>
5:13 pm - Tuesday April 19, 6878

የመግባባትና የመናበብ ዘመን...!!! (ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ።)

የመግባባትና የመናበብ ዘመን…!!!

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ። 

ዘመነ ማቴዎስ የመግባባትና የመናበብ ዘመን ይሁንልን!
ዘመነ ዮሐንስን አስመልከቶ ከአረጋውያን ገዳማውያን ተደጋግሞ የሰማሁትን በመጠቆም ከባድ የፈተና ዘመን ሊሆንብን ይችላል ብዬ ጠቆም አድርጌ ነበር፡፡ አባቶች እንደነገሩንም ከበድ ያለ ዘመን ነበር፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በቤተ ክርስቲያናችን ላይ ወደፊትም ሊቀጥሉ ጠሚችሉ በሦስት ግንባር ሊመደቡ የሚችሉ ጥቃቶችን የተጋፈጥንበት ዐመት ነበር፡፡ የመጀመሪያው ጥቃት አካላዊ ጥቃት ሲሆን በዚህ ብዙ አማኞች ስለእምነታቸው ብቻ ተገድለዋል፣ አካላቸው ጎድሏል፤ ሀብት ንብረታቸው በተለያየ መንገድ ወድሟል፤ ከነበሩባቸው ቦታዎችም ተፈናቅለዋል፡፡ ሁለተኛው ጥቃት ደግሞ በቤተክርስቲያነችን ላይ ሳይቋረጥ የሚደርስባት ተቋማዊ ጥቃት ነው፡፡ ይህም ሀገሪቱንና ሕዝቡን ወደሚፈልጉት አቅጣጫ ለመምራት እንደ አንድ እንቅፋት የሚመለከቷት ሁሉ የተለያየ ዘዴ ተጠቅመውና ጉዳዩን በአግባቡ ባለማጤንና አጀንዳ ቀራጮቹ የሰጧቸውን የቤት ሥራ የተቀበሉ ልጆቿን እጅ እያደረጉ ከባድ ጥቃቶች የተሠነዘሩበት ዐመት ነበር፡፡ የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴ፣ አነስ ያለም ቢሆን የትግራይ ቤተ ክህነት እንቅስቃሴ፣ ቅባትን ምክንያት አድርጎ ወደ ትልቅ ቀውስ የመክተት እንቅስቃሴ ከመዋቅራዊ ጥቃቶች በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡
ከዚህም ጋር የዛሬ ሁለት ዐመት የተፈጸመውን ሲኖዶሳዊ አንድነት ለማናጋትና ያንንም እንደ አንድ ዕድል የመጠቀም ፍላጎት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ አሁን እስካሳለፍነው ጳጉሜን ወር ድረስ የቀጠለ የጥቃት ሙከራ ነበረ፡፡ ይህኛው ጥቃት ለየት የሚያደርገው እንደ ሌሎቹ ለብዙው ሰው ብዙም ግልጽ አይደለም፡፡ ከሰሞኑ የቅዱስነታቸው ቤተ መንግሥት መግባት ጋር ተያይዞ  የተለያየ ፍላጎት ያለን ያስመሰለ አስተያየት ያወራወረው ሁኔታ የተፈጠረውም ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ይህን ጉዳይ ትንሽ ጠቆም ማድረግ አስፈላጊ ስለሆነ በመጠኑ መጠቆም ያስፈልጋል፤ ለነገ መንገዳችን ይረዳናልና፡፡
ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ይፋዊ አቀባበል በሚሊኔየም አዳራሽ በሚደረግበት ዕለት በሶማሌ ክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ግፍ ዕርቁን አጥብቀው ከሚጠሉት የፖለቲካ ኃይሎች ጋር ግንኙነት እንደነበረው ለመገመት የሚያስቸግር አልነበረም፡፡ በኋላም የሰሜን ኢትዮጵያ ጉዟቸውን ከርእሰ አድባራት ወገዳማት ቅድስት አክሱም ለመጀመር ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም በወቅቱ ቤተ ክህነት ውስጥ ያሉ አካላትን በአግባቡ የሚጠቀሙ የፖለቲካ ኃይሎች ያን እንዳይሳካ አደረጉት፡፡ ትንሽዬ አስተያየት የተሰጠበት ቢሆንም እንዳይራገብ ተደርጎ በጥበብ ታለፈ፡፡ ከዚያ ጊዜ አንሥቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ለችግርና ለአደጋ እንደተጋለጡ የሚያሳስቡ፣ የሚጎትቱና የሚስቡ ሥራዎች ነበሩ፡፡ ውስጥ ለውስጥም ልክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የተለየ ፍላጎት ያላቸው በማስመሰል የመለያየት ነገር ለመፍጠር ብዙ ጥረቶች እንደሚደረጉ ለማንም የተሠወረ አልነበረም፡፡ ከዚህ የተነሣ ብዙ ችግሮች በተለይ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚያስፈልጉ የተገቡ ነገሮችን ለማሟላት ቤተ ክህነቱን ከመጠን በላይ ዳተኛ እስከመሆን አድርሶት ነበር፡፡ ይህም ሁሉ እየሆነ ግን ችግሮቹን ጉልህ እንዳይሆኑ ያደረጓቸው በዋናነት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ የሚያስደንቅ አርምሞና ትዕግሥት ሲሆን ከእርሳቸው ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ በእርሳቸው ዙሪያ ያሉ አግልጋዮችና ቤተሰቦች ትዕግሥትና አስተዋይነት መሆኑን መዘንጋት አይቻልም፡፡ እነርሱ አብዛኛውን ነገር በሰፊ ትዕግሥት እንደሚያልፉት እኔ ራሴ ምስክር መሆን እችላለሁ፡፡
ይህም ሁሉ ሆኖ ግን አንዳንዴ ወጣ ያለ ነገር እንዲከሰት የተለያየ ፍላጎት ያላቸው አካለት ሙከራቸውን አላቆሙም፡፡ ከሰሞኑ የሆነው ለዚህ ምሳሌ መሆን ይችላል፡፡ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ምን እንደተነገራቸውና ምን እንዳጋጠማቸው ባናውቅም በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ በዓለ ሲመት አልተገኙም ነበር፡፡ ነገሮች በቅርበት ለሚከታተል ሰው ይህ ዝም ብሎ ሊሆን እንደማይችል መገመት ይችላል፡፡ ከዚሁ ጋር በውጭ ሀገር ያለ አንድ የሚዲያ ተቋም በሁለቱ አባቶች መካከል ልዩነት መኖሩን ለመዘገብ እዚህ አዲስ አበባ መግባቱንም ሰምተናል፡፡ ይህ በሆነበት ደግሞ  ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ቤተ መንግሥት መሔዳቸው በዜና ከተዘገበ አንሥቶ አላማ ያላቸው ለዐላማቸው በሚጠቅማቸው በኩል ሲነዙት ሌላው ደግሞ በቅንነትም ቢሆን የተጠቃ የመሰለውን ለመከላከልና ከሁኔታዎች ጋር በማገናኘት ዘገበው፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ግልጽ ለማድረግ ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን ወደ ቤተ መንግሥት የሔዱት በራሳቸው ጥያቄ አልነበረም፡፡ እንዲያውም ወደመኪና ሲያስገቧቸው ወደየት እንደሚወስዷቸውም ጠይቀው ነበር፡፡ በእኔ እምነት ችግሩ ሌሎች ሰዎች አስበውት ለምን ይፈጸማል የሚልም አይለም፡፡ ለእኔ እስከሚገባኝ ድረስ ችግሩ እንኳን እርሳቸው ይቅርና በእርሳቸው ዙሪያ ሁኔታው እንዲመቻች ያደረጉት አካላትም ከሆነ አካል የመጣላቸውን ግብዣ እንደዋዛ በቅንነትና በየዋሕነት ተቀብለው ሊያወዛግብ የሚችል ሀሳብ እንደሚያመጣ ባላሰቡበት መንገድ መሆኑ ነው፡፡ ሌላው ቀርቶ ጠቅላይ ሚንስትሩን ማመሰገናቸውም ሆነ ሥጦታ መስጠታቸው በአግባቡ ታስቦበትና ለየትኛውም አካል የፖለቲካ ትርፍ በማይውልም በማያስመስልም መንገድ ቢሆን ምንኛ መልካም ነበር፡፡
ምስጋናውንማ እንኳን እርሳቸው ይቅርና ከዕርቁ የተነሣ ማንኛችንም ብናደርገው የተገባ ነው ብዬ ከልቤ አምናለሁ፡፡ ደግሞም ከሀገር ሽማግሌዎቹ ጋር በመሆን ቤተ ክህነቱ በወቅቱ ለጠቅላይ ሚንስትሩና ለቀዳማዊት እመቤት ካባ ያለበሱበትን የምስጋና ሥርዓት ማስታወስ እንችላለን፡፡ ያን ጊዜ ማን ተቃወመ? እኔ እስከማስታውሰው ድረስ የተቃወመ አልነበረም፡፡ ምክንያቱም ለፖለቲካ ጥቅም በሚውል መንገድ ስላልተፈጸመ ይመስለኛል፡፡ አሁን የሆነውም ጥያቄ ያስነሣው በመደረጉ ብቻ አይመስለኝም፡፡ እንኳን ሌላ ፍላጎት ያላቸው አካላት ቀርቶ ጠቅላይ ሚንስትሩም ቢሆኑ ዕርቁንና የተመለሱ ቤቶችን እንደ ውለታም ሆነ ማስያዣ አድርገው እኒህን ዝምተኛ እና በመንፈሳዊ አርምሞ ያሉትን አባት ለራሳቸው የፖለቲካ ተግባር በሚጠቅም መንገድ  ወይም የቀነሰ ድጋፋቸውን ለመመለስ መጠቀም አለባቸው ብዬ አላምንም፡፡
መንግሥታቸው ከእስር የፈታቸውን ፖለቲከኞች ሁሉ ከየራሳቸው መርህ ውጭ በሆነ መንገድ ለራሳቸው የፖለቲካ ዐላማ ጥቅም ላይ ለማዋል እሽ እንደማይሏቸው ሁሉ ቅዱስ አባታችንንም ሆነ ቤተ ክርስቲያኒቱን ለፍላጎታቸው መጠቀም የለባቸውም፡፡ በርግጥ ይህ ሁሉ የእኛ የራሳችን የቤት ሥራ እንጂ እርሳቸው እስከጠቀማቸው ድረስ መሞከራቸው የሚያስነቅፋቸው አይደለም፡፡  ሌሎቹም እኮ ይህን ጥቅም ለማግኘት ነው ለተለያዩ የቤታችን ሰዎች ድጋፍ በማድረግ የክልል ቤተ ክህነት እስከማቋቋም ድረስ የተጓዙት፡፡ ስለዚህ ያን የምንቃወመው ከሆነ ይህንንም ልንቀበለው አንችልም፡፡ ይህን የመሰሉት የየትኞቹም የፖለቲከኞች ፍላጎቶች በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚደርሱ የመዋቅር ጥቃቶች ናቸውና፡፡
