>

ሲወለድ የታመመ ሲሞት ብቻ ይፈወሳል.. !!! (መስከረም አበራ)  

ሲወለድ የታመመ ሲሞት ብቻ ይፈወሳል.. !!!  

መስከረም አበራ    


ኢህአዴግ የሚባለው ህወሃትን የሶስት ዋነኛ፣የአምስት ምክትል ሎሌዎች ጌታ አድርጎ የኖረው ፓርቲ ፈርሶ ብልፅግና በሚባለው ፓርቲ ሲተካ የሃገራችን ፖለቲካ የተሻለ መስመር ይይዛል ብለው ተስፋ ካደረጉት ወገን ነበርኩ፡፡የተስፋየ ምክንያት በርካታ ነው፡፡አንደኛው የሃገራችን ፖለቲካ በቀላሉ እርምት ሊያገኝ የሚችለው እንዳይሆን አድርጎ ያበላሸው ኢህአዴግ ራሱ እንዳበላሸው አድርጎ ካስተካከለው  ነው በሚል ነበር፡፡ ሁለተኛው ምክንያቴ ህዝባዊ ለውጡን ከውስጥ ሆነው ያገዙ የኢህአዴግ ካድሬዎች ለውጥ የፈለጉት በአንድ ጌታ ስር ማደር ሰልችቷቸው፣በራስ እምነት የመኖር ክብሩ ተገልጦላቸው መስሎች ነበር፡፡ ሶስተኛው ምክንያቴ ኢትዮጵያን ለማስቀጠል እንሰራለን ሲሉ የኢህአዴግ ሰዎችንም ቢሆን እስከማመን የሚደርስ ተላላነት ስላለኝ ሳይሆን አይቀርም፡፡የሆነ ሆኖ ሃገራችንን ከህወሃት/ኢህአዴግ መዳፍ ማላቀቁ እንዲህ በቀላሉ የሚሆን ስላልሆነ ለውጥ ልናመጣ ነው ያሉ ሰዎችን ጊዜ ሰጥቶ ማየቱ ጥፋት አይደለም፡፡

ብልፅግና የተባለው ፓርቲ ሲመሰረት የሃገራችንን ሁለንተናዊ ችግር ይፈታል የሚል የጅል ተስፈኛ እንደማይኖር እሙን ነው፡፡ ተስፋው ቢያንስ እንደ ህወሃት ሰማይ የደረሰ ጌታ እና እንደ አጋር/አባል ፓርቲዎቹ ትቢያ ላይ ተንበርክኮ “አቤት ወዴት” የማለትን ያህል የተራራቀ የአዛዥ ታዛዥ ግንኙነት በብልፅግና ፓርቲ ውስጥ አይደገምም የሚል ነበር፡፡ሰማይ ከምድር እንደሚርቅ ተራርቆ የኖረውን የጌታ እና የሎሌ የፖለቲካ መስተጋብር ለማቀራረብ ይረዳል ብየ በግል አስበው የነበረው ከውጭ ሆነው ሲያዩት በኦህዴድ እና በብአዴን መኳንንት ዘንድ የመጣ የመሰለው የእሳቤ ለውጥ ነበር፡፡

ይህ ለውጥ ከኦህዴድ አኳያ የበለጠ ታግያለሁ ብሎ ለስድነት የሚዋሰን ጌትነት መሻት መጨረሻው እንደ ህወሃት መሆን እንደሆነ መረዳት አያዳግተውም የሚል ትልቅ ተስፋ ነበር፡፡ ከብአዴን አንፃር የድሮው ብአዴን ሆኖ በአማራ ህዝብ ትከሻ ላይ ለአንድ ተጨማሪ ወር እንኳን መኖር የማይታሰብ እንደሆነ እንደው በጥቂቱም ቢሆን መገንዘብ ተችሏል በሚል ነበር፡፡ሆኖም የኦሮሚያ ብልፅግና ሆኛለሁ ያለው ኦህዴድም  ሆነ የአማራ ብልፅግና ተብየ የአማራን ህዝብ እመራለሁ የሚለው ብአዴን ካድሬዎች ያሰብነውን ለውጥ በሚያመጣ መንገድ የተለወጡ አልሆኑም፡፡

