>
5:13 pm - Sunday April 19, 6308

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይለምልም:- የጋምቤላ ሕዝቦች ክልልን እንደ ማሳያ! በዲ/ን ተረፈ ወርቁ (ከጋምቤላ)

ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይለምልም:- የጋምቤላ ሕዝቦች ክልልን እንደ ማሳያ!

 
በዲ/ን ተረፈ ወርቁ (ከጋምቤላ)
 
1. እንደ መንደርደሪያ

ኢትዮጵያዊነት ሰው የመሆን ክብርን ያጎናጸፈን- የፈጣሪ/የአምላክ ፍቅር መገለጫ የኾነ ሕያውና ክቡር ማንነት ነው። የሚለው እሳቤ ብዙዎቻችንን ኢትዮጵያውያንን ያስማማናል ብዬ እገምታለሁ። ኢትዮጵያዊነት- በሺሕ ዘመናት ረጅም ታሪክና ገናና ሥልጣኔ ከፍ ያለ፣ ሰው የመኾን ከአምላክ ዘንድ የተቸረን ፍቅርንና የነጻነት ክብርን በዐድዋ ተራሮች ላይ በደም ያተመ ታላቅ፣ ሕያው ማንነት ነው፤ “The Adowa Victory provided practical expression to Ethiopianism: self-worth, dignity, unity, confidence, self-reliance, race pride, spirituality and freedom from colonialism.” እንዲሉ የደቡብ አፍሪቃው የነጻነት ታጋይ ኔልሰን፣ ሮሂላላ ማንዴላ።
ይህ ከአፍሪካ እስከ ሰሜን አሜሪካ፣ ከዐረቢያ ምድር እስከ መካከለኛው ምሥራቅ- ኢየሩሳሌም፣ ከግሪክ እስከ ሮማ፣ ከቻይና እስከ ህንድ፣ ከራሺያ እስከ ኮሪያ ልሣነ ምድር፣ ከታላቋ ብሪታንያ- ለንደን እስከ ጀርመን- ሀምቡርግ፣ ከሊግ ኦፍ ኔሽን እስከ ተባበሩት መንግሥታት፣ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት እስከ አፍሪካ ኅብረት፣ የነጻነትን ክቡርና ክቡድ መንፈስ ያተመ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ትንፋሹ ቢሰልም፣ ኃይሉ የደከመ ቢመስልም ዛሬም ሕያው ነው።
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት- ከእስራኤላዊው ነቢይ ሙሴ እስከ ነቢዩ መሐመድ፣ ከሔሮዱተስ እስከ ሆሜር፣ ከዱ- ቦይስ እስከ ማርከስ ጋርቬይ፣ ከቦብ ማርሌይ እስከ ፒተር ቶሽ፣ ከጆሞ ኬንያታ እስከ ንኩርማ፣ ከማንዴላ እስከ ታቦ እምቤኪ- የጥቁር ሕዝቦች ማንነትና የአፍሪካውያን የነጻነት ተጋድሎ ጉዞ ታሪክ ውስጥ- በክብር የላቀ፣ ከፍ የተደረገ ማንነት ነው።
2. ጋምቤላ፤ ኢትዮጵያዊነት ለዘላለም ይለምልም!
