብ እንደሆነ ለማስታዎስ ሁለት ማሳያዎችን ልጥቀስ።
የመጀመሪያው በአንድ ወቅት ፕሮፌሰር መስፍን ያሉበት እስር ቤት ውስጥ አቶ ስዬ አብርሃ ይገባሉ፣ ፕሮፍም “የፍትህ ስርዓቱን አብረን እናስተካክለው ብልህ እምቢ ብለህ አንተንም አንጥልጥሎ አመጣህ?” ያሉትን እና፣ ሁለተኛው ደግሞ የግል እስር ቤት የነበራቸው አቶ ገብረ-ዋህድ በፌደራል ፖሊስ ተከበው ሲያዙ “ይህች አገር ወዴት እየሄደች ነው?” ያሉትን ለማስታወስ እወዳለሁ።
ግፍ የማይገፉት እዳ ይዞ ይመጣልና፣ የአቶ ልደቱ የፍ/ቤት ትዕዛዝ ይከበር፣ የዋስትና መብቱ ይጠበቅ፣ የህክምናው ጉዳይ ከሁሉም በላይ አሳሳቢ ስለሆነ በፍጥነት ይፈታ!
Filed in: Amharic