>
5:13 pm - Thursday April 19, 8751

የእስክንድር እና የጃዋር ኢትዮጵያን ሳስባት!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

የእስክንድር እና የጃዋር ኢትዮጵያን ሳስባት!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

* ትላንት በዋለው ችሎት አቶ ጀዋር መሃመድ በእስር ቤት ውስጥ ለእሱና ከሱ ጋር ላሉ ሰዎች የተሟሉላቸው ነገሮች ለአቶ እስንድር እና አብረዋቸው ለታሰሩ ሰዎች መነፈጉን፤ እንዲሁም የእነ እስክንድር የእስር አያያዝ የከፋ መሆኑን ለችሎት መግለጹን ስሰማ ከአንድ አመት በፊት “የእስክንድር እና የጀዋር ኢትዮጽያን ሳስባት” በሚል ርዕስ የጻፍኩት ትዝብት ትዝ አለኝ። ትላንት በነጻው ሜዳ በእኩልነት ያላስተናገደቻቸው ኢትዮጵያ ዛሬ ደግሞ ሁለቱም በወንጀል ተጠርጥረው ቢታሰሩም መድሎው ግን አልቀረም። ይህን እውነታ ለመመስከሩ ጃዋርን ሳላመሰግን አላልፍም…!
 
ኢትዮጵያን በተመለከተም ይሁን ከኢትዮጵያዊነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ሁለቱ ግለሰቦች ፍጹም የተለያየ እሳቤ እና አቋም እንዳላቸው ግልጽ ነው። ሁለቱም ባመኑበት መንገድ የመሔድ፣ ያሻቸውን የማሰብ እና የመረጡትን የፖለቲካ አቋምም ሆነ ምልከታ የመያዝ መብታቸው ለውይይት የሚቀርብ አይደለም። ጃዋርን በአደባባይ መንቀፍ የሚፈሩ ሰዎች እስክንድርን ሲያብጠለጥሉ፣ ሲዘልፉ እና ሲያጣጥሉ ሳይ ገርሞኝ ነው ይህን አጭር ትዝብት ለመጻፍ የተነሳሁት። ትዝብቴም ኢትዮጵያ ሁለቱን ልጆቿን እንዴት ነው የያዘቻቸው የሚለውን ጉዳይ አንስቶ መወያየት የግድ ሳይል አልቀረም በሚል ነው።
ኢትዮጵያ የሁለቱም ነች። ኢትዮጵያን በተመለከተ እነሱ ያላቸው ምልከታ ከግምት ሳይገባ ማለት ነው። ጃዋር በአደባባይ ኢትዮጵያን ቅኝ ገዥ አድርጎ እና Ethiopia out of Oromia  የሚል መፈክር አያሰማ የፖለቲካውን ፍልሚያ የተቀላቀለ አክራሪ ብሔረተኛ ነው። ትግሉንም በብዙ ሺ ማይልስ ላይ ሆኖ እና ከወላፈኑም እርቆ የመራና የተሳካለት የመብት አቀንቃኝ ነው። እስክንድር ኢትዮጵያ የሁላችንም ነች፤ አንድ አገር፤ አንድ ሕዝብ፣ አንድ ባንዲራ የሚል መፈክር አንግቦ ለዲሞክራሲ የሚታገል ኢትዮጵያዊ ብሔረተኛ ነው። እዛው እሳት ውስጥ ቆሞ ሲታገል የኖረ፣ ለዛም እራሱ እና ቤተሰቦቹ ትልቅ ዋጋ የከፈሉ፣ እሱም በረዥም የእስር ዘመን ቁም ስቅሉን ሲያይ የኖረና በጽናቱ የሚታወቅ ጋዜጠኛና የመብት ተሟጋች ነው።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ ለጃዋር የተደላደለችና ያሻውን ለማድረግ የሚችልባት ምቹ ደሴት ስትሆን፤ ለእስክንድር ነጋ ደግሞ ትልቅ እስር ቤትና እሾህ የሆነችበት ምክንያት ምንድን ነው?  