>
5:13 pm - Monday April 18, 9729

ራስ ወዳድ መሪዎች (Narcisstic Leaders) ወሎ በአንበጣ - ጠ/ሚኒስትሩ በ ጎ ካርት (Go Kart) - ደረጄ ከበደ

ራስ ወዳድ መሪዎች (Narcisstic Leaders) ወሎ በአንበጣ – ጠ/ሚኒስትሩ በ ጎ ካርት (Go Kart)

 ደረጄ ከበደ

በአለም ደረጃ እውቅና ያለው በሜናሶታ ሮቼስተር የሚገኘው የሜዮ ክሊኒክ (Mayo Clinic) ስለ ናርሲሲዝም ምንንት የገለፀበት አጭር፣ ነገር ግን ጠቃሚ የሆነ ሜዲካል አርቲክል ፅፎአል። ራስን መውደድ ወይም ሰው ራሱን በጣም ተፈላጊ ወይም ተወዳጅ አድርጎ የመውሰድና ከሰዎች አድናቆትንና ምስጋናን የመሻት ተጠናውቶ ወይም አባዜ በቀላሉ የሚታይ ነገር ሳይሆን ከባህሪይ መዛባት የአእምሮ በሽታዎች አንዱ ነው (Narcissitic Personality Disorder)። ይህ መዛባት የራሱ የሆኑ የዳያግኖሲስ መስፈርቶች ያሉትና የምክረስነልቦና (Psychotherapy) ህክምና ክትትል ካደረጉ ተጠቂዎቹ በህይወታቸው አወንታዊ ለውጥ  ማየት እንደሚችሉ በጥናት ተደርሶበታል። ችግሩ ግን የዚህ ባህሪይ ቀውስ ተጠቂዎች በአብዛኛው ችግር አለብን ብለው ስላያምኑ የቴራፒስቶችን እርዳታ አይሹም። ያ ትልቅ ስህተት ነው ምክንያቱም ራሱን ከመጠን  በላይ የሚያገዝፍ ፣ ተፈላጊ ነኝ፣ ሰው ሁሉ ያድንቀኝ ያርግድልኝ የሚል ማንም በማህበራዊ ኑሮው ከፍተኛ ችግር ይደርስበታል፣ ሰዎች ሊቀርቡት አይችሉም፣ ሙገሳና አድናቆትን ካላገኘ ይከፋዋል፣ ብዙ ጊዜ ደስታን ከራሱ ሳይሆን ከሌሎች ነው የሚጠብቀው፣ ስለዚህም ደስተኛ ሰው አይደለም። ሌላው ክፉ ነገር ናርሲሲት ሰዎች ለሌሎች ፍፁም አዘኔታ የሌላቸው አይነቶች ናቸው ወይም ራሳቸውን በሌሎች ሰዎች ጫም ወይም ቦታ አድርገው (Emphaty)የሌሎችን ችግር የመረዳት ፍላጎት የላቸውም። የራሳቸውን ጎን ብቻ በማየት ነው ፍርድ የሚሰጡት ወይም ነገራትን ለመረዳት የሚሞክሩት።
ይህ ክፉ ባህሪይ ከምን ይመጣል? ናርሲሲዝም ከምን እንደሚመጣ በውል አልታወቀም ነገር ግን በዘር፣ በአስተዳደግ፣ በአንጎልና በባህሪ ቀረፃው ክፍል ከሚኖሩት የነርቭ ግንኙነቶች ችግር ሊሆን ይችላሉ ብለው ተመራማሪዎች ይናገራሉ።
Charles A. O’Reill የተባለ የስታንፎርድ ድህርምረቃ ቢዝነስ ዴፓርትመንት ፕሮፌሰር ራስ አግዛፊ ስለሆኑ መሪዎች (Narcissistic Leaders) ሲናገር፣ ከሚመሩት ድርጅት ወይም ሃገር ይልቅ የራሳቸውን እጀንዳና ዝና ለመካብ የሚሰሩ መሪዎች ይህን መጥፎ ባህሪያቸውን በዙሪያቸው ላሉ አመራሮችና ካቢኔ አባሎቻቻው ጭምር እንደጀርም ያስተላልፉታል