>

ሕክምና ካልሆነ በስተቀር የፖለቲካ ፈውስ የማይገኝለቱ ኦነጋውያንን ሰቅዞ የያዘው የጥላቻ ደዌ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

ሕክምና ካልሆነ በስተቀር የፖለቲካ ፈውስ የማይገኝለቱ ኦነጋውያንን ሰቅዞ የያዘው የጥላቻ ደዌ…!!!

አቻምየለህ ታምሩ

ጃዋር መሐመድን በመተካት “አያቶላህ” ለመሆን ከሚኳትኑን ኦነጋውያን መካከል ቀዳሚ የሆነው አንዱ የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ የፈጠረችው ሃይማኖታዊ የዘመን አቆጣጠር በመሆኑ “ሕዝቦች” ያላቸውን ኅብራዊነት የማያንጸባርቅ መሆኑን ነግሮናል።
ተስፈኛው አያቶላህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ፈጠረችው ያለውን የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ኅብራዊነትን የማያንጸባርቅ አድርጎ ሊያንቋሽሸው የፈለገው ኦነጋውያን አባቶቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክ ተዋህዶ ሃይማኖትን የአማራ ሃይማኖት አድርገው ያስተማሩትን ይዞ ነው። እዚያ ቤት ለመመርመር ፈቃደኛ ባለመሆን የሚጠሉትን ነገር ሁሉ የአማራ አድርገው አቋም ስለያዙ እንጂ ለመመርመር ፍቃደኛ ሆነው ትንሽ ጠለቅ አድርገው ለማሰብ አእምሯቸውን ቢከፍቱ ኖሮ አጋር ያደረጓቸው የትግራይ ብሔርተኞች የወጡበት የትግራይ ሕዝብ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታይ የሆነው ቁጥር መቶኛ ሲሰላ በአማራው መካከል ካለው የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታይ መቶኛ በልጦ እንደሚገኝ ይገለጥላቸው ነበር።
ኦነጋውያን ስለ ኅብራዊነት ሊሰብኩን የሚሞክሩት ኩሽ በሚል የፈጠሩት የዳቦ ስም ውስጥ እጩ ሊያደርጉ ከሚያስቧቸው ነገዶች መካከል አንዱ የሆውና የኦርቶዶክስ ክርስቲያ ተከታዩ ቁጥር መቶኛ ሲሰላ ከአማራውም ሆነ ከትግሬው የሚበልጠው አገው ያወጣውን ዝዋይ የሚለውን የጥንቱን የአገውኛ የቦታ ስም በኦሮሙማ ደምስሰው ወደ ባቱ በመቀየር ልሙጥነትን መታወቂያቸው አድርገው ነው።
ባጭሩ እዚያ ቤት እነሱ ከሚፈልጉት ውጭ ያለን ማንኛውም አድማስ የአማራ አድርገው ስለሚጠሉት የኢትዮጵያ ነገዶች የሚጋሩትና ያዳበሩት አድማስ ሲገኝ እነሱ የባረኩት ስላልሆነ ኅብራዊነቱ አይታያቸውም። እዚያ ቤት የአማራ የሆነ የማይጠሉት አንደ ነገር ብቻ አለ። ይህም የመንፈስ አባቶቻቸው በየስምንት ዓመቱ እየወረሩ ባለርሥቱን ገበሮ እያደረጉ የሰፈሩበትን መሬት ነው። ምናለ የአማራ አድርገው እንደሚጠሉት እንደ ኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ሁሉ የመንፈስ አባቶቻቸው በየስምንት ዓመቱ በወረራ የያዙትን የጥንት አማሮች መሬትም ቢጠሉትና ለቀውት ቢሄዱ?
ራሱን የሕግ ምሑር አድርጎ የሚቆጥረው ደጋሚ ወዳቀረበው “አስደናቂ” “ግኝት” ስንመለስ ባለም ላይ ያሉትን የዘመን አቆጣጠሮች ሃይማኖታዊ መነሻ ያላቸው ሆነው እናገኛቸዋለን። የግዕዙ ሊቅ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ “ባሕረ ሐሳብ” በሚል ባሳተሙት መጽሐፍ ገጽ 65 ላይ ስለ ዘመን አቆጣጠር መነሻ እንደሚከተለው ጽፈዋል፤
