>

መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም.  እና የተደበቀው የደርግ ታሪክ ...!!! (አቻምየለህ ታምሩ)

መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም.  እና የተደበቀው የደርግ ታሪክ …!!!

አቻምየለህ ታምሩ

አብዮት ተካሄደ እየተባለ ሲነገር የሰማውን ሳይመረምር ሲደግም የኖረ ሁሉ ከ46 ዓመታት በፊት መስከረም  2 ቀን 1967 ዓ.ም.  ደመዎዝ ለማስጨመር የተሰባሰቡ ሻለቆችና የበታች መኮንኖች ስብስብ  የሆነው ደርግ የመንግሥቱን ሥልጣን ከቀዳማዊ  ኃይለ ሥላሴ በኃይል ቀምቶ አብዮት ያካሄደ ይመስለዋል። እውነታው ግን ሌላ ነው።
ደርግ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ፓርላማ ያቋቋመው የሕገ መንግሥት ኮሚሽን  ያዘጋጀውን  ረቂቅ ሕገ መንግሥት አግዶ መስከረም 2 ቀን አዋጅ በማውጣው ባወጣው አዋጅ መሰረት ራሱን መንግሥት አድርጎ የሾመው የስምንት ወር እድሜ የነበረውና ዘመኑ በመገባደድ ላይ የነበረው የልጅ እንዳልካቸውና የልጅ ሚካኤል መንግሥት እድሜው ሲያበቃ በተዘጋጀው ሕገ መንግሥት መሰረት ምርጫ ተካሂዶ የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ሲመርጥ  ደርግ  መንግሥት የመሆን እድል ስለማይኖረው ሳይቀደም በመቅድም ነው።
አቶ ሐዲስ አለማየሁ በሐምሌ 1966 ዓ.ም. ደርግ ያቀረበላቸውን የ“ጠቅላይ ሚኒስትር ሁን” ጥያቄ  ውድቅ ያደረጉት ከልጅ እንዳልካቸው ጊዜያዊ መንግሥት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆን ሰው የቀረው እድሜ  ቢበዛ ሶስት ወር ስለሆነና በሶስት ወር ውስጥ እሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ የተረቀቀው ሕገ መንግሥት ታውጆ  ምርጫ ከተካሄደ በኋላ ሥልጣኑን በሕዝብ ለተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስትር እንደሚያስረክቡ የሚያሳይ እቅድ ሲያቀርቡ ደርግ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ በምርጫ መሪውን ለመምረጥ ገና በመሆኑ ምርጫ እንዲካሄድና በሕዝብ የተመረጠ ጠቅላይ ሚኒስትር መሪ እንዲሆን ፍላጎት የሌላቸው፤ ይልቁንም  ንጉሡን አውርደው እነሱ [ደርጎች]  መንግሥት መሆን እንደሚፈልጉ ሲነግሯቸው የኢትዮጵያን ሕዝብ የለውጥ ፍላጎት ተቀልብሶ እንዲህ አይነት ኅሊናዬ የማይቀበለው ሥራ አካል አልሆንም በማለት ነበር።
ይህ በደርግና በአቶ ሐዲስ አለማየሁ መካከል የተደረገው ንግግር የተካሄደው ሐምሌ 11 እና 12 ቀን 1966 ዓ.ም. ነው። ደርጎችም እንዳሉት አደረጉ። የጊዜያዊ መንግሥቱ እድሜ ሳያልቀና ሕገ መንግሥቱ ታውጆ በሕገ መንግሥቱ መሰረት ሕዝብ የራሱን ጠቅላይ ሚኒስትር ወደመምረጥ ሂደት ሳይገባ  መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም.   የኢትዮጵያ ሕዝብ  ጠቅላይ ሚኒስትሩን በድምጹ እንዲመርጥ መብት የሚሰጠውን ሕገ መንግሥት አግደው በሐምሌ ወር ለአቶ ሐዲስ የነገሯቸውን ፍላጎታውን ለማሟላት በአዋጅ በመንግሥትነት ተሰየሙ። የሆነው ይኼው ነው።
ባጭሩ ደርግ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. አዲሱን ሕገ መንግሥት አግዶ በአዋጅ በመነግሥትነት የተሰየመው ሥልጣኑ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀምቶ ሳይሆን የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ፓርላማ ያቋቋመው የሕገ መንግሥት ኮሚሽን ያረቀቀው ሕገ መንግሥት ሕዝብ በድምጹ ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንዲመርጥ የሰጠውን መብት በአዋጅ በማገድና የኢትዮጵያ ሕዝብ መሪውን ለመምረጥ የቀረው አንድ ወር ያህል ጊዜ  ሳይጠናቀቅ ነው።
ይህንን የደርግ ታሪክ በማስታውሻቸው ትተውልን ያለፉትን አቶ ሐዲስ አለማየሁን ነፍሳቸውን በገነተ ያኑርልን !  ከታች የታተመው ማስታወሻ ጀኔራል አማን ሚካኤል አምዶም ደርግን በመወከል  ከአቶ ሐዲስ አለማየሁ ጋር ካደረጉት ውይይት ውስጥ አቶ ሐዲስ  በእጅ ጽሑፋቸው ከትበው በመፈረም ያስቀሩልን ማስታወሻ ነው። የአቶ ሐዲስ ሙሉ ማስታወሻ በቤተሰባቸው ተዘጋጅቶ ወደፊት በሚወጣው የሕይዎት ታሪካቸው ውስጥ ይታተማል።
Filed in: Amharic