>

ኢትዮጵያዉያን ሁላችን ሊኖረን የሚገባ መሪ...!!! (ተስፋአብ ተሾመ)

ኢትዮጵያዉያን ሁላችን ሊኖረን የሚገባ መሪ…!!!

ተስፋአብ ተሾመ

* …. በዱላ የሚነዳ ሳይሆን እንደ መካከለኛው ምስራቅ እረኛ ያለ አውቀነው ምንከተለው መሪ እንፈልጋለን…!
ጥንት በመካከላቸው ምስራቅ ያሉ እረኞች ከኛ አገሮቹ እረኞች በመሠረታዊ ነጥብ ይለያሉ፡፡
መቼስ ብዙዎቻችን ቤተሰቦቻችን ከገጠር የሆኑ ናቸውና እረኝነትን በደንብ አድርገን እንገነዘባለን፡፡ ስለዚህ ስለእረኝነት በብዙ ማስረዳት አይጠበቅብኝም፡፡ ስለሆነም የመካከለኛው ምስራቅ እረኞች ከኛ ሚለዩበትን ነጥብ ላንሳ፡፡
በመካከላቸው ምስራቅ ያሉ እረኞች በጎቻቸውን ሲያሰማሩ ከበጉ ፊት ሆነው ይወጣሉ፡፡ (በሌላ አከባቢ የተለመደው በጉ ከፊት ሆኖ እረኛው ከኋላ ነው ሚሆነው) እረኛው ከፊት በመሆኑ የተነሳ መንጋው ላይ አደጋ ቢፈጠር ቀድሞ ሚጋፈጠው እረኛው ነው፡፡ ተኩላ ቢመጣ እረኛው ፊት ለፊት ይጋፈጠዋል፡፡ ስለበጎቹም መስዋዕት ይሆናል፡፡ (መልካም እረኛ ለበጎቹ ራሱን ይሰጣል!) ደግሞም ከፊት ለፊት እረኛው ሲሆን ወደ ለምለሙ መስክ በቀጥታ ራሱ ይመራል፡፡ እረኛው ከኋላ ሲሆን ግን ለምለም ስፍራን የማግኘት ከፊል ሃላፊነት በመንጋው ትኬሻ ላይ ይወድቃል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ እረኞች በበጎቻቸው ይታወቃሉ፡፡ መንጋው እረኞቹን በጠረን ጭምር ይለያቸዋል፡፡ የግሞም ያምናቸዋል፡፡ ስለሆነም እረኛው ከፊት ሲሄድ መንጋው እረኛውን በእምነት ይከተለዋል፡፡
እረኛው ከጀርባ ሆኖ አይነዳም፡፡ ነገር ግን ከፊት ሆኖ ይመራል፡፡ ከኀላ ሆኖ በብትር መንጋውን አይደበድብም፡፡ ከፊት በሃላፊነት ስሜት ሆኖ ሲራመድ ከኀላ መንጋው አምኖ ይከተለዋል፡፡
መንጋው እረኛውን ያውቀዋል፡፡ የግሞም ያምነዋል፡፡ ያለ በትር ገጉልበትም ይከተለዋል፡፡
እረኛው መንጋው አሳምሮ ያውቃል፡፡ እነርሱም ያውቁታል፡፡ከፊት ሆኖ ይመራል እንጂ ከኀላ ሆኖ በብትር ጉልበትም አይነዳቸውም፡፡ አደጋ ሲኖር ቀድሞ ይጋፈጣል፡፡ ደግሞም ወዴት መንጋው ምን እንደሚፈልግ ያውቃልና ወደ ለምለሙ መስክ ይመራቸዋል፡፡
እኔና ቤቴ እንዲህ ያለ መሪ እንመኛለን፡፡ ከጀርባችን ሆኖ ማይነዳን በበትር ጉልበት ማይገዛን በአደጋ ወቅት ተጋፋጭ ማያደርገን መሪ እንሻለን፡፡ እኔና ቤቴ ትልማችንን ሚረዳ ደግሞ የጥያቄያችን መልስ የት እንዳለ ሚያውቅ ወደ መልሱም ሚመራን መሪ እንሻለን፡፡
Filed in: Amharic