>

በመተከል ዞን በተፈጸመ ጥቃት ከ80 በላይ ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን እማኞች ገለጡ...!!! (ማህበረ ቅዱሳን)

በመተከል ዞን በተፈጸመ ጥቃት ከ80 በላይ ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን እማኞች ገለጡ…!!!

ማህበረ ቅዱሳን

 በመተከል ዞን በተፈጸመ ጥቃት በቡለንና ወንበራ ወረዳዎች ብቻ ከ80 በላይ ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ የተገደሉ ሲሆን በስድስት ወረዳዎች ሃምሳ ሁለት አብያተ ክርስቲያን መዘጋታቸውን በአካባቢው የሚኖሩ ክርስቲያኖች ገለጡ።
በማንዱራ ወረዳ 16፣ በድባጢ ወረዳ 7፣ በወንበራ 5፣ በዳንጉር 15፣ በጉባ 7 እና በቡለን አንድ በድምሩ ሃምሳ ሁለት አብያተ ክርስቲያናት መዘጋታቸውን፣ በአንድ ቤተክርስቲያን ላይ የቃጠሎ፣ በአራት አብያተክርስቲያናት ላይ የዘረፋ መከራ መደረጉንና ከአምስት ወረዳዎች ከስድስት ሽሕ በላይ ክርስቲያኖች ቀያቸውን ለቀው መሰደዳቸውን ገልጠዋል።
የጸጥታ ችግር ያለባቸው 6 ወረዳዎች ማንዱራ፣ ዳንጉር፣ ጉባ፣ ወንበራ፣ ቡለን፣ ድባጢ መሆናቸውን የአካባቢው ኗሪ ክርስቲያኖች ገልጠው የተፈጠረው ችግር ብሔር ተኮር ቢመስልም ቤተክርስቲያንን ወደ መዝረፍ፣ ኦርቶዶክሳውያንን ማተብ ወደ ማስበጥስ፣ በየክርስቲያኑ ቤት እየገቡ ቅዱሳት ሥዕላትን ወደ መቅደድ መሸጋገሩን ተናግረዋል።
ጥቃት አድራሾቹ በሚገባ ሠልጥነው በትጥቅ የተደራጁ መሆናቸውን የተናገሩት እማኞቹ ኦርቶዶክሳውያን በብዛት የሚኖሩባቸውን አካባቢዎች እየመረጡ ማጥቃታቸውን ገልጠዋል።
 ከጷጕሜ አንድ ቀን ጀምሮ በቡለን እና በወንበራ ወረዳዎች ብቻ ቍጥሩ ወደፊት የሚጣራ ሆኖ ከ80 በላይ ክርስቲያኖች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን፣ የተፈናቀሉ ክርስቲያኖች ንብረት በመዘረፉ ለረሃብ፣ ለሰቆቃና ለኀዘን መዳረጋቸውን ገልጠዋል። የካህናትና የዲያቆናት መኖሪያ ቤቶች ለጥቃት ዒላማ መሆናቸውንም ለማወቅ ተችሏል።
Filed in: Amharic