አለመለወጡ የሚብሰው ግን በብአዴን ላይ ነው፡፡ ኦህዴድ ተቀይሮ የህወሃትን ቦታ ልያዝ እያለ እንደሆነ ሽመልስ አብዲሳ አይሰማም መስሏቸው ካወሩት ብቻ ሳይሆን እነ ታከለ ኡማ ከሚተገብሩት ሁሉ መረዳት ይቻላል፡፡በርግጥ መለወጥ ሁሉ መልካም አይደለም፤ወደ ህወሃትነት መለወጥ ደግሞ ምን ማለት እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡

መለወጥ በፊቱ ዝር የሚል የማይመስለው የአማራ ብልፀግና ፓርቲ ነው፡፡ይህ ፓርቲ ከተለወጠም የሚለወጠው ወደ ብአዴንነት ወይም ኢህዴንነት ነው፡፡የአማራ ብልፅግና ፓርቲ አለመለወጥ፣ከተለወጠም ወደ በጎ አለመለወጥ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩትም ዋነኛው ምክንያት ግን ሲፈጠር ጀምሮ የተጠናወተው የዲዛይን ችግር ነው፡፡ይህ የብአዴን ዋነኛ ደዌ የሚመነጨው ብአዴንን ዲዛይን ካደረገው ህወሃት ሆኖ ተሰሪውን ብአዴንን ለማይድን በሽታ አሳልፎ ሰጥቶት ቀርቷል፡፡የብአዴን ነገር በእናቱ ሆድ ሲጠነሰስ ጀምሮ ለአንዳች አካላዊም ሆነ አእሯዊ ልምሻ ተጋልጦ መላ አካላቱ እንዳልሆነ ሆኖ የተወለደን ህፃን ልጅ ይመስላል፡፡ከእናቱ ሆድ ሲወጣ በተበላሸ የአካል ቅርፅ የተወለደ ልጅ የትኛውንም ህክምና ቢያገኝ ጤነኛ ልጅ ሊሆን አይችልም፡፡ይህን አይነት ልጅ ጤነኛ ለማድረግ የሚደረገው ድካምም ከንቱ ድካም ነው፡፡

ህወሃት ብአዴንን ሲሰራው የተሰራበትን አላማ እያመከነ እንዲኖር ነው፡፡ይህም ማለት  ብአዴን የተፈጠረው ለሰፊው የአማራ ህዝብ መብት መከበር ነው የሚል የይስሙላ ፕሮፖጋንዳ ነገር ነበረ፡፡ ሆኖም በእውነታው ዓለም ብአዴን የቆመው ይህን አላማ ለማምከን፣አማራውን ያለ እውነተኛ መሪ ለማስቀረት ነው፡፡ከአላማ በተቃራኒ መቆም ማለት ይህ ነው፡፡ይህን ደግሞ ከብአዴን በላይ የቻለበት ፓርቲ የለም፡፡

ህወሃት ብአዴንን ሲፈጥረው አማራ ሁሉ ጨቁኖኛል፣አማራ ሁሉ ጠላቴ ነው የሚለውን እሳቤውን ከልቡ ሳይፍቀው ግን ለአፉ ጭቁኑ አማራ ምንም አላደረገኝም ጠላቴ የአማራ ገዥ መደብ ነው ማለት የጀመረ ሰሞን ነው፡፡ህወሃት የሆዱን በሆዱ አድርጎ ድንገት ጭቁን ነህ ላለው ሰፊው የአማራ ህዝብ  ወኪል ይሆን ዘንድም ኢህዴንን “ብአዴን” ሲል ጠራው፡፡”ከዛሬ ጀምሮ ብአዴን ትባላላችሁ” የተባሉት መኳንንትም ከማኒፌስቶ 68 ጀምሮ እስከ ሽግግር ቻርተር ድረስ የኢትዮጵያ ታሪክ መርገም ሁሉ ምክንያቱ አማራ ነው የሚለውን የጌታ ህወሃትን የፖለቲካ ዘፍጥረት ያነበነቡ ጀመር፡፡