እንደ ቤተ ክርስቲያን የበላይ አባትነት የሚደረገው ግንኙነት ግን ቢቻል እንኳን ከመንግሥት ጋር ከሌሎቹም ፓርቲዎች ጋር ቢሆን ተቃውሞ የለኝም፤ ሊኖረንም ይገባል ብዬ አላስብም፡፡ ችግራችን የአባቶችን ዝምታ፤ የዋሕነት እና የአሠራራችንም ድከመት ተጠቅሞ ለአንድ የፖለቲካ አካል የተለየ ጥቅም የሚደረገው ሙከራ ነው ፡፡ ይህ ደግሞ ከአቡነ ቴወፍሎስ ዘመን ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከችግር በቀር ያተረፈልን ነገር የለም፡፡ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮም ተቀባይነት የለውም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ እንኳን ቀደም ባሉት ዘመናት የተፈጸመውን ቀርቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ሲሰደዱ የነበረውንም ሁኔታ እኔን ጨምሮ አብዛኛው የዚህ ዘመን ጎልማሳ ችግሩን የምናውቀው በታሪክ ነው፡፡ ብዙዎቸችን ያን ጊዜ ተማሪ ልጆችና ወጣቶች ነበርንና፡፡ ጉዳዩም የገባን ዘግይቶ የውጭና የውስጥ የሚለው ውግዘት ከተጀመረ በኋላ ነው፡፡ ነገሩን ማጥናትና መመርመርም የጀመርነው (በተለይ እኔ) ከዚያ በኋላ ነው፡፡ ግልጽ እየሆነልንም የመጣው ቀስ በቀስ ነበር፡፡ ዕርቅ እንዲፈጸም ጥረት በሚደረግበት ወቅት ብዙ ፈተናና መከራ እንደየአቅማችን ማሳለፋችንም አልቀረም፡፡ በተለይ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ካረፉ በኋላ የገጠመን ብዙ ነገር ነው፤ የሚነሣበት ጊዜ ስለሚኖር አሁን ያን ማንሣት አያስፈልግም፡፡ የሆነው ሆኖ በእግዚአብሔር ቸርነት እዚህ ደርሰናል፡፡
ከዚህ ሁሉ በኋላ ግን ሌላ ተመሳሳይ መዋቅራዊ ጥቃት የማስተናገድ አቅም አለን ብዬ አላምንም፡፡ ስለዚህም በዘመናችን እንዳይደገም ነገሮችን በተለምዶና በንዝህላልነት ሳይሆን በአትኩሮትና በጥንቃቄ መመልከት፣ በማስተዋል መናገርና ችግሮችን ከማስፋት መቆጠብ የሁላችንም ታሪካዊ ግዴታ እንደሆነ አምናለሁ፡፡ የሰሞኑን ሁኔታ ያራገበው በዐመቱ በክርስቲያኖች ላይ የተፈጸመው ግፍና መከራ እንዳለ ሆኖ መንግሥት በአደባባይ ምንም ዐይነት ሐዘኔታ ሳያሳይ ለራሱ ዐላማ ለመጠቀም ለምን ሞከረ የሚለው ይመስለኛል፡፡ ከዚህም ሁሉ በላይ ቀድም ብዬ ላነሣሁት ችግር ተጨማሪ ኃይል አድርገው ለመጠቀም ለሚያስቡ እንዲህ ዐይነት ሐሳብም ሆነ ፍላጎት በሌላቸውና በሚያስደንቅ አርምም ውስት በሚኖሩ አባት ስም ለምን ይደረጋል በሚል ቅዱስነታቸው በየትኛውም ውስብስብ ነገር ውሥጥ የሌሉበት መሆኑን በማሳያት ለሌሎች እኩይ ዐላማ ጥቅም ላይ እንዳይውል ለመከላከል እንጂ ለምን ሔዱም ሆነ ለምን አመሰገኑ የሚለው አይመስለኝም፡፡