ከሰሞኑን ለአንድ የጥናትና ምርምር ሥራ በጋምቤላ ሕዝቦች ክልል ነኝ ያለኹት። እናም ኢትዮጵያዊነት- በፍቅርና በአንድነት መንፈስ የጸና ማንነት መኾኑ ዳግመኛ እንዳስታውስ ያደረገኝን አንድ የጋምቤላ ገጠመኜን ላወጋችሁ ወደድኹ። ትናንትና ረፋድ ላይ ከአንድ የሥራ ስብሰባ በኋላ የጋምቤላ ክልል ተወላጅ የሆነ ሰው ወደ አንድ መንደር ለጉብኝት ይዞን ሄዶ ነበር። የሄድንበት መንደር ደግሞ የጎንደር፣ የትግራይ፣ የወሎ ሰፈር የሚል ስያሜ ያላቸው ናቸው።
በእነዚህ ሰፈሮች ያሉ ነዋሪዎች በአብዛኛው በ1977ቱ አስከፊ ረሃብ ወቅት የደርግ  መንግሥት ያሰፈራቸውና በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት ለኑሮ ወደ ጋምቤላ የመጡ በአብዛኛው የሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝቦች ያሉበት አካባቢ ነው። ሁኔታው ሀገራችንን በማያቋርጥ ቀውስ ውስጥ ከከተታት ከወቅታዊው የብሔር/የዘውጌ ፖለቲካ አንፃር- ይህ በጋምቤላ ክልል በሰላም እየኖሩ ያሉ የተለያየ ብሔር ያላቸው ኢትዮጵያውያን መኖራቸው ውስጤን ደስ አሰኘው። በዛ መንደር የታዘብኩት እውነታ- ነገ ሰው በመሆናችን ልኬት ብቻ ተከባብረን በፍቅርና በሰላም የምንኖርበት ዕድል በእናት ምድራችን ኢትዮጵያ ገና ፈጽሞ ያልጠፋ መሆኑን ማየቴ ልቤን ተስፋ ሞላው።
በዚህ የትልቋ ኢትዮጵያ ማሳያ በኾነው መንደር ቆይታችን ሌላው ያስገረመኝ ነገር በትግራይ ሰፈር ባለ ውብ ጫካና ተራራ ላይ፤ “የጋምቤላ ዳግማዊ ደብረ ዳሞ አቡነ አረጋዊ” የሚባል ገዳም አለ። ይህን በተራራ ላይ የሚገኘውን ገዳም ለማየት በጋምቤላ ሙቀት ልብሳችን በላብ ተነክሮ ከግማሽ ሰዓት ያህል ጉዞ በኋላ ነበር ወደ ገዳሙ የደረስነው። ገዳሙ ካለበት ተራራ ላይ ሆኖ ቁልቁል የጋምቤላ እልፍኟና ጓዳ ጎድጓዳዋ ሳይቀር ወለል ብሎ ይታያል። እንደ እንግሊዙ ወንዝ ቴንስ የጋምቤላ ከተማን መሃል ለመሃል ቆርጦ የሚያልፈውና በዓሣ ሀብቱ እጅጉን የታወቀው የባሮ ወንዝም በሩቅ ሲገማሸር ይታያል። የገዳሙ አካባቢ ተፈጥሮአዊ ውበትና ንጹሕ አየሩ ደግሞ የጋምቤላን ሙቀቱንና ድካሙን ፈጽሞ የሚያስረሳ ነው።
3. አቡነ አረጋዊ ከሮም እስከ አክሱም እና ጋምቤላ ምድር
በ፮ኛው መቶ ክዘመን በሃይማኖት ልዩነት ምክንያት ከሮም ወደአክሱማውያን ግዛት ተሰደው የመጡት አባ ዘሚካኤል፤ በአክሱማውያን አጠራር አባ አረጋዊ- በትግራይ ክልል እርሳቸው በዘንዶ ተሳፍረው ወይም ዘንዶውን እንደ ዘመናችን Cable car ተጠቅመውበት ተራራው ጫፍ ላይ በገደሙት በደብረ ዳሞ ገዳማቸው ይታወቃሉ።
እኚህ ከአውሮፓ ምድር የመጡ መናኝ አባት ቢያንስ እስከ ቅርብ ጊዜያት ድረስ በትግራይም ሆነ በመላው ኢትዮጵያ ማንም ቢሆን አውሮጳዊ ዘራቸው/ማንነታቸው ትዝ ብሎት አያውቅም። እርሳቸውም ራሳቸውን በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ ዘላለማዊ ፍቅር ሰማያዊ ዜጋ ያደረጉ የወንጌል ገበሬና ሐዋርያ ነበሩና- በፍቅር አክብሮ የተቀበላቸውን ልዩ ኢትዮጵያዊ ማንነትን በሰማያዊ ዜግነታቸው ወደፍጽምና ለማሳደግ የተቻላቸው የበቁ፣ መናኝ አባት ነበሩ።