ይላል። ስለራስ ብቻ የማሰብን ባህል በዙሪያቸው ላሉ ሁሉ ያጋባሉ ይላል። ይሀው ፕሮፌሰር ከሌላ የስራ ባልደረባው ጋር በመተባበር በራስ ወዳድ መሪዎች ባህሪይ ዙሪያ የተደረጉ 150 ጥናታዊ ፅሁፎችን ካገናዘበ በሁዋላ ስለ ነዚህ እኔ እኔ ሰለሚሉ መሪዎች ጨምቆ ያወጣቸው አስገራሚና አስፈሪ ድምዳሜዎች አስደንቀውኛል። የተደነቅሁበትም ምክንያት ምናልባት ከጥናቱ የተገኙት ባህሪያት በአሁኑ መሪያችን በዶ/ር አቢይ የየእለት ተግባራት ውስጥ ቁልጭ ብለው መታየታቸውን በመገንዘብ ነው እላለሁ። ፕሮፌሰር ኦሬይል ከደረሰባቸው ነገሮች መካከል ትኩረቴን የሳበው ራስ ወዳድ መሪዎች ከሌሎች ክፉ አለቆች ብለን ከምንላቸው የሚለዩት፣ ምንም ነገር ሲያደርጉ ለሃገሬ ወይም ለካምፓኒዬ ወይም ለድርጅቴ ብለው ሳይሆን ለራሴ ብለው የማድረግ ፀባያቸው ነው። ትልቁን ስእል አያዩም፣ ለሚመሩት አገርና ህዝብ ይጠቅማል ወይ ብለው አይጠይቁም። የነሱን ስም፣ ዝና፣ ከበሬታና ምናልባትም የገንዘብ ምላሽ የሚያሳድግላቸው ከሆነ በሚመሩት ድርጅት ወይም አገር ወጪ የራሳቸውን ማንነት ይገነባሉ። ያ ማለት በአጭሩ፣ አገርም ሆነ ድርጅት ከራሳቸው ጥቅም በሁዋላ የሚመጡ ናቸው ማለት ነው በእነዚህ መሪዎች አሰራር። ውነተኛ የለየላቸው ናርሲሲቲክ መሪዎች (Narcissitic leaders) በኦሬይል ጥናት መሰረት ሁልጊዜ ከራስ በላይ ነፋስ የሚሉና ጨዋነት ወይም ክብር የሌላቸው ናቸው (Selfserving and lacks Integrity)። ራሳቸውን እስከጠቀመ ድረስ ለህግ አይገዙም። ራሳቸው ለፃፉት ህግ እንኩዋን አይታዘዙም። የሚፈልጉትን ለማግኘት የዋሻሉ ያጭበረብራሉ። የሚገርመው ነገር ከተደረጉት 150 ጥናቶች እንደተደረሰበት ራስ ወዳድ መሪዎች የሚፈልጉትን ለማግኘት ሲዋሹና ሲያጭበረብሩ ሸፍጣቸውን በደንብ አሳምረው ያውቁታል። ነገርግን ምንም አያስደነግጣቸውም፣ የህሊና ወቀሳም እይኖራቸውም። እዚህ ላይ በራስ ወዳድነታቸው ተፎካካሪ የሌላቸው የሃገራችን መሪ ጠ/ሚኒስትር አቢይ ለምርጫቸው ያሰጉኛል ብለው የፈሩዋቸውን የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችና አባላት ላይ የውሸት ክስ  ጭነው በማገት ከጨዋታ ውጭ ለማድረግ አይናቸውን በጨው ታጥበው የሚሸርቡትን ሴራ ማስታወስ ግድ ይሉዋል። የራሳቸውን ክብር ለመጎናፀፍ ከመስመር የወጣና ጥንቃቄ የጎደለው ነገር ማድረግ ልማዳቸው ነው።