ይህን ሰፋ አድርጌ ያቀርብሁት ጉዳዩን መጠቀም የሚፈልገው አካል ብዙ ከመሆኑም በላይ እኛም አስተያየት ስንሰጥ ይህን አጣብቂኝ ወቅት አልፍን ተቋማዊ ጥንካሪያችን ለመገንባት ተገቢውን መንገድ እንድንመርጥ በገባኝ መጠን ለማሳሰብ ነው፡፡
ባሳለፍናቸው ዐመታት በተለይም በእነዚህ ሁለት ዐመታት በቤተ ክርስቲያን ላይ የሚደርሰው መዋቅራዊ ጥቃት ቤተ ክርስቲያኒቱን እንዳታንሠራራ አድርጎ ለመምታት የሚደረግ ጥረት መሆኑን ለመረዳት የሚያስቸግር አይመስለኝም፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉት ይዞታዋቿን የመንጠቅ፤ ክብረ በዓላቶቿን ማስተጓጎል፣ የመስቀልና የጥምቀት ቦታዎችን መቀማት ሁሉ የዚህ ዘመቻ አካሎች ናቸው፡፡
ሦስተኛውና ዋናው ጥቃት ደግሞ ሁለቱንም ጥቃቶች ተጠቅሞ በሕዝበ ክርስቲያኒ ላይ የሚደረገው የሥነ ልቡና ጥቃት ነው፡፡  ይህ ጥቃት ሰፊና አደገኛ ነው፡፡ በቅናትና በብስጭት አስጀምሮ ተስፋ መቁረጥ ጋር የሚያደርስ፣ የራስን ቤት የመጥላት፣ አባትን ያለማመን፣ እርስ በእርስ አለመተማመንና መጠራጠርን የሚያስከትል ፣ አንዳንዶችን እምነታቸውን ለመቀየር፣ አንዳንዶችን እምነት አልባ ያደረገ፣ ብዙዎችንም በኩርፊያ ውስጥ የከተተ፣ አገልግሎታችንን ያዳከመ፣ እርስ በእርስ እንድንሰነካከል የሚደርግ አደገኛ ጥቃት ነው፡፡ ይህ ጥቃት በሌሎች ጥቃቶች ታዝሎ ቢመጣም እጅግ ለከፋ አደጋ የሚያጋልጠን ግን ይህ ነው፡፡ ብዙውን ሰው በስሜት እንዲቃጠል ካደረገ በኋላ መደማመጥና መግባባት እንዳይኖር የሚያዲርግ፣ የደብረ ትዕግሥት የመድኃኔዓለም ልጆች መሆናችንን አስረስቶ ሁላችንም እየተቆረቆርን ነገር ግን እንዳንግባባ የሚያደርግ፣ በተለያየ መንገድ ወደሁላችንም ልቡና የገባ ረቂቅ  ጥቃት ነው፡፡
ከሁሉም በላይ ደግሞ ድክመታችንን አይተው ሥልት ነድፈው  ከዋና ሚዲያዎች እስከ ማኅበራዊ ሚዲያው ድረስ ትልልቅ የፕሮፓጋንዳ ማሽን ከፍተው የሚያወዛግቡን ጠላቶች ደግሞ የበረከቱበት ዘመን ነው፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ አሻራዋን ለማጥፋት ከፍተኛ ዘመቻ የተከፈተበት ዘመን ነው፡፡በአንድ በኩል የማኅበራዊ ሳይንስ አጥኝዎች ክርስቲየናዊ የባሕል ዘርመል (cultural gene) የሚሉትን ለማጥፋት በተጠና ስልትና ከውጭ በሚፈስስ ገንዘብ  እየተሠራ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኦርቶዶክሳዊ ባህልንና ማኅበራዊ ሥሪትን  በሌላ አዲስ ክርስቲያናዊ ባሕል የመተካትና እንዳልነበረች የማድረግ ዘመቻው ከሌላኛው የዐለም ክፍል በሚመጣ ገንዘብ እየተፋጠነ ነው፡፡ ይህ ሁሉ ባለበት ደግሞ በእቅድና በብልሃት የሚሠሩ ጠላቶቻችን የሚሳየውን ተጽእኖ አይተን በስሜትና በእልህ ፣ በቅናትና በንዴት ጦፈን መልሰን እራሳችን ለማድከም  እኛው ራሳችን እናግዛቸዋለን፡፡ ይህ ግን ከዘመነ ማቴዎስ ጀምሮ መቀየር አለበት፡፡
በሚዲያ የሚገለጹ፣ በሚዲያም የሚሠሩ ሥራዎች እንዳሉ ሆኖ ሁሉ ነገራችን ሚዲያ እና ወሬ ላይ መሆን ግን የለበትም፡፡  በርግጥ ቢመስልም ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በሥራ ወቅት የሚያጋጥሙንን ችግሮችም እንደ ትልቅ ነገር ማራገብና መልሰን ራሳችንን ማሰነካከልም መቆም አለበት፡፡ ውስጥ ለውስጥ መጎሻሸምና መሸነጋገልም መታረም አለበት፡፡ ይህ ማለት መተራረም መኖር የለበትም ሳይሆን እርሱም መንገድና አግባብ ያለው መሆኑን መዘንጋት ያለበትም፡፡ አንዱ እንዲህ አስቦ በትዕግሥት ሲያልፍ ሌላው ራሱን እንደ አሸናፊ ቆጥሮ የሚያቅራራበት ዘመንም ማቆም አለበት፡፡ የራሳችን ሰዎች በኃጢአት መውቀስ፣ አባቶችን መዝለፍና ምንም የማያውቁ ብዙ ንጹሐንን በራሳችን ድክመት ወደሌላ እምነት የማስረከብ ድከመትም በዘመነ ማቴዎስ መታረም ያለበት ነው፡፡ እጅግ ብዙው ድከመት የእኛ ስለሆነ ራሳችንን ለማረም፣ ሰዎችን በአግባቡ ለመረዳትና በአገልግሎትም ለመናበብ መጣር ይኖርብናል፡፡
በእኔ እምነት በዚህ ዐመት ያስፈልጉናል ብየ የማምንባቸውን የሚዲያ አገልግሎቶች ጠቁሜ ልፈጽም፡፡ የመጀመሪያዎቹ ሁለቱ የቤተ ክርስቲያናችንን ሚዲያዎች በሁለንተና ጠንካራና በሁሉም ተወዳጅ እንዲሆኑ መርዳትና አሠራራቸውንም እንዲያሻሽሉ ማገዝ ነው፡፡ ሚዲያ ሌሎችን ሁሉ የመድረሻ መንገድ እንጂ በሃይማኖታቸው ለበሰሉት ብቻ የሚዘጋጅ ተጨማሪ ድግስና ሽልማት አይደለም፡፡ ሚዲያዎቻችን ቨርቿል መቅደሶች መሆን የለባቸውም፡፡ ይልቁኑም  ኦርቶዶክስ ያልነበረን ሰው ኦርቶዶክስ ለማድረግ በቤቱ ለመሰበክ የሚጥሩ ጥሩ አፈ ሐዋርያ መሆን አለባቸው እንጂ፡፡ የሊቅንት መወዳደሪያ፣ የአገልግሎት መፎካከሪያም መሆን የለባቸውም፡፡  አማኙን ለማጽናት የሚያስችል አግልግሎት ማቅረባቸው ባይቀርም በዋናነት ግን ሌላውን የመድረሻ (outreach) መሣሪያዎች መሆናቸውን መርሳት የለብንም፡፡ ስለዚህ ከአዘጋጆቹና ከዝግጅቱ ጀምሮ ሌሎችን ለመሳብ በመጣር ፋንታ ሌላ ዐውደ ምሕረትና ቤተ መቅደስ ለማስመሰል ብቻ መጣጣር ብቻውን ይጠቅመናል ብዬ አላስብም፡፡ ይህ ማለት ግን ሌላውን ለማጥመድ ማስላትን እንጂ በዚህ ሰበብ አለማዊነትን እናስፋፋው ለማለት አይደለም፡፡ ይህን የምለው ሚዲያዎቻችን ከሚያቀጭጫቸው አንዱ የእኛ አስተያየት ስለሆነ የምንሰጠው አስተያየት የየግላችንን ፍላጎትና አምሮት ለማሟላት እንዲጥሩ ሳይሆን አማኞቿን ሁሉንም የወጡትን ሳይቀር በቅንነት ለመሰብሰብ ዐላማ ያደረገ መሆን አለበት ብለን  እንድናሳስብ፣ ካልሆነም ዝም እንድንል ለመለመን ነው፡፡