የዘመኑ የአክሱማዊነት/የኢትዮጵያዊነት እሳቤ ወይም ፍልስፍናም ይህን በፍቅር ላይ የተገነባ መንፈሳዊ ዜግነትን አምኖ ከመቀበል ባሻገር፤ ኢትዮጵያዊነት ሰው የመሆን ክብርን የሚያጎናጽፍ፣ የፍቅር ካባ ሆኖ ከዐረቢያ ምድር የተሰደዱ የነቢዩ መሐመድን ተከታዮች እንኳን ሳይቀር አቅፎ የተቀበለ ማንነት መሆኑን ለዓለም ሁሉ አሳይተውበታል።
ዛሬ አቡነ አረጋዊን ከአውሮፓዊ ማንነታቸው ወይም ዜግነታቸው ነጥለን፣ በፍቅር አክብሮ ከተቀበላቸው ኢትዮጵያዊነት አራቁተናቸውና ከሰማያዊ ዜግነታቸው አፋተናቸው- ትግራዋይ ማንነትን በግድ የደረብንላቸው አሳፋሪ ጊዜ ላይ ደርሰናል። በአንድ ወቅት ዲ/ን ዳኤል ክብረት በሀገረ-አውስትራሊያ ለወንጌል አገልግሎት በቆየበት አጋጣሚ፤ “ወደ አቡነ አረጋዊ ቤ/ክ እንዴት ትሔዳለህ- አቡነ አረጋዊ የወያኔ/የትግሬዎች ቤ/ክ ነው ያሉ ሰዎች ገጥመውት እንደነበር በመጦመሪያ መድረኩ/በብሎጉ ያሰፈረውን ጽሑፉን ያስታውሷል።
በዘርና በጎሳ ተከፋፍለን ጦር አውርድ ፍጥጫ ውስጥ የገባን እኔንና ትውልዳችንን- የእኚያ ኢትዮጵያዊነት ፍቅር፣ ኢትዮጵያዊነት ሰው የመሆን ክብር እንደሆነ ለዓለም የገለጹ የታላቁ አባት የአቡነ አረጋዊ ነፍስ፤ የአክሱማውያን/የኢትዮጵያውያን ታላቅ መንፈስ ምን ይለን ይሆን ግን…?!
4. እንደ ማጠቃለያ
በእኛ ዘመን ያ ሰው የመሆን ክብር ቱንቢና በፍቅር የተሰፋ ኢትዮጵያዊ ማንነት እጅጉን ጠቦን፣ ሰው የመሆን ክብራችን ተበሳስኮና ተቀዳዶ “እናንተና እኛ እኮ” ወደሚል የብሔር/የዘውጌ ክፍፍልና ልዩነት ውስጥ ወድቀን ዓለም ሁሉ አፉን በእጁ ላይ ጭኖ በምፀት የሚታዘበን አሳዛኝ ሕዝቦች ሆነናል። እናም ከየት እንደወደቅን እናስብ ዘንድ- ይህ አጭር ጽሑፍ ሕያውና ክቡር በሆነው የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ይለምናል፤ ይማጸናል።
የጋምቤላ ሕዝቦች ክልል ለታላቋ ኢትዮጵያ መገለጫ የኾነው የወሎ፣ የትግራይ፣ የጎንደር ሰፈር ከጋምቤላና ከሌሎች የሀገራችን ሕዝቦች ጋር ያለው የአብሮነት ኑሮና ማኅበራዊ መስተጋብር- ኢትዮጵያዊነት ዛሬም ሕያው ለመሆኑ ማረጋገጫ ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም። እንደ ኦባንግ ሜንቶ ያሉ የጋምቤላ ምድር ያፈራቸው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ለዚህ የኢትዮጵያዊነት ሕያውና ክቡር መንፈስ ትልቅ ምስክርና ማሳያ ናቸው። ፈጣሪ ሰላምሽን ያብዛው ጋምቤላ፣ ውቧ ምድር!

ኢትዮጵያዊነት/ሰው የመሆን ክብር ለዘላለም ይለምልም!!

Filed in: Amharic