>

ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 የብር ኖቶች የሚተኩ አዲስ የገንዘብ ዓይነቶችና አዲሱን የ200 ብር ኖት ይፋ አደረገች (ፋና ራድዮ - አ.ብ.መ.ድ)

ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 የብር ኖቶች የሚተኩ አዲስ የገንዘብ ዓይነቶችና አዲሱን የ200 ብር ኖት ይፋ አደረገች
ፋና ራድዮ – አ.ብ.መ.ድ

ሕገ_ወጥና ሐሰተኛ ገንዘቦችን በሚሰበስቡ #ባንኮች ላይ እስከ ኅልውና_ማሳጣት የደረሰ እርምጃ ይወሰዳል‼️ 
 
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2013  ኢትዮጵያ ነባሮቹን የ10፣ የ50 እና የ100 ብር ኖቶች ዓይነቶችን ሙሉ ለሙሉ በመተካት ለግብይት የሚሆን አዲስ የብር ኖት መጠቀም እንደምትጀምር ይፋ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አስታወቁ።
ነባሮቹን የብር ኖቶች ከሚተኩት በተጨማሪ በዛሬው ዕለት የ200 ብር ኖት ይፋ እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በፌስቡክ ገፃቸው ባወጡት መረጃ የገለፁት።
የ5 ብር ኖት ባለበት ቀጥሎ፤ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ወደ ሣንቲም የሚለወጥ ይሆናል ተብሏል።
እነዚህ አዲስ የገንዘብ ዓይነቶች ለሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግን ድጋፍ፣ ሙስናን እና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቀልበስ እንደሚረዱ ተጠቁሟል።
እንዲሁም የፋይናንስ ተቋማት የገንዘብ እጥረትን ለመቋቋም እንዲችሉም ያግዛል ነው የተባለው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲሶቹ የገንዘብ ዓይነቶች ላይ የተካተቱ መለያዎች አመሳስሎ ገንዘብ ለማተም የሚደረጉ ሕገ ወጥ ጥረቶችንም ለማስቀረት እንደሚያግዙ ገልፀዋል።
አዲስ የታተሙት የብር ኖቶቹ በአካላቸው ላይ የሚገኙ የደህንነት መጠበቂያ ምልክቶች ያሉባቸው ናቸው።
እነዚህን ያላሟሉ ወይም ተመሳስለው የተዘጋጁ ገንዘቦች የያዙ ወይም የሚጠቀሙ ግለሰቦች ካጋጠሙ ለፀጥታ አካላት መጠቆም እንደሚገባ ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅት የአዲሶቹ የብር ኖቶች አብዛኛው የህትመት ሥራ ተገባዶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግምጃ ቤት እንደሚገኝ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የስርጭት ስርዓት እና ዕቅድ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በሚመለከታቸው አካላት አማካኝነት እንደሚተገበር ተጠቁሟል።
በገንዘብ ቅያሬው ሂደት የጸጥታ ማስከበር አካላት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖራቸው የተገለፀ ሲሆን፥ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንደሚያስፈፅሙ ተነግሯል።
ለዚህም ከብሔራዊ መከላከያ ሠራዊት፣ ከብሔራዊ የመረጃ እና ደህንነት አገልግሎት እና ከፌደራል ፖሊስ የተውጣጣ ኮማንድ ፖስት ተቋቁሞ፤ ሂደቱን በበላይነት ያስተባብራል።
እንዲሁም የክልል መንግሥታት ተመሳሳይ ኮማንድ ፖስት አቋቁመው ሥራውን እንዲያከናውኑ ይጠበቃል።