ዶ/ር አቢይ የናስርሲሲቲክ መሪ ቲፒካል ምሳሌና አርማ ናቸው (The posterboy for Narcissism)። በየወቅቱ የሚያደርጉዋቸው ነገሮችና የህዝብ ገንዘብ የሚያጠፉባቸው ፕሮጀክቶች በሃገሪቱዋ ላይ ካሉት ነባራዊ የኤኮኖሚ፣ የፀጥታና የብሄር ግንኙነት ሁኔታዎች ጋር ፍፁም የማይሄዱ፣ አላስፈላጊ የሆኑ ግንባታዎች ናቸው። የመናፈሻዎች መአት፣ ማ ነው የሚጠቀምባቸው? ምናልባት ተረኞቹ የኦሮሞ ተወላጆች አዲስ አበባን የግላችን እያሉን ስለሆነ በመዲናዋ የሚደረጉ ፕሮጄክቶች በሙሉ ለኢትዮጵያውያን ሳይሆን ጠመንጃና ሰራዊቱን ለጨበጠው የኦሮሞ ብሄር ከሆነ እንጅ። በዚህ በወረርሺኝ ዘመን፣ በዚህ በረሃብ ዘመን፣ በዚህ በጄኖሳይድ ዘመን፣ በዚህ ህዝቡ ንፁህ የመጠጥ ውሃና የኤሌክትሪክ አገልግሎት በማያገኝበት ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትሩ መናፈሻ በመገንባት ተጠምደዋል። ጠ/ሚኒስትሩና መናፈሻ (Parrk) ስነልቦናዊ ግንኙነት ይኖራቸው ይሆን? ምናልባት በአሰተዳደጋቸው ወቅት መናፈሻዎችን በተመለከተ በህይወታቸው የተፈፀመ ነገር ይኖር ይሆን ወይ??? ያንን ለሳቸውና ለፈጣሪ እንተወው። አሁን ግን ራስ ወዳዱ (Narcissitic leader) መሪ ስለሚሞቱት፣ ስለሚራቡት፣ ስለወንጀል፣ ስለ ፍትህ፣ ስለመብት፣ ስለ ንግግርና ፅሁፍ ነፃነት፣ ስለ ህገመንግስት፣ ስለ ስራ አጥነት፣ ስለዘረኝነት፣ጉዳይ መጨነቅ አይፈልጉም። ጉዳያቸውም አይደለም። የናርሲሲቲክ መሪዎች ዋና ባህሪይ እንደሚያሳየው የራሳቸውን ፍላጎትና ስማቸውን የሚያስጠራ ነገር ለማድረግ ሲወስኑ ሺ ህዝብ ቢረፈረፍ ከ selfish ምኞታቸው ሌላ የሚታያቸው ነገር የለም።  ለምሳሌ የችግኝ ተከላውን እናስታውስ። ዶ/ር አቢይ የችግኙን ተከላ ሲያስቡ ለሃገር የሚሰጠውን የወደፊትና የዘለቄታ ጠቀሜታ አይተው ሳይሆን አይናቸው ላይ ያለው በችግኝ ተከላው ስማቸውን በትልቅ መንገድ ማስጠራት ነበር። ስለዚህም ነው በቢሊዮን የሚቆጠሩ ችግኞችን በሃገሪቱ ላይ በአጭር ግዜ ውስጥ ለመትከልና የአለምን ሬከርድ ባለቤት በመሆን በአለም የክብረወሰን መዝገብ ለመመዝገብ ቀመሩን አስተካክለው ነበር የጀመሩት። ትልቁ አላማቸውና የውስጣቸው ድብቅ ምኞት የችግኞቹ ማደግና አለማደግ አይደለም። ብቻ ሬከርድ መስበሩ ላይ እንጅ። አንድ ጊዜ ደግሞ የ 5 ሚሊዮን ብር ግብዣ አድርገው ነበር። ያም ከዛ በፊት ያንን ያህል ያስከፈለ እንጀራና ወጥ በየትም ተደርጎ እንደማያውቅ አጥንተው አሁንም የኢትዮጵያው ጠ/ሚኒስትር በታሪክ በውድነቱ ተፎካካሪ የሌለው ግብር አበሉ የመባል ህልምና ቅዥታቸውን ለማማሙዋላት ያለሙት ነገር ነበር። ራስ ወዳድ መሪዎች የራሳቸውን ስም ለመካብ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የማይምሱት ጉድጉዋድ የለም። በመንገዳቸው የሚቆም ወዮለት!
በስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ ከተፃፈው ጥናታዊ አርቲክል ራስ ወዳድ መሪዎችን በደንብ ስለሚገልፅ ይህን ኮቴሽን ላቅርብ
“But even worse, narcissists change the companies or countries they lead, much like bad money drives out good, and those changes can outlast their own tenure, Divergent voices are silenced, flattery and servility are rewarded, and cynicism and apathy corrode any sense of shared purpose in a culture where everyone’s out for themselves. In the extreme, they can destroy the institution itself.”
ተቀራራቢ ትርጉም
“እንዲያውም ከሁሉም በከፋ ሁኔታ፣ ራስ ወዳድ መሪዎች የሚያስተዳደሩዋቸውን ካምፓኒዎች ወይም አገራት የተለመዱ ስርአቶችና ቅቡል ባህል በራሳቸው በደረጃ ዝቅ ባለ አሰራርና ስርአት ይለውጣሉ። ከተሰራበት ንጥረነጎርች አንፃር ዝቅተኛ ዋጋ ያለው ከረንሲ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን ከረንሲ በዝግመት ቦታ እንደሚያስለቅቅ አይነት ማትለ ነው። በመንግስታቸው እነሱ ከዘረጉት አሰራር ለየት ያለ አቁዋም ያለው ሁሉ አደብ እንዲገዛ ይሆናል። ለመሪዎች ማጎብደድ፣ እንደአሽከር መታዘዝ ያሸልማል፣ ሁሉም ለየራሱ ብቻ በሚጨነቅበት በእንደዚህ አይነት አሰራር ጥርጣሪና ግዴለሽነት የጋራ የሆነ ተልእኮ እንዳይኖር ያደርጋል። እነኝህ ራስ ወዳድ መሪዎች በመጨረሻ የሚመሩትን ሃገር ወይም ድርጅት ያጠፉታል”
ከላይ አርቲክሉ ያስቀመጠው መረጃ በሃገራችን በጠ/ሚኒስትር አቢይ ስርአት በደንብ የታየ ነው። በዶ/ር አቢይ ፍላጎት ብቻ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይጠየቅ ለብዙ መቶ አመታት የኢትዮጵያ ህዝብ መለያና ኩራት በነበረው በአንበሳ ምትክ ፒኮክ የተባለች ፍጥረት ተተካች። አንበሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለው የጀግንነታችን አርማ ነው። ጠ/ሚኒስትሩ ህዝብና ፓርላማ ሳያማክሩ ብቻቸውን የብዙ መቶ አመታት አርማ መቀየር፣ ምን ያህል ህዝቡን እንደናቁትና የግል ፍላጎታቸውን ከማንምና ከምንም አስበልጠው እንደሚያዩ ያሳያል።   እሳቸው ለራሳቸው ነዋ የሚኖሩት !!። የናርሲሲት መሪ መለያ ከሁሉም በላይ እኔ እቀድማለሁ ነው። ነባር እሴቶታቻንን የመቀየራቸው ጉዳይና የታሪክ ቅርሶችን በእድሳት ስም ማጥፋታቸው የራስ ወዳድ ባህሪያቸውን ይጠቁማል። ዶ/ር አቢይ ቤተመንግስቱን በራሳቸው መንገድ ለዋውጠውታል። እንዳንድ ሰዎች አሳመሩት ሊል ይቃጣው ይሆናል ነገር ግን ስንት ለህዝብ አስፈላጊ ነገሮች ሳይሙዋሉ ቶሎ ብለው የሚታዩ ነገሮችን የመለዋወጥ ስራ ላይ የሮጡበት ምክንያት በተፈጥሮ ካላቸው ራስን የማግዘፍ ዝንባሌ (Grandeosity)የመጣ ነው።
