>
5:13 pm - Sunday April 20, 6617

ታሪክ ራሱን ደገመና አረፈው...?!? (ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው)

ታሪክ ራሱን ደገመና አረፈው…?!?

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሽፈራው

 የ2001 ዓ/ም “የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ” ክስ ውሳኔ ለእኔ ክስ ማዳመቂያ “መረጃ” ብለው አያይዘውብኝ ነበር።  እስር ቤት የሚነበብ ብርቅ ነውና  ሳገላብጥ በርካታ የሚያስገርሙ ነገሮችን አገኘው። አንደኛውን ግን ለማመንም ከበደኝ። በእስር ላይ የነበሩ የሕግ ባለሙያዎችን ዞሬ አናገርኳቸው። እነሱም ተገረሙ። በዚህ መዝገብ የተፈረደባቸውን ከእስር በኋላ አግኝቸ ጠይቄያቸው ነበር። ለእነሱም ብዙ እንቆቅልሽ ሆኖባቸዋል።
ነገሩ እንዲህ ነው። በክስ መዝገቡ አንድ ስሙ ያልተጠቀሰ ሰው አለ። በቅፅል ስም ነው የሚጠሩት። መዝገቡ ላይ ብቸኛ መገለጫው “ዳን” የምትለው ብቻ ነች። “ዳን የአባቱ ስም ያልታወቀ” ይሉታል። ዳን የሚባለው ራሱ ትክክለኛ ስሙ ስለመሆኑ አይታወቅም። ይህ “ዳን” የተባለ  በመዝገቡ በሌለበት ተብሎ 25 አመት ተፈርዶበታል። ግን የአባቱ ስም እንኳ አይታወቅም። ስሙ ራሱ አይታወቅም። አንድ ሰው ደግሞ ለመከሰስ ሰውነት ያስፈልገዋል። ሙሉ ስም ያስፈልገዋል። አድራሻ ያስፈልገዋል። እንበል ይህ “ሰው” ተፈረደበት። ማን ተብሎ ነው የሚያዘው? የአባቱ ስም አይታወቅ፣ አድራሻ የለው። ስሙ ራሱ በቅፅል ስም “ዳን” ይላል እንጅ ትክክለኛ ስሙ መሆኑ አይታወቅ።   በቅፅል እየተጠራ ዳዊት ይሁን፣ ዳንኤል ይሁን ምኑም የማይታወቅ 25 አመት የፈረዱበት በምንድን ነው? የማይታወቅ ሰው? አንድ ፍርድ ሲፈረድ ተፈፃሚ መሆን አለበት። ተፈፃሚ የሚሆነው ደግሞ ሰውዬው ሲታወቅ ነው።
በእርግጥም ይህ “ሰው” ማን ነበር ሲባል አብዛኛዎቹ የሚያምኑት የትወና ስም እንደነበር ነው። ሙሉ ስሙም ሆነ አድራሻው ያልተገለፀው ደግሞ በወንጀሉ ተሳትፈዋል ያሉትን ሰዎች አግኝቷቸዋል ተብሎ ድራማ ስለተሰራ ነው! አንድ ሰው “ዳን” በሚል ያገኛቸው ነበር ተብሎ ነው ክሱ የተቀናጀው። ይህ መንፈስ ይሁን ሰው የማይታወቅ “ዳን” ከሌሎቹ ጋር ተነጋገረው የተባለው ነበር አብዛኛውን ለማስከሰሻ ያደረገው።
 ተመልከቱ!
እስክንድር ነጋ በሽብር የተከሰሰው ሁለት ከማይታወቁ ሰዎች ጋር ነው። ሁሉም ተከሳሾች የአያት ስም አላቸው። አድራሻ አላቸው። እድሜያቸው ተፅፏል። የእስክንድር መክሰሻ የሆኑት ሁለቱ ሰዎች ብቻ እስከአባት ስም ተጠቅሰዋል። የአያት ስም የለም። አድራሻ የለም። እድሜና መሰል ጉዳዮች የሉም። በጣም የሚገርመው እስክንድር ጋር በሽብር የተከሰሰው አንደኛው ሰው የሞት ፍርደኛ ሆኖ ከእስር ቤት ያመለጠ ነው ብለዋል። ከእስር ቤት ያመለጠ ሰው ሙሉ መረጃው ፍርድ ቤት ውስጥ ይገኛል። እስር ቤት ውስጥ ይገኛል። ሆኖም ግን ፍርድ ቤት ጉዳዩ ያለቀ፣ እስር ቤት የነበረ ሰው የአያት ስም፣ አድራሻና እድሜን ጨምሮ መረጃዎች የሉትም! ልክ ዳን የተባለው ሰው የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አደረጉ ከሚባሉት ጋር ተነጋግሯል ተብሎ ማስፈረጃ እንደሆነው ሁሉ የእስክንድር ክስ ሙሉ አድራሻ የሌላቸው ሰዎች ጋር ተደረገ የተባለ ነው።
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው ክስ በቅፅል ስም ብቻ ነበር። የዚህኛው እስከ አባት ተጠቅሰዋል። ግን አስፈላጊ ከሆነ የአባትን ስም መጨመር ይቻላል። እስከ አባት የፈጠራ ስም መስጠት ይቻላል። የእነ ዳን ጉዳት በእስክንድርም ተደገመ? ታሪክ ራሱን ደገመ?
አሸናፊ አወቀ ማን ነው? ከእስር ቤት አመለጠ ተብሎ የአያቱ ስም እንኳ መጠቀስ ያልተቻለው ፍታዊ ገ/መድህን ማን ነው? እነዚህ አድራሻ የሌላቸው ሰዎች እነማን ናቸው? የዚህኛው ዘመን “ዳን” ይሆኑ?
Filed in: Amharic