ድርጅቱን እንዲመሩ የተሰየሙት መሪዎችም የሚታየውን የአማራ ህዝብ ድህነት ይገነዘቡ ዘንድ የሰው ልጅ ልቦና ያልፈጠረባቸው፣ከአማራ ህዝብ ጋር የመንፈስ ቁርኝት የሌላቸው፣ምናልባትም አማራ ወደሚባለው  ክልል የሚወስደው መንገድ በየት በኩል  ወዴት እንደሆነ ለማወቅ መሪ የሚያስፈልጋቸው  የህወሃት ግዙዎች ናቸው፡፡የነዚህ ሰዎች ራስ ደግሞ ኤርትራዊው በረከት ስምኦን ነበር፡፡ከፅንሰቱ በዚህ መንገድ የተፈጠረበትን አላማ እያመከነ እንዲኖር ዲዛይን የተደረገው ብአዴን ስም ቢቀይር፣መዋቅር አስተካከልኩ ቢል ከተሰራበት ግብሩ ፈቅ ነቅነቅ ሊል አልቻለም፡፡

ብአዴን የተሰራበት የራስን አላማ አፈር የማልበስ፣በገዛ ህዝቡ ላይ ጦር ነቅንቆ ማቁሰል፣ቢለዋ ስሎ በጀርባ የማረድ  ግብር በራሱ ትልቅ ችግር ሆኖ ሳለ ሌላ ችግርን ወዷል፡፡ ይህ ችግር የህወሃት እና የኦህዴድ የጥንካሬ ምንጭ የሆነው የክርስትና አባት(God father) አልቦ ድርጅት መሆኑ ነው፡፡ እንደ እኛ ሃገር ተቋማዊነት ባልበረታበት፣ፖለቲካውም የቤተሰብ መልክ ባለው የዘውግ እሳቤ በሚደወርበት ኋላቀር የፖለቲካ አውድ የክርስትና አባት ፖለቲካ የአንድ ፓርቲ የጥንካሬ ምንጭ ነው፡፡ህወሃት ከጫካ ጀምሮ ስብሃት ነጋ፣ስዩም መስፍን፣አባይ ፀሃይየ የሚባሉ በርከት ያሉ ክርስትና አባቶች ያለው ድርጅት ነው፡፡በመሆኑም የፓርቲው አባላት በጥቃቅን ነገሮች ላይ ልዩነት ቢኖራቸውም የትግራይን  ህዝብ ጥቅም በተመለከተ ግን በጋራ የሚያዩት ራዕይ አላቸው፡፡

ከዚህ ራዕይ ፈቀቅ ሲሉ እነዚህ የክርስትና አባቶች ከመስመር የወጣውን በውግዝም ሆነ በእርግማን ወደ መስመር አንዲገባ ያደርጋሉ፡፡በተመሳሳይ ኦህዴድም አባዱላ ገመዳ የሚባል ክርስትና አባት አለው፡፡ኦህዴድ እንደሰው፣ አባዱላ እንደ ድርጅት ደግሞ ኦነግ የሚባል የክርስትና አባት ስላለው የተቋቋመበትን የኦሮሞ ብሄርተኝትን ዋነኛ ዓላማዎች ለሰኮንድ ችላ ሳይል ያለ ይሉኝታ ያስፈፅማል፡፡ኦህዴድን በህወሃት ወንበር ለመቀመጥ ያበቃውም መንገዱን የሚመራው ክርስትና አባት ያለው ፓርቲ መሆኑ ነው፡፡

የኦህዴድ የፓርቲ ክርስትና አባት ኦነግ ለኦሮሞ ቆምኩ የሚሉ አካላት ሁሉ ሊያሟሉ የሚገባቸውን ስትራቴጂያዊ ግቦች  ቁልጭ አድርጎ አስቀምጦለታል፡፡ ይህን ስትራቴጅ እንደ ኦህዴድ ለማስፈፀም ደግሞ አባ ዱላ የተባለው ክርስትና አባት ቅድመ-ሁኔታዎችን ያስተካክላል፡፡ ከነዚህ ቅድመ-ሁኔታዎች አንዱ ህወሃት በመንበሩ ላይ እያለ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ፖለቲካ ስጋት እንዳይሆንበት ሲል በፓርቲው ላይ የሚያሳርፈውን ጡጫ በመከላከል ይልቅም ከለላ በመስጠት ወጣት የኦሮሞብሄርተኞች ፓርቲውን እንዲቀላቀሉ ያላሰለሰ ሚና ተጫውቷል፡፡