ከላይ በመጠኑ የዳሰስኩት ከመጠን ያለፈ የራስ ወዳድነት (Narcissitic Personality) ባህሪይ ምን እንደሚመስል ነው። ሰሞኑን በወሎ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ የወሎ ህዝብ ጩሀት በግዴለሹና ራስ ወዳድ በሆኑት ጠ/ሚኒስትር የተዘጋ ጆሮ ላይ ወድቆአል። እሳቸው ጎ ካርት ይነዳሉ
1/ የወሎ ገበሬዎችና እናቶች በአንበጣ መንጋ ተውጠው የሃገሪቱን መሪ ይጣራሉ።
2/ የሃገሪቱ መሪ በእንጦጦ ፓርክ ጎ ካርት እያሽከረክሩ ይፈነድቃሉ። ቢዚ (Busy) ናቸው
3/ በዋሽንግተን DC እኚህን “”ኬረዳሽ” መሪ ለሺ አመት ይንገሱልን እባኮ ሊል ሰራውን ትቶ የተሰበሰበ ማሰቢያው የተወላገደ ጥርቅም ሲጮህ ዋለ።
ይቺን ሁለት ቀን የምናየው ጉድ ከግርምት የዘለለ፣ ከሃዘን ያሻቀበ፣ ከብስጭት የናረ ሆኖብኝ እንዳንዴ ራሴን “”ወይ ጉድ!!!!” “አንድ ጤና ነኝ  የሚል መሪ፣ በሚመራት አገር ውስጥ የሚሆነውን ሰቆቃ እያየና እየሰማ ይህን ያህል ግድየለሽነት ማሳየት እንዴት ይቻለዋል”? እያልኩ ኮምፕዩውተር ስክሪኔ ላይ አይኔን ተክዬ አገኘዋለሁ።
መረገም እንዲህ ነው። ኢትዮጵያ ሃገራችን በሌላው አለም ታይተው የማይታወቁ በአስተሳሰብ ውራ የሆኑ መሪዎችን እያፈራረቀች ታስተናግዳለች። በሃገራችን የምናያቸው ክስተቶች “”የባሰ አለና አገርህን አትልቀቅ” እንዲሉ፣ መሪዎቻችን በአፍሪካ ደረጃ  እንኩዋን የዘቀጡ ሆነው አግኝተናቸዋል። ከዚህ በላይም ዝቅጠት ሊኖር አይችልም በሚያሰኝ ደረጃ።
አይኔን ኮምፒዩተሬ ላይ ስክቼ የቀረሁት ሶስት ነገሮችን አይቼ ነበር። የመጀመሪያው ምስል በአንበጣ መንጋ የተዋጠችው ወሎ ጎስቁዋላ እናቶች ወድቀው ፈጣሪን ሲማፀኑ፣ ሌላዋ እናት ደግሞ ቢሊዮን አንበጦችን በልብሳቸው እንደዝንብ እሽ እያሉ ባለ በሌለ ሃይላቸው ከእህላቸው ሲያባርሩ የሚያሳይ የረዳት አልባ እናት ምስል ነበር። የአንበጣው ብዛት በመንግስት ደረጃ በአየርና በምድር ማጥፊያ ካልተረጨ በጥቂት ግለሰቦች የሚገታ አለመሆኑን ምስኪን እናቶቻችን አላወቁም። መንግስት ደግሞ የለንም!!!
ሁለተኛ የተደመምኩበትና ፈዝዤ የቀረሁበት ነገር ደግሞ በየጊዜው በሃገራችን በመንግስት የተቀነባበረ ጄኖሳይድ በተግባር በተፈፀመ ቁጥር የጠ/ሚኒስትሩን ስምና ዘውድ ለመጠበቅ “ኢትዮጵያን ለማዳን” በሚል መደበቂያ “በአቢይ ግብረሃይል” ተጠራርተው የሙዋቾቹን ጨሀት ለመዋጥ የሚሰበሰቡ በትልቅ ጥቅም የታሰሩ የእኩያን ጥርቅም ሃፍረት የለሽ ቻቻታ ነበር። በኮምፒዩውተሬ ስክሪን ያዩሁትና የሰማሁት ንግግራቸውና እንቅስቃሴአቸው ከድንዛዜም