>

ኹለት ጌታ ያለ አንድም የለውም.. !!! (አባይ ነህ ካሴ)

ኹለት ጌታ ያለ አንድም የለውም.. !!!

አባይ ነህ ካሴ

የሀገራችን ባለ ሳምንት ባለ ሥልጣናት ኹለት እግር አለን ብለው ኹለት ዛፍ ካልወጣን እያሉ ናቸው። መጽሐፋችን ለኹለት ጌቶች መገዛት አይቻልም ይላል። ማቴ ፮ ፡ ፳፬።
ነቢየ እግዚአብሔር ለኹለት ጌታ የማደርን ነሀር ከጥንት አውግዞታል። “ኤልያስም ወደ ሕዝቡ ሁሉ ቀርቦ፦ እስከ መቼ ድረስ በኹለት አሳብ ታነክሳላችሁ? እግዚአብሔር አምላክ ቢኾን እርሱን ተከተሉ፤ በኣል ግን አምላክ ቢኾን እርሱን ተከተሉ፡ አለ።” እንደተባለ። ፩ነገ ፲፰ ፡ ፳፩። መስፍኑ ኢያሱም ከነቢዩ አስቀድሞ “የምታመልኩትን ዛሬ ምረጡ” ሲል አስጠንቅቆበታል። ኢያ ፳፬ ፡ ፲፭።
በዚህ የሥልጣኔ ዘመን የኹለት አማልክት ባሪያ መኾን በራሱ አነጋጋሪ ነው። ይባስ ብሎ በባለ ሥልጣናት ዘንድ ሲኾን። ይባስ ብሎ ሁሉም ስሕተት ሲኾን። ያው ምንም አምልኮ የለም ማለት ነው።
ሰይጣን የለም ብሎ የሚያምን አምላኩ ማን ቢኾን ነው? በዚህ የሚደሰት ራሱ ሰይጣን መኾኑም አይደል። ሰይጣን የለም ለሚሉ አምላካቸው እግዚአብሔር አይደለም። በዚህ ጊዜ አለ ያሉት አምላክ አይኖራቸውም። የለም ያሉለት ሰይጣን ደግሞ አምላካቸው ኾኖ ይሰየማል።
ዋቄ ፈናዎች ገነትም ሲዖልም የሉንም ይላሉ። የጽድቅም የኩነኔም ቦታ ከሌለ ለሰይጣንስ ቢኾን መገበር ምን ይጠቅማል? ለአምልኮ ባዕድ የሚደረገው ሸብረብ እግዚአብሔርን ከማስቆጣት በቀር ለኢትዮጵያ ቅንጣትም በረከት አያመጣላትም።
እነ በላይ መኮንንም ዋቄ ፈታዎችን እንመልሳለን ብለው ሔደው ቀልጠው ቀሩ። ዋቄ ፈታ የመንግሥት ሃይማኖት እንዲኾን በብዛት እየተደከመለት ይመስላል።  ፕሮቴስታንቲዝምም እንዲሁ። የሚገርመው ለኹለቱም የሚጫወተው አንድ ቡድን መኾኑ። በጨዋታ ሕግ ከራሱ ጋር የሚጋጠም ቡድን የለም። ልምምድ ላይ ቢኾን እንኳ ቢያንስ ማልያው ይለያያል። ግን ነጥብ የለውም።
Filed in: Amharic