ይህ ሚናውም እንደ ዶ/ር አብይ፣አቶ ለማ፣አቶ አዲስ አረጋ፣አቶ ሽመልስ አብዲሳ፣ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የመሳሰሉ የሃገርን በትረ ስልጣን የሚመኙ የኦሮሞ ብሄርተኞች ብቅ እንዲሉ ረድቷል፡፡እነዚህ አዲስ ኦሮሞ ብሄርተኞች ራሳቸው አንደተናገሩት “አደናግረው”፣”አሳምነው” እና “ቆምረው” የፌደራል ስልጣን ላይ ወጥተው በኦነግ ልብ ታስቦ በስልጣን እጥረት ምክንያት ገቢራዊ ያልሆኑ የኦሮሞ  ብሄርተኝት ዋነኛ ህልሞችን ወደ እውንነት ለመቀየር እየሞከሩ ነው፡፡

በአንፃሩ ብአዴን ለራሱ ከእናቱ ሆድ ሲወጣ ይዞት በወጣው የዲዛይን ችግር ወለድ ደዌ በመሰቃየት ላይ ሲገኝ እመራዋለሁ የሚለውን ህዝብ ደግሞ ለስለት እና ለድንጋይ ሞት አሳልፎ ሰጥቶ ፈዞ ቀርቷል፡፡ብአዴን የተፀነሰው በእንጀራ እናት ማህፀን ውስጥ በመሆኑ ምንም አይነት የፖለቲካ ዓላማ እየተመገበ ያደገ ፓርቲ አይደለም፡፡ሰው በእናቱ ተወልዶ በእንጀራ እናት ቢያድግ የተለመደ ነገር ነው፡፡ ከጅምሩ ለልጇ እድገትን ሳይሆን መቀጨጭን በምትመግብ እንጀራ እናት ሆድ ውስጥ ተፀንሶ መወለድ ግን በምድር ላይ ታይቶ የማይታቅ ነገር ነው፡፡

የብአዴን የእንጀራ እናቶቹ በረከት ስምዖን ፣አዲሱ ለገሰ አና ተፈራ ዋልዋ የሚባሉ በየደረሱበት አማራውን የሚያንቋሽሹ እንጅ ለአማራው ህዝብ ጥቅም የሚሆን አንዳች ስትራቴጅያዊ ዓላማ የማያስቀምጡ ሰዎች ናቸው፡፡እነዚህ ሰዎች ከኢህዴን ወደ ብአዴን የተቀየረው ጉደኛ ፓርቲ መስራቾች ቢሆኑም የአማራን ህዝብ በእውነት የሚመራበትን ስትራቴጅ ለቀጣዩ ትውልድ የሚያቀብሉ፣መንገድ የሚያቀኑ አባዱላ ለኦህዴድ የሆነውን አይነት የክርስትና አባቶች ሊሆኑ አይችሉም፡፡የዚህ ጉዳይ መዘዝ የአማራ ህዝብን ለሰላሳ አመት በማይታጠፍ ሰይፍ እንዲታረድ ምክንያት ሆኗል፡፡

እንጀራ አባት እንጅ ክርስትና አባት የሌለው ብአዴን በዚሁ አስገራሚ አፈጣጠሩ ሳቢያ በድርጅቱ ውስጥ ምንም አይነት ወደ በጎ የመለወጥ ክስተት እንዳይኖር እግድ ሆኖበታል፡፡መቀየር ካለም ወደ ባሰ አሽከርነት፣ወደ ተባባሰ ዓላማ የለሽነትና ወደ ሚያስገርም ለህዝብ መከራ ስሜት አልቦነት ነው፡፡ይህ ብአዴን ከተፈጠረበት እስከ ዛሬ ድረስ እንደ ጥላ የሚከተለው እውነተኛ መልኩ ነው፡፡ይህን አስቀያሚ መልኩን ለራሱ ይዞ ቢቀመጥ ብዙም የሚያስጨንቅ ነገር ባልነበረው፡፡ ችግር የሆነው ብአዴን የሚናቅበትን መናቅ ወደ አማራ ህዝብ ማስተላለፉ ነው፡፡

