>

ኦሮሞን ባርያ አድርጎ የሸጠው ባርያ ፈንጋይ ማን ነበር? (አቻምየለህ ታምሩ)

ኦሮሞን ባርያ አድርጎ የሸጠው ባርያ ፈንጋይ ማን ነበር?

አቻምየለህ ታምሩ

የኦሮሞ ብሔርተኛው ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን በጃዋር መሐመድ ቴሌቭዥን ቀርቦ “በዲሞክራሲያዊነቱ ወደር የለውም በሚሉት   የገዳ ሥርዓት ላይ በመሰንዘር ላይ የሚገኙ ጥቃቶች” ያላቸውን ትችቶች ለመከላከል ሞክሯል። ሆኖም ግን  በዘመኑ በተመዘገበ፤ በቀዳሚ የታሪክ ማስረጃ ላይ ተመስርተን የዘር ማጥፋትና የወረራ ወታደራዊ ሥርዓት ስለሆነው ስለ ገዳ  የሰነዘርነውን ትችት እንደ ታሪክ ባለሞያ እንዱንም  እንኳ በማስረጃ ላይ ተመስርቶ ሳይከላከል እሱና ሌሎች የኦሮሞ ብሔርተኞች ስለ ገዳ ድርጅት የፈጠሩትን ፕሮፓጋንዳ ብቻ አስተጋብቶ ከቴሌቭዥኑ መስኮት ወርዷል።
አስተርጉሜ በሰማሁት ዲስኩሩ ውስጥ ያስተጋባው አንዱ የፈጠራ ትርክቱ ግን ሳያስገርመኝ አልቀረም። የገዳ ድርጅትን እውነተኛ ታሪክ የምናቀርብ ሰዎችን “ ኦሮሞን ባርያ አድርገው ይሸጡ የነበሩ ነፍጠኛ ልጆች በሰዎች እኩልነት የሚያምነውን የገዳ ሥርዓት የባርያ አሳዳሪዎች ሥርዓት አድርገው የመተቸት የሞራል ልዕልና የላቸውም” ሲል ደፋር ንግግር አድርጓል። ይገርማል!  ጤና ይስጥልኝ ፕሮፌሰር መሐመድ ሐሰን ማነው ኦሮሞን ባርያ አድርጎ የሸጠው? እስቲ ዶሴው ይውጣና ይመርመር።
ኦሮሞን ፈንግሎ ማን ባርያ አድርጎ እንደሸጠው የሚያሳይ የታሪክ ማስረጃ ስናፈላልግ ፕሮፈሰር ሳንድራ ሼል የተባሉ የታሪክ ምሑር “Children of Hope፡ The Odyssey of the Oromo Slaves from Ethiopia to South Africa በሚል በቅርቡ ያሳተሙትን ጥናት እናገኛለን።
ከታች የታተሙት ሁለት ጥናታዊ መግለጫዎች ዛሬ ኦሮምያ ክልል ከሚባለ አካባቢ በባርያ ነጋዴዎች ተፈንግለው ወደ ደቡብ አፍሪካ የተሸጡ የኦሮሞ ልጆችን ማን ፈንግሎ እንደሸጣቸው የሚያሳዩ የፕሮፈሰር ሳንድራ ሼል ጥናት ውጤቶች ናቸው።  ወደ ደቡብ አፍሪካ የተሸጡ የኦሮሞ ልጆችን ማን ፈንግሎ እንደሸጣቸው የሚያሳየው ይህ  የፕሮፈሰር ሳንድራ ሼል  የጥናት ውጤት  የሚገኘው ፕሮፈሰሯ  “Children of Hope፡ The Odyssey of the Oromo Slaves from Ethiopia to South Africa” በሚል ርዕስ  አዘጋጅተው በኦሀዮ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው ከገጽ 65 እና 66 ነው። ፕሮፈሰር ሳንድራ የኦሮሞ ልጆችን ማን ፈንግሎ እንደሸጣቸው ያጠኑት ተፈንጋዮቹ የኦሮሞ ልጆች ራሳቸው ከሰጡት የራስ ምስክር ነው። ጥናቱ የሚያጠቃልለው እስከ 1882 ዓ.ም. ድረስ የተፈነገሉትን በመቶዎች የሚዎጠሩ የኦሮሞ  ወንድና ሴት ልጆችን ነው።
ከታች በታተመው ጥናት መሰረት 35 ፐርሰንቱ የኦሮሞ ልጆች በኦሮሞ ተወላጆች እንደተፈነገሉና ባርያ ተደርገው እንደተሸጡ ተናግረዋል። 23 ፐርሰንቱ ደግሞ በሲዳማ ተወላጅ  ፈንጋዮች እንደተሸጡ ቃላቸውን ሰጥተዋል። የተቀሩት  ተፈንጋዮች ከተለያዩ የኢትዮጵያ ነገዶች በተወለዱ ባርያ ነጋዴዎች  እንደተፈነገሉ ተናግረዋል።
