>
5:13 pm - Saturday April 20, 7393

“ለዜጋው የሚጨነቅና የሚቆረቆር መንግሥት ቀድሞ እርምጃ ይወስዳል...!!!”  (ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ)

“ለዜጋው የሚጨነቅና የሚቆረቆር መንግሥት ቀድሞ እርምጃ ይወስዳል…!!!” 

 ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴ 

ባሕር ዳር፡ ጥቅምት 03/2013ዓ.ም (አብመድ
በኢትዮጵያ በፖለቲካ ምስቅልቅል ምክንያት የችግሩ ገፈት ቀማሾች ንጹሐን እየሆኑ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል መተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች ‘‘የታጠቁ ኃይሎች ፈጸሙት’’ በሚባል ተደጋጋሚ ጥቃት ንጹሐን በተደጋጋሚ ተገድለዋል፤ ንብረት ወድሟል፤ ዜጎችም ተፈናቅለዋል፡፡ የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎም ሃይማኖትንና ብሔርን መሠረት ያደረገ ጥቃት መፈጸሙና ንጹሐን ሰለባ መሆናቸውም ይታወሳል፡፡
ከላይ የተገለጹትን መሠል ጥቀቶች እንዲቆሙ ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብትና ፌዴራሊዝም መምህሩን ዶክተር ሲሳይ መንግሥቴን አነጋግረናል፡፡ የንጽሐን ደኅንነትና በሕይወት የመኖር መብታቸው እንዲጠበቅ ከግጭቶቹ ጀርባ እንዳለ የሚገመተው የትግራይ ክልል መንግሥት ከስህተቱ ተምሮ ከፌዴራል መንግሥቱ ጋር ለመሥራት ዝግጁ እንዲሆን ዶክተር ሲሳይ ይመክራሉ፡፡
የፌዴራል መንግሥትም የትግራይ ክልል ፖለቲከኞች በእልህ ተነሳስተው የሚያስተላልፉት ውሳኔና እርምጃ ሕገ-ወጥና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ቢሆንም በሆደ ሰፊነት ለመደራደር፣ ለመግባባትና ወደ ትክክለኛው መንገድ እንዲመለሱ ለማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት ዶክተር ሲሳይ አመላክተዋል፡፡
የአሸናፊነትና ተሸናፊነት ጉዳይ ቀርቶ ሁሉም አሸናፊ የሚሆንበት አሠራር መፈለግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ይህ የንጹሐንን ሕይወት የሚታደግና ሕዝብንም አስተሳስሮ የሚያሻግር አንደኛው መንገድ እንደሆነ እምነታቸው መሆኑን ዶክተር ሲሳይ ገልጸዋል፡፡
በሀገራዊ ለውጡ ምክንያት ፍራቻና ስጋት ውስጥ የወደቁ አካላት ችግሮችን መፍጠራቸው የሚጠበቅ መሆኑንና ለዚህ ተዘጋጅቶ ክፍተቶችን መዝጋት ከመንግሥት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል፡፡ ‘‘የእኔ አሠራርና አካሄድ ትክክል ነው’’ በሚል ማስረገጫ ለማግኘት መንፈራገጥ እንደማይቀርም አስገንዝበዋል፡፡
የፌዴራል መንግሥትም የሰው ልጅ ሕይወት እንዳይጠፋ፣ ሀብትና ንብረት እንዳይወድም የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን ለማክሸፍ ቢንቀሳቀስም በቂ እንዳልሆነ የፌዴራሊዝም መምህሩ አብራርተዋል፡፡ ሕግና ሥርዓት በማስከበር በኩል የተሳካ ተግባር እንዳልተፈጸመም ነው ያብራሩት፡፡
የአርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በተፈጸመ ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱንና መንግሥት ጠንካራ እርምጃ መውሰድ እንደሚችል ማሳየቱንም ዶክተር ሲሳይ አስታውሰዋል፡፡ ነገር ግን መንግሥት እርምጃዎችን አስቀድሞ የመውሰድ ድክመት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡
መንግሥት አስቀድሞ እርምጃ የመውሰድ ልምዱ በጥንካሬ የሚነሳ ቢሆን ኖሮ ከአርቲስቱ ግድያ በኋላም ከፍተኛ ጥፋት ላይከተል ይችል እንደነበረ አስቀምጠዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚፈፀሙ ጥቃቶችም አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አሳሳቢ ጭምር መሆናቸውን ዶክተር ሲሳይ ገልጸዋል፡፡ “የፌዴራልና የአማራ ክልል መንግሥታት ለምን በዝምታ እንደሚመለከቱ አላውቅም” ሲሉም ዶክተር ሲሳይ ይጠይቃሉ፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት በአንጻራዊነት ጠንካራ ልዩ ኃይል እንደገነባ በመግለጽ ችግሩ ሳይባባስ በታጠቁ ኃይሎች እርምጃ መውሰድ ይችል እንደነበርም አመላክተዋል፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ዳተኛ እንደሆነ በመተቸትም ወቅሰዋል፡፡ ከአማራ ክልል ውጭ በሌሎች ክልሎች የሚኖሩ ተወላጆች ደኅንነታቸው እንዲጠበቅ ግፊት ማድረግ እንደሚችልም ጠቁመዋል፡፡
በየክልሎቹ መንግሥታት እርምጃ የማይወሰዱ ከሆነ የአማራ ክልል መንግሥት የራሱን ኃይል ልኮ የሕግ የበላይነት ለማረጋገጥና ንጹሐን በሰላም እንዲኖሩ ለማድረግ እንደሚገደድ በመግለጽ ጫና ማሳረፍ እንደሚኖርበትም ዶክተር ሲሳይ አመላክተዋል፡፡
 የፌዴራል መንግሥቱም ሕጋዊ የእርምት እርምጃ መውሰዱ ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ “ለዜጋው የሚጨነቅና የሚቆረቆር መንግሥት ቀድሞ እርምጃ ይወስዳል፤ ይህ የንጹሐንን ሕይወት መታደግ የሚቻልበት ሁለተኛው መንገድ  ነው’’ ብለዋል ምሁሩ፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በሚኖሩ ንጹሐን ላይ እየተፈጸሙ ያሉ ግድያዎችን አውግዞ የክልሉና የፌዴራል መንግሥታት ሥርዓት እንዲያስከብሩ ማሳሰቡ የሚታወስ ነው፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት በንጹሐን ላይ የሚፈጸሙ መሰል ጥቃቶችን እንደማይታገስም ነበር በክልሉ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በኩል የገለጸው፡፡
ዘጋቢ፡- ኪሩቤል ተሾመ
Filed in: Amharic