የገንዘብ ቁጥሮቹ በሚያጎላ መሳሪያ ሲታዩ ከጥቁር ወደ አረንጓዴ ፍሎረሰንት ቀለም እንደሚለወጡ ብሄራዊ ባንክ አስታውቋል።
ለአይነ ስውራንም የእውቅና ምልክት ያለው ሲሆን የብሩን ዋጋ በእጅ ዳሰሳ ማወቅ የሚችሉበት የደህንነት መጠበቂያ ያለው ነው።
በተመሳሳይ ገንዘቡ ወደ ላይ ወይንም ወደታች ሲዞር የሚንቀሳቀስ ደማቅ የቀለም ፍንጣቂ የደህንነት መጠበቂያ ምልክት እንዳለውም ነው ተነግሯል።
የብር ኖቱ ሲዳሰስ የመጎርበጥ ስሜት እንዲሁም የኖቱ ዋጋ ይታያል።
የሚሽከረከር ደማቅ ቀለም ኮኮብ አዲስ የደህንነት መጠበቂያ ክር፤ በክሩ ውስጥም NBET፣ ኢብባ እና ገንዘቡ አይኖቶች ተፅፈው ይገኙበታል ነው የተባለው።
ገንዘቡ ወደ ብርሃን አቅጣጫ ተደርጎ ሲታይ በላይ ላይ ከሚገኘው ምስል ፊት ለፊት ተመሳሳይ ደብዛዛ ውሃ መልክ ያለው ምልክት እንደሚታይ ተጠቁሟል።
የብር ኖቶቹ በብርሃን አቅጣጫ ሲታዮ ኳስ መሳይ ምልክት ከኖቶቹ በስተኋላ ካለው ተመሳሳይ ምልክት ጋር በፍፁም ትይዩ ሆነው በአንድ ቦታ ላይ ያርፋሉ።
እንዲሁም አንበሳው ምስል ራስ ላይ አልትራቯዮሌት ጨረር ሲበራበት ወደ ቢጫነት የሚለወጥ ፍሎረሰንት ምልክት አለው ተብሏል።
FBC
ሕገ ወጥና ሐሰተኛ ገንዘቦችን በሚሰበስቡ ባንኮች ላይ እስከ ኅልውናማጣት እርምጃ እንደሚወሰድ ጠ/ሚ አስጠነቀቁ‼️ 
ሕገ ወጥና ሐሰተኛ ገንዘቦችን በሚሰበስቡ ባንኮች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ አስጠንቅቀዋል። የኢትዮጵያ መገበያያ ገንዘብ መቀየርን በማስመልከት ዛሬ በተደረገው ውይይት ላይ ዶክተር ዐብይ አህመድ እንደተናገሩት ከብር ኖቶች መቀየር ጋር በተያያዘ ሕገ ወጥና ሐሰተኛ የብር ኖቶችን የሚሰበስቡ ባንኮች መኖራቸውን መንግሥት ከፋይናንስ ደኅንነት መረጃ አግኝቷል፡፡ በመሆኑም ‘‘አዲስ የገንዘብ የብር ኖቶች መቀየራቸውን ተከትሎ መንግሥት ሕገ ወጥና ሐሰተኛ የብር ኖቶችን የሚሰባስቡ ባንኮች ላይ ጠበቅ ያለ እርምጃ ይወሰዳል’’ ብለዋል፡፡
መንግሥት የባንኮችን ችግር ለመፍታት የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎችን መውሰዱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘‘ባንኮችም በተለይ አሮጌውን ገንዘብ በአዲሱ የመቀየር ሥራ ሲሠራ ሐሰተኛና ሕገ ወጥ ገንዘቦችን ከመሰብሰብ በመቆጠብ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል’’ ማለታቸውን ኢ.ፕ.ድ ዘግቧል፡፡ ኃላፊነታቸው በማይወጡና ሕገ ወጥ ድርጊት በሚፈጸሙ ባንኮች ላይ መንግሥት ኅልውናቸውን እስከማቋረጥ የሚደርስ እርምጃ እንደሚወስድ ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ያስጠነቀቁት፡፡ በዚህ ወቅት የአዳዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች አብዛኛው የሕትመት ሥራ ተገባድዶ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግምጃ ቤት እንደሚገኝና የስርጭት ሥርዓት እና ዕቅድ የተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል። ኢትዮጵያ ገንዘቧን የሚወክል ምልክት እንዳልነበራት ይታወቃል። በቅርቡ ለብር መለያ የሚሆን አዲስ ምልክት ተዘጋጅቶ በጥቅም ላይ እንደሚውልም ተገልጿል።
Filed in: Amharic