በጥናቱ የተካተቱ በባሪያ ነጋዴዎች የተፈነገሉ የኦሮሞ ሁሉ በሰጡት የቃል መሰረት ግን  አንድም የአማራ ተወላጅ የሆነ ሰው በመፈንገል ባርያ አድርጎ እንደሸጣቸው የሚያሳይና ማስረጃ ሆኖ ሊቀርብ የሚችል  የአንድም  ተፈንጋይ  እንኳን የቃል ምስክር የለም። ተፈንጋዮቹ የኦሮሞ ልጆች ራሳቸው በሰጡት የቃል ምስክር ባብዛኛው የፈነገላቸው የኦሮሞ ተወላጅ ባርያ ነጋዴ መሆኑን በተናገሩበት ሁኔታ፤ አንድም የአማራ ተወላጅ ፈንግሎ እንደሸጠ እንዳቸውም ተፈንጋዮች ባልተናገሩበት ሁኔታ ነው እንግዲህ “የታሪክ ምሑሩ” ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን ያለ አንዳች ማስረጃ  በጥላቻና በጨበጣ አማራን በባሪያ ሻጭነት የሚከሰው። በታሪክ  ተመዝግቦ የምናገኘው እውነትና  ተፈንጋዮቹ የኦሮሞ ልጆች ራሳቸው በሰጡት የታሪክ ምስክር መሰረት ግን ኦሮሞን  ፈንግሎ  ባርያ አድርገው የሸጠው  ጎረቤቱ  የኦሮሞ ተወላጅ የሆነ ማርያ ፈንጋይ  መሆናቸው ነው።
 ፕሮፈሰር ሳንድራ ሼል በጥናታቸው የሚነግሩን ሌላም አስዳማሚ  የታሪክ እውነት አለ። የኦሮሞ  ተወላጅ ባርያ ፈንጋዮች  ባሪያ አድርገው የሸጧቸውን  የአሮሞ ልጆች ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ደቡብ አፍሪካ ድረስ በመላላክ ገንዘብ ጭምር እየከፈሉ ነጻ እንዲወጡና ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ማድረጋቸውን ይነግሩናል።  ከነዚህ  በኦሮሞ ተወላጆች  ወደ ደቡብ አፍሪካ ከተሸጡት ባሮች መካከልም ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ገንዘብ ከፍለው ነጻ ያወጡት ያንዱ ሰው ትውልዶች በማውሳት በደርግ ዘመን ከኢትዮጵያ ወደ ካናዳ ተሰደው አሁንም ድረስ ካናዳ ውስጥ እንደሚኖሩ ነግረውናል። የተዘመገው የታሪክ እውነት ይህ ሆኖ ሳለ ነው እንግዲህ ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን ሳያፍር የኦሮሞ ተወላጆች የሰጧቸውን የኦሮሞ ባሮች ገንዘብ ከፍለው ነጻ ያወጧቸውን የዐፄ ምኒልክ ልጆች “ኦሮሞን ባርያ አድርገው ይሸጡ የነበሩ ነፍጠኛ ልጆች የገዳ ሥርዓትን የባርያ አሳዳሪዎች ሥርዓት አድርገው የመተቸት የሞራል ልዕልና የላቸውም” የሚለው።
በስተመጨረሻም  ሳይመረምሩ እነ ፕሮፈሰር መሐመድ ሐሰን  ያራገፉባቸውን የአህይነት ጭነት ተሸክመው እየዞሩ አማራን በባርያ ፈንጋይነት የሚከሱ የኦሮሞ ብሔርተኞችንና ደጋሚዎቻቸውን  «ወሬ ሲነግሩህ ሀሳብ ጨምርበት» የሚለውን የአያቶቻችን ጥልቅ ምክርና ታላቁ ጥላሁን ገሰሰ «አመልካች ጣት» በሚል በተጫወተው ዘፈን  ውስጥ፤
ባንዷ ስትጠቁም ከጣቶችህ መሀል፣
ሶስቱ ግን ራስህን ይመለከቱሀል፤
 በሚል ያቀነቀነውን ግጥም በመለገስ ልሰናበት!
_____
ከስር የታተመውን Oromo Man with Berta Slave የሚል መግለጫ ያለውን ታሪካዊ ፎቶ የገኘሁት ወለጋ ውስጥ ወንጌል ሲስብክ የኖረው ወንጌላዊው John G. Hall  “Ethiopia in the Modern World (Explorations of Africa)” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ. በ2002 ካሳተመው መጽሐፍ  ከገጽ 50 ላይ ነው።
Filed in: Amharic