ከህወሃት/ኢህአዴግ  እስከ ኦህዴድ/ብልፅግና ሃገሪቱን የሚመሩ ዘውገኛ መሪዎች ብአዴንን በሚያዩበት የንቀት ዓይን የአማራን ህዝብ ያያሉ፡፡ህወሃት በብአዴን የተነሳ የአማራን ህዝብ የመናቁነገር ተወርቶ አያልቅም፡፡ ከሁሉ የሚብሰው ግን የወልቃይት ጠገዴን መሬት ወስዶ ህዝቡን በገዛ መሬቱ ላይ ግዞተኛ ማድረጉ ነው፡፡በጦር ሜዳ ጀብዶ ስልጣ የያዘው ህወሃት ቀርቶ ራሱ ብአዴን እሽኮኮ ብሎ ስልጣ ላይ ያስቀመጠው ጠ/ሚ አብይ ለአንድ ክልል ህዝብ ብለን ህገ-መንግስት አንቀይርም ሲሉ ንቀታቸውን ጠቆም አድርገዋል ሲቀጥልም የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ የመልካም አስተዳደር እና የልማት እንጅ የማንነት አይደለም ሲሉ ተሳልቀዋል፡፡ይህ ሁሉ የሆነው የብአዴን ለንጉስ ማጎንበስ የአማራ ህዝብ ማጎንበስ ተደርጎ በመቆጠሩ ነው፡፡

ብአዴን ወደ በጎ እንዳይቀየር ዋነኛ ደንቃራ የሆነበት የቆየ ምክንያት  በረከት ስምኦን የሚባል የህወሃት ዋርድያ በቁራኛነት ስለታሰረበት ነው፡፡ይህ ሰውየ ከጅምር እስከፍፃሜ ፓርቲውን ሲያሾር የኖረ ሰው ነው፡፡በረከት ስምኦንን የብአዴን ዋርድያ አድርጎ ያሰረውን የህወሃትን ገመድ መበጠስ ዘጠኝ ሱሪ መታጠቅን ይፈልግ ይሆናል እንጅ የማይቻል ነገር ግን አልነበረም፡፡ብአዴን ደግሞ እንኳ ዘጠኙ አንዱም ሱሪ እየሰፋ የሚወርድበት ካድሬ የተጠራቀመበት እንደሆነ ማሳያው ዛሬም ድረስ “ህዝቤን ያስገደልክልኝ ሆይ ካባ ይገባሃል” ባዩ ሰውየ ከሰው ተመርጦ ክልሉን እየመራ መሆኑ ነው፡፡

የሆነው ሆኖ በኦህዴድ ውስጥ አባዱላን የመሰለ ክርስትና አባት ያመጣው አጋጣሚ ለብአዴንም ሊሆን የሚችልበት የመጀመሪያው አጋጣሚ አማራ የሆነ ሰው ክልሉን እንዲመራ የሆነበት አቶ አያሌው ጎበዜ የተባሉ ሰው ወደ ስልጣን የመጡበት ዘመን ነበር፡፡ሆኖም ሰውየው ራስ ደህና ባይ ነገር ሆነው ኖሮ በኢህአዴግ ቤት የአማራ ክልልን ለመምራት ቅድመ ሁኔታ ተደርጎ የተቀመጠውን የአማራን ህዝብ ስቃይ እንደ አስደሳች ዶክመንተሪ ፊልም ቁጭ ብሎ ከማየት ያለፈ አንዳችም የሚታወሱበት ስራ ሳይሰሩ ወደ ሚሄዱበት ሄደዋል፡፡