አልፎ በድን አድርጎኝ ነበር። ለመሆኑ ኢትዮጵያን ለማዳን ጠ/ሚንስትሩ የመለመሉዋቸው ኦነግ ሸኔዎች፣ ኦነጎችና ቄሮዎች አማራንና ኦርቶዶክስን፣ ወላይታን ጉራጌንና ጋሞን መጨፍጨፍ አለባቸው??? ሰዎች በውሽት ክስ መታሰር አለባቸው? ጠ/ሚኒስትሩ የዴሞክራሲ ለውጥ መጣ ከሚሉበት ፕሮፖጋንዳቸው ጋር የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎችን አስረው ምርጫ ለማካሄድ መከጀላቸውን ይህ የDC ው የእኩዮች ጥርቅም እንዴት ያስታርቀዋል?? ጠ/ሚኒስትሩ ህግን በማስከበርና ገዳዮችን ወደ ፍርድ በማምጣት ኢትዮጵያን እንዲያድኑ አለበለዛ ከስልጣናቸው እንዲሰናበቱና ወደ ህግ እንዲቀርቡ ይህ ጥርቅም ለምን አይጠይቅም? ኢትዮጵያን ለማዳን የተሰለፈ ጄሌ ከሆነ?? የዚህ ጥርቅም ጉዳይ የሚገርመው ኢትዮጵያ የምትድነው ህግንና ደህንነትን በሃገሪቱዋ ላይ በማስከበር ሳይሆን የጄኖሳይድንና የዘር ማጥፋት ወንጀልን በመደበቅ፣ የጠ/ሚኒንስትሩን  አስተዳደር ስኬታማ ቢሆንም ባይሆንም በማስቀጠል ነው ብለው መውጣታቸው ነው። ባጭሩ የDC ው የዛሬው ስብስብ ትክክለኛ ስሙ “ኢትዮጵያን እናድን” ሳይሆን “ጠ/ሚኒስትር አቢይን እናድን”ነው።
3/ ሶስተኛው ኮምፒዩውተሬ መስኮት ላይ በድንዛዜ የተከለኝ ነገር ደግሞ በነዚህ እናቶች ሰቆቃና ቁስል እንጨት የመስደድ ያህል በዚህ በመከራቸው ወቅት አንድ ቅንጦት ያሰከረው ሰው ኮፍያውንና የፀሃይ መነጥሩን ደንቅሮ ጎ ካርት ላይ ቁጭ ብሎ እያሽከረከረ ከፊቱ የሚታየው “የሁሉ ብርቁ” ገፅታ፣ ዥዋዥዌ ላይ ተቀምጦ ወላጆቹ ከሁዋላ እየገፉት እንደሚፈነድቅ ህፃን የሚያደርገው፣ “ኬረዳሽ” ፣ የእድሜ ሽቅብ፣ “የብስለት ቁልቁል” ሰው ምስል ነበር።
እኛ በኮምፒዩውተሬ ስክሪን የማያቸው ሰው፣ እነኛ በአንበጣ መንጋ ተውጠው ለረሃብ የተጋለጡትን እናቶች እንዲያስተዳድሩ የስልጣን መሃላ ፈፅመው ቤተመንግስት የተቀመጡ ሰው ናቸው። ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ።
– አገሪቱ በነፍሰገዳዮች ስትታመስ በመናፈሻ ግንባታና በቱሪስት  አስጎብኚነት የሚባዝኑ። 
 
– አዝመራ በአንበጣ ሲያልቅ ፒክኒክ ሄደው የሚፈነጩ   
 
– የቤታቸውን ለቅሶ ረግጠው ሱዳንና ሊባነን እዝን የሚልኩ
 
– ንፁሃንን በውሸት የሚያስሩና የሚያንገላቱ፣ መሪ ናቸው
በፍፁም ጤነኛ አእምሮ ያለው መሪ ሊያሳይ የማይችለውን ባህሪይ የሚያሳዩ፣ ሊያደርግ የማይችለውን ድርጊት የሚያደርጉ፣ የ21 ኛው ክፍለ ዘመን ራስ ወዳድ (Narcissistic) መሪ የእኛው የኢትዮጵያውያን መሪ ተብለው የተቀመጡ ጠ/ሚኒስትር አቢይ ናቸው።
እኚ ሰው የአስተዳደር ስልታቸው ሃገርን በተግባር መምራት ሳይሆን በድለላ ማወናበድ ነው።
1/ “በሬ ሆይ ሳሩን አየህና ገደሉን ሳታይ”
  የህዝብን ጆሮና አእምሮ በባዶ ተስፋ ንግግርና ፊትለፊት