ከእነርሱ ቀጥሎ ደግሞ እንደ አደባባይ፣  ሰማያት የሰሜን አሜሪካ የካህናት ኅብረት ዝግጅቶችና የመሳሰሉ የኢንተርኔት ሚዲያዎች እየተደገፉ ሌሎችም በተለያዩ ቋንቋዎች ጭምር እየተበራከቱ በታቀደ መንገድ ጥቅም የሚሰጡ እንዲሆኑ ማገዝም በእጂጉ አስፈላጊ ነው፡፡
ከዚህ በተረፈ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰጡ አገልግሎቶችንም ተረድተንና ተገንዝበን የሚናበቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ከማያቸው ትምህርተ ሃይማኖት ላይ ብቻ ትኩረት አድርገው ጥሩ አገልግሎት የሚሰጡት  እንደ መጋቤ ሐዲስ ነቅዐጥበብ  መምህር ሳሙኤል፣ መምህር ጳውሎስ መልክአ ሥላሴ፣  መምህር በላይ ወርቁ፣ ዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ፣ ዲያቆን ዮርዳኖስ አበበ፣ ዲያቆን አቤል ካሳሁንና የመሳሰሉ ( ሌሎችም እጂግ ብዙዎች) የመሳሉ አሉ፡፡ ለወቅታዊ ጉዳዮች መልስ ከመስጠት ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አስተያየት የሚሰጡ እንደነ መልአከ ሰላም ቀሲስ ደጀኔ ሺፈራው፣ መምህር ዶክተር ዘበነ ለማ ፣ መጋቤ ሐዲስ ዶክተር ሮዳስ ታደሰ፣ ሊቀ ኃይላት ፍሬሰው ደምስ፣ መምህር ሰውአለ በላቸው፣  መምህር ምሕረተ አብ አሰፋ፣ ዲያቆን ዐባይነህ ካሴ አርክቴክት ዮሐንስ መኮንን፣ መምህር ተመስገን ዘገዬ እና ሌሎች እጅግ ብዙዎች ደግሞ እንደየተሰጣቸው ጸጋ፣ እንዳላቸው ልምድና እውቀት ዘርፈ ብዙ አገልግሎት የሚሰጡ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጉድለትና ስሕተት የመሰለውን በማጋለጥ  ደግሞ የራሱን መንገድ የያዘ (በእርሱ አካሔድ የራሴ አስተያየት ያለኝ መሆኑ ሳይዘነጋ) መምህር ዘመድኩን በቀለ አለ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ መጥፎ ምግባራትን እየተዋጉ ያሉት እንደ መምህር ደረጀ ነጋሽ ያሉት አሉ፡፡  የእንግሊዝኛ ተናጋሪውን የውጭውን ትውልድ በማገልግል ደግሞ እንደነ ቀሲስ ሰይፈ ሥላሴ (በቅርብ ያየኋቸው ሌሎችም ቀሳውስት አሉ) ፣ ዲያቆን ኤፍሬም መገንታ፣ ዲያቆን ዳዊት እና ዲያቆን ጎርጎረዮስ ደጀኔን የመሰሉ አዲስ ተስፋ ሰጭ አገልጋዮች አሉ፡፡ በትግርኛና በኦሮሙኛ የሚያገለግሉም ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ታሪክን መሠረት አድርገው ለሚከፈቱብን ጥቃቶች  መልሶችን በመስጠት ደግሞ  እንደ ቀሲስ ዶክተር አምሳሉ እና ደብተራው በአማን ነጸረ በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡  እነዚህ የጠቃቀስኳቸው በማኅበራዊ ሚዲያው ከሚታዩትና ይህን ጽሑፍ ሳዘጋጅ ወደ አእምሮዬ የመጡልኝ ብቻ መሆናቸው ይታወቅልኝና ሌሎች ያልጠቀስኳቸው እጅግ ብዙዎች መኖራቸውን ሁላችንም የምናውቀው ነው፡፡
ጅማሮው ጥሩ ቢሆንም አገልግሎቱ ግን የተናበበና የተገጣጠመ ነው ለማለት አይቻልም፡፡ ብዙ ድከመቶችና ውሱንነቶች እንዳሉብንም የታወቀ ነው፡፡ ድክመታችን የሚጀምረው  ከመጓተት ነው፡፡ እንዲህ ዘርፍ ዘርፍ ይዞ የሚቻለውን ማድረግ ለእኔ ጥሩ ሆኖ ሳለ አንዳንዴ ግን የሁሉንም አስፈላጊነት ረስተን ሰው ሁሉ አንድ ዐይነት እንዲሆን ማሰብና መተቼት ሳይ ያስገርመኛል፡፡ ሲሆን ሲሆን ማን በየትኛው መንገድ ያገልግል ብሎ መመዳደብና መረዳዳት ይገባ ነበር፡፡ ካልሆነ ግን እንደእገሌ ካልሆንክ የሚለው መጓተት እጅግ ጎጂና ከፍተኛ ጉዳት የሚያደርስ መሆኑን መዘንጋት ተገቢ አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ የደጋፊና የቲፎዞ ሰለባነት፣ ያልተገባ ውድድርና ፉክክር የሚመሰል ውስጥ የመውደቅ አደጋም ይታይበታል፡፡ ለምንሰጠው አገልግሎት አድማጭና አንባቢን አክብሮ ጠላትንና ታዛቢን ተሳቢ አድረጎ ከሚዲያው ውጭ መሬት ላይ በጸጥታ ከሚጋደሉት ጋርም አናብቦና አስልቶ በማገልገልም ከፍተኛ ውስንነት እንዳለብን የታወቀ ነው፡፡ አልፎ አልፎም በኮመንትና ላይክ ደጋፍ ከመደሰት አንሥቶ አላማ ቢስነት ያለበት የሚመሰል ትርምስም ይታይበታል፡፡  በማናቀርበው ጉዳይ የእውቀት የዝግጅትና የአቀራረብ ውስንነቶችም አሉብን። ጥናት ቢደረግ ደግሞ ሰፋ፣ በርከትና ወሰብሰብ ያሉ ችግሮችም ይኖሩብናል፡፡ እነዚህን ሁሉ ያነሣሁት ለአንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ ዘመነ ማቴዎስን ሳንነጋገር ሌላውን ለመረዳት የምንጥርበት፣ ሳይገባን በመሰለን በድፍረትና በችኮላ ከመነቃቀፍና ከመተቻቸት የምንወጣበት፣ መተራረም ሲያስፈልግ በተገቢው መንገድ ብቻ የምናደርግበት በአጠቃላይ ራሰን የመግዛት፣ የመግባባትና የመናበብ ዘመን እንዲሆን ለመለመን፣ ለማሳሰብና ለመመኘት ነው፡፡  የሚጠብቀን ሥራ ሰፊ ተጋድሎውም ጽኑ ቢሆንም ከተግባባንና ከተናብብን ድከመቶቻችንንም በቅንነት ለማረም ከተጋን ግን ተስፋውና ድሉም ትልቅ እንደሚሆን አይጠረጠርም፡፡ እግዚአብሔር በቸርነቱ ረድቶን የመግባባትና የመናበብ ዘመን ያድርግልን ፣ አሜን፡፡
Filed in: Amharic