>
5:13 pm - Monday April 18, 3672

ዲሞክራሲ ከቤት ነው የሚጀመረው  (መኮንን ከተማ)

ዲሞክራሲ ከቤት ነው የሚጀመረው 

መኮንን ከተማ

ዋናው ምርጫ ከመገባቱ በፊት እራሳቸው የፕለቲካ ፓርቲዎች በዲምክራሲ ነው ወይ የሚተዳደሩት ብላችሁ አስባችሁ ታውቃላችሁ?
በዲሞክራሲ የሚመሩ ቢሆን ኖሮ የአስተዳደር ለውጥ መኖር አልነበረበትም ወይ? ከ100 ሚልዮን ሕዝብ በላይ ባለበት ሀገር እንዴት ነው እነዛኑ ሰዎች ለብዙ አመታት የፓርቲዎቻቸዉ አመራር ሆነው የምናያቸው? አይገባኝም ሊገባኝም አይችልም።
ፓርቲዉ የህዝብ ነው ወይስ የግል ድርጅት እስከማለት  ደርሻለሁ። ተከታዮቻቸዉም እንዴት ይሄን ማየት አለመቻላቸው ይገርመኛል። ዲሞክራሲ ወይ ህገ መንግስት እያልን ስንጩህ የራሳችንን የፖሊቲካ ፓርቲ ሁኔታ እንመልከት። ዲሞክራሲ እኛ ጋር ከሌለ እንዴት በትልቁ መድረክ ና እያልን እንጠራዋለን? በዚህ ሁኔታ ሊመጣ አይችልም። ሁሉም በፓርቲዉ ላይ መስራት ይጠበቅበታል።
ለእኔ ፓርቲው ከሰው በላይ መሆን አለበት። ከሰው አምልኮት ወደ እውነተኛ የፖሊቲካ ድርጅት መቀየር አለበት። ማለትም እንደ ምራባዉያን ፓርቲ በየጊዜው ልዩ አመራር የሚያወጣ የጥቂት ሰዎች ንብረት ያልሆነ። ምራባውያን ያልኩት የነሱን ዲሞካራሲ ስለምንመኝ ነው። ታድያ አንዱን ኮርጀን ሌላዉን መተው የለብንም። ከወሰዱ ላይቀር ሁሉንም ነው መውሰድ።  ያንን ያረገ ነው ለእኔ ስለ ዲሞክራሲ ማውራት የሚችለው።
ባልሳሳት የ1966 ለዉጥ የንጉሳዊ አገዛዝ በቃን ስለተባለ ነበር። ታድያ ከዛ በኅላ አንድ ሰው የፓርቲው ሀላፊ ሆኖ17 አመት ከዛም ሌላዉ ደግሞ 25 አመት ሀገርን እየመሩ እዚህ ደርሰናል። መቸም ተመርጠን ነው እንደማይሉ አውቃለሁ። ለምን ህዝቡ ያንን ሁሉ አመት በአንድ ሰው መገዛት ስለማይፈልግ ነው ለውጦች የመጡት።
በራሳቸው ፓርቲ ውስጥ ዲሞክራሲ ከሌለ እነዚህ  ሰዎች ስልጣን ቢይዙ ሀገሪቷን በምን መልክ እንደሚይስተዳድሯት የታወቀ ነው። የፖለቲካ ድርጅቶች የጥቂት ሰዎች ንብረት መሆን የለባቸዉም። የፖለለቲካ ድርጅቶች ማንም ሰው የሚካፈልበት እና መመረጥ የሚችልበት መድረክ መሆን አለባቸው። አለዛማ ወደ ንጉስነት ወይም ዘውዳዊ አገዛዝ ተመልሰናል ማለት ነው።
ትልቁ መድረክ ላይ ና ከማለታችን በፊት እስቲ ብዙ ሳንሄድ እዛው ፓርቲዎቻችን ጋር ዲሞክራሲን እንጥራው። ወደድንም ጠላንም ዲሞክራሲ ከቤት ነው መጀምር ያለበት።
Filed in: Amharic