ቀጥለው የመጡት አመራሮችም ቢሆኑ የዚህን ሰውየ ፈለግ ከመከተል ያለፈ የሰሩት ስራ የለም፡፡በጋራ ተናበው ትርጉም ያለው ስራ መስራት ቀርቶ በጋራ የሚያልሙት ህዝባዊ ዓላማ የለም፡፡ ሁሉም የሚያልመው የራሱ ኑሮ የደቀነበትን ፈተና የሚያቀለበትን የራሱን ዓላማ ነው፡፡አንዱ V8 ላይ ለመውጣት ሲያልም ሌላው ከ V8 ላለመውረድ ያልማል፣ሌላው ከሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲም ቢሆን ዶክተር የሚባልበትን ጥበብ ሲያሰላ ሌላው እዴት በንጉስ ፊት አጎንብሶ የፌደራል ባለስልጣን አንደሚሆን ይተልማል ሌላው እንዴት የፌስቡክ አክቲቪስት ቀጥሮ የራሱን ፖለቲካዊ ኪሎ እንደሚጨምሮ ያልማል፡፡በፓርቲው ውስጥ ያለው የአመራር ፍዘት ከዚህ ዝብርቅርቅ ዓላማ የሚነሳ ነው፡፡ አንድ አላማ የሌለው ሰው ፈር ያለው አመራር ሊሰጥ አይችልም፤በራሱ ግላዊ ዓላማ ፍቅር የናወዘ ሰው ለህዝብ ሊቆም ከቶም አይቻለውም፡፡

እንዲህ ባለ ልሙጥ የታዛዥነት ምግባር ዘመናቸውን ያሳለፉት በአዴኖች ህወሃትን በመጣሉ ከቆየ ማንነታቸው ጋር የማይጣጣም ስራ ሰሩ በሚል አማራጭ የሌለው ህዝብ በእነሱው ላይ ተስፋ አደረገ፡፡በዚህ ሰዓት የክልሉ መሪ የነበሩት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልልን የሚመራው ፓርቲያቸው ከሚታወቅበት የአቤት ወዴት ባይነት አባዜ የራሱ ነፍስ ያለው ሰው እንደሚያደርገው ያለ ፖለቲካ እንዲያራምድ ያደርጋሉ የሚል ትልቅ ተስፋ ተጥሎ ነበር፡፡ ምክትል ጠቅላይ  ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በባህርዳር ከተማ ተገኝነተው “እስካሁን አንሰማችሁም ነበር አሁን ግን ፈጥነን እንሰማችኋለን” ሲሉ በመናገራቸው ተስፋው የበለጠ አድጎ ነበር፡፡ሆኖም ችግሩ ከፅንሰት ውልደት የመጣ የዲዛይን ችግር ስለሆነ ፈቅ ነቅነቅ ማለት አልተቻለም፡፡ጭራሽ የክልሉን ባለስልጣናት ሽጉጥ ያማዘዘ ልዩነት ተፈጥሮ ቁጭ አለ፡፡

የሽጉጥ መማዘዙ ምክንያት ምን እንደሆነ አጥግቦ የሚነግር አንድስ አንኳን ከእውነት የወገነ ሰው ጠፍቷል፡፡እስከ ዛሬ ከተነገረው ሁሉ በበኩሌ ፍንጭ የሰጠኝ የፖለቲካ አመራሩ እና የፀጥታ ክፍሉ ተስማምቶ መስራት አለመቻል እንደሆነ ጀነራል ተፈራ ማሞ የፃፉት ፅሁፍ ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ የሰጠው ፍንጭ የፖለቲካ አመራሩ የተባለው አካል አሁን አሁን ከሚሰራው ከበፊቱ አንኳን የባሰ የአጎብዳጅነት ስራ ጋር ሲነፃፀር ከፀጥታ አካሉ ጋር ያልተስማማበትን ምክንያት ለመገመት አያዳግት፡፡የሆነው ሆኖ አሁን በፖለቲካ አመራሩ ላይ የሚሰነዘረው ፍላፃ የሚነሳው ከፀጥታ ሃይሉ አንዳይሆን በደንብ ታስቦበት የተሰራ ይመስላል፡፡

ሆኖም ከዚህ በኋላ የሚነሳው ተግዳሮት ዶክመንተሪ ፊልም ሰርተው የማያድበሰብሱት፣እከሌ ብለው ከሚረግሙት አንድ አካል ሳይሆን ሉዓላዊ ከሆነው ህዝብ የሚነሳ የፊቱን የትቂቶች የጠመንጃ ሞት ቅንጦት የሚያደርግ፣ለወሬ ነጋሪ የማያስተርፍ የዲን እሳትም ሊሆን ይችላል፡፡ሲወለድ የታመመ ሲሞት ብቻ ይፈወሳል!

Filed in: Amharic