  በሚታዩ ጥቃቅን ማባባያዎች ህዝብን መዋሸት። ከልብ ባልሆነ
  ማስመሰል ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ፣ አንድነት፣ እያሉ የህዝብን ልብ
  ማነሁለል። “ከፍሬው ገለባ”  በሆኑ ተግባራትና “ጉንጫ አልፋ”
  ተረቶቻቸው የህዝብን ትኩረት ከሴራዎቻቸው ማራቅ።
2/ እሳቸው የህዝብና የኢትዮጵያ ወዳጅ መስለው ቀርበው አገር
   የማፍረስና ኢትዮጵያን በኦሮሞ ቅኝ ገዢነት የመቀየስ
   የእለት እለት እንቅስቃሴያቸውን ደግሞ በጎን በቅርብ
   በሚያምኑዋቸው “የኦሮሞ ፈርስት” አውጠንጣኝ ግበረ
   አበሮቻቸው ማስፈፀም
3/ በውጪው አለም ያለውን ገፅታቸውን መገንባት። አስተዋይና
  ተቆርቁዋሪ መሪ መስሎ መታየት።  ከውጪ መንግስታት መሪዎች
  ጋር በመለጠፍ ማንም ተፎካካሪ የላቸውም። የሚመሩዋትን አገር ለገዳዮች፣ ለዘራፊዎች ለቤት አፍራሾችና
  ለፅንፈኞች አሳልፈው ሰጥተው እሳቸው ጎረቤት አገራትን
   አስታርቃለሁ ብለው በሃገሪቱ ላይ ህዝብ እየታረደ ጥሎ መሄድ።
4/ ወንጀለኞችን፣ ህዝብን ያረዱ አራጆችን፣ ባንክ ዘራፊዎችን ወዘተ
    መቅጣት ሳይሆን መሾም።
5/ ከሁሉም በላይ ትልቁ አሰራራቸው ህዝብን በጥቅም በመግዛት አፍ ማስያዝ ነው። በመፀሃፋቸው “እርካንና መንበር” ላይ ያሰፈሩት ብዙዎች ትኩረት የማይሰጡት አረፍተ ነገር አለ “ ሰዎች ራስን ወዳድ ናቸውና በጥቅም ግባባቸው”
መፍትሄው
የኢትዮጵያ ህዝብ መሪ አለኝ ብሎ በጠ/ሚኒስትሩ ላይ መደገፍ የገዛ ሰቆቃውን ማስቀጠልና ማቻኮል ይሆናል። ህዝቡ በሰላማዊ መንገድ መብቱን ለማስከበር በአደባባይ መውጣት ያስፈጋል። ዛሬ ኢትዮጵያን እናድን ብለው ዶ/ር አቢይን ለማዳን በ DC የወጡ የታሪክ ተጠያቂዎች፣ በሃገሩቱዋ ላይ ስለሚያልቀው ህዝብ፣ ስለታገቱት ተማሪዎች፣ በሃሰት ስለተከሰሱት ወገኖቻችን፣ ስለ ደሃዎች መፈናቀል፣ ስለህገወጥ የኦሮሞዎች ሰፈራ፣ ስለሰዲስ አበቤው በመዲናዋ ባይተዋርነት ግድ የላቸውም።
ህዝብ ትልቅ ትንሽ ሳይል ተረኞቹን መቃወም አለበት።
ነፃነታችንንና መብታችንን የምናስከብር እኛው ነን እንጅ ሌላ ሶስተኛ አካል የለም። ስለዚህ ለመብትና ለነፃነት እንታገል።
የመንግስት ቸልተኝነት ከእኛ ደካማነት የተነሳ የመጣ ነው። ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ በለእዳ አይቀበለውም። ጨው ሆይ ለራስህ ብለህ ጣፍጥ ነው ነገሩ።እኛ ስንንቀሳቀስ ብቻ ነው ሌሎች የሚያግዙን። ጨርቄን ማቄን ሳንል ወደአደባባይ እንውጣ። የዛሬዎቹ የDC የአቢይ ግብረሃይል ሰልፈኞች ገዳዮችን አትንኩ ብለው ሳያፍሩ ወደአደባባይ ከወጡ እኛ ተጠቂዎቹ የጄኖሳይድ ሰለባዎቹ ደጁን የፈራንበት ምክንያት ምንድነው?
References
How narcissistic leaders destroy from within
Filed in: Amharic