«ክብ የሆነ ነገር ሲከብ ከየትኛውም ቦታ መጀመር ይቻላል፤ የዘመን አቆጣጠር /ዓውደ ዓመትም/ ይኸው ነው፡፡ ዋናው ነገር አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ አንድ ታላቅ ታሪካዊ ድርጊት ፈልጎ እርሱን መነሻ ማድረግ ነው፤ የዘመን አቆጣጠሮቹም ልዩነት መንስኤው ይኸው ነው»።
ፕሮፌሰር ጌታቸው ቀጠል አድርገውም በምሳሌነት ሮማውያን የሮም ከተማ የተቆረቆረችበትን ጊዜ መነሻ ማድረጋቸውን፤ በኋላም ታላቁ እስክንድር የነገሠበት ዘመን የዘመን ቆጠራ መነሻ ሆነው እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ነብዩ መሐመድና ተከታዮቻቸው ከመካ ወደ መዲና ያደረጉትን ስደት መነሻ የሚያደርገው ኢስላማዊ የዘመን አቆጣጠርም ሌላው ተጠቃሽ ነው፡፡ የምዕራባውያኑ የጁልየስና የጎርጎርዮሳውያን እንዲሁም የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር ሁለም ዘመንን የሚቆጥሩት ከክርስቶስ ልደት መነሻ አድርገው ነው።
ልብ በሉ! የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ሃይማኖታዊ ነው ብሎ አጀንዳ የፈጠረው ኦነጋዊ የሚቀምበት የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር [Gregorian Calendar] ሃይማኖታዊ ነው። የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር መነሻው የክርስቶስ ልደት ነው ብያለሁ። የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርም መነሻው የክርስቶስን ልደት ነው። ኦነጋውያን ግን የክርስቶስ ልደትን መነሻ ያደረገውን የምዕራባውያንን ወይም የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር እየተጠቀሙ የክርስቶስ ልደትን መነሻ ያደረገውን የኢትዮጵያን የቀን አቆጣጠር ግን የአማራ ሃይማኖት የሚያደርጉት የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ፈጠራ ስለሚመስላቸው ይጠሉታል።
እስቲ የሕግ “ሊቁ”ን ጠይቁት?! ሃይማኖታዊ ያልሆነ የአለም ሕዝብ ዘመን የሚቆጥርበት የዘመን መቁጠሪያ አለን? የምዕራቡ አለም ዘመን የሚቆጥርበት የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር [Gregorian Calendar] ሃይማኖታዊ የዘመን አቆጣጠር አይደለምን? የምዕራቡ አለም ከክርስቶስ ልደቱ በፊት ያለውን ዘመን ቅድመ ክርስቶስ ወይም በእንግሊዝኛ Before Christ ወይም BC ብሎ ዘመን የሚቆጥረው፤ ከልደቱ በኋላ ያለውን ዘመን ደግሞ ዘመነ ምሕረት[ይህ እኛ ዓመተ ምሕረት የምንለው ነው] ወይም በላቲን Anno Domini ወይም A.D. ወይም በላቲን አጠራሩ “Anno Domini” በማለት ዘመን የሚቆጥሩት የክርስቶስን ልደት መነሻው አድርገው አይደለምን? ይህን ሃይማኖታዊ አይደለምን?
የአረቡ አለም ቢሆን ዘመን የሚቆጥረው ሃይማኖትን መሰረት በማድረግ አይደለምን? የነብዩ መሐመድን ልደት [መውሊድ አልረሱል]፣ ነብዩ መሐመድና ተከታዮቻቸው ከመካ ወደ መዲና ያደረጉትን ስደት [አልተቅዊም አልሕጅሪ] እና የነብዩን ሞት [ወፋት አልረሱል] መነሻ የሚያደርገው የአረቡ አለም ዘመን አቆጣጠር ሃይማኖታዊ አይደለምን?
Filed in: Amharic