ጃዋር ሲያዋርዳት፣ ሲዘልፋት እና ሲያንቋሻት በነበረችዋ ኢትዮጵያ እንደ አንድ መሪ ተከብሮ፣ በከፍተኛ የታጣቂዎች አጀብ ታጅቦ ከአንድ የአገሪቱ ጫፍ ወደ ሌላ እንደልቡ እየተዘዋወረ፣ ያሻውን እየተናገረ፣ መንግስትንም ጭምር እያስፈራራ እና እየዘለፈ ያሻውን ሲያደርግ፣ በሕዝብና መንግስት ላይ ሲዝት እና ሲፎክር፣ ተከታይ ጀሌዎቹን እያዘዘ የሚፈልገውን ሲያደርግ ጠያቂ የለውም። ባጭሩ ኢትዮጵያን እንደልቡ ያለ ሕግ እና ሃይ ባይ ሳይኖርበት እየፈነጨባትም ነው። ሲሻው ሸምጋይ፣ ሲሻው ምሁርና መካሪ፣ ሲሻውም እንደ አንድ የመንግስት ባለሥልጣን፣ ሲሻውም እንደ ለውጥ አቀንቃኝም ሆኖ በመንግስት መድረኮች እንደልቡ ይናገራል።
በተቃራኒው ለኢትዮጵያ ክብር፣ ለኢትዮጵያዊያን መብት እና ነጻነት ሲሟገት፣ ሲጽፍ፣ ሲታገል፣ ሲታሰር፣ ሲፈታ፣ ሲደበደብ እና ሌሎች መከራዎችን ሲቀበል የኖረው እስክንድር ሃሳቡን በነጻነት እንዳይገልጽ፣ ሰዎችን በሕጋዊ መንገድ እንኳን አደራጅቶ ላመነበት የመብት ጉዳይ መንቀሳቀስ እንዳይችል በከፍተኛ የመንግስት ባለሥልጣናት ጭምር ዛቻ እና ማስፈራሪያ የሚሰነዘርበት፣ እንኳን ከክልል ክልል ሊዞር በአዲስ አበባ እንኳን ስብሰባ ማድረግ እንዳይችል የተከለከለባት፣ ለደህንነቱ የሚያሰጋ አደጋም ሲገጥመው እንኳ የመንግስት ጥበቃ እና ከለላ የማይደረግለት፣ የፖሊስ ባለስልጣናት ጭምር ዛቻ እና ማስፈራሪያ የሚሰነዝሩበት፣ የእሱን ሃሳብ የደገፉ ሰዎች የሚታሰሩበት እና የሚዋከቡበት፣ በሰበብ አስባቡ ስብሰባዎችን እና ጋዜጣዊ መግለጫ እንኳን እንዳያረግ ክልከላ እና ወከባ የሚፈጸምበት፣ ከዛም አልፎ ሥርዓት አልባ በሆኑ ግለሰቦች በአደባባይ ልንገለው ነው እያሉ ዛቻ ሲሰነዘርበት በግላጭ እያየን ነው።
ጃዋርም ሆነ እስክንድር ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች የሚያራምዷቸው ሃሳቦች ላይ በዝርዝር መግባት አልፈልግም። ከሁለቱም ጋር የምስማማበትም የምለያይበትም ጉዳይ አለ። ነገር ግን ኢትዮጵያ ለሁለቱ ልጆቿ፤ ለአንዱ ሲኦል ለሌላው ገነት የምትሆንበት ጊዜ ግን ማብቃት አለበት። መንግስት አንዱን ዜጋ ከነወንጀሉ እና ጥፋቱ እያሽሞነሞነ ሌላውን የሚገፋባት አገር የምትሆንበት ጊዜ መቀጠል የለበትም። ጃዋርም ሆኑ እስክንድር ባጠፉት ልክ ሊወቀሱ፣ በጣሱት ሕግ ልክ ሊጠየቁ ይገባል። እንዲሁም በሰሩት መልካም ነገርም ልክ ሊመሰገኑ እና ሊሸለሙ ይገባል። ለጃዋር እናት ለእስክንድር እንጀራ እናት የምትሆን ኢትዮጵያ ለሁላችንም አትሆንም።
የአንዱን ዜጋ ነጻነት ለማስፋት የሌላውን ዜጋ መብት እና ነጻነት ማጥበብ ተቀባይነት የለውም። ሁሉም ዜጋ እኩል መብት እና ነጻነት አለው። ሁሉም ዜጋ እኩል መብትሙ፣ ነጻነቱም ሊጠበቅለት ይገባል። ሁሉም ዜጋም ከሕግ በታች ሆኖ እኩል ተጠያቂነትም መስፈን አለበት።
Filed in: Amharic